Thursday, April 19, 2012


ጥቁሯ ቦርሳዬ

 ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት

(ክፍል 2)



    ስሙኝማ ዝም ብላችሁ ንባቡን ብቻ ትሸከሽካላችሁ…አረ ሼም ቆንጠጥ ያድርጋችሁ.. እንተዋወቅ አይባልም እንዴ? ብቸኝነት ድንኳኑን ጥሎ እንደ ፋሺሽት ጣሊያን በቅኝ ግዛት ሊይዘኝ ሲታገል..እኔም በኢትዮጵያዊ ወኔ አልገዛም ባይነቴን ይዤ ስታገል ጎበዝ እኛም አለን በርታ ትላላችሁ ብዬ ስጠብቅ….ገብጋቦች!!..ማለቴ የሰላምታ ንፉጎች፡፡ በዛ ላይ አይዞህ ወንድማችን ትላላችሁ ስል….ኤጭ እቴ እዚህ ፌዝ ቡክ ላይ የፈሰሰ ውሃ ማቅናት አይቻልም ማን ለማን…



      ክፍል አንድ ላይ ስጨርስ ካሰፈርኩት ለማስታወስ ኳል እያረኩ ልመለስበት፡፡ ያኔ እንዲያው በደፈና ሞናሊዛዬ ነሽ እንዳለው በደፈናው ደፈንኩት፡፡ ‹‹..እስካሁን ማነህ አላላችሁኝ ማንነቴ አላስፈለጋችሁም፡፡ እኔም ኮራ ያልኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ ፍቅርን እንደሸማ የተላበስኩ፡፡ ጥቃትን የማልወድ፣ ድህነት ቢይዘኝም በባዶ ኪሴ ኩራት የጠፈነገኝ..ከእግዚአብሄር ቀጥሎ ለውጭ ዜጋ የሚሰግድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ (ይቺ ቃል የሚያጎበድድ በሚል ትታሰብልኝ ለዚህም ማስረገጫ ላጣቅስ…

  

   ማስረገጫ አንድ፡- ከወገናችን ይልቅ የውጭ ዜጋ በፍጥነት፣ በትህትና የምናስተናግድ፡፡



    ማስረገጫ ሁለት፡- የራሳችን ምሁሮች ተመራምረው ከሚነግሩን ግኝት ይልቅ ለውጭዎቹ ተራ ወሬ ጆሮ ምንሰጥ፣ ያሉትን የምናመልክ ሌላው ቀርቶ ጥይት መድኃኒት ነው ቢሉን የምንቀበል ቂቂቂቂ..ለወገናችን ክብር ያለን ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ያሳያል አይደል?

  

    ማስረገጫ ሶስት፡- ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዝረጋለች የሚለውን ቅዱስ ቃል ገልብጠን ለስንዴ እርዳታ እና ለአበድሩኝ ወደ ነጮቹ የዘረጋን…)



    ብቻላችሁ እንዳልኩት ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ማነህ ብላችሁ አልጠየቃችሁኝ እኔም እገሌ ነኝ አላልኩ፡፡ ኩራት እራት ማለት እንዲህ አይደል? ግን ለምን አትሞክሩትም? ኩራት እራት በሉና ጦማችሁን ሞክሩት እስኪ…ጨጓራችሁ እኩለ ሌሊት ላይ እንደ እንጨት ሰራተኛ መፈቅፈቂያውን ይዞ ሲፈቀፍቃችሁ..ሁሉም ዜሮ ዜሮ ብሎ ራሱ ዜሮ እንደሆነው ዘፋኝ ዜሮ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ አውቃችኋል አይደል? ይህ ታሪክ የጸሀፊው አይደለም፡፡ ፀሀፊው የፈጠረኝ የእኔ ነው፡፡ ምናብ ወለድ ፍጡር ነኝ፡፡ የጸሀፊው ፍጡር ታሪክ ነው፡፡



