Friday, March 8, 2013

የሞት ጉዞ
 ልጠይቅህ ለማይረባ ስደትህ መሞት ለምን አስፈለገህ?
በነዛር ዳግ ተጻፈ…
ይህንን ጥያቄ የምጠይቅ ወንድሜ ከልብ ሆነ እንድትሰማኝ እፈልጋለ፡፡ ያለኸው የትም ይሁን የት ቢያንስ ትንሽ ጥያቄ እና መልዕክት አዘጋጅቼ ካለሁበት ቦታ ላይ እኔው ስደተኛ ወንድምህ እንዲህ እልሃለ ፡፡ በደንብ ስማኝ ወንድሜ በየትኛውም የስደት ስሜት ላይ ሁን ችግር ላይ ጥያቄዬን እንድትመልሰ እለምንሃለ፡፡

        አሁን ያለኸው ምኑንም በማታውቀው ሰሜት ውስጥ ሆነ ሰደት..ሰደት የሚለውን የልብህን ትርታ እያዳመጥክ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ከገባህበት የኑሮ አዘቅት ውስጥ ለመውጣት በምን በኩል አድርገህ አገሩ ጥለህ እንደምትወጣ  እያሰብክ ነው፡ በጎንደር ሱዳንን አለያም ቀይ ባህርን እንደምትሻገር፣ ሶማሊያን እንደምታልፍ እና የተሰፋው ምድር አረብ አገር እንደምትገባ ልብህ ሻቅሏል፡፡ እዛም ለመግባት ልብ እንዲጀግን፣ ወንድነት ዘራፍ እንዲል ከዘመድ፣ ከጎረቤት ከአካባቢ ከምታውቃቸው ሰዎች ውስጥ ያሳለፉትን የባህር ጉዞ ገድል ደጋግመህ አሰበሀል፣ ሰምተሃል፡፡ እነሱም የነገሩ ጥሩ እንጂ ችግሩን ስላልነገሩህ አንተም ከማን አንሳለ ብለህ መንገድ ለመጀመር አኮበኮብክ፡፡
 
        ከዛ በፊት ግን እነሱ ያልነገሩህን እውነታ፣ የሸሸጉትን ጉድፍ ላውጋህ..ምስጢር ያደረጉትን ታሪክ ላንቆርቁርልህ፡፡  የደረሱበትን ሰቃይ ያሉበትን ችግር እኔም ካለሁበት ቦታ ሁኜ ያየሁትን እርግጠኛ ሆኜ የሰማሁትን ደሞ መረጃ ፈልጌ እነግርሀለ፡፡ ታዲያ ስታነብ ነገሩ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ቢሆንብህ አይገርመኝም፡፡ ሙት ነው የምልህ አንተ የሰማው ነገር ሌላ ተኩሎ ተሽሞንሙኖ..አምሮ ነው፡፡ ያለው ሀቅ ደግሞ ተገልብጦ እንደሻማ በርተህ እንደቆሻሻ ተገፍተህ ነው፡፡
     አንተ ለመሰደድ አስበህ ተዘጋጅተህ ያለኸው እንዴት እንደምትሰደድ እንጂ ሰለምትከፍለው ሞት አይደልም ፡፡ ሞት እንዳለ ሰምተ ቢሆን እንኳን ቀኔ ከደረሰ ልሙት የሚለውን ደካማ አባባል ታጉተመትማለህ፡፡ እግዚአብሄር ያውቃል ብለህ እሳት ውስጥም ትገባ ይናሆል፡፡ እግዚአብሄር ግን እርዱኝ እረዳችኋለሁ አለ እንጂ ገደል ግቡ እኔ አወጣችኋል አላለም፡፡ ካለበለዛ ግን ልብ በል ተረት ይዘህ ተረት ሆነህ ነው የምትጓዘው፡፡ እሱም ይሁን ግድ የለም:: ዋናው የሰቆቃ ቦታ ስትገባ ሞት አሰር አጅ ጣዕም እንዳለው የምትረዳው ብዙም ሳትቆይ ጀልባ ላይ የሚያሳፍሩ በመኪና አፍነው የሚጭኑህ…በረሀውን ስምንትነሰ ዘጠኝ ቀን በእግር የሚነዱህ አረመኔ ደላሎች እጅ ስትገባ ነው ሞትን የምትመርጠው፡፡

