Monday, April 16, 2012


                         ግሩም ተ/ሀይማኖት
       እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬት አፍወርቅ ተክሌ..
                                         
      እረፍተ ዜናቸውን /የሞታቸውን ዜና/ ያረዳኝ ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ዘገባ ነው፡፡ አዘንኩ፡፡ በእውነት አዘንኩ ብቻ ሳይሆን አንጋፋዎቹ መከታተላቸው አስደነገጠኝ፡፡ በሰዓቱም ስለተደናገጥኩ የለጣፊውን ማንነት ልብ ስላላልኩ እገሌ ብዬ ማመስገን አልቻልኩም፡፡ ከዛ በኋላ በርካቶች ለጥፈውታል፡፡ ሁሉንም ላመሰግን ወደድኩ፡፡ ከምንም በላይ ያስደነገጠኝ የጥበብ ሰዎቻችን እና የኩዳዴ /የፋሲካ/ ጾም ቁርኝት ነው፡፡ ከሁሉም የከፋው የዘንድሮው ሁለት ወር ጸም ሶስት አንጋፋዎችን አሳጣን፡፡ ጾሙ ሲገባ በአጻጻፍ ስልቱ ከልጅነቴ ጅምሮ የምወደው ጋሽ ስብሀትን አጣን፡፡ እኩለ ፆሙ አካባቢ በትርጉም ስራቸው በርካታ የስለላ መጻህፍትን ያስነበቡን፣ በርካታ መጽሀፍትን የተረጎሙት ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ተርጓሚ ማሞ ውድነህን አጣን፡፡ የሁሉም ሲታሰብ ቤተሰብ የማጣት ያህል ነው የተሰማኝ፡፡
  
    ጋሽ ማሞ ውድነህን ከሁሉ በላይ የማውቃቸው ለሰርካለም አሳታሚ ድርጅት /ቢሮአችን/ በነበራቸው ቅርበት ነው፡፡ ሞታቸውን ስሰማ ቶሎ የታወሰኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሰርክዓለም ፋሲል ናቸው፡፡ በተለይ እስክንድር ነጋ ይወዳቸው ነበር፡፡ ያከብራቸዋልም፡፡ በእስር ሳለ ስለሆነ ስላልቀበራቸው ምን ተሰምቶት ይሆን? የተሰማውን አንድ ቀን ጽፎ እንደሚያስነብበን አምናለሁ፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በገዢው ፓርቲ ‹‹አሸባሪ..›› ተብሎ በእስር ላይ ነው፡፡ ቢሆንም ፔን ኢንተርናሽናል በምርጥ ጋዜጠኝነት ተሸላሚ አድርጎ ስለመረጠው ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ሲያንሰው ነው እንጂ የሚበዛበት አይደለም፡፡ አንድ ቀን እውነት ሲያሸንፍ፣ ስልጣን ኤስፓየርድ ሲያደርግ፣ ነገር ሲገለበጥ እስክንድርም ነፃ ይሆንና....እስከዛው ግን በቀጣይነት ስለ እስክንድር ነጋ በማሰፍረው ፅሁፍ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ወደ ጅምሬ ልመለስበት፡፡

   የእረፍተ ዜናቸው ያስደነገጠኝ እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬት አፍወርቅ ተክሌ አንድ ጊዜ ‹‹ለውዱ ግሩም ተ/ሀይማኖት ከመልካም ምኞት ጋርና ከወንድምነት ጋር..›› ብለው በእጅ ፅሁፋቸው ፅፈው ፊርማቸውን ያኖሩበትን ማስታወሻ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ይህ ማስታወሻ ከላይ ያስቀመጥኩት ፎቶዎች ያሉበት ነው፡፡  የእሳቸው፣ የቤታቸው እና አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ያኖሩት ድንቅ ስዕላቸው ያለበት ሆኖ ከውስጡ በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የተፃፈ የህይወት ታሪካቸው ያለበት ነው፡፡ ሰዓሊ ሆኜ አይደለም የተገናኘነው፡፡ ስለ ስዕል ምንም አይነት ግንዛቤ የለኝም፡፡ ቢያንስ ጥሩ ተመልካች አይደለሁም፡፡ በልጅነቴ በስዕል ፕሮፌሽናል ደደብ ከመሆኔ የተነሳ ጂኦግራፊና ባዮሎጂ በካርቦን ነበር የምገለብጠው፡፡ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግርማ የሚባል ካርቱኒስት የሚስላቸውን ካርቱኖች እያየሁ ትንሽ ሞካክሬያለሁ፡፡ ታዲያ በደፍተር ሉክ ላይ ከመሳል አልፌም አላውቅም፡፡

   ኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ጊዜ ለምኒልክ መጽሄት፣ ሌላ ጊዜ ለምኒልክ ጋዜጣ ቃለ-ምልልስ ሳደርጋቸው ነው የተቀራረብነው፡፡ የጋዜጣውን ቃለ-ምልልስ በኋላ አቀርበዋለሁ፡፡

   በአንድ ወቅት ቀንዲል ቤተ-ተውኔት ውስጥ በጥላሁን የህይወት ታሪክ ዙሪያ አንድ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ሳንዲያጎ ፕሮዳክሽን ወይም ሙዚቃ ቤት ነው ያዘጋጀው፡፡ ድንገት ጊዜው ከመርዘሙ ጋር ሳንዲያጎ ሙዚቃ ቤት ይባል ፕሮዳክሽን ከተሳሳትኩ ይቅርታ፡፡ በወዳጄ ጋዜጠኛ ወርቅአፈራሁ አሰፋ ጠሪነት ቦታው ላይ ተገኘሁ፡፡ ጋሽ አያልነህ ሙላትን ላናግረው ቢሮ ስገባ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን አገኘኋቸው፡፡ አጋጣሚው የገረመኝ ስለእሳቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መረጃ ነበረው እና ቃለ-ምልልስ ባደርጋቸው ጥሩ እንደሚሆን ጠቁሞኝ ነበር፡፡ በቀጥታ ራሴን አስተዋውቄ የአለም ሎሬትነት ማዕረግ ሊሰጣቸው እንደሆነ መረጃ እንዳለኝ ነግሬ ቃለ-ምልልስ እንድናደርግ ጠየኳቸው፡፡ ቀናት አመቻችተው ሲመቻቸው እንደሚደውሉልኝ ተነጋግረን ስልክ ቁጥሬን ሰጠኋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ካሉኝ የማስታውሰው ‹‹ሞባይል ስልክ የሚባል ነገር መያዝ አልወድም፡፡ ስራ ያስፈታል፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ እየሰራሁ ቢደወል እንዴት የምናደድ ይመስልሀል?›› አባባላቸው እውነት መሆኑን ጋሽ አያልነህ ሙላት ጠንቅቆ አስረዳኝ፡፡

     እደውልልሀለሁ ብለው ስልክ ቁጥሬን የመውሰዳቸውን ነገር ግን ማንም ቢሯችን ሰዎች አልተዋጠላቸውም፡፡ ‹‹..እሳቸው እኮ የፈለገ መገናኛ ብዙሀን በደብዳቤ ጠይቋቸው እንኳን እሺ አይሉም...›› የሚለው ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ደካማ ጎኔ ጠንከር ብሎ ወይም ተጠራጣሪው ጎኔ አመዝኖ ሌላ አርቲስት ቃለ-ምልልስ አደረኩኝ፡፡ ከ13 ቀን በኋላ ግን በቢሮው ስልክ ሲደውሉ እኔ ስላልነበርኩ እስክንድር ይመስለኛል ወይም ሰርክዓለም መልዕክት ተቀበሏቸው፡፡ በማግስቱ አራት ሰዓት ቀጠሮ እንደተያዘልኝ ነው መልዕክቱ፡፡ በሰዓቴ ጦር ኃይሎች አካባቢ ያለው ቪላ አልፋ ቤታቸው ደረስኩ፡፡ ሰዓት ላይ የማያዛንፍ አቋም እንዳላቸው ሰምቼ ነበር እና በሰዓቱ ተጠንቅቄ ደረስኩ፡፡ ይህን ቤታቸውን ደርግ ወስዶባቸው እንደነበር ሲመለስላቸው ለማደስ ብቻ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳወጡበት ራሳቸው ነገሩኝ፡፡ በውበቱ ተማርኬ መፍዘዜን አውቀው ይሆን የነገሩኝ? እያንዳንዱ ነገር ጥበብ ወለድ ረቂቅ ስራ ነው፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ስገባ ግን ረጅም አመት ወደ ኋላ የሚመልስ እና የልጅነት ጊዜዬን የሚያስታውስ ምስል አየሁ፡፡ የአባታቸው ነው፡፡

