Saturday, August 18, 2012


ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር

ክፍል አራት

እርሰ በአርሳችን የመበላላታችን ጭካኔ ውጤት

      በግሩም ተ/ሀይማኖት



  ሰላም ወዳጆቼ…ሰላማችሁ ይብዛ! አሜን!! ለምን ገመናችን ተነካ ብላችሁ የተሳደባችሁ ስድባችሁ ባዶነታችሁን ያሳያል እንጂ ክብሬን አይነካም እና..ምላሳችሁ ይብዛ!!!…ወገን እየሸጣችሁ በሰው ደም የሰከራችሁ ስካራቸሁ ይጥፋ..ወገናችሁን መሸጥ መለወጥ የለመዳችሁ ይሄ መጥፎ አባዜያችሁ ከላያችሁ ይታጠብላችሁ…ለሁላችንም ልቦና ይስጠን፡፡ አሜን!!!! በሉ፡፡



    በአረብ ሀገር ያሉ ሴቶችን ስም አጠፋህ የሚሉ ጥቂት ሀሞት ዘልዛላ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ ምንም አልላቸውም፡፡ ችግራቸው አንብቦ መረዳት ነውና ቃላት መቁጠሩን ሳይሆን አስተውሎ…ማገናዘቢያውን ህሊና ይስጣቸው፡፡ እነዚህን አንባቢዎቼ ልበላቸው? ወይስ ‹‹አንቡብልኝ ብዬ ሳስነብብ ለሰው መርዶ ይመስለኝና…›› የሚለውን ዜማ አስታዋሾቼ በአረብ ሀገር የሌለ ሰቆቃ እና ስም ማጥፋት ነው የምትጽፈው ባይ ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ አስተያየት የሚሰጠው አረብ ሀገር ኗሪ ለእኔ አግዞ ነው እየዋሸ ያለው ማለት ነው? እውነታውን ቢክዱ አልፈርድባቸውም፡፡ ለእኔ ሲሉ ከዋሹልኝም ተመስጌን የዚህን ሁሉ ሰው ፍቅር የሰጠኸኝ አምላክ፡፡ አያዩ አያዩምና እየሰሙ አይሰሙምና ልቦና ስጣቸው..አሜን!! ከኳታር የመጣ አንድ የግል መልዕክት እንዳበሰረኝ እየተሳደበ ያለው ልጅ /እዚህ ጋር የማንንም ስም ለመጥቀስ አለመፈለጌ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ላለመንካት መሆኑ ይታወቅልኝ/ ስራውን እንዳላጋልጥበት በመፍራት እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡ አንድ እህቴ የገጠማትን ገጠመኝ አታሎ እንዴት ለሁለት የውጭ ዜጎች ሊሸጣት እንደነበር ገልጻልኛለች፡፡ ታሪኩን በቀጣይነት ስለምጠቀምበት ለጊዜው ወደ ጀመርኩት ልሂድ፡፡



      መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል….ነው፡፡ የራሳቸውን ገላ ከመሸጥ አልፈው ሌላው ገላውን እንዲሸጥ የሚደልሉ መኖራችውን አረብ ሀገር ያለ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ማለት ግን በአረብ ሀገር ያሉ ሴቶች በሙሉ ይሸረሙጣሉ ማለት አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ እየገለጽኩ ያለሁት እውነታ ጥቂቶች ባራከሱት ስም ሁሉም እየተሰደበ ነው አልኩ እንጂ ሁሉም አንድ አይነት ነው አላልኩም፡፡ አልልምም፡፡ በጣም ስርዓት ያላቸው አንገታቸውን ደፍተው የሄዱበትን አላማ የሚያሳኩ ሞልተዋል፡፡ ቤተሰባቸውን ጥቂት ከማጉረስ አልፎ መሰረታዊ ለውጥ ያስከተሉ እንዳሉ አናውቃለን፡፡ ለፍቅረኛቸው አለያም ለትዳር አጋራቸው የገቡትን ቃል ጠብቀው የሚቆዩ በዋዛ የምናሰላቸው አይደሉም፡፡ ለነገ ህይወታቸው መመስረቻ የሚሆን ለፍተው የቋጠሩ አጋጥመውኛል፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ከምናያቸው የህዝብ ማመላለሻ ታክሲ ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጋው አረብ ሀገር መጥተው በሰሩ እህቶች ለቤተሰብም ይሁን ለራሳቸው መተዳዳሪያ የተገዛ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡



   እንዲያውም ላባቸውን አንጠፍጥፈው፣ የደረሰባቸውን መከራ ተቋቁመው የሚኖሩ መኖሩ በጉልህ ሊጻፍ የሚገባው ነው፡፡ በዚህ አጸያፊ በምንለው ተግባር ተሰልፈው ያሉት 10 በመቶ የሚሆኑት እንኳን አይሆኑም፡፡ በእነዚህ ጥቂቶች ሁሉም ይሰደባል እያልኩ ነው፡፡ ከእነዚህም በመጥፎ ተግባር ላይ ከተሰማሩት ውስጥ ራሳቸውን ለውጠው ቤተሰባቸውን የለወጡ አሉ፡፡ በተጨማሪ አብዛኛዎቹ ወደው ሳይሆን ሁኔታዎች ናቸው የሚገፋፉዋቸው ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት የጻፍኩት ታሪክ ላይ ማስተላለፍ የፈለኩት በዚህ አይነት ሁኔታ ተገደው ሊገቡበት ይችላሉ የሚል መልዕክት የሰነቀ ነው፡፡ ችግራቸው ካለፈ በኋላ የሚወጡ የመኖራቸውን ያህል ‹‹…የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም..›› ብለው ሌሎችን ሁሉ እየደለሉ የሚከቱ ብሎም የሚያቃጥሩ መኖራቸውን በአረቡ አለም ላይ ያለን ሰዎች እያየን ነው፡፡  እኔ ወደ የመን ከመምጣቴ በፊት የተደረገ አሁንም የሚደረግ አንድ ታሪክ ብተነፍስ ብዙ ያስረዳልኛል፡፡ ተንፍስ የምትሉ እጃችሁን አውጡ…እዛ ጋር ማነሽ ሁለት እጅ ማውጣት….አባባ ተስፋዬ ትዝ አሉኝ፡፡ እኛን ስርዓት ለማስተማር አትጋፉ..አንተኛው እዛ ጋር.. ሲሉ ዞረን እያየን ቁጭ በሉ እስኪሉን የጠበቅነው…ድካማቸውን፣ እኛን በስርዓት ለማነጽ ያደረጉትን ነገር፣ ብሎም ያደግንበት ስርዓትና ቤተሰባዊ ከበሬታ /መከባበር/ ዛሬ የት ጠፍቶ ይሆን? በሬድዬ ፋና አፋልጉኝ እናስነግር እንዴ?

  

     ወደ ታሪኬ ልመለስ…እዚህ አንድ ደላላ አለ፡፡ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው ይሉታል፡፡ ለዚህ ደላላ ወኪል ሆና የምትሰራው ሴትዬ ሳሪስ አካባቢ ነው ያለችው፡፡ የሴትዮዋ ልጆች የመን ውስጥ ከሰውዬው ጋር ሰራተኛ እያሉ ከኢትዮጵያ የሚያግዙትን ሴቶች ማስቀጠሩ ብቻ አላረካቸውም፡፡ የሚያዋጣ አዲስ የስራ መስክ ፈጠሩ፡፡ ወይም በኢህአዲጊኛ አባባል ለስራ ካላቸው ተነሳሽነት አዲስ የስራ ፈጠራ ፈጠሩ እንደበል? መሸጥ ጀመሩ፡፡ ስለጉዳዩ ያጫወተችኝ ዛሬ በኤች.አይ.ቪ ተለክፋ አንድ ልጇን ይዛ ወደ ሀገር የተመለሰች እህታችን ነች፡፡ ሀገር ከገባች ስድስት ወር ቢሆናትም ዛሬ ያለችበትን የጤና ሁኔታ አላውቅም፡፡ የመን ውስጥ ብቻ 7 ጊዜ አፖርሽን ማድረግዋን ስትነግረኝ 4 በግድ በተደረገ ወሲብ የመጣ ጽንስ ነው ያስወረደችው፡፡ በመጨረሻው ጊዜ ልክ የዛሬ አመት በ03/07/2011 የወለደችውን ልጅ ግን አግብታ ቢሆንም እርግዝናዋ ሲመጣ አስረጋዡ ሄደ፡፡ ወደማይቀረው አለም ነጎደ-ነፍስ ይማር፡፡ አሟሟቱ ድንገት ወይም አሁን ይዛ የገባቸውን ልጅ ልትገላገል አዋላጅ ፍለጋ ከሆስፒታል ሆስፒታል ተንከራተተች፡፡ ሁሉም ሊቀበሉ እና ሊያስተናግዱዋት አልፈለጉም፡፡ ሰበቡ የኤች.አይ.ቪ ተጠቂ ስለሆነች በሆስፒታላችን አናዋልድም ብለው ነው፡፡ በመጨረሻ UNHCR ቢሮው ቅድመ ክፍያ አድርጎ በብዙ መለማመጥ ሙተወከል የሚባል ሆስፒታል በኦፕሬሽ ወለደች፡፡

