Wednesday, May 8, 2013

ግንቦት አንድ፣ አድባርና ትዝታው ዛሬ ላይ ሆኜ…

ግንቦት አንድ፣ አድባርና ትዝታው ዛሬ ላይ ሆኜ

                በግሩም ተ/ሀይማኖት
   ስሞኑን ሁሉም ስለ ግንቦት ልደታ ብዙ ብለው እኔም ትዝታዬን አንጎዳጉጄ ዝምታዬ ውስጥ በዝምታ አልጎምጉሜ ዝም ብዬ ነበር፡፡ ታዲያ በስደት ንፍሮ ቀቅሉ ጎረቤት ሰብስቡ ልል ነው? ለመሆኑ ኮንደሚኒየም ላይ አድባር እንዴት ይሆን? ምነው ባየሁ ኖሮ…ለነገሮ ባየሁ ብሎ ነገር የለም፡፡ አላየሁማ ደግሞም ለማየት መመኘትም ብዙ ደግ አይደለም፡፡ የስንቱን ናፍቆት እና ምኞት ተሸክሜ ልኖር ነው፡፡ ስለዚህ ነው ዝም ብዬ በውስጤ ያልጎመጎምኩት፡፡ ግና ዝም ብልም፣ ልርሳህ ብለውም እንድረሳው ያላደረገ አንድ ትዝታ ቀስቃሽ ፎቶ የለጠፈች ዝምታ አቋራጭ ልጅ እንድጫጭር አድርጋኛለች፡፡ ሸዋ ወልዴ ከላይ ያለውን ፎቶ ለጣፊዋ ነች፡፡ በስደት ቤይሩት ቢሆንም ያለችው በዓሉን በስደት ያሉበት ቦታ እንዴት እንዳከበሩት በምናቤ እንድቃኝ አድርጋኛለች፡፡ እንዲያውም አብሬያቸው ቁጭ ብዬ ቡናውንም እነሱ በአካል እኔ በምናብ ጠጥተናል፡፡ ሸዋ ካለች በኦርቶዶክስ ዙሪያ ያሉ ነገሮች መፈለግ ይቀላል፡፡ ስደት ነኝ ብላ የያዛት ነገር የለም፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስርዓታዊ መንገድ የተዘጋጀ መንፈሳዊ ፊልም በስደት ሀገር ሆና ሰርታለች፡፡ አሁን ደግሞ እኔ ላይ በግንቦት ልደታ ትዝታ ዙሪያ ፊልም ሰራች፡፡ እግዚአብሄር አብዝቶ ይባርካት፡፡ እናንተም ላነበባችሁት ይህ ፅሁፍ መነሻ ነች እና መርቋት፡፡ እናንተ እሷን እስክትመርቋት እኔ ወደ ወጌ ላምራእኔን ግን ስለማትምርቁኝ እራሴን መርቄያለሁ፡፡ እግዚአብሄር ይስጠኝ!!!

       በዘልማድ ‹‹አድባር›› ይባላል ግንቦት አንድ ቀን የሚከበረው የግንቦት ልደታ፡፡ እምቤታችን ማሪያም የተወለደችበት ቀን ነው፡፡ ታዲያ ይሄ አድባር የሚለው ነገር መቼ እንደ ተጀመረ እና ለምን እንደሚባል ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ እኔ ደግሞ እንደምታውቁት ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቀውን ቀርቶ ከክፍል ክፍል የሚዞርበትን ሚጢጢ ጥናት አላጠናም፡፡ ስነፍ ነኝ:: ዛዲያ በእዛው ጎበዝ እንድትሆን አትሳልም ነበር እንዳትሉኝ አደራ፡፡ አታስዋሹኝ እና ዶሮ ይመስል ስለት ነገር እጠላለሁ፡፡ ስለት ለው ነገር አልወድም..

