Tuesday, June 4, 2013

ስደት ያጨለመው ልጅነት ‹‹ልጄን የማበላው…የማስተምርበት…›› እንባ..ለቅሶ




         በግሩም ተ/ሀይማኖት
   አንዳንዴ በስደት ተወጥቶ የሚታየው ነገር ራሱ ያማል፡፡ አልሳካ ብሎ የሰው እጅ የሚታይበት ወቅት ምን ይሰማል? የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ ስደትም ስደት አስከፊውን የአረብ ሀገር ስደት…ከአረብ ሀገርም ስለየመን እናውራ ብንል ዘግናኝነቱ፣ የበዛ ነው፡፡ የመን ደሞ ጥሩም አለ መጥፎም አለ። ሞቱም፣ ዱላውም፣ መደፈሩም፣ ማግኘት፣ ማጣቱም ሁሉም አለ። የመንም ይኖራል። ለጉድ!!..ይኖራል። ኑሮ ከተባለ ሀበሻ በየመንም እየኖረ ነው ማለት ይቻላል።
    ይህም ስደት ነው።
    የተሻለ ሳይሆን ብዙ ብዙ እውነት የማይመስሉ እውነቶች የተሰገጡበት ህይወት ነው በየመን ያለው። ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል ኮካኮላን ያስተረተው በየመን ያለ ሀበሻን ኑሮ ታይቶ ነው ማለት ይቻላል። በየመን ከሚኖረው በከፋ ሁኔታ የሚኖሩም አሉ፡፡ ሱማሊያ እና ጅቡቲም የሚኖሩ መኖራቸውን ሳትረሱ ማለት ነው።
     ችግር የማይነቅለው የለም፡፡ ተሰደናል። ሀበሻ በየመን እጅጉን አሰልቺ የሆነ ደግሞም ያልሆነ ዝብርቅርቅ ህይወት ከጥሩ ጎኑ መጥፎው ያመዘነበት ኑሮ መሀል ተሰንጎ ነው የሚኖረው።
    እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት፣ ጥርጣሬ..የበዛበት ነው ህይወቱ። መሰደብ -ሀበሺ..ሸቃላ..ኦሪያ..-ሱማሌ..-አስወድ..የዘውትር መጠሪያ ነው፡፡ ኤጭ!..ድሮስ ክብር በሀገር አይደል? ነው እንጂ። ክብር በሌለበት ተንቆ፣ ተዋርዶ መኖር፡፡ የራስ ያልሞቀ የራስ ያልደላ….ይህን ሁሉ ያስባለኝ ሰሞኑን አንድ ገጠመኝ ገጥሞኝ ነው፡፡
    የተደፈሩና ችግር የተፈጠረባቸውን ሴቶች ለማግኘት ጎራ እልበት ከነበረው ኢንተር ሶስ የተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ስራው የማውቀው ዝናቡ ክስት እና ብስቁል ብሎ አገኘሁት፡፡
 ዝናቡ ተክሌ ገ/እግዚአብሄር ይባላል፡፡ በውስጤ ሁሌም አደንቀዋለሁ፡፡ አንድ ልጅ አለው፡፡ ፊልሞን ዝናቡ ልጁ ሲሆን እናቱ የስምንት ወር ልጅ ጥላበት ይህችን ምድር ተሰናብታለች፡፡ ድፍን ሰነዓ ያለ ሀበሻ ነው ያዘነው፡፡ ልጁን ምን ያደርገዋል? እንዴትስ አድርጎ ያሳድገዋል ሲባል ብዙ መላምቶች ተደመጡ፡፡ ቤተሰቦቹ ጋር ይላከው፣ አንድ ጥሩ ስራ ያላት ፈልጎ ያግባ…ብዙ ብዙ ተባለ፡፡ ጎሽ ለልጇ ስትል ተጎዳች የሚለውን ወንድ ለልጁ ሲል ተጎዳ አስብሎ በታየበት ሁሉ ልጁን እንኮኮ አድርጎ አሳደገ፡፡ ቤተሰቡም ጋር አላከም፡፡ ሚስትም አላገባም፡፡ ልጄን በእንጀራ እናት..ብሎ ይሆን?..ምላሹ እሱ ጋር ነው፡፡ ዛሬ ፊልሞን ስድስተኛ አመቱን ይዞ በህይወት ምህዋር ላይ እየሰገረ ነው፡፡  
