Monday, March 4, 2013

ሃበሻ ለሃበሻ በጩቤ ተጋደለ !

የማለዳ ወግ . . . ግፉአን እህቶች ፤ ዲፕሎማቶቻችንና አንገታችን ያስደፉን የእኛ ሽፍቶች . . .

by Nebiyu Sirak on Monday, March 4, 2013 at 4:00am ·


   የማለዳ ወጌን በኮረብታማዋ የጣፍ ከተማ ስንሸራሸር ባጋጠሙኝ ክስተቶች ልቃኝ ስንቆራጠጥ ምሽቱን ከተለያዩ ቦታወች የሚደርሱኝ አንዳንድ የስልክ ጥሪዎች መልዕክት ሃሳቤን በታተነው ፡፡ የደረሱኝ መረጃዎችን ከሰሞኑ ካየሁት በአንድ የሳውዲ ድንበር ከተማ በሃበሾች ተሰራ የተበለ ወንጀል የሚያሳይ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ጋር እያገናኘሁ ከራሴ ጋር መነጋገር መርጫለሁ፡፡ እናም አንዱን መጨበጥ አቅቶኝ መንቆራጠጥ ይዣለሁ ! እናም የቴሌቪዥኑን "ሪሞት" ቁጥሮች በጣቶቸ እየነካካሁ አዲስ ወሬ ያለበትን ጣቢያ ስፈላልግ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምሽቱ ዜና ወደ አረብ ሃገር ስለሚላኩ የኮንትራት ሰራተኞች ጉዳይ ዜና ቢጤ ሲያቀርብ ደረስኩና አትኩሮት ሰጥቸ መከታተል ጀመርኩ፡፡ አይቸ ጨረስኩናም ስሜቴ ቢነካብኝ የማለዳ ወጌን ከጣይፉ የእረፍት ቀናት ውሎ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወዳሳየኝ የኮንትራት ሰራተኞች ሃበሳ የመብት ጥበቃና ምሽት ወደ ሰማሁት የወገኖቸ ስጋት  ዳሰሳየን ለማድረግ ወሰንኩ. . . ! እንዲያ ሆነና "ግፉአን እህቶች ዲፕሎማቶቻችንና አንገታችን ያስደፉን የእኛ ሽፍቶች " በሚል የማለዳ ወግ ዳሰሳየን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀረብው ዜና እንዲህ ስል ጀመርኩ . . . 
 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዱባዩን ቆንስል ሓላፊ ምስጋናው አረጋን እማኝ አስደግፎ አንድ ዜና ምሽት ላይ አቅርቦ ተከታተልኩት፡፡ "በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንስል ችግሮችን ለመቅረፍ ስምምነቶች ይደረጋሉ!" የሚለውን ቀዳሚ ዜና ሰማነው ፡፡ ከዙሁ ጋር በቀረበው የዜናው ትንታኔ በኮንትራት ሰራተኞች ላይ ደላላሎች የሚያደርሱባቸውን በደልና የእህቶቻችን አበሳ ኢቲቪ ነካክቶታልም፡፡ በደላሎች የተበደሉትና በአሰሪዎች አደጋ የደረሰባቸውን እህቶች ሳይቀር ከራሳቸው ከባለጉዳዮች ሰምተናል ! መልካም ነው !  እኔም ሆንኩ የቀረነው ጉዳዩ ያገባናል ወገኖች በአረብ ሃገር በኮንትራት ስለሚላኩ ዜጎች የመብት ጥበቃ ጉድለት ደጋግመን የምናነሳ የምንጥለው ጉዳይ ትኩረት መሰጠቱ መልካም ነው ፡፡ ዱባይ የሆነውን ሳውዲ ከሆነው ጋር ማወዳደር አልሻም፡፡ ያም ሆኖ የዜጎች ሁለንተናዊ አበሳ ምክንያቱ በርካታ ቢሆንም ከገጠር ከተሞች በደላሎች ገንዘባቸውን እየከሰከሱ እንደ እንስሳ እየተጋዙ የሚሸኙት  እህቶች በአረብ ሃገራት ባሉ የመንግስታችን ተወካዮች በቂ የመብት ጥበቃ አይደረግላቸውም፡፡ የተበደሉትን ነጋ ጠባ አያለሁና ለዜና ሽፋን ብቻ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ ሃላፊዎች የሚሰጡት መግለጫ ስሰማ ሁሌም ያመኛል፡፡ እውነቱ መነጋገር ካስፈለገና የሚሰማ ከተገኘ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ መንግስት ሌላው ሁሉ ቀርቶ ችግሩን መቅረፍ ባይችል እንኳ ጋብ እንዲል ከፈለገ ከደላሎች ተጀምሮ ፤ በእድሜ ላልደረሱ እህቶች ፓስፖርት እንዲያገኙ የሚያግዙት ተቋማትን፤ ወደ አረብ ሃገር የተሰደዱትን ዜጎች መብት ማስከበር የተሳናቸውን የአረብ ሃገር ዲፕሎማቶቻችን መፈተሽ ግር ይለዋል፡፡ ወደ አረብ ሃገራት የሚላኩት ዲፕሎማቶች ለአባይ ግድብ ገንዘብ ከማሰባሰብ ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የገንዘብ ማሰባሰቢያ የልማት ማህበራትን ከማደራጀት ጎን ለጎን የዜጎቻቸውን መብት የማስጠበቅ ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት አለመወጣታቸውን በውል ሊጤን፤ ትኩረት ሊሰጠውና ሊመረምር ይገባል፡፡