    ከፍተኛ ጥናቱን ትቼ ባለችኝ ትንሽ መረጃ መሰረት የማስታውሰውን ላውጋችሁ፡፡ ማጣቀሻ ዋቢ መፀሐፍት ቢኖሩ በደንብ ባወጋኋችሁ ነበር፡፡ የግንቦት ልደታን ከቤት ወጥታችሁ ጊቢ ውስጥ ቡና አፍልታችሁየሚል የኦርቶዶክስ ስርዓት /ቀኖና የለም/ ለዚህ ነገር መነሻው የኦሮሞ ባህል ስነ-ስርዓት ነው፡፡ ይሄ የያዘን ዘር ቆጠራ አባዜ አይለቀንም አይደል ቶሎ ብላችሁ ዘሬን ልታጠያይቁ እንዳትሞክሩ፡፡ከሁሉም ያለብኝ ሁሉም የሚመለከተኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በቃ! ከፍ ሲል አፍሪካዊ ዝቅ ሲል ኢትዮጵያ ነኝ ከዛ በታች በብሄር በጎሳ እንዳትመነዝሩኝ አደራ፡፡ አልመነዘርም፡፡

    በኦሮሞ ማህበረሰብ ባህል እና እምነት ውስጥ ፈጣሪን የማመስገኛ እና የመለመኛ ሁለት ስርዓት አለ፡፡ እሬቻ ይባላል፡፡ እስካሁን ያለውን አንብባችሁ እንዴት ያንን ከዚህ ያገናኛል የሚል ሀሳብ ከተፀነሰባችሁ በዚህ ሰዓት እንኳን እውነታን ለመረዳት እንዘጋጅ፡፡ እሬቻ ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል ነው፡፡ ከግንቦት ልደታ ጋር ግን ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ የተወራረሰ ባህል ወይንም መንገድ ግን አለው፡፡ እሬቻ በአመት ሁለቴ ይከበራል፡፡ አንዱ መስከረም ላይ መስቀል በዓል በዋለ ቀጥሎ ባለው እሁድ የሚከበረው ነው፡፡ ወንዝ ዳር፣ ሀይቅየመሳሰሉት ውሀ ያለበት ቦታ ለምለም ቄጤማ ተይዞ የሚደረገው ሲሆን አላማውም ዝናቡን አዝንበህ ይህን ለም የሰጠኸን አምላክ ተመስገን ለማለት ነው፡፡

   ሁለተኛው ደግሞ ግንቦት ወር ላይ የሚደረገው የተራራ ሬቻ የሚባለው ነው፡፡ ይህ አከባበሩ ልመና ነው፡፡ መጪው ወቅት ክረምት ነውና ዝናቡን ስጠን ለከብቶቻችንም ግጦሽ የሚሆንውንእኛንም ከብቶቻችንንም ጠብቀን የሚል ስለሆነ ‹‹ቦረንትቻ›› ይባላል፡፡ የቦረና ልጆች ልመና በመባልም ይታወቃል፡፡ የተራራ እሬቻ ስለሆነ ትልቅ ዋርካ ስር ስለሚደረግ ሌላው ሰው ዛፉን የሚለመን ይመስለዋል፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ ዙሪያ ያናገርኳቸው በደብረዘይት ዙሪያ የዋቄ ፋና ማህበር አሰባሳቢ ‹‹ፈጣሪን አንተ እንደዚህ ዋርካ የገዘፍክ ነህ፣ ከለላችን ነህ፣ መሰባሰቢያችን ነህ ለማለት ነው…›› ዋርካው ስር የሚደረገቀው ብለውኛል፡፡ ተራራ ላይ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን በሰፈር፣ በቤትም እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡ ግንቦት መሆኑም አንድ ላይ ስለሚያከብሩት እየተለመደ መጣ፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ከእኛ ግንቦት ልደታ ጋር ተገናኝቶ ጊቢ፣ ሰፈር ውስጥ ተሰባስቦ ማክበር ጋር ተዛመደ፡፡ ግንቦት ልደታ ሊከበር የሚገባው ግንቦት አንድ ቀን ብቻ መሆን ሲገባው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እና አሁንም አንዳንድ ቦታ ከዚህ ስርዓት ወጥቶ ከግንቦት አንድ እስከ ሰላሳ ባለው ጊዜ ይከበራል፡፡ ከዋቄፈታ የተራራ እሬቻ ጋር ያለው ዝምድና የፈጠረው እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ በዓሉን ከግንቦት አንድ ውጭ ማክበር የእምነቱ መሰረት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡

     እኛ ሰፈር ስለነበረው አደባር አከባበር ላወጋ ቢሆንም አነሳሴ እግረ መንገዴን ነገርን ነገር ጠልፎት ወደ ሌላ ገባሁ፡፡ ተመልሻለሁ ይታወቅልኝ፡፡ ታዲያ ትዝታው ዛሬም በስደት ሳለሁ ጊቢያችን ውስጥ የነበረ ስነ-ስርዓት ትውስ አለኝ፡፡ ጊቢው ውስጥ ያለው ቤት በቀበሌ የተወረሰባቸው አቶ ሞገሴ በእኛ አጠራር አባባ ሞገስ ናቸው ሰብሳቢ፡፡ ገና ሳምንት ሲቀራቸው አዋጡ ይላሉ ጋቢያቸውን እንደለበሱ በረንዳ የሌለው ቤታቸው በር ላይ ባለ ሶስት እግሩ ዱካ ወንበር ላይ ተኮፍሰው፡፡ ይሄ እዚህ ጋር ይሁን ጊቢው ይፀዳአንቺ የቀረብሽን አታዋጪምታዲያ ጊቢያችንን ብታዪት ትንሽ ቤት ያቆረ እንዳይመስላችሁ፡፡ 18 በላይ ነው፡፡ ሙሰሊሞችም አሉ፡፡ ዘሜ፣ አቶ ሙሳ፣ ጣይቱ አሊ..ከማስታውሳቸው ውስጥ ናቸው፡፡ እነሱም አብረው ያዋጣሉ፡፡ አብረውን አድባር ብለን የምንሰባሰብበት ቦታ ተቀምጠው ይቋደሳሉ፡፡ ያኔ ፍቅር ጋቢ ነበር፣ ቡልኮ ነበርእንዳሁኑ አንገት ልብስ አክሎ ተሸማቆ ሰዉ በቋፍ አልሆነም ነበር፡፡ የጎሪጥ አይተያይም፡፡