       አሁን ግን ለዝናቡ የህይወት መሰናክል የሆነበት UNHCR ነው፡፡ የስደተኛነት ማረጋገጫውን ለማግኘት 11 አመት ደጅ አስጠንቶታል፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊያኑ ላይ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ 20 አመት በማንዴት (በስደተኛነት ማረጋገጫ)ከኖረ በኋላ ማንዴቱን ነጥቀውት 5 አመት በቀጠሮ እየተመላለሰ ያለ ይማም የሚባል ሰውም አለ፡፡ በቀጠሮ ብቻ 12 አመት ያስቆጠረ አጋጥሞኛል፡፡ የእነዚህን ብሶተኞች ድምጽ በተከታታይ  ለማቅረብ ድምጽ ልሆናቸው ቃል እገባለሁ፡፡ ወደ ዝናቡ ታሪክ ስመለስ..ዝናቡን ዝናብ እንደመታው ውሻ ክስት ጥቁርቁር ብስቁልቁል ብሎ ነው ያገኘሁት፡፡
       ‹‹ምነው  ዝናቡ የታመምክ መሰለኝ››
       ‹‹መታመምስ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ ግን ከዛ ወደባሰው እያመራሁ ነው፡፡ ስራ አባረሩኝ፡፡ የሚላስ የሚቀመስ የለኝም ደግሞ ታውቃለህ ብቻዬን አይደለሁም፡፡ እኔንስ ይራበኝ ይጥማኝ…ፊልሞን…›› መናገር አቃተው፡፡ እንባ ተናነቀው፡፡ የእኔ አይኖች የእሱን ተከትለው ቋሳቸውን ጋቱ፡፡ ደሀ እንባ እንጂ ሌላ ምን አለው? ምንስ ልርዳው? እኔ ልቤ ቢያዝንም ኪሴ ጠባብ ነው፡፡ የራሴን እጅ ብቻ ነው የሚስገባው፡፡
      ‹‹ስራ በምን ምክንያት አባረሩህ?››
      ‹‹ኢንተር ሶስ በUNHCR ስር ያለ በእነሱ የሚታዘዝ ቢሆንም ቢሮው የስደተኛነት ማረጋገጫውን ሳይሰጠኝ 11 አመት በቀጠሮ እንዳመላለሰኝ እያወቁ መታወቂያውን ማግኘት ካቻልክ ብለው አባረሩኝ፡፡ አስብ እነሱ ያላሰሩኝ…›› አሁንም ቅጭም ባለው ፊቱ ላይ የሀዘን ድባብ ተንሰራፋ፡፡ የስደተኛ መታወቂያውን ሳይሰጥ ያመላለሰው UNHCR ቢሮ ሆኖ ሳለ በስሩ ያለው ኢነተር ሶስ ለምን አባረረው? ግራ ያጋባል፡፡
   ‹‹..ይሄንን ሴሚስተር ከፍዬ የማስጨርስበት ስለሌለኝ ልጄም ትምህርት ሊያቋርጥ ነው፡፡..›› ምን እንደምለው ግራ ገባኝ፡፡ ‹‹አቤቱ ፈጣሪ አምላኬ ምነው ስደት አውጥተህ የወገኑን ችግር እየሰማ የሚያነባ አደረከኝ፡፡ በአንድ ወቅት እኔም እዚህ ሀገር እንደመጣሁ ልጆች አስጠግተውኝ ስራ አጥቼ የሰው እጅ ባየሁበት ወቅት የጻፍኩት ግጥም ትዝ አለኝ፡፡
                          ሰው ካደረከኝ
                ሰው ካደረከኝ ስጋ ለባሽ
                ሆዱን ወዳድ እህል ቆራሽ
                ሰው ካደረከኝ ደካማ
                ካልጠጣ የማይችል ሲጠማ
                ሰው ካደረከኝ ጥሮ ግሮ ኗሪ
                ለምን አስቀመጥከኝ አድርገህ ተጧሪ
                    መጋቢት 19 1998 ነበር የጻፍኳት፡፡ ዛሬ እግዚአብሄር ይመስገን ለእኔ ልክ ነው፡፡ አሁንም ያስታወስኩት ‹‹ልጄን የማበላው…የማስተምርበት…ለእለቱ ሆዱ ለነገ ማንነቱ ትምህርቱ…›› ብሎ አባቱ ሁለቱንም በማጣት ጭንቀት ውስጥ መግባቱን በማየት ነው፡፡ ሰነዓ ውስጥ በርካታ ማስተማር አቅቷቸው ልጅነታቸው በጨለማ ተውጦ በየቤቱ ያሉ ሞልተዋል፡፡
   አሁን ግን ዝናቡን ምን ላድርገው? ከኔ ተርፎ የሚንጠባጠብ አይኖርም፡፡ ልጁ ይራብ ብዬ ዝም ማለትም አልችልም፡፡ ትምህርቱን ግን አቅም የለኝም፡፡ ወገን ለወገኑ ነው እና እባካችሁ ቢያስ ይሄን ሴሚስተር የሚጨርስበትን መላ በሉ፡፡ ለወገን በዚህ ሰዓት ከመድረስ በላይ ምን ህሊናን የሚያረካ ይኖራል፡፡  እባካችሁ ለትምህርቱ ብቻ እርዱት ልታገኙት ለፈለጋችሁ በስልክ ቁጥር…..
     
       00967734560471 ዝናቡ ብላችሁ አናግሩት