    እዚህ ጋር አምሮ ተኩሎ ይሳል እንጂ በህጻንነቴ የማውቃቸው ሰው ምስል ጋር ተመሳሰለብኝ፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ከፍ ብሎ ያለ ካብ ጊቢ ውስጥ የነበሩ ‹‹የአፈወርቅ አባት›› ስንላቸው የሚያባርሩን ሰው ለመሆናቸው አልተጠራጠርኩም፡፡ ግን የወጣትነትና የሽምግልና፣ የመክሳትና የመወፈር ለውጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ የአባት ጡረተኞችን አይነት አለባበስ ከነ ኒሻናቸው እንደሚለብሱ እንኳን ያኔ አሁንም በአይነ ህሊናዬ ይታዩኛል፡፡ አርባ ደረጃ..ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ፣ ቅ/ማርያም፣ አራት ኪሎም በተወሰነ ቦታ ያደጋችሁ እኝህን ሰው ታውቋቸው ይሆናል፡፡

   ከሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ጋር ሻይ ጠጥተን ከስቱዲዮ ጀምረው ቤታቸውን እያዞሩ ሲያሳዩኝ በመሀል ብልጭ እያለ ደስታዬን ሰልቦኝ የሚሄደው ‹‹ለምንድን ነው የአፈወርቅ አባት..›› ሲባሉ ያባርሩን የነበረው? ይሄን የመሰለ የሚያኮራ ልጅ እያላቸው? ችግሩ ምንድን ነው? የሚል ሀሳብ ነበር፡፡ የአንድ ሰው ጊቢ፣ የአንድ ሰው ስቱዲዮ የምጎበኝ አልመሰለኝም፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም ነው የሆነብኝ፡፡ ይሄ እንደ ፕላዝማ ስክሪን የሰፋ ፊቴ ስሜቴን ያሳብቃል መሰለኝ፣ አለያም ጥሩ አንባቢ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይሄ የመጀመሪያዬ ቤት ስለሆነ ነው ቪላ አልፋ ያልኩት እንጂ መገናኛ እና አዋሳም ከዚህ የማይተናነሱ ቤቶች አሉኝ ሲሉ በግርምቴ ላይ ግርምት እንድጨምር አድርገው ነገሩኝ፡፡ የሽልማታቸው ብዛት ዛሬ ላይ ሆኜ ማስታወስ የሚከብድ ነው፡፡ የልብሶቹ ለብቻ ዋንጫዎቹ፣ ኒሻኖቹ.. ሁሉም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ እንደ ቢሮ የሚጠቀሙበት ቦታ ላይ በትልቅ ወረቀት ላይ ያገኙትን ሽልማቶች፣ መቼ እንደ ተሸለሙ፣ የሸላሚው ድርጅት ወይም ሀገር ዝርዝር ተመዝግቦ ተቀምጧል፡፡ አስታውሳለሁ ሰባ ሁለት አካባቢ ነበር፡፡

     ስላየሁትም፣ ስለሰማሁትም፣ ስናወራ ስለታዘብኩትም ለመጠየቅ መቅረፀ ድምፄን አስተካክዬ ተቀመጥን፡፡ በመጀመሪያ የጠየኳቸው ጥያቄ ከስማቸው በፊት ስለሚገቡት የማዕረግ መጠሪያዎች እና ሙሉው ካልተጠራ ስለሚሉበት ምክንያት ነበር፡፡ ይህን ቃለ-ምልልስ ሐምሌ 6 እና 13 1993 ዓ.ም ለንባብ በበቃው ‹‹ምኒልክ›› ጋዜጣ ላይ ነበር ያሰፈርኩት፡፡ በአጋጣሚ ካስመጣኋቸው መረጃዎቼ ጋር መጥቶ እጄ ላይ ስላለ  የሰጡኝን ምላሽ ላስነብባችሁ፡፡

