Tuesday, May 8, 2012

ስለ ልጅነቴ እውነት እውነቱን እናውራ ካልኩ ብዙ ደስ የሚል ባይሆንም በድህነታችን ላይ የተመረኮዘ ጦሽ..ጧ../ባያስቅም ለሞራሌ ስትሉ ሳቁ/ የሚያደርግ ወግ አወጋችሁዋለሁ።ጆሮዎትን ለመስማት አቀባብሉና አበድሩኝ። ተኖረና ተሞተ ያሉት የአለቃ ገ/ሀናን አይነት ህይወት ባይሆንም አኛም ሰፈር ተኖሯል። ምን ይጠበሰ እንዳይሉ..አሳ እንዳልል ተወልጄ ያደከበት ሰፈር አሳ በስህተት ካልሆነ አይገባም። ወንዝ የለ ሀይቅ የለ ከየት ይመጣል?የአሳ ስዕሉን እንኳን ይዞ መገኘት ሰው በማጓጓት እና ምራቅ በማሰዋጥ ወንጀል ያሰከስሳል። 4ኪሎ እና 6 ኪሎ መሀል 5 ኪሎ ብለው ይጠሩታል፡፡ ማን መዘነው እንደትሉኝ ተወለድከበት አልኩ እንጂ መሰረትኩት አ...ላልኩም።

ዘውዱ አዲስ፣ነብዩ ሀይሉ፣ወንደሰን ሰብስቤ፣ ዳንኤል መሀሪ..ተወልጄ ያደኩበት ጊቢ ያሉ ልጆች ናቸው። የረሳሁዋችሁ አትቀየሙ። አንተነህ ፑሲን ግን አልረሳሁም።ዛሬ ዘውዱ አሜሪካን በዲቪ ሰበብ ከትሟል። ነብዩ እና ወንደሰን የት እንዳሉ አላውቅም። የት ናችሁ ከሰማችሁ አለን በሉኝ። ዳንኤል ግን ኤርትራዊ ስለሆነ መውጣቱን አውቃለሁ እንጂ የት አንዳለ ምንም መረጃ የለኝም። ዳንኤል ይህችን መጣጥፍ ካገኘሀት ሰላምታዬን ማድረሴ ብቻ ሳይሆን ዘውትር እንደማስብህ ተረዳ። /ማኸዛይ ኩሉ ጊዜ ይዝክረካ-ሰላም ንዓካ/ ብዙ ትዝታ ያለኝ ግን ከጌታሁን መሳፍንት፣ከተካልኝ ተክሌ፣ከቀìላ ሲሳይ፣ከካሳሁን የሺጥላ፣ሳሙኤል ብስራት..ታዩ…ሽፈራሁ ሀብቴ፣ካሳሁን መኮንን.. ሰይፈ ጌታቸው….ብዙ ነን። ሰይፈ ነፍሱን ይማር በሞት ተለይቶናል።

ከነዚህ ውሰጥ ጌታሁንን ከሁሉም ይበልጥ እወደዋለሁ። ጌትሽ አጭር እና ቀጭን በመሆኑ እንዝርት የሚል ቅêል ስም አለው። እኔ ድንጋይ ስወረውር ባለመሳቴ ጠጅቱ የምትባል የሰፈር ሰው ቦምቤ አለችኝ። ይህች ቅêል ስም ከራሴ መተለቅ ጋር ተያያዘችና ቦምብራስ የምትል ታፔላም ሆና ነበር። ትንንሽ ቦምብ መኖሩን ቢያውቁ ስያሜውን ይፍቁልኝ ነበር። አባቴ ሁሌም ሱፍ ሱሪና ኮት ያሰፋልን ስለነበር ከበተር ፍላይ ከረባት ጋር ስለማደርግ እና ካቆሸሽኩ ሰለምገረፍ ጓደኞቼ ኳስ ሲጫወቱ እኔ ቁጭ ብዬ ስለማይ አካሄዴንም ጨምሮ ባንታለም ሰብስቤ ሚኒስቴር የሚል ቅêል ስም አውጥቶልኛል። ሁለት በሉ።

