Tuesday, September 3, 2013

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረቡ አለም….(2)

    ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረቡ አለም….(2)
        በግሩም ተ/ሀይማኖት
 ‹‹..እኛስ በስደት ሀገር ምን እየሰራን ነው? ወገን ወገኑን አሳልፎ የሚሸጥበት፣ ለአደጋ የሚያጋልጥበት፣ ጥቂቶች በሚሰሩት መጥፎ ተግባር ሁሉም የሚወቀስበት፣ የሚታሰርበት ሁኔታ የለም? አለ፡፡ ይህንንም ለማየት እንሞክራለን፡፡ በተያያዥነት እንዲረዳይ ወይም መገለጽ አለበት የምትሉት ሀሳብ/መረጃ/ ካለ ላኩልኝ፡፡..›› ብዬ ነበር ባለፈው ጽሁፌ የዘጋሁት፡፡ ‹‹…በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማየት የሚገባ ነገር አለ፡፡….. በተለይ በአረቡ አለም ላይ ሽርሙጥናን ስራ አድርገው ገላቸውን መቸርቸር ብቻ ሳይሆን ሀገር የሚያሰድቡ ሞልተዋል……በሌብነትም ቢሆን ተሰማርተው ሰርተን እንዳንበላ ስማችንን እያተፉ ያሉ በርካታዎች አሉ…›› የመሳሰለ አስተያየት የሰነዘራችሁ አላችሁ፡፡ ብዙ እህቶችም ሆኑ ወንድሞች የተለያየ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የሁላችሁንም ሀሳብ እንደ ሀሳብነቱ እቀበላለሁ፡፡ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ የሚታፈነው ወያኔ ጋር እንጂ እኔ ጋር አይደለም፡፡ ጥቃቅን ስድቦች ለወረወራችሁ ከአነስተኛ እና ጥቃን ስድብ አምራችነት አውጥቶ በሰፊው የብልግናውን ካባ ያልብሳችሁ ስል እመርቃችኋለሁ፡፡ የአምስቱ አመት ትራንስፎርሜሽን እቅዳችሁ በስድቡም መስክ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግም ሳይሆን አይቀርምና ካሰባችሁበት ያድርሳችሁ፡፡

        ከሁሉም በላይ ግን አንድ ወዳጄ ያለውን አስፍሬ ወደ ሀሳቤ እግባለሁ፡፡ ፍሬሰናይ ከበደ ይባላል፡፡ የሰጠው አስተያየት….በነገራችን ላይ በቅንፍ ውስጥ የማደርገው የራሴን ሀሳብ እና ምላሽ ነው፡፡ ‹‹….ግሩም ተክለሃይማኖት በጻፈው ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። የስም ማጥፋት ያስመስላል ላልከው ግለሰብ፡ ነቃ በል ነው የምልህ??(ወዳጄ ምነው ስም ማጥፋት ምንድን ነው? ምንስ አገናኘው? ያልተሰራ ይሆን የተናገርኩት? እስኪ በመረጃ እንነጋገር?) ግብረገብ ባለው ቃል ስለጻፍክ ትክክለኝ የሆንክ እንዳይመስልህ! በሃገር ውስጥ እያለን፡ ውርደት ውስጥ የከተተንን ፋሽስት ወያኔና ሻቢያን ታግለን ወይም ተዋግተን እናሰወግድ ጥሪ ላንተም ሆነ ለሌላው ተጠራ፤ ከዚያም በኋላ በነጻው ፕሬስም ተባለ፡ አረብ ሃገር አማራጭ ሆነና፡ ግሩም የጻፈው ሆነ፤ በግልጽ እየታየ ያለ ነገር ሆነ። በስደቱ ዓለም ተሁኖ፡ ያሰደደውን ፋሽስት ወያኔ ዱርዬ ወንበዴ ቡድን መታገል ይሻላል? ወይስ ሽርሙጥና ????? ነጻነት ይሻላል ወይስ ጊዜያዊ ሽርሙጥና አላስፈላጊ የንዋይ እርካታ??? መስማት ብቻ አይደለም፡ ያሳፍራልም።