    ንፍሮ ይቀቀላል፣ አነባበሮ ይነባበራል፣ ቡና እቃው ይዘጋጃል፣ በግ ይታረዳል፣ ጠላው ነጭ አረቄውኡኡአይ! አሁን አሁን አለኝ፡፡ ታዲያ እኔ የሚደርሰኝን ነገር ሁሉ ብዙውን በስጋ እለውጣለሁ፡፡ አንዴ ታዲያ በግ ታርዶ፣ ተገፎ፣ ተቆራርጦ..ብረት ምጣድ ላይ ይንቻቻልዋይ!..ዋይ!.. ድረሱልኝ፣ ጉረሱኝ በሚልበት ሰዓት ነው፡፡ ምራቄ ከጉሮሮዬ ጋር ታሻርኮ ድምፅ እያወጣ ያጋልጠኛል፡፡ ምራቁን ዋጠ አሰኙኝ፡፡ ደሞ ምራቁን ዋጠ የሚለውን ጎመጀ በሚለው ይተረጎምልኝ፡፡ ምራቁን ዋጠ በሰለ አስተዋይ ሆነ የሚለው ዛሬም አይነካኝዞር ሲሉ አንዷን ብድግ….እኔን ተከትሎ የታላቅ ወንድሜ ደኛ ነው ብድግ አደረገ፡፡ ጓጉቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ አፉ ከማለቱ ምን አለፋችሁ ንጋቱ የሚባለው የፈንጂ ፍንጣሪ አይኑን ነክቶት ጡረታ የወጣ ወታደር ‹‹ቁጭ አድርግ! ሳይቋደስ አንተ ባለጌ..›› አለና ያነሳውን ልጅ በ10 አለቂኛ ተቆጣው፡፡ ፈራና ሊመልስ ሲል አምጣ እኔ ልመልስ ብዬ በላሁት፡፡ ንጋቱ የሚሉት ወታደር በኩርኩም ቆጋኝ፡፡ የሚቆጋ ይቆጋውና!..ታላቅ ወንድሜ በሰዎች ዘንድ የተወደደ ዝምተኛ ነው፡፡ ግን የሚሰራውን ተንኮል እሱ ይሰራዋል የማይባል ነው፡፡ እኔ በመመታቴ ተናዷል፡፡ አስቀምጥ የተባለው ልጅ ጊቢው እዛ አይደለም፡፡ ከወንድሜ ጋር በጣም ስለሚቀራረቡ እሱን ብሎም ስለሆነ የመጣው ‹‹አስቀምጥ›› ብሎ ስለሰደበው በሁለቱም ነገር ተናዷል፡፡ የተሰጠንን የበግ እንትን/ ስታነቡት እንዳታፍሩ ነው እንጂ የበግ ቆለጥ ማለት አፍሬ አይደለም/ ይዞ ማዕድ ቤት ገባ እና ኩራዙ ላይ ያለውን ጋዝ ቀብቶ ተመለሰ፡፡ ወደ ብትረት ምጥዱ ስር ወረወረው፡፡ ያየው የለም ያዩትም ሊጠብስ መሰላቸው ቦግ ቦግ አለና ‹‹ዱዋ!!!!!›› ፍንዳታውን ሲያቀልጠው ሁሉም በድንጋጤ ጨው ሆኑ፡፡ ንጋቱ የሚባለው ደንግጦ ወደ ኋላው ሊፈነገል ምንም አልቀረውም፡፡ ሚሊዮን የሚባለው የቀበሌያችን ሊቀመንበር ባያረጋጋ የተፈጠረው ነገር ብዙ ይሄድ ነበር፡፡

     እኛማ አጋጣሚውን ጠብቀን ንፍሮ ዘግነን ኪሳችን ደበቅን፡፡ ወንድሜ ግን በዚህም አልተደሰተም ነበር እና ንጋቱ የሚባለውን ሌላ ጊዜ ተበቀለው፡፡ እንዳይበላ ተቆጥተው ያሰመለሱት ልጅ ግን የተከለከላትን ስጋ ዳግም ሰርቆ አገኛት እና አጣጣመ፡፡ ሰዓቱ ደረሰና ቡናው ተፈልቶ ጫወታው ደርቶ ምርቃት ተንጋግቶ የሚሰጠው ታደለን፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት ከእሬቻ ጋር ሌላ ያመሳሰለው ነገር በተን በተን የሚደረገው ነገር ነው፡፡ እኔ ደግሞ ይህን ልጅ እያለሁም እቃወማልሁ፡፡ ለነገሩ ሆዳም ስነበርኩ ለእህሉ አዝኜ እንጂ ትርጉሙ ገብቶኝ አይመስለኝም መቃወሜ፡፡ አቃቂን የምታውቁ መካና የሚባለው ቦታ እሬቻ ሲደረግ አይ ነበር፡፡ እዛ ተማሪ በነበርኩ ሰዓት የሚበትኑትን ለቅሜ እበላም ነበር፡፡ አድባር ላይ እንደዛው ነኝ፡፡ አይ ልጅነት ተደባድበን ሁሉ እናነሳው ነበር፡፡ አይ!..ሸዋ!...ብዙ አስባልሽኝ፡፡ አስታወስሽኝ፡፡