     አሁን አንተ ማነህ ካላችሁ ለስሜ አልጨነቅም፡፡ ከበደም በሉኝ አበበ፣ ጀማልም በሉኝ እንድሪስ…መጠሪያው አያጨቃጭቀንም፡፡ ሰው ሆኖ መገኘት ነው ዋናው፡፡ ለእኔ ስሜ ምግባሬ ነው፡፡ አልዳሰስ አልከሰስ…ሳልፈጠር በፍጡር የተፈጠርኩ፡፡ ያለነበርኩ በእሱ ዘንድ የኖርኩ፡፡ ለእናንተ እንግዳ ነኝ፡፡ ለፀሀፊው እስኪፈጥረኝ አርግዞ  እስኪወልደኝ ምን ያህል እንዳማጠኝ እሱኑ ጠይቁት፡፡ ያለ ግንኙነት ተፀንሼ በወንድ ምጥ የተወለድኩ ነኝ፡፡ ደግመዋለሁ ለስሜ አልጨነቅም ማንነቴን ባልነግራችሁም ምግባሬ ይገልጸዋል እውነቱን ይዞ መሄድ ነው ፍላጎቴ፡፡ ብዙ መታዘብ አዘውትራለሁ.. ታዲያ አፈር ስሆን ጋሽ ኦብዘርበር እንዳትሉኝ፡፡ አስቡት እስኪ በእንግሊዘኛ ሳቅ ከየት አምጥቼ እስቃለሁ?…በአማርኛ ከሆነ በፈለጋቸሁት ጥሩኝ ግን ማን ብባል ነው ደስ የሚላችሁ? ስም ነገሩኝ እስኪ…  በዚህ ዘመን ለበዛ ትርጉም አልባ ስም ምን ችግር አለ አንዱን ለጥፉልኝ፡፡ ታዲያ አደራ ሊሊ ኪኪ ባቢ ቦቢ..እንዳትሉኝ፡፡ እነዚህ ስሞች ይደብሩኛል፡፡ ደስ የሚል ስም ብታወጡልኝ ችግር የለም አትከፍሉበት፤ አይፈልጣችሁ አይቆርጣችሁ ደስ ያላችሁን አንሱ እና…እህ!..ትርጉም ያለው ቢሆን ግን ደስ ይለኛል፡፡

    

   እንድታስቡ  የምፈልገው መኖሪያ አድራሻዬ ጥቁሯ ቦርሳ ውስጥ ወረቀቶች መሀል ተኝቼ ነው የምገኘው፡፡ ስትፈልጉ እዛ ኑ ታገኙኛላችሁ….ወይኔ ጉዴ!.... የት ላይ ነበር ያቆመኩት? እንኳን የሴት የወንድ ጓደኛ መምረጥ፣ ማግኘት እንደሚከብድ ነግሬያችሁ የለ? ወንድ ጓደኛ ለመያዝ ሲታሰብ እንደ ውሻ እጅ እጅ፣እንደ ሌባ ኪስ ኪስ የሚያይ መሆኑ ያሳፍራል፡፡ ትርፍራፊ የማበላው ውሻ ሳይሆን የእኔ የምለው ጓደኛ ነበር ፍላጎቴ እና ተውኩት፡፡ ‹‹ብቸኝነቴን ነው እኔ ማስታውሰው…›› የሚለውን ደጋግሜ ባዜምም አዲስ ስልት እና ስትራቴጂ ቀይሼ ብቸኝነቱን ልዋጋ ጦር መምዘዝ አላስፈለገኝም፡፡ የህይወት ጦሯም፣ ሞተሯም ሴቶች ናቸው እና የግራ ጎኔን ልመነትፍ፣ ለስላሳ አጣጪዬን /ያው ከውሀ ለስላሳ ይቀንሳል ብያችኋለሁ አስታውሱ../ የሄዋንን የልጅ ልጅ እጣ ፋንታዬም ትሁን እጣ ጦሴ ለማግኘት ፍለጋ በድጋሚ ጀመርኩ፡፡ የበዚያ ሰሞኑ ሀሙስ ሰርግ ነበረ እና ትከሻዬን ሰብቄ ልጨፍርም በአጋጣሚው ጥሬ ልጭርም ሄድኩላችሁ፡፡ ያው መቼም ጠርተውናል ያበሉናል ብዬ ነው፡፡



   ከርዕስ ውጭ ትንሽ እናውራ…ሰነዓ ያለ ሀበሻ ሞኝ ነው ሰርግ ይደግሳል፡፡ ቤተሰቡ የችግር አረንቋ እንደካባ ከላዩ ተመርጎበት፤ ማጣት እንደኩፍኝ ሳይሆን እንደፈንጣጣ አዥጎርጉሮት፣ ርሀብ ጨጓራው ላይ ሲጨፍርበት እሱ እዚሀ አፈሰማይ አብልቶ ያስጨፍራል፡፡ ይሄ የብዙዎች ገጠመኝ እና እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ አንዱ ወዳጄ /መቼስ ጠላቴ አይባል ወገኔ ነው/ ኢትዮጵያ የማውቀው ምስኪን ቤተሰብ ያለው እዚህ የመን ‹‹…የእገሌ ሰርግን የሚያክል የለም፡፡ ስድስት ማርቼዲስ ተከራይቶ..ከነመልሱ አዳራሽ ተከራይቶ..የነበረው ግብዣ..ህዝቡን ያበላው….›› እየተባለ የሚወራለት ሰሞን ነው የመን የገባሁት፡፡ ልጁ የጓደኛዬ ወንድም ነው፡፡  በዛው ወቅት ግን ከደ/ዘይት ከተማ ወጣ ብላ የምትገኝ እናታቸው በችግር መሟቀቋን ስለማውቅ ለእሱ ጥላቻ እንጂ አድናቆት አልቸርኩትም፡፡ ለጉራ ሲባል በችግር የተያዘን ቤተሰብ መርሳት የማንነት ማጣት ነው፡፡  የመን በልቶ ማደር በቸገረበት ሁኔታ እየኖሩ ሰርግ ምን ደስ ሊል? እስከመቼ የቦይ ውሀ ሆነን እንጓዛለን? ሰው ስላደረገ ብቻ እናደርጋለን? ወደ ርዕሳችን እንመለስ