     በስደት ዓለም ሆነን ሃገራችንን አልረሳንም ስንል፡ ስለነጻነታችን በምናምነው ተቃዋሚ ድርጅት ውስጥ ሆነን ስለሃገራችን ነጻነት እንታገላለን እንጂ፡ ሃገራችንን ነጻነት ካሳጧት  የጎረቤት ሃገር ዱርዬዎች ጋር እንኳንስ ልጅ ወልዶ መኖር፡ እያንድናዷ ቀን ስለነጻነታችን እናውራ.. ሃገራችንን ሳናሳፍር ወገናችንን ከመጦር ወደ ኋላ ሳንል ወይ ፍንክች የሚሉም አሉ። እነዚህ ዓላማ የለሽ ለሱዳን ወንድ የሚታገሉት፡ የወለዷቸው ልጆቻቸው ሃገራቸው የት እንደሆን አውቀው ሃገራቸውንና ወገናቸውን አውቀው ኢትዮጵያዊ ነን ብለው፡ ወይስ ሱዳናዊ ነን ብለው እንደሚምታታባቸውና አድገው እንደሚጠሏቸው ባወቁ። የራስን ሆድ ለመሙላት ልጅ ካላሰቡት ቦታ ፈጥረው ትውልድን የሚያሰቃዩ ወንጀለኞች ናቸው። ካደጉትና ዜግነት ከተምትታባቸው አድምጠናል፤ አንብበናል። ወንድማችን ግሩም፡ አላስፈላጊ ኮሜንቶችን ማጥፋት አዲሱን ትውልድ ማዳን ነውና እግዚአብሄር ይስጥልን።…..›› ይላል ፍሬ ሰናይ ከበደ፡፡ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

     በዚህ ርዕስ የመጀመሪያውን ፅሁፍ እንደለቀኩ -ሜሌም ሆነ ስልኬ የግል መልዕክቶች በመቀበል ተወጠሩ፡፡ 142 በላይ ሰዎች ቻት ያደርጉኝ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን አብዛኛዎቹ ያስተላለፍኩትን መልዕክት በትክክል ካለመረዳት የመነጨ ጭንቀት ነበር ያማከሩኝ፣ የወቀሱኝ፡፡ ካስተላለፍኩት መልዕክት ባፈነገጠ መልኩ የተረዱኝ የተረጎሙብኝ አሉ፡፡ ከዛም ተነስተው የሰደቡኝ ሞልተዋል፡፡ ስድብ ለብስልት መገለጫ አይሆንም፡፡ እውነታ የያዘ ሰው ይሄ ይሄ ነው እውነታው ቢለኝ የማልቀበልበት መንገድ የለም፡፡ አስተውላችሁ በማንበብ ወገን ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃ ግፍ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሰሩ ስህተቶችን ብንነጋገር እና መፍትሄ ካገኘንም፣ መርዳት የምንችለውን ብንረዳ ቀና ወገናዊነት ነው፡፡

‹‹..ሴቶቹ በሴትኛ አዳሪነት ተሰልፈው አሰደቡን፣ አዋረዱን የምንለውን ያህል ወንዶችም በዚሁ መስክ ተሰማርተው መገኘታቸው ያሳፈራል፡፡ ኩሉን ተኩሎ ሊፒስቲክ ተቀብቶ ታይት አድረጎ ለገበያ የሚቆም፣ ተደውሎለት ፒክ የሚደረግ ኢትዮጵያዊ አለ መባሉ ምን አይነት ስሜት ይጭርባችኋል? ዱባይ ካሉ ኢትዮጵያዊያኖች ጋር በዚህ ዙሪያም አውርቻለሁ፡፡ እመለስበታለሁ፡፡ …›› ነው ያልኩት፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ ተነስታ የሰደበችኝ ልጅ አለች፡፡ ይሄ ማለት ዱባይ ያሉ ሴቶች በሙሉ ይሸረሙጣሉ ማለት ነው? በየትኛው ስሌት እና አባባል እንደተተረጎመ ዲክሽነሪ ላይ ቢፈለግ አይገኝም፡፡