     እመነኝ እየነገርኩ ያለሁት ገና አገርህን ብሎም አህጉርህን ጥለህ ሳትወጣ ሰላለው ሀቅ ነው፡፡ መቼም ለመሰድድ የተነሳ ልብ በአገሩ ወርቅ ሲዘንብ ቢያይ እንኳን ሊሰደድበት ያሰበው አገር ገብቶ የበለጠ እንቁ ይዞ መመጣት እንጂ አገሩ ላይ የሚዘንበው ወርቅ ለሱ መዳብ ነው፡፡ አንተም ምንም ቢኖርህም ያለህን ሸጠህ ተበድረህ ወደጉዞ ወደ ህልም አለም ታደርጋለህ፡፡ ሙት ህልም ነው፡፡ ገነት አድርገህ የሳልካት ሲኦል ሆና ትጠብቅሀለች፡፡ በውሸት ዝና ሰምተህ የተስፋ ምድር ወዳደረካት ሀገር ለመግባት ስትሰናዳ የሚያገኙህ ደላሎች አንተን በእጃቸው እስኪያሰገቡ አፈ ቅቤ ናቸው፡ የተሸከምከውን ገንዘብ እስኪረከቡ ድረስ ወዳጅነታቸው ልዩ አሳቢነታቸው ከእናት ልጅም በላይ ሆኖ እምነት ለእነሱ ልዩ ይሆናል፡፡ እነሱን ከሁሉም አሰበልጠ ልትመለከታቸው የምትሄድበትን ባህር የሚከፍሉ አድርገህ ልክ እንደ ሙሴ ልታያቸው ትችላለህ፡፡ ሙሴ የሰራውን ታላቅ ታምር ሰለምታውቅ፡፡

     ቤተሰብህን ተሰናበተ ከእናትና አባትህ ምርቃት ተቀብለህ ጉዞውን በመረጥከው መንገድ አድርገህ ወደ ስደት ሰትወጣ የሚታይ ሁሉ ሌላ ው፡፡ ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ገና መድረሻህን ሳታውቅ ምን መሰራት እንዳለብ ታስባለሁ፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ባህር አሻጋሪ ደላሎች የነገሩህን ነገር፣ የሰጡህን የተሰፋ ክምር ሰለምታስብ ነው፡፡ እነሱ ስራቸው አንተን ከተሳካላቸው አሻግረውህ በመሸጥ ካልሆነም ካንተ በድለላ ሰለሚያገኙት ገንዘብ እንጂ ያንተ ሞት ለነሱ ምናቸው ነው? ምናቸውም አይደለም፡፡ አንተ ብትሞት ካንተ ያልተማረ እውነቱ ያልተዋጠለትን ደግሞ ይወስዳሉ፤ ይሸጣሉ፡፡ ለዚህም ሲሉ እውነቱን የሚነግሩህ እንዳይመስልህ፡፡ አረብ ሀገር ገብተህ ሰለምታገኘ ገንዘብ፣ ሰለምትዝቀው ወርቅ እንጂ ሰለሚደርስህብ ሰቃይ ባህር ላይ ከነህይወት ሰለመጣል፣ በበረሃ ሰለመንከራተት እንዲሁም ሰለሞት አያወሩህም፡፡ ይህን ለምን አልነገሩኝም ካልክ ግን እውነትም ሞኝ ያውም በህይወቱ ቅልልቦሽ የሚጫወት ሞኝ ነህ፡፡ የተገለበጠ የነገር ታሪክ ውስጥ ራስህን የምታገኝው ጀልባዋ አንድ  ኪሎ ሜትር ሳትሄድ ነው፡፡ ወይም የተሳፈርክበት መኪና ከተማ ጥሎ እስኪወጣ ነው ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ አንተ ደግሞ የሰማህው ይህ አይደለም ፡፡ አይንእያየ ትደበደባለህ፣ ስደት ሴት ያደርግል፡፡ ትራባለህ፣ ትደፈራለህ፣ ብልት ይቆረጣል፣ ከባሰም ከነነፍስ ወደ ባህር ትወረወራለህ ወይም ትሰቀላለህ፡፡ ለዚህም  ምስክር የሚሆን ሰው ብታገኝ አታምንም፡፡ ራሱ የምትወረወርበት ባህር አፍ አውጥቶ ካልተናገረ…አረ ቢናገርም አታምነውም፡፡