ከጌታሁን ጋር ትምሀርትም አብረን ነው የምንማረው። አርመን/አሁን ብሔራዊ ቤተመንግስት/ የሚባለው ት/ቤት ነው የተማርነው። ብሩክታይት አሰፋ..አሁን ካናዳ አለች የፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር ልጅ፣..ፍሬህይወት አጥላባቸው.. ሳባ ተርዲ የሚባሉ የምንቀርባቸው ልጆች ናቸው። ሳባ ተርዲ ለጌትሽ ሴት ጓደኛው ነበረች። ሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የገጠመኝን መዓት ላውጋችሁ ፦ ቲችር አበበ የምንላቸው አንድ እግራቸው አጠር ያለ የክፍል ሀላፊያችን በአንደኛ ሴሚስተር አንደኛ መውጣቴን ገልጠው ሰርተፊኬቴን ሲያቀብሉኝ አሰጨበጨቡልኝ። እግዚአብሔር ይስጣቸውና ያኔ ባያስጨበጭቡልኝ ኖሮ ሳይጨበጨብልኝ እሞት ነበር። ከዛ በሁዋላ ጭብጨባን ዳግም አላገኘሁትም። ለማየት እንኳን ምክር ቤት እሱንም በቴሌቪዥን ነው የማየው። ቀጠሉና ሁለተኛ ለወጣው መስፍን ተ/ሀይማኖት ሰርተፊኬቱን ካቀበሉ በሁዋላ አጫሽ ስለሆኑ ሁሌ ያስላሉ። በሳል የታጀበ ጥያቄ መረቁለት።

<<..ወንድማማቾች ናችሁ?>> ጢም የከበበው አፋቸውን ሞጥሞጥ አድርገው ሲያፈጡብኝ ፈራሁ እንጂ <<..በአማርኛ ክፍለ ጊዜ ላይ ያስተማሩንን አዛምድ እኛ ላይ ሊሞክሩት ነው እንዴ?እኛ ቤተ ሙከራ ያለ አይጥ ነን >> ልላቸው አሰብኩ። ምን ያደርጋል ስለምፈራ ፍርሃቴን ተሸክሜ ቀረሁ። እሳቸው ግን ድፍረት አገኙና በአንካሳ እግራቸው ከፍ ዝቅ እያሉበት ብላክቦርዱ ጋር ቆመው እያስተዋሉን <<..ደሞ በመልክም ትመሳሰላላቸሁ..>> ሲሉ ሽርደዳ የሚመስል ቃላት መረቁልን። አሁን የማላስታውሰው ስድብ በውስጤ ሰደብኳቸው። ለነገሩ እንኳን አላስታወስኩት የስድብ ጥሩ የለው። ነብሳቸው ይማረውና በመጥፎ ድርጊት ስለሚታሙ በሱው የሰደበኩዋቸው መሰለኝ። ሁሌም አውቶቡስ ላይ ከሴቶች ሁዋላ ቆመው ይተሻሹና..አንድ ጊዜ አንድ ሴትዬ እንትናቸውን ይዛ ስትጎትታቸው በዓይኔ አይቻለሁ። ከዚህ የራቀ አልሰደበኩዋቸውም። ከፈለጉ ራሳቸው አያስታውሱ እኔ ምን አቀጣቀጠን? አባቴን ዋልጌ አድርገው ከእናቴ ውጭ እንደወለደ ለምን አሰቡ ብዬ ነው መሳደቤ።

ከውስጥ ኔትወርካችን ተገናኝቶ ይሁን ተጠላልፎ ድንገት ሳናውቀው እኩል <<አይደለንም>> አልናቸው። አልተዋጠላቸውም። እንኳን ሊዋጥላቸው ከጆሯቸውም የገባ ሳይመስሉ << ለማንኛውም ተጠያየቁ>> የሚል ማሳሰቢያ ቢጤ ወርውረው ሰርተፊኬት ማደል ቀጠሉ። አጠገቤ የተቀመጠው አላዛር ነጋሽን ቢሉ የሁለታችንም ራሰ ጠበደል በመሆኑ ሊያመሳስሉን ይችላሉ የሚል እሳቤ ከማሰቢያዬ ውስጥ ስንቅር አለ። እስክንወጣ ተነቆራጥጨ ጠበኩ። ስንወጣ መስፍንን በጥያቄ አጣደፍኩት።
<<የአንተ አባት ምን አይነት ነው? የእኔ አባት ቀይ ረጅም ሽበታም ነው..የአውራ ጎዳና መኪና ይነዳል ትልቅ የነዳጅ ቦቲ..>> በጥሞና ሲያዳምጠኝ ቆይቶ <<የእኔም አባት አንተ እንደምትለው ነው ብዙ ጊዜ ክፍለ ሀገር ነው።ግን ትላንት ማታ መጥቶ ነበር።..>> አለና የቲቸር ሳያንስ እሱም ጥርጣሬ አርሶ ስለዘራብኝ ቤቴ ልወስደው አሰብኩ።

የልጅነት ታሪካችን ቢውራ..ቢወራ የሚያልቅ አይደለም። ቀጣዩን ሳምንት እመለስበታልሁ። ከደበራቸሁ ግን ገትረው በሉኝ።እገትረውና ቴዘር ትጫወቱብታላችሁ። ከተመቻቸሁ ጭብጨባችሁን አሰሙኝ። ወደፊት እንላለን።
ቸር እንሰንብት
See More