Saturday, February 16, 2013

የነብዩ ሲራክና በሳውዲ አረቢያ የሪያድ እና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማህበርውዝግብ ለምን አስፈለገ?


እንነጋገር መነጋገር መግባባትን ያመጣል
የነብዩ ሲራክና በሳውዲ አረቢያ የሪያድ እና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማህበርውዝግብ ለምን አስፈለገ?

    በግሩም ተ/ሀይማኖት
   ሰሞኑን ፌስቡክ ድረ-ገጽ ላይ የተለያዩ ሰዎች ሲወነጀሉ ይስተዋላል፡፡ ከነዛ ውንጀላዎች መካከል የሳዑዲ አረቢያውን ሳየው ስለስደተኛ የተመለከተ ነውና ሳበኝ፡፡ በዛ ያለውን ውንጀላም ስመለከተው በጥላቻ ላይ የተመሰረተ የሚመስል ነገር ይታያል፡፡ ነብዩ ሲራክ ምን አደረገ? ምን አላደረገም? ታገል ሰይፉስ? ሀና መታሰቢያስ?…ሌሎቹስ? እኔ ማንም ይወቀስ ማን ከጀርባው ያለውን ባላውቅም ተወቃሹ የሰራውን ያህል ወቃሹ ሰርቷል ወይ የሚለውን ማየት ግድ አስቀድማለሁ፡፡
     ስለዚህም ነብዩ ሲራክ ለስደተኛው የቻለውን ያህል ድምጽ ሆኗል፡፡ ታዲያ ለምን ተወቀሰ? የመን በጦርነት ማዕበል ስትናጥ የመን ላለን ስደተኞች የነብዩ ሲራክ፣ የአሉላ ከበደ እና ጃለኔ ገመዳን ያህል ድምጽ የሆነ ማን ነበረ? የመን ያለ ስደተኛ ለሶስቱ ክብር አለው፡፡ ብሶቱን፣ ችግሩን፣ ጩኸቱን አሰምተውለታልና፡፡ ወያኔ አንዴ ዜጋውን የረሳ፣ የገፋ ነው፡፡ ተቀዋሚዎችስ የት ነበር ድምጻቸው? ለወገኑ ጩኸት እና እልቂት ጆሮ የማይሰጥ ተቃዋሚ በስም ተለብዶ ቢቀመጥ ፋይዳው ምንድን ነው? ከቤት ንብረታችን በጦርነት ተፈናቅለን መጠጊያ በማጣት UNHCR በር ላይ መፍትሄ ጥየቃ ተኝተን ነበር፡፡ በጦርነቱ ምክንያ ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል፡፡ UNHCR በር ላይ በወታደር ጥይት፣ በአስለቃሽ ጋዝ፣ በውሃ….አሰቃቂ ድብደባ ተደርጎብናል፡፡ ይህን ሁሉ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሶስት ጋዜጠኞች ዘገባ ውጭ ማን ወገኔ አለን? ተቃዋሚዎች ወገኖቻችን ተጎዱ ብለው ያቅማቸውን ተቃውሞስ አስሙ እንዴ? ወይስ የወያኔ ሰዎች እንደሚሉት ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ የመን ያለ ስደተኛ ቤት ሲጠረግ የወጣ ቆሻሻ ነው ብለው ከሰው፣ከዜጋ አልቆጥንም? በዚህ ነገር ከተቃዋሚም ከወያኔ ጀሌዎችም አልታደልንም፡፡ ምንም ያልሰሩ ተጎብረው ለምን እነሱን መውቀስ አልተፈለገም? ትንሽም ቢሆን ስለስደተኛ ችግር የሚናገረውን ማጥቃት ተፈለገ?
     ‹‹ከጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ ጀርባ ያለው መጋረጃ ሲገለጥ!!..›› በሚል ርዕስ የቀረበውን ቅሬታ አየሁት፡፡ ሬድዬ ጣቢያው እኛም የመን ያለውን ሁኔታ በተደጋጋሚ ብንልክላቸው የህዝብ ችግር መሆኑን ዘንግተውት ይሁን ጉዳዩ አይመለከታቸውም ወይ እስክንል በዝምታ ያለፉበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ስለየመን የቀረበውን ዘገባ ሁሉ እነሱን ትተን ለነብዩ መስጠት ጀመርን፡፡ እሱም ፈቅደው ያሳለፉለትን ይሰራል እነሱ ፈቅደው የላቀረቡለትን ምን ማድረግ ይችላል? ይህን ከግንዛቤ ማስገባት ግድ ይላል፡፡
    ከጽሁፉ መካከል ‹‹ ..ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የመረጃ እጥረት ያለበት ከመሆኑ አንጻር የሚያቀርባቸው ዜናዎች ከሳውዲ እስር ቤት ያልዘለሉ እና በኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳዮች ላይ ከማጠንጠን ይልቅ ጊዜያዊ ባልሆኑ የግለሰብ ጉዳይ ገባ ወጣ የሚቆዝሙ ተራ ወሬዎች ናቸው።…›› መረጃ እጥረት አለበት ከማለት የምናቀውን መረጃ ካልሰጠነው ማንኛውም ጋዜጠኛ ሙሉ መረጃ ማቅረብ እንደሚቸግረው ስውር አይደለም፡፡ ሌላው የሚዘግበው የግለሰብ ጉዳይ ነው ማለትስ ምን ማለት ነው? የግለሰብ ጉዳይ ተራ ነገር ነው እንዴ? ግለሰብ ዜጋ አይደለም እንዴ? ግለሰብ ወገን አይደለም? ለዚህ ነው እንዴ ወገን ተጎዳ ለወገን ድረሱ ሲባል ችላ የሚባለው? የግለሰብ ስብስብ አይደል እንዴ ህዝብ የሚሆነው? እስር ቤት ያለ ኢትዮጵያዊስ ቢሆን ዜጋ አይደለም? ስለእስር ቤት መጻፍ የለበትም? እናንተ ይሄን ዘግብ ይሄን አትዘግብ ልትሉ ስልጣኑስ አላችሁ ወይ? ወያኔ እንደመደበው እናንተ ጋርም የዜጋ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አለው እንዴ? የዜጋ (የሰው) አይብና ጎመን የለውም፡፡ ይሄን አባባል ሳየው ሰው እናንተ በምትፈልጉት የሀሳብ ምህዳር ካልሄደ መውቀስና መዝለፍ የምትፈልጉ ያስመስላችኋል፡፡ እናንተ የማታደርጉትን ለምን ሰው እንዲያደርግ ትጠብቃላችሁ? ከእናንተ የሚጠበቀውን ትግል አድርጋችኋል ወይ? ነብዩ የሚዘግባቸው የግለሰብ የስደት ስቃይ ታሪኮች የኢትዮጵያዊያን ስቃይ ታሪክ አይደለም እንዴ? ይሄ ወያኔ ለዜጎች ያለውን ፍቅር ነው እንዴ የሚያሳየው?
  
