Saturday, July 6, 2013

ንጉስ አብርሃ በየመን እንዴት ነገሰ (ክፍል 2)


       
                      በግሩም ተ/ሀይማኖት
    ንጉስ አብርሃ የየመን ንጉስ ነበር፡፡ እንዴት? የንጉስ አብርሃን በየመን መንገስ በተመለከተ ለማስጨበጥ የፈለኩትን ሀሳብ ጥሩ መወያያ ያደረጉት ወዳጆቼ ሰፋ አድርጌ እንድጽፍ አድርገውኛል፡፡ ችርስ!!! እንሱንም ከመወያይት አያርቃቸው፡፡ ታዲያ ተወያይቶ ምግባባትን እንጂ ግራ መጋባትን እንዳያድለን እየለመንኩ ነው፡፡ እስካሁን ላለው በመግባባት መሆኑ ያስደስተኛል፡፡ በተለይ ወዳጄ ፍሬሰናይ ከበደን፣ ፍጹም ዘሚካኤልን ዳኒን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ ታሪኩ ሊነበብ የሚገባው ነገር ቢሆንም ቀልድ በዛበት። ያልከ/ሽ/ኝ ፍጹም ዘሚካኤል እቀበላለሁ፡፡ ግን ለመዝናኛነትም አስቤ ነው፡፡ አንተን ብሎ አዝናኝ እረፍ ካላችሁም ምን አደርጋለሁ፡፡ ‹‹…አላለልኝም እችለዋለሁ…›› የሚለውን እያቀነቀንኩ በልሙጡ አስነካዋለሁ፡፡ ደግሞ እኮ ንባብ ቶሎ የሚሰለቻቸው ብዙ መኖራቸውን ከግምት በመክተት ነው፡፡ ግን በራሴ ጽሁፍ…

    በመቀጠል.. በመጀመሪያ ታሪኩ ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩት ንጉስ አፄ ካሌብ ናቸው አብርሃ ደግሞ የጦር አበጋዝ ነው። (ምክትል እንጂ ዋና አይደለም) ወይም መከላከያ ሚኒቴር ነው። የእሱ ምክትል ደግሞ ታናሸ ወንድሙ አፅብሃ ይባላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጀመሪያ የመንን የያዘው (የተቆቆጣጠረው) አብርሃ ሳይሆን አፅብሃ ነው። (ፈጽሞ ስህተት) ለዚህ ማስረጃ ብትጠይቁኝ ላቀርብላችሁ እችላለሁ…የአብርሃንም ሆነ የአፅብሃን እንዴት እንደሞቱ ልነግርህ እችላለሁ…. በማለት ያሰፈርከው ወዳጄ ዳኒ በጣም ስህተት መሆኑን በቀይ ስክርቢቶ ሳይሆን  ጎላ ባለ ቀይ ፓርከር ኤክስ አድርጌ ያለህን ማስረጃ እንድታቀርብ እጋብዝሀለሁ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ንጉስ ካሌብ መሆናቸውን እኔም ገልጫለሁ፡፡ አብርሃ ወ አጽብሃ ከዚህ ጋር የተገኛኘ ነገር የላቸውም፡፡ አብርሃ ወ አጽብሃ እኮ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነው እንጂ የየመን ንጉስ ሆነው አያቁም፡፡ አረ ሼም ነው ሰዎቹን ያለ ቪዛ ያለ ይለፍ ወረቀት ከሀገር አወጣሀቸው እኮ፡፡ ሁለቱም ወንድማቾች  ውቅሮ ከሚባለው በቅርብ ርቀት ነው የመቃብር ስፍራቸው፡፡ (ባለራዕዩ መሪያችን ቢኖሩ የአብርሃ ወ አጽብሃ ታሪክ ወይም መቃብር ለትግራይ እንጂ ለቀሪው ኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ነው? ይሉን ነበር እንደ አክሱም ሀውልት፡፡ ነፍስ ይማር)
 