    እዚህ ሳውዲ አረቢያ በሁለት አመት ውስጥ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኮንትራት ሰራተኞች በኢንባሲና በቆንስል እውቅና  እንደገቡ ይነገራል፡፡ በአንጻሩ ማረጋገጫ ቪዛ ተሰጥቷቸው ወደ ሳውዲ የገቡትን የኮንትራት ሰራተኞች መዳረሻ አይታወቅም፡፡ ዜጎች መጥተው ወደ ስራ ስለሚሰማሩበትና በስራ ሂደቱ ችግር የሚያጋጥማቸው ከለላ ሲጠይቁ እንኳ የሚኬድበት የመብት ጥበቃ የት ድረስ ነው ብሎ ለሚጠይቅም መልሱ ያሳፍራል፡፡ ይህን ሁሉ ደፍሮ የሚጠይቅ ቢገኝ የመንግስት ተወካዮች በአካባቢው ስለመኖራቸው ይጠራጠራል፡፡ ከከፋ አደጋ ላይ የወደቁ ዜጎች  በአካል አግኝቸ፤ ለዜጎች መብት ማስጠበቅ የተመደቡልንን ሃላፊዎች ጠይቄና የነዋሪውን  አስተያየት አድምጨ የደረስኩበት ድምዳሜ "ሰሚ እስኪገኝ መገለል መሰደብ ግልምጫና አደጋውን ተቋቁሞ መጮህ  ነው " ከሚል ድምዳሜ በመድረሴም ይህው ዛሬም እጮሃለሁ ! እንጮሃለን !