      ሰዎች ልብ በሉ ከርዕስ ውጭ.. የተፃፈው እኔን አይመለከትም የጸሀፊው ሀሳብ ነው፡፡ እኔ አቅሜ ውስን፣ የምናገራት ምጥን ነች፡፡ ሰርጉ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ አንዷ አይኔን ብቻ ሳይሆን እግሬን ጭምር ሳበችው እና እብስ….እየጨፈረች ነው፡፡ ሙዚቃው ሐገርኛ ይሁን እንጂ ውዝዋዜው የውጭኛ ነበር፡፡ ከመሞከሬ በፊት የእሷን እንቅስቃሴ ማጥናት ግድ አለኝ እና ማየት ጀመርኩ፡፡ እናንተዬ የአንዳንዱ ዳንስ ስታዩት የሚገርም ነው፡፡ በቃ!.. ቡኮ የሚለውስ የሚመስል አለ፡፡ ሸማ እየሰራ የሚመስል እንቅስቃሴ የሚያሳይ አለ፡፡ ኧረ!..ልብ ካላችሁት ሾፌርም፣ ቀያሽ መሀንዲስም፣ አትክልተኛም የሚመስል አለ፡፡ እናላችሁ የእኔዋ በአይኔ የመረጥኳት ተጋጣሚዋን የምታጠቃ ቦክሰኛ ትመስላለች፡፡ ወዳጄ ትንሽ ችግር ያለ ቀን ጥርሴን በኪሴ የምታሲዘኝ ልምድ ያላት ቦክሰኛ መስላ ታየችኝ ‹‹ አልመጣም ቀረሁኝ ሸጌ…›› ብዬ ቀኝ ኋላ ዙር ነዋ!.. የሚገርመው ስዞር እንዳጫፍራት አንዷ ጋበዘችኝ፡፡ ቅጥነቷ እና ርዝመቷ ተደማምረው ሲያሳጧት ውሀ የነካው ፓስታ አስመስለዋታል፡፡ ትምዘገዘገዋለች፣ ትርገፈገፈዋለች.. አቤት!!..ጭፈራ ይሄ ነገረኛ ቴሌቪዥን ከሚያመጣቸው ተወዛዋዦች ትበልጣልች ብል ‹..ወይ ፎንቃ በአንዴው ቲፎዞ ሆንካት…› እባላልሁ ብዬ ስለፈራሁ ነው ያላልኩት፡፡

 

      ህዝቡ በደስታ ሰክሯል፡፡ ወጭው የሙሽሮች ጭፈራው የእኛ ሆኖ ብናደምቅላቸው ምን አለበት? ውይ የኔ ነገር ለካ ትራንስፖርት አውጥቻለሁ፡፡ ምናለ በነካ እጃቸው ቢከፍሉልን ኖሮ..አያዞራቸው፣ አያሳብዳቸው፡፡ በመቶ ዶላር ሰርተው በ3 ሺህ ዶላር መደገስ እብደት ስለሆነ ቀድመው ነው ያበዱት፡፡ እዳውን ከፍለው እስኪጨርሱ ልጅ ተወልዶ በእከከኝ ልከክልህ ኑሮ ለትምህርት ይደርሳል፡፡ አንዳንዴ ዘፈኖችን ከማስማት ይልቅ ማዳመጥ ጥሩ ነው፡፡ ‹‹አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው..›› ብሎ ነበር ድምጻዊ ጥላሁን ነፍሱን ይማርና፡፡



