Tuesday, August 28, 2012

የአቡነ ጳውሎስን ሞት ስሰማ ሶስት ነገሮች ታወሱኝ
የአምላክስራ ግሩም

ከፈጣሪያቸው ይልቅ ቀጣሪያቸው መለስን ይፈራሉ የሚባሉት የአቡነ ጳውሎስን ሞት ስሰማ ሁለት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ቀጣሪያቸውን ያልኩት በአንድ ወቅት ጳጳሱ የሲኖዶሱን ህግ ሊቀይሩ ፈልገው በተነሳው ውዝግብ ዙሪያ አለቃ አያሌውን ቃለ-ምልልስ ስሰራ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖና ውጭ ጳጳስ በህይወት እያለ በመንግስት የተቀጠሩ ቀኖና የሻሩ ናቸው ስላሉኝ ነው፡፡

የአቡነ ጳውሎስም ሞት ስሰማ ትዝ ያሉኝ ሶስት ነገሮች…አንደኛ ተወልጄ ያደኩበት ሰፈር ቅ/ማሪያም ቤተክህነት ፊት ለፊት በመሆኑ ሲወጡ ሲገቡ ወታደራዊ ሰላምታ እየሰጡ ‹‹ታጋይ ጳውሎስ!..›› የሚሉዋቸው ሁለት ልጆች ታወሱኝ፡፡ ሁለተኛው በሳቸው ጠባቂዎች እንደተገደሉ የሚነገረው ባህታዊ እና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መጥተው ከፊቴ ድቅን አሉ፡፡ ሶስተኛው በጎንደር ሀገረ ስብከት ውስጥ የተሰራውን ሙስና አጋልጨ በእሳቸው እና በዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴ ከሳሽነት ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እኔና ጓደኛዬ ላይ የተፈጸመብን ግፍ ታወሰኝ፡፡ ለሶስቱም ትዝታዎቼ ምክንያት አለኝ፡፡ በተለይ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የተደረገብኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከህሊናዬ የሚፋቅ አይደለም፡፡

በዕለተ ሀሙስ አረብ ሳይት ላይ ብቅ ጥልቅ የሚጫወተው ኢቲቪ ድብብቆሽ ጫዎታውን ስለቀጠለ ሀገሪኛ መረጃ የሚያቀብለን ብቸኛው ኢቢኤስን እያየሁ ነው፡፡ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው በተፈጸመበት ወቅት ብዙ እውነት የማይመስሉ ሙገሳዎች ከአስተያየት ሰጪዎች ሰማሁ፡፡ እውነት ለእሳቸው ነው ሌላ የማላውቀው አቡን ሞተዋል ያስብላል፡፡ መቼም ከተጠናወተን መጥፎ አመል ውስጥ ሰው ሲሞት ጨካኙን ደግ ሌባውን ንጹህ ማድረግ፣ ሰው ያልሆነውን ነው ብሎ መካብ ዋነኛው በሽታችን ነው፡፡ ምናለ ዋሽተን ያልሆኑትን ከምንቀባጥር ዝም ብንል በዝምታ፡፡ መቼ ይሆን አካፋን አካፋ የምንለው? ‹‹..ካልሆነም ዝም አይነቅዝም..›› ይባላል እኮ፡፡ በተለይ አንድ መምህር/ሰባኪ/ ነኝ ያለ ሰው አድርባይነቱ ሳይሆን በዚህ ውሸትን ባዘለ አንደበቱ የሚሰብከው እንዴት ይሆን? የሚል እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ በቲቪው ፕሮግራም ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ መሰራት ያለበትን ነው የሰሩት፡፡ የሰዎችን ሀሳብ መገደብ የለበትምና..ስለሳቸው ግን ከተባለው ውጭ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እኔ ግን የማስታውሰው እና የማውቀው እውነታ ተቃራኒ ነው….

