Wednesday, October 17, 2012


ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገራት
በግሩም ተ/ሀይማኖት
 መሰረት
   አረብ ሀገር ለሁሉም ጎርብጧል፣ ሁሉም ተበድሏል፣ ሁሉም ጉዳት ድርሶበታል አያስብልም፡፡ በለስ የቀናቸው ሞልተዋል፡፡ የበቤተሰብ ችግር ቀርፈው ለራሳቸውም ጥሪት የቋጠሩ ጠንቃቃ እና አላማ ያላቸውም ብዙ ናቸው፡፡ አላማ ኖሯቸው እድልና አጋጣሚ ፊቱን አዙሮባቸው የለፉበትን ያጡ፣ ምላስ ጠልፏቸው ፍቅር መስሏቸው የለፉበትን በትነው እድሜያቸውን አባክነው በዜሮ ፎሪ የወጡም መኖራቸው እንዳይረሳ እላለሁ፡፡ ሁሉም የየራሱ ፍላጎትና አላማ ቢኖረውም ሳይሳካለት ሲባዝን የከረመውን ቁጥር ማስላቱ ግን ያማል፡፡ ቸግሯቸው ተገደው ራሳቸውን ለገበያ ያቀረቡ የመኖራቸውን ያህል ፈልገው ደግሞ በመጥፎ ስራ የሚሰማሩም መኖራቸውን ግምት ውስጥ መክተት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሆድ ለባሰው ..›› የሚያስተርትም ውል ያጣ የመከራ ቋት የሚገፉ እህቶቻችን መኖራቸውን ማሰብ ግድ ይላል፡፡ ተከታዩን ታሪክ የምታነቡ ሁሉ ምን እንደተሰማችሁ ጣል ብታደርጉ ደስ ይለኛል፡፡
  
    መሰረት ትባላለች ሁሌም ስትታይ ደስተኛ ነው የምትመስለው፡፡ መሳቅ፣ መጫወት የግል ሀብቶቿ ይመስላሉ፡፡ የምን ይመስላሉ ናቸው እንጂ፡፡ ደስ የሚል ጠይምነት የተላበሰ ከለር አላት፡፡ በስደት አስከፊነት ዙሪያ አንድ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ጥናት ሳደርግ ሰዎችን አፈላልጎ ማነጋገር ነበረብኝ፡፡ ፎርም በትኜ ለማስሞላት ተገደድኩ፡፡ መረጃ ለማግኘት ያለውን ወጣ ውረድ በመጀመሪያ ደረጃ ያጠነከረው ድብቅነት እና እፍረት ነበር፡፡ ይህን መሰናክል ለማለፍ ስል ሴቶቹን ሴቶቹ እንዲያናግሩልኝ አደርግ ነበር፡፡ ይህን በማድረግ ከተባበሩኝ ውስጥ ዋናውን ሚና የተጫወተቸው ጸሀይ በየነ ስትሆን በመቀጠል ሔለን ገ/እግዚአብሄር፣ አስመረት ገ/እግዚአብሄርን ጥሩ መረጃዎችን በማቅረብ አሁን አዲስ አበባ ቢገቡም ሰብለወርቅ ታደሰ የሳሪስ ልጅ እና አይናዲስ ኢደሳ የቃሊቲ ልጆች ነበሩ፡፡ ምስጋራዬ ዘውትር አይለያቸውም፡፡ መንታ ያድርጋችሁ ብዬ መርቄያቸዋለሁ፡፡ እንዳልኩት ካረገላቸው ደስተኛ ነኝ፡፡ ከእነዚህ ልጆች መካከል አንደኛዋ መሰረት የተባለችን ልጅ ጠቆመችኝ፡፡ ልጅቷ ለእሷ ልትነግራት ያልደፈረችው አሳዛኝ ታሪክ እንዳላት ነበር የነገረችኝ፡፡

     ልጅቷን እንደምንም አገኘኋት እና ቀጠሮ ያዝን፡፡ በተነናኘንበት ሰዓት የየመንን ምድር ከረገጠች ሰባት አመቷ ነው፡፡ ያው የመን ረጅም ሰዓት ለማውራት፣ ሰው ቤት ግብዣ ሲባል፣ ሰርግ፣ ልደት ላይ፣ ለቅሶ ቤትም ቢሆን ሰብሰብ ብሎ ጫት መቆረጣጠም የተለመደ ነው፡፡ እኔ እና እሷ ስንገናኝ ትቅም እንደሆን ቡና አቀራርቤ ልጠብቅህ ስላለችኝ ተዘጋጅቼ ጫቴን ውሀዬን ለእሷም ሰንቄ ነው የሄድኩት፡፡ አፋችንን አበስንና ወጋችንን ቀጠልን፡፡