   ከኢንባሲና ቆንስል የመንግስት ተወካዮችና ደጋፊዎች እኔም ሆንኩ ጉዳዩ ሆንኩ ያገባናል የምንል ወገኖች በጥሩ አይን አያዩንም፡፡ በዜጎች መብት ገፈፋ ዙሪያ በምንሰነዝራቸው የሰሉ ተጨባጭ ሂሶች እንደ ተቃዋሚ ጠላት የመታየት እድል ቢሆንም እንችለዋለን !  ሰብእና የሚሻውን ጉዳይ ከፖለቲካ ጋር እያጣረስን እለመዘባረቃቸን ያልተመቻቸው የመንግስት አካሄድ የማይመቻቸው ተቃዋሚዎች በበኩላቸው " ቀንደኛ ወያኔ ! " የሚል የፖለቲከኛ ስም ከመለጠፍ አልፈው " ቀንደኛ ሰላይ " ይሉናል፡፡ ሌት ተቀን የምንጮህበት የወገን ድምጽ እንዳይሰማ ግርታን እየፈጠሩና በተራው ሰብዕናችን ላይ ጥላሸት እየቀቡን ይገኛሉ፡፡ የወገናቸው ህመም አንድም ቀን የማያማቸው እኛን የጎዱ እየመሰላላቸው በባዶ ሜዳ ያቅራራሉ፡፡ እንዲህ ተቃዋሚው ሲቃወመን ፤የመንግስት ተወካዮችና ደጋፊዎች  " የሃገር ጠላት፤ጸረ ልማትና ከሀዲ" እስከመባል ያደረሰንን የወገን አበሳ ዛሬ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሆነው በኢቲቪ ሲነገር ማየትና መስማቴ ቢያስን አስደስቶኛል፡፡ ያም ሆኖ " ችግሮችን አቅርቦ ለመፍትሄው እየሰራን ነው " ለማለት የሚውል ፕሮፓጋንዳ እንዳይሆን ያሰጋኛል፡፡ አልረጋ ባለው የጂዳ ቆንስል መስሪያ ቤት አዲስ ተመድበው የመጡ ሃላፊዎች የኮንትራት ሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አይሎ በመጣበት አጋጣሚ ነዋሪውን ሰብስበው በማማከርና መፍትሄ በማፈላለግ አንድ ይሉን ዘንድ እንደ ዜጋ መክሬ ነበር፡፡ አልሰሙኝም ! ይባስ ብለው በደል የደረሰባቸውን ፍትህ ሳያገኙ በጊዜያዊ ማቆያ እስር ቤት ታጉረው ወደ ሃገር እንዲገቡ በማድረግ " ከፊት ዘወር" የማድረግ እርምጃ መትጋታቸው አሳዝኖን ከርሟል፡፡
    ሃላፊዎች ሆይ ! በተለይም በህጋዊ ኮንትራት የመጡ እህቶች በጠራራ ጸሃይ ግፍ ተፈጽሞባቸው ሸፋፍናችሁ አትለፉት ! ፍትህን ሳያገኙ ወደ ሃገርም አትላኳቸው ! መንግስት መብት ለማስጠበቅ የሚሆን ባጀት ባይኖረው ነዋሪውን በችግሩ ዙሪያ አመካክሩት ! መፍትሄ ታገኛላቸሁና !

መረን የለቀቁት የእኛ ሽፍቶች. . .