ትዝታ አንድ፡- በቅጽል ስማቸው ፑሲ እና ነጬ በመባል የሚታውቁት ልጆች በይፋ ወታደራዊ ስላምታ እየሰጡ ‹‹ታጋይ ጳውሎስ!!›› ይበሉ እንጂ የአካባቢው ሰውም ሆነ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና የሚያውቁ በድብቅ ይህን ከማለት ወደኋላ አላሉም ነበር፡፡ በወያኔ መመረጣቸው ብቻ ሳይሆን በፖሊስ ዲፌንደር መኪና ከፊት ከኋላ መሳሪያ ባነገቡ ጠባቂዎች ከመታጀባቸው ጀምሮ ታጋይ ጳውሎስ የተባሉበትን ነገር ከዘረዘርኩት ጊዜም ቦታም አይበቃም፡፡ በቲቪ ካየኋቸው አስተያየት ሰጪዎች መካከል ‹‹..ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ፣ ለጋስ፣ ደሀ ረጂ..፣..›› ምንትሴ..ቅብርጥሴ የሚሉ ግነት የሞላቸው ነገሮች ናቸው ይህን እንዳስታውስ ያደረገኝ፡፡ በተለይ ‹‹..ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ…›› የምትለው ነገር አልዋጥልህ አለኝ፡፡ ገዳማት ሲፈርሱ የታገሉት ትግል ስለመኖሩ መረጃ ስላጣሁ ነው አልዋጥልህ ያለኝ፡፡ ለቅዳሴ ጧፍ የሚያጡ ደብሮች ባሉዋት ኦርቶዶክስ ባጀት ጥይት የማይበሳው ፍሪጅና ስቶቭ ያለው ሶስት መኪና ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተው ሲያስመጡ ይህም ሀይማኖትን መውደድ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው በእሱ ቤት ያደረ አገልጋይስ በጋርድና መሳሪያ መጠበቁ ሀይማኖቱን ወይስ ራሱን መውደዱን ያሳያል? ለነገሩ ራሳቸውን መውደዳቸው አይደል የራሳቸውን ሀውልት ሲኖዶሱ ሳይፈቅድ እየተቃወማቸው ያቆሙት?

ትዝታን ትዝታ ሲስበው ከእሳቸው በፊት በነበሩት በአቡነ ተ/ሀይማኖት ጵጵስና ዘመን ለዘመን መለወጫ ገብቶ ገንዘብ ያልተቀበለ የአካባቢው ልጅ የለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጳጳስ ምን እንደሆነ እንኳን በማላውቅበት ሰዓት ነፍሳቸውን ይማረውና ልጆች እንግባ…እንግባ ብለውኝ ቤተክህነት ገባን፡፡ አሁን ስማቸውን የማላስታውሰው..ዘበኛ አሰላፊነት ተሰልፈን አቡነ ሰላማ ይመስለኛል ስማቸው ይዘውን ገቡ፡፡

ክስት ባለ ሰውነታቸው ላይ ልዩ ግርማ ሞገስ የተላበሱት ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ተ/ሀይማኖት መስቀል እያሳለሙ የክርስትና ስም ይጠይቁን ጀመር፡፡ ተራዬ ደርሶ ክርስትና ስሜን ተናግሬ መስቀል ተሳለምኩ፡፡ ከእየሩሳሌም የመጣ መስቀል በክር በክር ተደርጎ አንገታችን ላይ እያጠለቁልን አስር አስር ብር ሰጡን፡፡ እንደ ሀይማኖት አባትነታቸው..እኛም እንደ ልጅነታችን ማን እንደጀመረ ባላስታውስም ዝቅ ብለን እግራቸውን እየሳምን ወጣን፡፡ በዚህ ጊዜ ያስተዋልኩት አሁንም የማስታውሰው ጫማ አለማድረጋቸውን እና እግራቸው ልስልስ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ነገር ሲገርመኝ ስላደኩ ነው መሰል በአንድ ወቅት ቤተክህነት ይሰሩ የነበሩ የጓደኛዬን እናት ጠየኳቸው፡፡ ደርግ ይሰሩልኛል ብሎ ቢመርጣቸውም እንደፈለገው ሳይሆን እንዳልፈለገው ሆነው ተገኙ፡፡ የአራት ኪሎው ቅዱስ ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ደውል ፓርላማ ውስጥ ስለሚበጠብጥ ተብሎ እንዳይደወል ታገደ፡፡ ቀጠለናም መውጫ በሩ በግንብ ተዘጋ፡፡ ለማስከፈት ያደረጉት ትረት ሰሚ አጣ፡፡