   የምንጨፍርበት ዘፈን አለቀ እና የደረጄ ደገፋ‹‹አበራሁኝ ሻማ ሞቅ አለ ጎጆዬ በራሴ ተማመንኩ ኮራሁ በምርጫዬ..›› የሚለውን ከፈቱት፡፡ መቼም ነገር ማንሸዋረር ለምዶብናል አይደል አንሸዋረርኩ እና ኮራሁ በምርጫዬ የምትለውን..‹‹ኮራሁ በሻማዬ..›› አልኩላችኋ፡፡ ሻማዬ ናት ከጨለማ ያወጣችኝ፡፡ የመን መብራት እንደ መንግስት ሰማያት ተስፋ ነው፡፡ በቀን ሁለት ሰዓት ሊበራ አለያም ብቅ ላይልም ይችላል፡፡ ሁሌ የመብራት መስመሩን ተቃዋሚዎቹ መቱት ይባላል፡፡ አመት ከአራት ወር ‹‹ንፋስ ነው ዘመዴ..›› እንዳለው አረጋኸኝ እኛም ሻማ ነው ዘመዴ ብለናል፡፡ ከውጭ ሀገር እንግዳ ሲመጣ እና የምርጫው ሰሞን ግን ለሳምንት ለሳምንትም  ቢሆን አብርተውልናል እና እናመሰግናለን፡፡ ሌላ ቀን ተመታ እየተባለ እንግዳ ሲመጣ እና ምርጫ ሰሞን የማይመታው እንግዳ አክባሪ ሆነው አይመስላችሁም? ምስጢር አለው ካላችሁ ፈልጋችሁ ድረሱበት፡፡



    ከተማው በጨለማ ከመዋጡ ጋር በየቦታው ጄኔሬተሩ ሲንፈቀፈቅ ግዙፍ ፋብሪካ ውስጥ የምንኖር ሁሉ ይመስለኛል፡፡ በቃ!..የማርያም መንገድ ካገኘሁ መገስገስ ነው፡፡ ‹‹ገስግስና በለው..ገስግስና በለው..ጠላትን እንደ በሬ.. ›› የሚለው ዜማ ትዝ አለኝ፡፡ ወደ ታሪኩ ስመለስ አዲስ ሞቅ ደመቅ ያለ ባህላዊ ዜማ ተከፈተ፡፡ ጋባዥ ሳልሻ፣ አጫፋሪ ሳልፈልግ ንሽጥ አድርጎኝ ድረግም፡፡ እናቴ የማይወጡት ዘቅጥ ውስጥ ገባሁላችኋ፡፡ ቡርቅ..ቡርቅ..ትከሻዬን ሰበቅ ሳደርግ አምሬያት ይሁን ማርኬያት ወደ እኔ አንዲቷ ቆንጆ መጣች፡፡ ‹‹እሰይ ደስ ይበለን እሰይ ደስ ይበለን አውዳመት መጣልን..›› የሚለውን ዜማ ገልበጥ አደረኩላችሁ እና ‹‹እሰይ ደስ ይበለኝ..እሰይ ደስ ይበለኝ አጣማጅ መጣልኝ..›› አልኩ፡፡ ምነው እኔ ላይ ሲሆን ተኮሳተራችሁ ሁሉም የየሰዉን እየገለበጠ ነው የሚዘፍነው፡፡ እንኳን የእኛ የአረቦቹ እና የፈረንጆቹ ሁሉ ተገልብጦ አልቋል እኮ!!..፡፡



    ጭፈራውን ሳስነካው ላቡም አባይ ስለሚገደብ ከወዲሁ ፈርቶ በእኔ አናት ላይ መንገድ የቀየሰ እስኪመስል አጥለቀለቀኝ፡፡ በዚህች ሰዓት አንዱ ከኋላዬ ነካ..ነካ.. ሲያደርገኝ በጭፈራዬ የተማረከ ሰው እንዳጫፍረው አለያም ላቤን እንድጠርግ ሶፍት ሊሰጠኝ እንጂ እንደ አዝማሪ ቤት ግርባሬ ላይ ሊለጥፍልኝ አይሆንም ብዬ ዞርኩላችሁ፡፡ ከዛ ምን እንደተፈጠረ አላውቀውም፡፡ ቤት የተቃጠለ እስኪመስለኝ የቀለም ሁሉ አይነት ቦግ ብሎብኝ ሲጠፋ ተዝለፍልፌ ወደኩ፡፡ ምን ባጣፈሁ ነው የእናቴን ገበር ምጣድ በሚያክል እጁ በጥፊ የከደነብኝ፡፡ አሁን ሳስበው ያኔ ይቺ ድንቡሎ ፊቴ እሱ እጅ ላይ ስታርፍ የቡሄ ሙልሙል መስላ ይሆን? ምነው ያኔ ፎቶ ባነሱኝ ነበር፡፡ እኔ ወድቄ እሱ ለያዥ ገናዥ አስቸገረ…



             አንዴ ታጥቤ፣ ደሜን ጠራርጌ እመለሳለሁ ጠብቁኝ፡፡