      በፊት እንደገለጽኩት አብርሃ አሪየልን ገሎ በመንገሱ የኢትዮጵያው ንጉስ አፄ ካልብ ተናደዱ፡፡ በመናደዳቸውም አብርሃን ለመውጋት ምለው ነበር፡፡ አብርሃ በብልጠቱ ማህላቸውን ካስነሳቸው በኋላ አምኖ ሊቀመጥ ባለመቻሉ የሚያስደስታች ነገር ለመስራት ብዙ ይጥር ነበር፡፡ ሰዎች ከየመንም ተነስተው ሆነ ከሌላ ቦታ የመንን አቋርጠው ወደ ካባ (መካ) ሲሄዱ ያያል፣ ይሰማል፡፡ አሁን ባብ አል-የመን የሚባለው አካባቢ በጣም ግዙፍ ቤተክርስቲያን ለመስራት አሰበ፡፡ ያሰበውን ቂም ይዞብኛል ብሎ ለፈራው አፄ ካልብ ‹‹…እነሆ በረከት ንጉስ ሆይ የሚያስደስትህ ከሆነ ይህን ልስራ..›› አለ፡፡ ፍቃድም አገኘ፡፡ ረጅም ጊዜ የወሰደ "አል ቊለይስ" የተባለ ቤተክርስቲያን ሰራ። በአይነቱም ሆነ በግዝፈቱ በዛን ወቅት በጣም የተለየ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ለጉብኝት ክፍትሆኖ አለ፡፡

   አዋጅ አስነገረ፡፡ ‹‹..እዚሁ በቅርቡ ትልቅ ቤተክርስቲያን እንደ መካ ያለ ስለሰራን መካ በመሄድ ፋንታ እዚህ ተጠቀሙ፡፡ ይህ ማለት እምነታሁን ለውጡ ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም በእየእምነቱ አለ፡፡ ከመካ የመጣ ሰው ወደዚህ ቤተክርስቲያን በመግባት ቤተክርስቲያኑን በሰገራ እና በሽንት አቆሸሸው ይላል የጻፉት ታሪክ፡፡ ሲቀጥልም አብርሃ ይህንን በተመለከተ ጊዜ ንዴቱን መቆጣጠር አልቻለም ነበር። ስለዚህ ሰራዊት አዘጋጅቶ መካን ለመውረርና ለማጥፋት ወሰነ።

   ካዘጋጀው 13 ዝሆኖች መካከል ሙሃሙድ የሚባል ግዙፍ ዝሆን ይገኝበታል። (The year of elephant ተብሎ ያ-ወቅት የሚጠራው በዚህ ምክንያት ነው) ለጦርነቱ ጉዞ ሰራዊቱን ለማሰባሰብ ‹‹እንቁም›› ያለበት ቦታ ዛሬ ድረስ ‹‹ንቁም›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ታክሲ ገብተህ ንቁም ብትል እዛው ወስደው ያወርዱሀል፡፡ ጉዞው ተከውኖ አብርሃ እያሸነፈ መካ ደረሰ። የነብዩ አያት አብዱል ሙጠሊብ ያቀረቡትን እርቀ ሰላም አልቀበል ብሎ ካባን ለማትፍረስ ጉዞውን ቀጠለ። የነብዩ አያትም ከተማዋ ከሚደርስባት ሰማያዊ መቅሰፍት ይጠበቊ ዘንድ ከከተማ ወጥተው ወደ ከፍታ ቦታ ከነቤተሰቦቻቸው እንዲሸሹ ለሰዎች ነገሩ፡፡ ሽሽቱ ቀጠለ..…

    የአብርሃ ጦር መካ መግቢያ ላይ አልሙሃሲር የተባለ ሸለቆ እንደደረሰ በወፍ መንጋ ተከበበ ተደበደበም። አብርሀም ከዚህ ጥቃት ለመሸሽ ወደ የመን ተመለሰ ዳሩ ግን በመንገድ ሳለ በጥቃቱ ስጋው ተበጣጥሷል። (ይህ ነው ቢባልም ጂዛን ላይ እንደሞተ ነው የሚነገረው፡፡ ያውም ወፏ የያዘችውን አጥንት ስትለቀው ወርዶ በረቀሰው የሚልም አለ፡፡)
 
     አብርሃ በስልጣን ላይ ባለበት ወቅት ያው ለንጉስነቱ እንዲሰግዱለት እንዳስገደዳቸው እነሱም አንሰግድም እንዳሉት ይነገራል፡፡ ታዲያ ብልሁ አብርሃ የቤቶቻቸውን በሮች ከአንድ ሜትር ትንሽ ብቻ ከፍ አድርጎ በማሰራቱ ሲወጡ እና ሲገቡ የግዳችን ሰገዱለት ይባላል፡ ለዚህ ይባላል ግን ማረጋጫ አለው፡፡ አሁን አሮጌው ሰነዓ የሚባለው ባብ አል-የመን ያሉ በእሱ ጊዜ የተሰሩ 14000 ቤቶች ምስክርነት ለመስጠት ቆመዋል፡፡ ቤቶቹን በተመለከተ ዳግም ልመለስበት እስኪ….ሰላም አሰንብቶ ያገናኘን፡፡