በዚህን ጊዜ ያ-የተዘጋ የቤተክርስቲያን በር እስኪከፈት ጫማ ላለማድረግ እና ከጥራጥሬ ውጭ እህል ላለመብላት ቃል ገብተው እስከሞቱበት ዕለት የተዘፈዘፈ ሽንብራ እና ጥራጥሬ እየበሉ ኖሩ፡፡ ታዲያ ትዝታዬ ብቅ ያለው የአሁኑ ደግ ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ የተባሉት ዋልድባን የሚያክል ገዳም ሲጠረመስ እንኳን ድምጻቸውን አልሰማሁም፡፡ አቡነ ተ/ሀይማኖት በደሞዛቸው የሚያስተምሯቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ልጆች ነበሩ፡፡ በአካባቢያችን ልጁን ማስተማር ያልቻለ ሰው ማመልከቻ አጽፎ ሲሄድ ይረዱ ነበር፡፡ አሁን ደግ፣ ለጋስ ሲባሉ የሰማሁት አቡነ ጳውሎስ ግን ደሞዛቸውን ከአቡነ ተክለሀይማኖት በሶስት እጥፍ ቢያሳድጉም ባጀት የለም በሚል ግንፍሌ ድልድይ ጋር የነበረው የልጆቹን መኖሪያ የአቡነ ገሪማን ፊርማ ባዘለ ደብዳቤ ከረቸሙት፡፡ ቦታው ለቢሮ እና ለተለያየ ነገር እንዲውል ሆነ፡፡

ትዝታ ሁለት፡-እለቱ ሀሙስ መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ ቦሌ ማተሚያ ቤት ጋዜጣ ለማሳተም ልሄድ ስል ግርግር እስጢፋኖስ ጋር አየሁ፡፡ ዕለቱ የእሲጢፋኖስ በዓል የሚከበርበት በመሆኑ ብዙም ትኩረት ሳልሰጠው ነበር ያለፍኩት፡፡ ቦሌ ማተሚያ ቤት ስደርስ ግን ጳጳሱ አንዱን ባህታዊ ገደሉ የሚል ግነት የተሞላበት መረጃ ደረሰኝ፡፡ ለማተሚያ ቤቱ ካሜራ ክፍል የምሰጠውን ሰጠሁና ለማጣራት ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ተመለስኩ፡፡ ሰዉ ሁሉ የሚያወራው የተምታታ ሆነብኝ፡፡ ቦታው ላይ ከነበረ ሰው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አቃተኝ፡፡ አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይደግመውም፡፡ ጠባቂያቸው እንጂ እሳቸው አይደሉም የሚለው ሀሳብ ደጋግሞ ደረሰኝ፡፡ ወደ ቦሌ ማተሚያ ቤት ተመልሼ የጋዜጣውን ህትመት እየተከታተልኩ ሳለ ድካም ተሰማኝ እና ማሙሽ የሚባል ልጅ፣ ጌታመሳይ ገ/መስቀል ማራቶን የሚባል የስፖርት ጋዜጣ የሚከታተል ልጅ ወደ ተቀመጡበት ተቀላቀልኩ፡፡ ወሬው ስለዚሁ ጉዳይ ነበር አንድ በትክክል ቦታው የነበረ ልጅ ስለነበር ትክክለኛ መረጃ ሰጠን፡፡ በጠባቂዎቻቸው ነው ባህታዊው የተገደሉት መባል ብቻ ሳይሆን የብረት አንካሴያቸውን እየወዘወዙ ወደ ጳጳሱ በማምራታቸው እንደሆነ ችግሩ የተከሰተው ሰማሁ፡፡