      የመጣችው በባህር ነው፡፡ የየመንን ምድር ከመርገጧ በፊት ባሬን የስድስት ወር ቆይታ አድርጋለች፡፡ ለምንድን ከባህሬን ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰች እና በባህር ዞራ የመን እንደመጣች ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ ለማናገር የፈለኩበትን ምክንያት ደጋግሜ ከልምምጥ ባላነሰ ሁኔታ አስረዳኋት፡፡

     ‹‹ተወኝ!..ተወኝ!..እንዲሁ የውስጤን በውስጤ ይዤ ለይምሰል ሰው መስዬ ልኑርበት፡፡ መስሎ መታየት ታውቃለህ አርቲፊሻል ሳቅ እሱን ልሳቅበት..ቁስሌን ነካክተህ ላታድነው አታመርቅዘው፡፡ ከእነ ህመሜ፣ ከእነ ቁስሌ፣ መኖር የቻልኩት ድረስ ልኑር ልታገል፡፡ በዚህ ዙሪያ ባናወራ እመርጣለሁ ልትተወኝ ፍቃደኛ ነህ….›› አለችኝ፡፡ ይበልጥ ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ የማዕድን ቁፋሮ ያህል ታዬግ፣ ታግሼ ለምኜ በኋላ ጥሩ ነገር እንደማገኝ ገመትኩ፡፡ ማግባባት የምችለውን ያህል ለማግባባት ሞከርኩ፡፡ የሚንዠቀዠቀው እንባዋ የእኔንም ስሜት በሀዘን ድባብ ጠፍሮ እንባዬን አስፈሰሰው፡፡ እስከመቼ ተሰደን በየሰው ሀገር አዝነን ስናለቅስ እንኖራለን የፈሰሰ እንባችንስ የሚቆጠርልን መቼ ነው ዋንጫው አልሞላ ይሆን? እስኪሞላ እንዳለቀስን እንኑር? እንባችን ዋንጫ ቀርቶ በርሜል፣ በርሜል አልፎ ወንዝ አይሞላ ይሆን..?›› ብዙ ብዙ አሰብኩ፡፡

    ‹‹ስማኝ ግሩም የእኔን ታሪክ ሰምቶ ከማዘን፣ ከንፈር ከመምጠጥ ውጭ ተሰምቶህ አንተ ያነባኸውን ያህል ሊያነቡ ይችላሉ ግን ከመሰደድ ወደኋላ አይሉም፡፡ ችግር መጥፎ ነው እያየህ እሳት ውስጥ እንድትገባ ያደርግሀል፡፡ እንደ እኔ አይነቱ ርሀብ የሚያዳፋው ምግብ ፍለጋ መጓዝ ስላለበት የሰማውን ችግር፣ ያየውን ተጎድቶ የተመለሰ ወገኑን ይረሳና ይሰደዳል፡፡ እኔ ያለውን ችግር ሰምቻለሁ፡፡ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ የእኔ ታሪክ ምንም አይፈጥርም፡፡ አይለውጥም፡፡ ተወኝ!!..መሳቂያ መሳለቂያ ለቤተሰቦቼ ማፈሪያ ለመሆን ካልሆነ ምን ሊጠቅም ..›› በጥያቄ ተሞልታ ስታፈጥብኝ ፈራኋት፡፡ አይኖቿ ፈጠው ዘልተው ውስጤን የሚመረምሩ መሰለኝ፡፡ ለማሳመን ያልቆፈርኩት ጉድጓድ ያላስረዳኋት ሁኔታ የለም፡፡ ሮዝማን የሲጋራ ፓኮዋን ከቦርሳዋ አውጥታ ለኮሰች፡፡ ዝምታ ጋርዶናል፡፡ ሁለት ሶስቴ ሳብ ቡልቅ..አድርጋ ጭሱ ተጉለለለ እያለ ያሻቅብ ጀመር፡፡ በጭሱ ውስጥ አሻግራ እያየች ‹‹እሺ ምን እንድነግርህ ፈለክ?›› ሁኔታዋ አስፈራኝ፡፡ ታሪኳን ሳልሰማ አሳዘነችኝ፡፡