 

     ‹‹..እንኳን ማርያም ማረችሽ..›› ለማለት ስሄድ ደነገጥኩ፡፡ በብዙ ሰው ተከባ የማውቃት ልጅ ብቻዋን ተንጋላ ተኝታለች፡፡ ለወትሮው አጀበ ብዙ ነበረች ባሏ ሲሞት አጅሬው ነው የገደለው..እያሉ ጥቂት ሰዎች ርቀዋት ነበር፡፡ እንዲህ ብቻዋን ትቀራለች ብዬ ግን አላሰብኩም፡፡ ብዙ ሰው ስለምታውቅ ግርግር ይኖራል ያልኩበትን ሰዓት አሳልፌ መሄዴ ነው፡፡ ስገባ ጠላታችሁ ስቅቅ ይበል ተሳቀኩ፡፡ አብራኝ ሄለን የምትባል ጉዋደኛዬ /እህቴ/ አለች፡፡ ምንም ከጠያቂ የመጣም ሆነ ገዝታ ያስቀመጠችው የሚበላ የሚጠጣ ነገር ባለመኖሩ ባዶ እጄን በመግባቴ ይበልጥ ተሳቀኩ፡፡ እጄ ላይ ያለው ሳንቲም ከታክሲ ከተረፈ አንድ ደረቅ ዳቦ የሚገዛ ሽርፍራፊ ሳንቲም ብቻ ነው፡፡ ምን ላድርግ? በእርግጥ ቤት ያስቀመጥኩት ሳንቲም አለኝ፡፡ ቤቴ ግን ሩቅ ነው፡፡ ‹‹አልበር እንዳሞራ ሰው አድርጎ ፈጥሮኛል…›› ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ብቻዋን ጥያት ወደ ቤቴ መሄድ እንደሌለብኝ ራሴን አሳመንኩት፡፡ ሄለን ከእኔ ጋር ሆስፒታል ማደር አትችልም፡፡ ጠዋት ስራ ስለምትገባ እንቅልፍ ይጥላታል፡፡ ሁለተኛ እህቷ ልትቆጣ ትችላልች፡፡



    ገንዘብ መያዝዋን ስጠይቅ 3.000 የየመን ሪያል እንዳላት ነገረችኝ፡፡ ተቀበልኩዋት፡፡ ብዙ ምስሎዎት በሀብታሚያ የተራመድኩ እንዳይመስሎት፣ ሶስት ሺህን ያህል እንዴት በቦርሳዋ ይዛ ትሄዳለች እንዳይሉ…በዶላሪኛ ሲቀየር ያኔ 15 አሁን 12 ዶላር ነው፡፡ 



    ወጣንና ሄለንን ታክሲ አሳፈርኳት፡፡ ለበሽተኛዋ የምትበላው እና የምትጠጣው ገዛዝቼ ስገባ ከተበደርኩት ሳንቲም ላይ ለራሴም ራሴ ራት ጋበዝኩት፡፡ ተመልሼ ስገባ ‹‹መጣህ?..›› አለች፡፡ አይኗ ግን እጄ ያነጠለጠለው ላስቲክ ላይ መሆኑን ሳይ ርሃብ ሸንቆጥ እንዳደረጋት ገምትኩና ፈጠንኩ፡፡ እንዳጎርሳት አልፍልግችም፡፡ የዚህ ሀገር ባህል አለ፡፡ ወንድ እና ሴት እንደፈለጋቸው አይሆኑም፡፡ ለዛ መሰለኝ እና ‹‹አንቺም የእነሱ ባህል ያጠቃሻል? ቀና ብለሽ መጉረስ አቅቶሽ የለ? ላጉርስሽ…›› አልኩና አጎረስኳት፡፡ አብልቻት ስጨርስ ቀስ በቀስ ወሬያችን ደራ፡፡ የመጣችው አሽጣል በሚባል ደላላ ነው፡፡ ስሟን መጥራት ያልፈለኩት ሳሪስ ያለች ሴትዬ 4000 ሺህ የኢትዮጵያ ገንዘብ አስከፍላ ላከቻት፡፡ የሴትዮዋ ልጅ እዚህ የመን ውስጥም ከአየርማረፊያ ድረስ መጥቶ ተቀብሎኝ ደላላው ቢሮ ወሰደኝ፡፡