ስለ ወንዶቹ ድርጊት ተወያይቻለሁ ነው ያልኩት፡፡ ቢሆን እንኳን ዱባይ ያሉ ጥቂት ሴቶቻችን የሚሰሩት ነገር የለም? ወገኖቻችን ላይስ ግፍ አልተፈጸመም? በቅርቡ ተጫውተውባት ዛፍ ላይ አንጠልጥለው ራሷን ሰቀለች የተባለች የለችም? በደረሰባቸው ግፍ አብደው ኮሚኒቲ ውስጥ የነበሩ የሉም? አሁንስ አይኖሩ ይሆን? ለሶስት ተጫውተውባት የፌስቱላ ችግር ገጥሟት አዋጡላት ተብሎ የታከመች የለችም? በስም ብቻ ሳይሆን በፎቶ ጭምር የማውቃቸው ወንዲኛ አዳሪዎች የሉም? /ለሴቶች ሴተኛ አዳሪ ከተባለ ለወንዶች ወንዲኛ አዳሪ የሚለውን ልጠቀም እንጂ እስከዛሬ ስላልተለመደ ቃል ያለው አልመሰለኝም፡፡/ ጥቂት በጣም ጥቂት እህቶቻችን ለሚያገኟት ሳንቲም ብለው በቪዲዬ ተቀርጸው መጠቀሚያ አልሆኑም?

   እንዲያውም እዚህ ጋር አንድ ገጠመኜን ላሰፍር ወደድኩ፡፡ አንድ ፈረንሳያዊ ተጓዥ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የመን የጋዜጠኞች ማህበር ስብሰባ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩና ስሄድ አገኘሁት፡፡ እሱም ተጋብዞ ስለነበር ሁለታችንም የተጋባዥ ወንበር ላይ ነው ያለነው፡፡ ከየት እንደመጣሁ የጠቀኝ እና ወሬ ተጀመረ፡፡ በወሬያችን መካከል እዚሁ እንደምኖር ተነፈስኩ፡፡ የመን ትንሽ ጊዜ ስለሚቆይ አብራው የምትዝናና ሀበሻ ሴት እንዳስተዋውቀው ጠየቀኝ፡፡ አንደኛ እኔ አቃጣሪ ደላላ አለመሆኔን ሁለተኛ ማንኛዋም ሀበሻ የእንደዛ አይነት ፍላጎት እንደሌላት እና ለስራ እንደመጣች ነገርኩት፡፡ የዛሬ ወር ዱባይ ነበርኩ ብሎ የያዛትን ዲጂታል ካሜራ ከነካካ በኋላ ፊልሙን ዝግጁ አድርጎ እንዳየው አቀበለኝ፡፡ አፍ እና ጭን ተጋጥመው /.../ በስሜት ጥድፊያ ይዋከባሉ፡፡ ፊልሙን ለማየት እንዳቀረቀርኩ ደረኩ፡፡ አንገቴን ቀና እንዳላደርግ ሀፍረት በግሩፕ ሰፍሮብኝ ሸብቦ ያዘኝ፡፡