     እስኪ ባህሬን ከሄድሽበት ጀምረሽ ንገሪኝ ከዛ ለምን ወደ የመን መጣሽ..›› አልኩ እና ምላሽዋን ጠበኩ፡፡ ደጋግሞ ግንባርዋ ቋጥር ፈታ ቋጥር ፈታ አለ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ይህን አስጠሊታ እና አስፈሪ ቴፕህን ዝጋልኝ፡፡ ያስፈራል፤ በእውነት የማውቀው ሰዎች ተሰብስበው ገመናዮን የምናገር እስኪመስለኝ ድረስ አስፈርቶኛል፡፡ እንደልቤ ነጻ ሆኜ ማውራት የምችል አልመሰለኝም..›› አለችኝ፡፡ አጠፋሁትና ወረቀትና ስክርቢቶ ይዤ ልረሳቸው የምችለውን ነገሮች ብቻ መመዝገብ ፈለኩ፡፡ ለማንኛውም ብዮ ሞባይሌን ሪከርድ ላይ አድረጌ ደረት ኪሴ ዶልኩት፡፡

      ‹‹የአዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ልጅ ነኝ..›› ስትል ጀመረች፡፡
    
       ‹‹..ዝቅተኛ በጣም ዝቅተኛ ከሚባለው ማህበረሰብ በታች የሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደኩት፡፡ መማር አልቻልኩም፡፡ ጨርቆስ ገበያ ውስጥ ጉልት እነግድ ነበር፡፡ እናቴ ስትታመም ታናሽ ወንድሜን ጨምሮ መብላት አልቻልንም፡፡ ሽርሙጥና ጀመርኩ፡፡ ቄራ /ቡልጋሪያ/ ደሴ ሆቴል፣ አብነት አካባቢ ቅዳሜ ቡና ቤት፣ በአካል ፀ፣ አራት ኪሎ ዘውዲቱ ሆቴል፣ ሳምሶን….ኤጭ!!..ዝርዝሩ ምን ያደርጋል… ሰራሁ ጠብ አይልም ቤተሰቦቼን ከችግር አላወጣሁም፡፡ እድል ለተቸገረ ሳይሆን ላለው ነው ፊቷን የምታዞረው፡፡ በመልክ መተናነስ ሳይሆን ገበያው ወደ እኔ አልዞር አለ፡፡ በዚህ ስራ ላይ እያለሁ በከፋኝ ሰዓት አብዱራህማን አልራሚ የሚባል ባሬን የሚኖር ሰው ተዋወኩኝ፡፡ የመናዊ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አሳዘንኩት መሰለኝ ሊረዳኝ ፈቀደ፡፡ ፓስፖርት እንዳወጣ 500 ብር ሰጠኝ፡፡ የሚገርምህ ምንም አይነት ነገር ከእኔ አልፈለገም፡፡ በዚህ እርዳታው ሁሌም ሳመሰግነው እኖራልሁ፡፡

      ‹‹ፓስፖርቱን አውጥቼ ሰጠሁት፡፡ ባህሪን ሲሄድ ይዞልኝ ሄደ፡፡ እዛ ለሚያውቀው ደላላ እንደሰጠ ስልክ ደውሎ ነገረኝ፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ቪዛ መጣልኝ፡፡ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ጨርሼ ባህሬን እስክገባ ያለምኩት ህልም ሳስታውሰው አፍራለሁ፡፡ ለቤተሰቦቼ ረድቼ ተለውጨ እነሱንም ለውጬ..ተወው እባክህ ህልምም ቅዠት ይሆናል እኮ!..ያሰብኩት ያለምኩት ሁሉ ጉም ሆነ፡፡