    ይህን ስሰማ በፊት ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች ውስጥ አንዱን ሊያጠናክር የሚችል መረጃ ትሰጠኝ ይሆናል ብዬ ጥያቄዬን ማከታተል ጀመርኩ፡፡ ቢሮው ውስጥ ማደሪያ አለ እዛ ሲያሳድሩ እና ኮንትራት ላመጡለት ሰው እስኪያስረክቡ ሌላ ግፍ ይሰራሉ ይባላል እውነት ነው? እፍረት ፊቷ ላይ ክልብስ ሲል በቅስፈት አየሁት፡፡ የደረሰባት ነገር እንዳለ ገመትኩ፡፡ ማበረታት ያስፈልጋል እና አንዲት ልጅ የደረሰባትን ነገር እንደነገረችኝ ስሟን ሳልነግራት አወጓኋት፡፡ ለእኔም እንዲሁ ነው የገጠመኝ አለችና ጀመረች፡፡ በል በለው…እያልኩ አሰፋ ማሞ ወጣቱን ፋይዳ ለሌለው እልቂት እንደከተተው እኔም አሷን ወደማናዘዙ ገባሁ፡፡ በእየአንንዱ ንግግሯ መካከል ማደፋፈር ግድ ነበር፡፡



   ‹‹..ከኤርፖርት ወስዶኝ ቢሮው ስንገባ ከምሽቱ 5 ሰዓት ተኩል ነው፡፡ በቢሮው አቋርጦ ቁልቁል በደረጃ ወረድን አስጠሊታ ሽንት ቤት ይመስላል፡፡ ማደሪያዬን አሳይቶኝ ሲመለስ ክፍል ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሳላጤን በጨለማው እጅ አረፈብኝ፡፡ ልጮህ አፌን ስከፍት ሽሽሽሽ… የሚል ነገር ሰማሁ፡፡ የሚሆነውን ጠበኩ..ብቻ የሚሰሩት ስራ ተወኝ፡፡ አረመኔዎች ናቸው፡፡ እናታቸው እዛ ባራችንን በልታ…እ!!...›› አለችና እልኋን በተቃጠለ አየር መልክ ለማስወጣት ስታምጥ አየኋት፡፡ ከዚህ ሁኔታዋ ለመረዳ የቻልኩት በሌሎቹ የደረሰ ሁሉ እንደደረሰባት ነው፡፡ ግን የማወቅ ጉጉቴ ንሮ..ንሮ..በየአንዳንዱ ንግግሯ መሀል እያደፋፈርኩ፣ ሰምቼዋለሁ እያልኩ አውጣጣኋት፡፡ ቀፋፊ በሲሚንቶ የተሰራ አልጋ መሳይ መደብ ላይ በሶስት ቀን ውስጥ ሶስት ሰው እንደተገናኛት እፍረት በሸበበው ቁርጥርጥ ቃላት አሰማችኝ፡፡ እነዚህ ኮንትራት ስራ እያለች የምትልከው የሳሪሷ ሴትዬ ልጆች ያልሰሩት ግፍ.. ያላለቀሰችባቸው የሀበሻ ሴት የለችም፡፡ ካራቸው ለራሳቸውም ስሜት መተንፈሻ ያደርጋሉ የሚል ነገር ብሰማም ይህን እውነት ያሉ ሴቶች ግን አልገጠሙኝም፡፡ ለኮንትራት ስራ የሚሄዱ ሴቶች ኤች.አይ.ቪ ተመርምረው ስለሆነ ያለሀሳብ የግፍ ወሲብ ለመፈጸም ገንዘቡን የሚያዘንብ አረብ በመብዛቱ ወገናቸውን መሸጥን ለአረቦቹም አስተማሩ፡፡