     ካሜራውን ስመልስለት መቅረጽህን ታውቃለች? ለነገሩ ይህቺ ልጅ ሀበሻ አይደለችም አልኩት፡፡ ለማምለጫ እንጂ ልጅቷን ኢትዮ ስፖት ዌብ ሳይት ላይ ተደጋጋሚ እርቃን ገላ በሚያጋልጥ ሁኔታ ፎቶ ተነስታ ስትለቅ ነው የማውቃት፡፡ በደንብ እንደምታውቅ እና ክፍያውን ጨምሮ እንዳደረገው ነገረኝ፡፡ የፈለገውን ያህል ቢከፍላት 1000 ዶላር በላይ አይከፍላትም፡፡ እሱ ግን የሚያፍሰውን ያፍሳል፡፡ እህቶቻችን ባለማወቅ ከወሲብ ውጭ ሌላም ንግድ መጠቀሚያ እየሆኑ ነው፡፡ እዚህ የመን ውስጥ አሁን ሳዑዲ ያሉ ሁለት እህትማማቾች አውቅ ነበር፡፡ ትልቅየዋ ጀርመናው ጓደኛ አላት፡፡ ከእሱ ጋር የምታደርገውን ነገር በህገ-ወጥ ሁኔታ ስትፈጽም ታናሽዬው ቪዲዮ ካሜራ ይዛ መቅረጽዋን ከራሷ አንደበት ሰምቻለሁ፡፡ እንደጀብዱ በተሰበሰብንበት ያወሩልን 500 ዶላር ሰጥቷቸው ነበር፡፡ እነዚህ አይነት ነገሮች በመጀመሪያ የራስን ሰብዓዊ ክብር፣ ሞራል ከማዝቀጥ አንጻር ቀጥሎ የወገንን ብሎም የሀገርን ስም....እያልን እንድናስብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንዳሰው ችግራችንን እንነጋገር ነው አላማዬ፡፡ ባለማወቅም የሚሰራ ነገር መኖሩንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

    ሌላው በሞባይል ስልኬ ከደረሰኝ መልዕክት ውስጥ ስሟን ካስተዋወቀችኝ በኋላ ‹‹....እግዚአብሄር ይመስገን አለኝ፡፡ /አይ እታለም ቢኖርሽ ለምን ተሰደድሽ?/ ለራሴ እና ለቤተሰቦቼ እንጂ ጎረምሳ ልቀልብ አልወጣሁም፡፡/...... ያሳድግሽ፡፡ እኔም እኮ እያልኩ ያለሁት ለራሳችን ምን ያህል አውቀናል? ቤተሰብ በችግር ሲማቅቅ እኛ ለምን ስራ ጠልቶ እንደ ውሻ እጅ እጅ የሚያይ ሰው እንቀልባለን ነው፡፡/ እና አረብ ሀገር ያሉ በተለይ ዱባይ አያልክ ሰውን ባታጎሳቁል ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎችን ወክዬ መናገሬ ግን አይደለም፡፡ ያለከውን የሚሰሩ አሉ፡፡ የሉም አልልም፡፡ እናንተ ጋርም እንዳሉ እህቶቼ ይነግሩኛል፡፡ እዚህ ዱባይ የብዙ ሴቶችን ትዳር እና ጓደኝነት እንደምትበጠብጥ ልብ ያልክ አልመሰለኝም፡፡..›› ይላል፡፡ ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው በተለይ ዱባይ ያልኩበት ቦታ የት ነው? እኔ ያልኩት ‹‹..ጥቂቶች ደግሞ በሉብናን /ቤይሩት/ ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን.. ኩዌት ያሉ ሴቶቻችን የሱዳን ወንዶች ሲሻሙ እና የለፉበትን አባክነው ቤት ተከራይተውላቸው ማስቀመጣቸው…›› ነው፡፡ ያውም ጥቂቶች እንጂ ሁሉም አላልኩም፡፡ እህቴ ቅድሚያ አስተውሎ ማንበብ ቢቀድምስ?
   
ሌላው ደግሞ ሱዳን ውስጥ ራሱ የተወሰኑ ሴቶች የሰሩበትን ማብላት ብቻ ሳይሆን ተደባድበው ፖሊስ ጣቢያ እንደደረሱ ካርቱም ነዋሪ የሆንን የምናውቀው ነው በማለት አንድ ወዳጄ ነግሮኛል፡፡
     አሁን ጠለቅ ያለ መረጃ እጄ እየገባ ነው እምለስበታልሁ፡፡