Friday, May 3, 2013
ሰበር ዜና ተብሎ የተሰበረ ፍርድ ውሰኔ ተላለፈ
የዛሬውን ሰበር ዜና ያስነበበን ወሰንሰገድ ነው፡፡ እሱ ያለውን የተከወነውን ነው የሳየን፡፡ ተባረክ ስለው የፈረደውን ዳኛ ምን ማለት እንዳለብኝ አላሰብኩምና አልረግመውም አልመርቀውም፡፡ የታዘዘውን ፈጻሚ ነውና ምን ማለትስ ይቻላል፡፡ ፍትህ ባልነገሰበት ፍትህ መጠበቅ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው ነው፡፡ ቴሌቪዥኔን እንደፈለኩ በሪሞት ኮንትሮሉ እንደምዝረው ሁሉ እነሱም እንደፈለጉ የሚያዙት የፍትህ አካላት አዋቅረው ህገ-መንግስት ብለው ያጸደቁትን ሲሽሩት ማየትስ ይሄ የመጀመሪያ ነው እንዴ? ወያኔን የተቃወመ ሁሉ አሸባሪ የሚባልበት ፎርሙላስ የተፈበረከው በእነሱ አይደለ?
መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱ አሸባሪ ብሎ ሲወስንባቸውስ አቃቢ ህግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ብቁ ነበሩ ወይ? ያኔ ምን አይተው ፈረዱ አሁንስ እሱ ብቁ ሆኖ ነው ያጸደቁት? የሚለውን ማየት በቂ ነው፡፡ “እውነት ተደብቆ አይቀርም” ሲል እስክንድር ነጋ ከፍርዱ በኋላ በችሎት ውስጥ መነገሩም ተዝግቧል፡፡ አንድ ቀን እውነት እንደሚወጣ እነሱስ ሳያውቁ ቀርተው ነው? ህሊናቸውን ሸጠው ሆነ እንጂ፡፡ ያኔም እነ እስክንድር አንገታቸውን ሲያቃኑ እነሱ ያፍራሉ ብዬ አልጠብቅም፡፡ ትላንት የልባቸውን የሰሩ ህዝብ ያስጨፈጨፉ ሁሉ ተገደን ነው ምን እናድርግ ሲሉት ህዝቡ ስለሚያምናቸው እነዚህም ‹‹ተገደን ነው›› ይሉናል፡፡ ይልቅ “የተከራከርነው ፍትህ እናገኛለን ብለን አይደለም፤ ፍትህ ወዳድ በመሆናችን ነው” የምትለው የናትናኤል አነጋገር ትመቻለች፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)