     ዋናውም ሰውዬ ጀመረ አሁንም ይሰራል፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች ግን ማሀረቤን ያያችሁ አላየንም እየተጫወቱ የጠገበ ውሻ አይጮህም ብሂልን ሲተገብሩ የየመን መንግስት ሁኔታውን ደርሶበት ዳግመኛ ወደ የመን እንዳይገቡ አገዳቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን የጠየቃቸው አካል የለም፡፡ ለወገኑ ተቆርቋሪ የሆነው መንግስት በድብቅ ሽልማት ሳይሰጣቸውስ ይቀራል? ስንዝር ያለተራመደ ሁሉ ሲሞት መቃብሩ ላይ በጉልህ ‹‹..ሩጫዬን ጨርሻለሁ!!›› ተብሎ እንደሚጻፍለት ከንቱ ነው እዚህ ያለ ኤምባሲ፡፡ ሀሺሽ ይዛ ሀገራችንን ቅሌት ውስጥ እንደከተተችው ዲፕሎማት በርበሬ እና የመን ውስጥ ክልክል የሆነ ነገር /መጠጥ/ ከመነገድ የዘለለ ስራ የላቸውም፡፡ ወገን ተበደልኩ ጥቃት ደረሰብኝ ብሎ ወደ ኤምባሲ ሲሄድ መልሰው ለደበደቡ እና ጉዳት ላደረሱ ሰዎች መልሶ ማስረከቡ ‹‹እኛ ለገረድ አልመጣንም!..›› እያሉ መዘባነናቸው የታወቀ እና በስደተኛው ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡



    በአንድ ወቅት ኮሚኒቲውን በሊቀመንበርነት የሚመራው ሰው ሁንም አለ፡፡ ችግር ደርሶባት አድኑኝ ብላ ወደ ኮሚኒቲ የሄደችን ሴት አሳልፋችሁ ስጡኝ ያሉ የመናዊያን ትንሽ ገንዘብ አጎረሱት፡፡ አታስቡ የመን ሙስና ወንጀል አይደለም፡፡ በቃ!..በህይወት ማላውቃቸው አያቴ ውሻ በበላበት ይቾሀል ይሉ ነበር..ሲባል የሰማሁትን ተረት እውነታተገበረው አሉኝ፡፡ በደረሰባት ድብደባ እና ስቃይ ጭንቀት ውስጥ ገብታ እሳቤቀዋ ትንሽ ተዛብቶ ሳለ ወደ አሰሪዎችሽ መመለስ አለብሽ ብሎ ጥብቅና ለአረቦቹ ቆመ፡፡ ሊመልሳትም ቆርጦ ወሰነ፡፡ ልጅት ራሷን እዛው ኮሚኒቲ ውስጥ በገመድ ሰቀለች፡፡



    አሁን በቅርቡ ወዳጄ እና የሞያ ባለደረባዬ ነብዩ ሲራክ ‹‹…በጅዳ ቆንስል ግቢ የውሃ ገንዳ ሰው በላ ! ኢትዮጵያዊቷ ሞታ ተገኘች!..በሚል ያቀረበውን ዘገባ እንመልከት እስኪ..ልብ በሉ ይህች ኢትዮጵያዊ ሞታ የተገኘው በጅዳ ቆንስል ኢንባሲ ግቢ በሚገኘው ገንዳ ውስጥ ነው፡፡ አሁን እኔ ያለኳችሁም በየመን ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ውስጥ ነው ራሷን ያተፋችው፡፡ አለም ደቻሳ በቤሩት ቆንስላ በር ላይ ነው ያን የመሰለ አሳፋሪ ተግባር የተፈጸመባት፡፡ ሌሎችም የደረሱ በደሎችን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ይህን ይህን ስናይ የኢትዮጵያ መንግስት ከኋላ ቆሞ ‹‹እሰይ ስለቴ ሰመረ..›› ሳይል ይቀራል፡፡ በወገን ደም የቀለደ መንግስት እህቶቻቸውን የሚሸጡ ደማቸውን የሚመጡ ትውልዶችን የሚያበረታታ መንግስት አሁንም ከሳዑዲያ ወደ የመን የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን እያሰቃየ ነው፡፡