        በሌላ በኩል በተጨማሪ ዘገባ ደግሞ ‹‹…አቶ ነብዩ በወቅቱ የዚህን ወጣት ህይወት ከሞት ለመታደግ ህክምና ማግኘት የሚችልበትን መላምት በመፍጠር ወገናዊነት እና ርህራሄ ያልፈጠረባቸውን የወያኔ ጀሌዎች አስተባብሮ የዚህን ኢትዮጵያዊ ወጣት ችግር ቀርቦ መረዳት ሲቻል ወጣቱ በዚህ ፎቶ ላይ እንደተገለጸው ወድቆ ብርድ እና ጸሃይ ሲፈራረቅበት አይቶ ማለፉ የሚያሰተዛዝብ ከመሆኑም በላይ እራሱን የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ዘጋቢ ነኝ ብሎ የሚጠራውን የአቶ ነብዩ ሲራክ ልብ እንደ ወያኔዎቹ በኢትዮጵያውያን ላይ ምን ያህል እየደነደን መምጣቱን ያሳያል።…›› የሚል ሰፍሮ አየሁ፡፡ አንድ ጣትህን ሰው ላይ ለመጠቆም ስትሞክር የሚታጠፉት ሶስቱ ወደ አንተ እንደሚያመለክቱ አትርሳ የሚል ጥቅስ እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ ይህን ለማለት የተነሱ ሰዎች ለምን እራሳቸው ወገናዊነት እና ርህራሄ እንዲፈጠርባቸው አልፈልጉም፡፡ መላምቱን እናተስ መፈለግ አይጠበቅባችሁም ነበር? ነብዩ አይቶት ዝም ካለ ያስወቅሰዋል፣ ያስጠይቀዋል፡፡ ነብዩ መየቱን ያዩት ሰዎች ራሳቸውስ ለምን ዝም አሉ? እዳውን ሀላፊነቱን ለእሱ ሰጥቶ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ እጅ የመታጠብ ያስል ወቀሳ መሰንዘሩ አያሳዝንም? አያሳፍርም? ከላይ ያነሳችሁት ጽሁፍ ላይ ‹‹…ስለእስር ቤት፣የግለሰብ ጉዳይ..›› ነው የሚዘግበው ብላችኋል፡፡ አሁን ደግሞ ስለግለሰብ ለምን አልዘገበም ትላላችሁ…አልተምታታም? ነብዩ ልክ ነው ልክ አይደለምም እያልኩ አይደለም፡፡
     ግን ማወቅ ያለብን እውነታ የራሱ አይደለም ራዲዮ ጣቢያው፡፡ ወይም ፕሮግራም መሪ አይደለም፡፡ ወኪል ነው፡፡ ስለዚህ ያየውን የዘገበውን ፕሮግራም መሪዎች ካልፈቀዱለት ምን መብት አለው? ምን ማድረግ ይችላል? ምንም፡፡ የጀርመን ድምጽ ሬድዮ አዘጋጆች ዘገባውን ካላቀረቡለት ጽፎ በማህበራዊ ድረ-ገጾች መበተን ነው ያለው አማራጭ፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ሁለት ነገሮችን ማንሳት እወዳለሁ፡፡