  ላለፉት ሁለት ቀናት የሚሰማው አልገባቸው ያለ ብቻ ሳይሆነ የሚሰሙት ስጋት ያጫረባቸው " ፍተሻ አለ !. . . ጥብቅ ቁጥጥር አለ . . .የምታውቀው ነገር አለው ወይ? "  እያሉ ይደውሉልኛል ፡፡ ". . . ሪያድ ፤ጀዛን ፤ ጂዳ ፤ ሃሚስ ምሸት፤ አብሃ፤ቢሻ . . . ሃበሻ ለሃበሻ በጩቤ ተጋደለ !" ሲባል ሰምተን ዜናው አስገርሞን ሳያበቃ ሌላ አስደንጋጭ ዜና እየሰማን ነው ፡፡  እውነት ነው ሰሞኑን ደግሞ መረን የለቀቁት የእኛ ሽፍቶች ፤ የሃገሬ ጋጠ ወጦች በድንበር የገጠር ከተሞች እየሰሩት ያለው ያሳፍረን አንገታችን ያስደፋን ይዟል፡፡ ስራቸው ምድረ ሃበሻን ከማሳፈር አልፎ እንገነባዋልን የምንለውን ገጽታ ጥላሸት ቀብቶታል፡፡ ይህ የማንክደው እያየን እየሰማን ያለነው ተቸባጭ መረጃ ነው፡፡ በየመን ድንበር ከተሞች ከየምን ዳላሎች ጋር በእገታ ተስማርተው ወንዶችን ገንዘብ አምጡ በማለት በመደብደብ አልፎ ብልታቸውን እስከ መቁረጥ የደረሰ ከስብ እና ውጭ የሆነ ስራ የሚሰሩት የእኛ ደላሎች ስለመሆናቸው በአይናቸው ያዩ ብቻ ሳይሆኑ የጥቃቱ ሰለባዎች አጋጥመውኛል፡፡ ሴቶችን በመድፈር ፤ ሲላቸው እያገቱ ከመደለል ፤ በእገታ የያዟቸውን ትርፍ ገንዘብ ለመቃረም ስራ እንደሚያስቀጥሯቸው ሰምተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ እኒሁ በድንበር የሚንቀሳቀሱ ሽፍታ ዜጎቻችን ከዚህ መሰሉ አስነዋሪ ህገ ወጥ ተግባር ተሸጋግረው መሳሪያ ወደ መሸጥ፤ ወደ ግድያና ወደ መሳሪያ ንግድ መሸጋገራቸውን እንደሰማ ነበር፡፡ ሰሞኑን የተሰራጩት የመገናኛ ብዙሃኑን ዘገባዎች ግን የምንሰማውን አስረግጠው በምስልና በድምጽ አሳይተውናል አሰምተውናል !
 መረጃዎችን ተከትሎ በምዕራብ የሃገሪቱ ክፍል ትላልቅ የሳውዲ ከተሞች የከተመው የሃበሻ ልጆችን ስም አርክሰውታል፡፡ እንታመን ፤ እንከበር በነበረበት ምድር ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቀውና "በስማ በለው" ሲነገር ለማመን የሚቸግረንን እውነት እኛታችን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ስራ በሽፍቶች የመፈጸሙ ስጋት ብዙውን ሰላማዊ ነዋሪ ስጋት ላይ ጥሎታል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ መነገር  ያለበት እውነት ነውና ልንናገርው ግድ ይላል !  አዎ ትናንት ከትናንት በስቲያና ዛሬ ተሰሩ የተባሉ ወንጀሎችን ተከትሎ እየተስተዋሉ ያሉት ፍተሻዎች ምንጫቸው ምንድ ነው ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ኑሯቸን በሰላማዊ መንገድ ስንገፋ መረጋጋት የሚታይበት ኑሯችንን የሚያከፉ እርምጃዎች በእኛ ዜጎች ተወሰዱ ተብሎ ለማጥራት በሚወሰደው እርምጃ በአብዛኛው ተጠቂዎች ወንጀለኞች  አይደሉምና ያሰጋናል! ብዙዎች የምንጠቃበት በጣም ጥቂት ጋጠ ወጥ ሽፍቶች የሚፈጽሙት ወንጀል መሆኑን የመንግስት ተወካዮቻችን ይሰብስቡና ይስሙን ! የሰሙትንም ለሚመለከተው አካል ተናግረው መብታችን ያስከብሩልን ! ያ ካልሆነ ዛሬ ትናንት አይደለም ! ሂደቱ በዚህ ከቀጠለ አባቶች "ለሃጣን የመጣ ለጻድቃን!" እንደሚሉት  እንዳይሆን ያስፈራል ብየ የዛሬዋን የማለዳ ወግ ስደመድም ሃላፊዎች ሆይ ይህም ያገባችሗልና ነዋሪውን ጥሩና አነጋግሩት አመካክሩት እላችሗለሁ !

ቸር ያሰማን  !

ነቢዩ ሲራክ