  ወደ ወዳጄ ነብዩ ሲራክ  ዘገባ ልመለስ…ወቅቱም ሌሊት በግምት 315 አካባቢ መሆኑን ለማዎቅ ችያለሁ፡፡ የዚህች እህት ሞታ መገኘት እንደሰሙ ምክትል ቆንስል ሸሪፍ በቦታው በመገኘት የአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሬሳውን ከጉድጓድ አውጥተው ነብሷ ከስጋዋ ያልተለየውን እህት ለማዳን ሲታገሉ የአይን ምስክር ነበሩ፡፡ብሏል ነበዩ…በሆዳቸው ባለተረፈች…ባለተረፈች ሳይሉ ይቀራሉ?ሞቷን አይተው ለመርካት ይሆን ቦታው የተገኙት? የመጥፎ ስራቸውን ውጤት ፍሬውን ሊያቸጭዱ መሆን አለበት፡፡

   

     እንደታዘብኩት በወቅቱ የነበሩት መርማሪዎች እጅና እግሯ ታስሮ እያለ በገንዳው ውስጥ ገብታ ስለሞተችው ስለዚህችው ልጅ አሟሟት ዙሪያ ግራ በመጋባት መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ በቦታው ነበርኩ፡፡ የወቅቱ የቆንስሉ ዘበኛ የነበሩት አቶ ገሬ ስለ ተፈጠረው ሁኔታ ማብራሪያ ሲሰጡም ሟች ገና ከምሽቱ በግምት 400 ሰአት አካባቢ ወደ ካፍቴሪያው ግቢ እንደመጣችና የዓዕምሮ ህመምተኛ በመሆኗ ከመጮህ በቀር አድራሻና ስሟን ባለመናገሯ እጅና እግሯን በማሰር ወደ ጊዜያዊ መጠለያው እንዳስቀመጣት ተናግሯል፡፡ ከዚያም አቶ ገሬ ሲያስረዳ ከምሽቱ 200 አካባቢ ግቢን በሙሉና ገንዳውን ጨምሮ ከሰወች ጋር በመሆን ቢያፈላልጋትም የውሃው ገንዳ ገበድ ያለ ብረት መዝጊያ ገርገብ ብሎ እንዳገኘው በመብራት ቢመለከትም ምንም ነገር እንዳላየ ገልጿል፡፡ አቶ ገሬ በማከል ሲናገር ብዙም ሳይቆይ ግን ልጅቷ ከገንዳው ገብታለች ብሎ በመጠራጠሩ ገንዳውን ለማስፈተሽ ለፖሊስ ጥሪ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ከዚያ ፖሊስ መጥቶ ገንዳው ሲፈተሽ የዚህች ሬሳ ተገኝቶ በፖሊሶች እንደወጣ በቦታው ተገኝቸ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በመጨረሻም የቆንስሉ ዘበኛ ለጥያቄ ወደ ጣቢያ መወሰዳቸውን ተመልክቻለሁ፡፡ እኔን ጨምሮ ዲፕሎማቶችና የኮሚኒቲ ሃላፊዎች ንጋት ላይ ወደ የቤታችን ተመልሰናል፡፡


          ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካቶች ያበዱ የኮንትራት ሰራተኞች በቆንስሉ ግቢና በጊዜያዊው መጠለያ ከአርባ የማያንሱ በአሁኑ ሰአት እንደሚገኙ ከቆንስሉ ያገኘሁት መረጃ ያስረዳል፡፡ በቆስል ከዚህ በፊት ተጠልለው የነበሩ አንዳን እህቶች በቆንስሉ በተጠጋንበት ቆንስል መስሪያ ቤት ዘበኛ አቶ ገሬ በሴትነታቸው ሊያጠቋቸው እስከመደብደብ እንደደረሱ ለቆንስል መስሪያ ቤቱ መከሳቸውን በመረጃ ማቅረቤ አይዘነጋም ፡፡ ዛሬ በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርኳቸው አምባሳደር መርዋን ከዚህ በፊት ስለተፈጸመው ጥፋት ጠይቄያቸው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸውልኛል፡፡

By: Nebiyu Sirak…. ›› ይላል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል እነዚህ ከአርባ ባላይ ሴቶች ወደው ለመዝናናት ያበዱ ናቸው የሚል ይኖራል?