1… ከተወሰኑ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ውጭ እነሱ የሚፈልጉትን ሀሳብ የሚያራግብ ካልሆነ፣ በእነሱ መስመር ተጉዘህ ካልሆነ ለመለጠፍ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ ብዙዎች ስለመናገር መጻፍ መብት ልክ እንደ ወያኔ ከአፍ ባልዘለለ ይደሰኩራሉ እንጂ ሀሳብህን ረግጠው በእነሱ አላማ እና መስመር ያለውን ብቻ ነው የሚለጥፉት፡፡


2…እነሱ ፍቃደኛ ሆነው ቢለጥፉ አለያም በፌስቡክ ድረ-ገጽ ላይ ‹‹..ይህን ግለሰብ እርዱት መታከሚያ አጥቶ..›› ቢባልስ ማን ሊደርስለት ነው? ማን ሊረዳው ነው? በተደጋጋሚ ያየነው ነው እኮ፡፡ እኔ ብዙዎችን ለማዳን ያቀረብኩትን ጥያቄ ሁሉም ያሳዝናል ብሎ ከማለፍ ውጭ ውጤት አላየሁም፡፡ ብልቱን ተቆርጦ ሀረጥ የሚባል የIOM ካምፕ ውስጥ በቂ ህክምና ሳይደረግለት አለ፡፡ ወገቡ አጥንት ተሰብሮ ችግር ውስጥ ነው ማሳከም የምትችሉ ሰዎች..የመሳሰሉ ጥጥሪዎች አቅርቤ መልስ የሚሰጥ አልተገኘም፡፡ ብርድ ታሞ ቢባልማ ያሳዝናል የሚል ላይኖርም ይችላል፡፡

     አሁን በቅርቡ ያተከሰተውን ሁለት ድረ-ገጾች ለጠፉት የኢሳት ሬድዮ ጥሪዮን አሳልፎልኛል፡፡ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ግን ለታማሚዎቹ ማንም መልስ አልሰጠም፡፡ ከዚህ ከዚህ አንጻር ሲታይ ተስፋ መቁረጥም ይኖራል፡፡ ጽሁፉ ላይ ሳይ ደግሞ በነብዩ በኩል ያለውን ችግር ቀርባችሁ ለመረዳት የሞከራችሁበት አጋጣሚ ያለ አልመሰለኝም፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ ከመወቃቀስ መነጋገር ይበጃል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ነገ ተነስታችሁ ሀሳባችንን ስለተጋፋህ ብላችሁ የወያኔ ተለጣፊ ማድረግና መኳል ብትጀምሩ ከሀሳብ ነጻነትን፣ የመናገር ነጻነትን፣ የመጻፍ ነጻነት ይገድበል ከምንለው ወያኔ አያመሳስላችሁም? በሳውዲ አረቢያ የሪያድ እና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማህበር
እና በነብዩ ሲራክ በሁለታችሁም መካከል ክፍተት ስላለ ተቀራርባችሁ ለመነጋገር ሞክሩ፡፡ መነጋገር መግባባትን ያመጣል፡፡