       ባሬን ዋና ከተማ ማናማ ስደርስ ከአየር ማረፊያ የተቀበለኝ አረብ ነው፡፡ ደላላው ነበር፡፡ መክተብ /ቢሮ/ ወሰደኝ፡፡ ትንሽ ከተማዋን ያየሁት እሰከ ቢሮው ሲወስዱኝ ነው፡፡ አሰሪዎቼ እስኪመጡ የክብር እቃ መስዬ ተጎለትኩ፡፡ አያናግሩኝም አላናግራቸውም ብል በምን ቋንቋ? አያቸዋለሁ ያዩኛል፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ በአንድ መኪና አባትና ልጅ መጡ፡፡ ሻንጣዬን ጭኜ ከኋላ ገባሁ፡፡ ከከተማው ወጥቶ የተኩል ሰዓት ያህል የሚያስኬድ ቦታ ነው ቤታቸው፡፡ ጊቢ ውስጥ እንደገባን ሻንጣዬን እንዳወረድኩ አባትዬው ልጁን ጠርቶ ገንዘብና የመኪና ቁልፍ ሰጥቶ ላከው፡፡ ሻንጣዬን ጠልጠል አድርጌ ከኋላ ተከተልኩት፡፡ ምድር ቤት የሆነ ክፍል አሳየኝ እና ሻንጣዬን አስቀመጥኩ፡፡ አንድ ፒጃማ ነገር ይዞ መጣ፡፡ ባኞውን አሳየኝ እና እንድታጠብ በምልክት ነገረኝ፡፡ ‹‹ጥሩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው..›› ብዬ ስለ ደካከመኝ ለመታጠብ ገባሁ፡፡

      ታጥቤ ስወጣ ሰውዬው ክፍሌ የተባለው ውስጥ ያለችው አንድ ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ ልብሴን የሚያስተካክል መስሎ ተጠጋኝ፡፡ አነቀኝ፡፡ የሚፈልገውን ላለማስፈፀም ትግል ጀመርኩ፡፡ ከኪሱ ብር አወጣና በእጄ ሊያስጨብጠኝ ሞከረ፡፡ ኢትዮጵያ እያለሁ ምን እንደምሰራ ያወቀ መሰለኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ቢሆንም ገላዬን በዙር በአዳር እየተመንኩ ከመቸርቸር ለመዳን ነው ስደት የመጣሁትና የአላስነካም ትግሌን ቀጠልኩ፡፡ በሬ በጥፊ መጣል በሚችል ግዙፍ እጁ በቡጢ ነረተኝ፡፡ ወደኩኝ፡፡ በእርግጫ ደገመኝ፡፡ መከላከል አልቻልኩም፡፡ አሰረኝ፡፡ በመደበኛው ቦታ ሲጨርስ እሱ እረፍት ሲያደርግ እኔ እንደታሰርኩኝ ነው፡፡ ቀጠለና ትክክለኛ ባልሆነ ቦታ ደገመ /እሱዋ ያለችውን ቃል አልተጠቀምኩም/፡፡ ህመሙን ግድ ሆኖብኝ ቻልኩ፡፡ የመኪና ድምጽ ሲሰማ ጥሎኝ ወጣ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ልጁ መጣ፡፡ ታስሬ ሲያየኝ በቀጥታ ልብሱን ማወላለቅ ጀመረ፡፡ እሱም በአባቱ ድርጊት ላይ ተደመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ እችላለሁ የመኝታ ቤቴን ቁልፍ እየተቀባበሉ ለሁለት የሚያደርጉትን ቀጠሉ፡፡ የሰውየው ሚስት ማለት የልጁ እናት ታማ ሆስፒታል ተኝታ ነበር፡፡ እሷን በማስታመም ላይ የነበረች አንድ ፊሊፒንሳዊ አብራት ነበረች፡፡ ሲመጡ ስታየኝ ገና አዘነች፡፡ የተያየነው ከ13 ቀን በኋላ ነው፡፡

      እሷ ስለለመደችው እኔ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አስባ ነው ማዘኗ፡፡ ማታ ላይ እኔ መኝታ ቤቴ በር ላይ ሆነው አባትና ልጅ ያወራሉ፡፡ አባት እኔ ጋር ልጅ ፊሊፒንስዋ ጋር ገቡ፡፡ ይሄ ሁኔታ በዚሁ በየቀኑ ቀጠለ፡፡ ተመካክረን ሁለታችንም አንዳችን መኝታ ቤት ለመተኛት ሞክርን፡፡  ሁለቱም አንድ ላይ ግብተው ስራቸውን እየተያዩ ቀጠሉ፡፡ ምን አይነት ሀገር እንደሆነ አባትና ልጅ የማይተፋፈርሩበት፣ ግብረ-ገብ የሚባል ነገር የሌለበት መሆኑን ለማወቅ ከዚህ በላይ ምን ማረጋገጫ ያሰፈልጋል፡፡
     ወር ላይ የወር አበባዬ ቀረ፡፡ ለማን ላማክር?
                   የዚህን ታሪክ ቀጣይ ይዤ እመለሳለሁ