    እየደረሰ ያለውን በደል እና ሰቃይ ችለህ ወደምትሻገርበት አገር ለመግባት ትጓዛለህ፡፡ ሶማሌ አልያም የመን ልትገኝ ትችላለ፡፡ የባሰ ደግሞ ጅቡቲ ከጣህ..፡፡ በቃ! እዚህ አካባቢ ያለው ሁሉ ጨለማ ነው፡፡  ብትጮህ የሚሰማ የለም፡፡ የሚደርስ የለም፡፡ ሁን ያሉህን ትሆናለ አድርግ ያሉሁን ልታደርግ ትችላለ፡፡ አሁንም ለእዚህ ማሰረጃ የምነግር የሩቅ ጊዜ ተሞክሮ ሳይሆን በቅርቡ አሁን በቅርቡ የመን ላይ እየሆነ ያለው ነገር በቂ ነው፡፡
     ምን ያህል ዜጋ የመን ላይ ያልተገደበ ስቃይ፣ በደል፣ ግፍ፣ እየደረሰባቸው እንደሆነ በእዚህ ክፍለ ዘመን ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል አሰቃቂ ነገር በወንድም በእህቶቻችን ላይ እየደረሰ ነው፡፡ በጥቂት ኢትዮጵያዊያን እና የአረብ ዜጎች ገንዘብ አምጡ ተበለው ታፍነው በበረሃ አየሞቱ የወሲብ ሱስ ባናወዛቸው ሰዎች የሚደፈሩ ሞልተዋል፡፡ በቁማቸው በእሳት የሚቃጠሉት የማንም ዜጎች ሳይሆኑ የአንተው ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ እነሱም ከሀገራቸው ሲወጡ እንዳንተው ብዙ ህልም ይዘው ነው፡፡ የተገኙት ግን በመቃብር አፋፍ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ሞት ምንድነው? ይሄ ሞትስ ለማን ነው? አንተንም የምጠይቀው ይህንን ነው፡፡

   እድለኛ ሆኖ ዕድል ቀንታው ሳውዲ አረቢያ፣ ዱባይ ኩዌት ብቻ አንዱ የነፍስህ መሻት የወደደው አገር ላይ ገበተሀል መቼም ከተራራ በላይ የሆነ መከራ፣ ሰቃይ አልፈህ ሰለመጣ ባለመሞት አምላክን አመስግነህ ሊሆን ይችላል፡፡ ያለፍከው ግን ሂደት እንጂ ውጤት አልነበረም፡፡ እንኳን በህገ-ወጥ መንገድ ሀገራቸው ገበተህ፡፡ በህጋዊ መንገድ ለገባው ስደተኛም የማይመቸው የአረብ ምድር የተደላደለ ኑሮ ህይወት ይሰጥሃል ልል አልችልም፡፡ የሰማህው ነገር ሁሉ ከንቱ የሚሆንብህ ሀገር ያለህን የሰውነት ሰሜት ሰታጣ በምድረ በዳ የሳልከው ስዕል ስታሰበው እውነትም ያኔ ስንት ሞት እንደሞትክ ይገባሃል ፡፡

   መኖሪያ ፈቃድ የለ፡፡ ገንዘብ የለ፡፡ ቤት የለ ምንም ሁን ብቻ ሰትገኝ ምን ስህተት እንደሰራህ ይገባሀል፡፡ ከፖሊሰ ጋር አይጥ እና ድመት ስትጫወት በራብ ስትቆላ በውሃ ጥም ስትቃጠል ምሬቱ ያኔ ይገባሀል፡ እንዲሁም እርግጠኛ ሁነህ ሰራ ብታገኝ እንኳን ሰለማይከፈልህ ደሞዝ ስታሰብ ማበድ ትጀምራለ፡፡ ብሶትህን ለሰው አታወራ አጠገብ ሊኖር የሚችለው የምትጠብቅ ግመል ወይም የምታጥበው መኪና ብቻ ነው፡፡ አሁን አንድ ነገር ይገለጽልሃል፡፡ ያለህበት ምድር ዝናብ የሌለው ደመና እንደሆነ ሁሉ የአንተ የስቃይ እና የብሶት ጩኸት ለአረቦች ምንም እንዳልሆነ አስብ፡፡