     ‹‹አንዴ ለአንባቢህ ሙሉ ስሜን ከነማዕረጌ መስጠት አለብህ ከዛ በኋላ ግን እየደጋገምክ ያንን ማለቱ የሞኝ ለቅሶ ነው፡፡›› አሉኝ በዚህ ብስማማም አንዴ ሲናገሩ ‹‹ስትጠሩ አንጠልጥላችሁ በግማሽ አትጥሩኝ ከጠራችሁ ሙሉውን ጥሩ ካልሆነ ግን በስሜ ብቻ ጥሩኝ..›› ሲሉ ሰምቻለሁ ስለዚህ አሁን ካሉኝ ጋር አይቃረንም? ወይስ ይህ ነገር ተደጋግሞ አሰልችቶት ነው ይህን ያሉት? አልኳቸው፡፡ አይኔ ግን ትርጉማቸው ያልገባኝ አብስትራክት ስዕሎች ላይ ይንከራተታል፡፡ ‹‹ምን መሰለህ..›› ሲሉ ጀመሩ፡፡

    ‹‹ምን መሰለህ በፅሁፍ ለሚደረግ ነገር ሲጀመር ሙሉ አርዕስቱ መጠራት አለበት፡፡ ማለት እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬየት አፈወርቅ ተክሌ የሚለው መስፈር አለበት፡፡ እነዚህ አርዕስቶች...አንተ አጋጣሚ እዚሁ ክፍል ውስጥ ነው ያለኸው አንኳር..አንኳር የሆኑ ዲፕሎማዎችና የምስክር ወረቀቶች አሉ፡፡ ይህንን አይተህ ሁሉንም ነገር መረዳት ትችላለህ፡፡እነዚህ ነገሮች ሲሰጡ ሴኔት ተቀምጦ፣ ኮሚቴ ተቀምጦ ወይም የአካዳሚ አባላት ተቀምጠው ይህ ሰው እስካሁን ድረስ በሰራው ስራ ይህ ማዕረግ ይገባዋል ብለው ነው የሚሰጠው፡፡ በስራህ በድካምህ የመጡ ናቸው፡፡›› ሲሉ ውስጤ ተፀንሶ የሚላወስ ብልጭ ያለ ጥያቄ ነበርና የእነዚህ ነገሮች /ሽማቶች/ ዋጋቸው ወይም ጥቅማቸው ምን ያህል ነው? አልኩኝ፡፡

     ሲመልሱልኝ ‹‹..እነዚህ ነገሮች ከዩንቨርስቲ ዲግሪ በላይ ናቸው፡፡ ሲሰጡህ እኛ ለዚህ በቂ ነህ ብለን እናምናለን ትቀበላለህ ወይ ብለው ይጠይቁሀል፡፡ እቀበላለሁ ካልክ ያንን ስም ማክበር ማስከበር ግዴታህ ነው፡፡ እኔ ይሄ ይጠራ፣ ይሄ ይጠቀስ የምለው ለዛ ነው፡፡ ካልሆነ አፈወርቅ ተክሌ በቂዬ ነው፡፡ ለማናም አርቲስት ለማንም የፈጠራ ሰው ስሙ በቂው ነው፡፡ እነፒካሶ እርዕስት ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ ግን በጽሁፍ ከሆነ ያ-ያገኙትን እርዕስት መፃፍ አለበት፡፡ በመናገር ከሆነ ግን ፒካሶ ነው የምትለው፣ ዳቪንቺ ነው የምትለው፣ እከሌ ነው የምትለው፡፡ እኔንም አፈወርቅ ልትለኝ ትችላለህ፡፡

     ግን በሀገራችን የሆነው ምንድን ነው፡፡ መንግስት የሰጠህ አርዕስት ካልሆነ በስተቀር የተከበሩ፣ ክቡር መባል አትችልም የሚል መንፈስ ጭቅላታቸው ውስጥ ገብቷል፡፡ እንጂ ለእኔ አፈወርቅ የሚያሰኘኝ ስራዬ ነው፡፡ እሱ ይበቃል፡፡ ግን ለምንድን ነው ይሄን የሚቃረኑት?..›› አሉኝ፡፡ በዚህ አይደለም ያበቃነው፡፡ ጠቅለል አድርጌ እመለስበታለሁ፡፡
                        ቸር እንሰንብት፡፡