    ቀጥለህም ህልምህን ታሰባለህ፡፡ ለቤተሰብ የገባሀው ቃል፣ ልትገዛ የወጠንከው መኪና፣ ልትሰራ ያሰብከው ቤት፣ እነዚህ ሁሉ በአይነ ህሊና ይመላለሳሉ፡፡ ትንሽ ካሰብክ የሰማኸው ታሪክ የዘመድ፣ የጎረቤት፣ የአብሮ አደግህ ሁሉ ትዝ ይልሃል፡፡ እሱ ትዝ ሲልህ ከራስ ጋር እልም ያለ ፀብ ውስጥ ትገባለ፡፡ የሰማኸው ይህ ሰላልሆነ ግር ማለትብቻ ሳይሆን ታበረዳለህ፡፡ አብሮ አደግህ ደብዳቤ ጽፎ ዘመድህ ስልክ ደውሎ የነገሩ ሁሉ ግራ ይገባሃል፡፡ ተበድረህም ተለቀትህም ተሰደድ፡፡ ሳውዲ ዱባይ ግባ፡፡ ሰራ በሽ በሸ ነው ገንዘቡ ተቆጥሮ አያልቅም ያሉህ ይህን ስላልሆነ ታስባለህ፡፡ የገዙትን ቤት እና መኪና ወይም አንዱ ህንጻ ስር ተነሰተው የላኩትን ፎቶ ታስታውሳለ፡፡ በዚህ ነው ከራሰ ጋር ብጥ ብጥ ውሰጥ የምትገባው፡፡
ሁሉም መራራ የሚሆንብህ ደግሞ ስንት ጊዜ ከሞት ጋር እንደተፋጠጥክ ስታሰበው ነው፡፡ ምን አልባት ክው ብለህ ልትቀር ሁሉ  ትችላለህ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሞትን በአይን አይተኸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ታሪክ ወጥተህ ራስህን የምታገኘው ህልም የማይፈታበት ምድረ በዳ ላይ ነው፡፡ ወይ አትወጣ ወይ አትገባ፡፡

  እዚህ ጋር ሳልነግር የማላልፈው ሃቅ ሀገር ሁነህ የሰማሀው እውነታ እና ወዳጆችህ ያሉት የሰማይ እና የምደር ያህል የተራራቀ የሆነው በምን መሰለ፡፡ ምን አልባት እነሱ እድለኛ ሆነው ወይም በሌላ መንገድ ሂደው ካልሆነ በሰተቀር ሀገር ገዝተው ያየኸው ነገር ሁሉ ሰርተው እንዳላመጡት እኔም ምስክር እሆናለሁ፡፡ አንተም ጨክነህ በራስህ ፈርደህ ከመጣህ እውነታውን ትረዳለ፡፡
 
     እውነቴን ነው ያልኩህ አንተ ግን ይሄኔ ራሱ እዛ ተቀምጦ እኔን አትምጣ ይላል ብለህ ብታሰብ መብትህ ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ቢያንስ በሞት መንገድ አትጓዝ፡፡ የምትከፍለው ዋጋ እና ሞት ለማን እንደሆነ ደጋግመህ አሰብበት፡፡ ከዛም ሰትሰደድ ቢያን በእውነተኛው መንገድ ውጣ ነው የምል፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ሁሉም  ነገር ዘግይቶ ይገባሃል፡፡ ያኔ በጸጸት እሾህ ትጠቀጠቃለህ፡፡
 
     እይ ወንድሜ የምነግር ነገር አንድም ሀሰት የሌለው እውነታ ነው፡፡ የነገርኩ ግን ሁሉንም አይደለም፡፡ ሁሉም እውነታ እንደምትጓዝበት ባህር የሰፋ ስለሆነ ነግሬህም አውርቼም አልጨርስም፡፡ እያልኩ ያለሁት ቆም ብለህ ደግመህ ደጋግመህ አሰብ ከዛ የሆነውን ተቀበል፡፡ መንገዱ አድካሚ ቢሆን አንኳን ባትጠቀምም ትደርሳለህ፡፡ ከዛ ትክክለኛው ቦታ ስትገኝ አንተም ታሪክህን ትተርካለህ፡፡ የባህር ስቃይህን የበረሀ ውሃ ጥምህን ትናዘዛለህ፡፡ ከዛ በኋላ ሞትህን ስታሰበው መንገድ ላይ ሞተው ቀብራሃቸው ሰለመጣኸው እንዳንተው ስደተኞች አሰብ፡፡ መንታ መንታ እንባ ታለቅሳለህ፡፡ በማልቀስ ዝም አትልም ይህን ሁሉ ዋጋ የተከፈለው ለማን እንደሆነ ይሄ ሞትሰ ለምን / ለማን እንደመጣ ቢደላህም ባይደላህም ስታሰበው ትኖራለህ፡፡
  
    እኔም ይሄንን ሞት የከፈልከው ለማን እንደሆነ አጠይቅሃለ? ማብቂያውስ ምንድነው? አሁን ለጊዜው ለአንተ የምለው ይህን ይመሰላል ፡፡ ከውቂያኖሱ ጨልፌ የነገርኩህ ፡፡
   ቀጣይዋ ያንተው እህት (እህቴ) ናት ፡፡ እሷንም ይሄ ሞት ለማን እላታለሁ፡፡
ይቀጥላል ፡፡