ዋናው ነገር ግን ይህ አልነበረም፡፡ የተገደሉትን ባህታዊ ማንኛውም ቤተክርስቲያን ለቀብር ቦታ እንዳይፈቅድ ተወገዘ፡፡ እኝህ ባህታዊ ጳጳሱን እንኳን ሊገድሉ አስበው ቢሆን በቀልን ምን አመጣው? በቀል ካልሆነስ የሚቀበሩበትን ቦታ መከልከሉ ምን ይሆን ጥቅሙ? ፈረንሳይ ለጋሲዮን እየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ራስ ካሳ ቤት ተገኝቶ ህዝቡ በዘልማድ ጭቁኑ ሚካኤል የሚለው ቤተክርስቲያን የቀብር ቦታ ፈቀደ፡፡ የደብሩ አስተዳደር ተወገዙ፤ ቤተክርስቲያኗ ከሲኖዶስ ትዕዛዝ አፈንግጣለች ተባለ፡፡ በመወገዝ ብቻ አልበቃም አመታዊ የጥምቀት በዓልን ታቦቱ ከሌሎቹ ታቦታት ጋር ጃንሜዳ እንዳይወጣ ታገደ፡፡ ሐምሌ አስራዘጠኝ ማናፈሻ ጀርባ በቀበሌ 22 መዝናኛ ገባ ብሎ የማርያም ፀበል ያለበት ቦታ ከአድባራቱ ተነጥሎ አደረ፡፡ የሚገርመው ግን የኢየሱስ ደብር ታቦት ሚካኤልን ጥሎ ከሌሎቹ ጋር ጃንሜዳ አላደረም፡፡ እዛች አነስተኛ ቦታ ላይ አብረው አደሩ፡፡ ህዝቡም በእልህ አድምቆት አደረ፡፡ አስታውሳለሁ እኛም ጃንሜዳ ቢሆንም ያመሸነው አዳር ያደረግነው እዛ ነው፡፡ እንኳን ሰው ታቦት በሚያግዱት ጳጳስ ማን አስተዳድሩ አላችሁ ብለው ለእየሱስ ደብር ካህናት ዋጋቸውን ሰጡዋቸው፡፡

ትዝታ ሶስት፡- ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በጦርነቱ ለተጎዱ ቤተክርስቲያናት ማደሻ ከጎንደር አገረ ስብከት ጽ/ቤት ጥያቄ ቀረበ፡፡ በወቅቱ ጠ/ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ነበር ጥያቄው የቀረበው፡፡ ምንም አይነት ባጀት የለንም 10 ቶን ቡና ተፈቅዶላችኋል እሱን ወስዳችሁ ሽጡና በትርፉ የተወሰኑትን አድሱ ተባለ፡፡ ይሄን ቡና ወስዶ የመሸጡን ሀላፊነት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴን ወከሉ፡፡ ቡናው ተሸጦ ግን ለቤተክርስቲያኗ ማደሻ ሳይሆን ለአፍ ማሰሻ፣ ለኪስ ማደለቢያ ነው የሆነው፡፡

ቢታይ ቢታይ ሁሉም ዝም..ሆነ፡፡ ነገሩ የከነከናቸው አንዳንድ ካህናት ቤተክህነት ድረስ ለክስ ከጎንደር መጡ፡፡ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ተባሉ፡፡ መፍትሄም ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በዚህን ጊዜ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ አሳትም ነበረ እና ሙሉ መረጃውን ሰጡኝ፡፡ አጣርቼ ትክክለኛ ማስረጃ በመሆኑ ለህዝብ አቀረብኩት፡፡ የመረጃውንም ኮፒ ጋዜጣው ላይ አቀረብኩ፡፡ ወዲያው በብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ክስ ተከፈተብኝ፡፡ የክሳቸው ፍሬ ሀሳብ ትክክለኛ እና መጠየቅ ያለበትን ነው የጠየቁት፡፡ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ ያወጣውን ዘገባ አይተን ሁኔታውን ለማጣራት ሞክረናል፡፡ የተጠቀሱት ግለስብ የቀረበብኝ ማስረጃ ፎርጅድ ነው እኔ ስለሁኔታው አላውቅም ስላሉ ጋዜጠኛው ላይ ክስ ተመስርቶ ያለው ማስረጃ እንዲረጋገጥ፡፡ ትክክለኛ ከሆነ የጉዳዩ ባለቤቶች እንዲጠየቁ፡፡ ያቀረበው ማስረጃ ትክክለኛ ካልሆነ እና ፎርጅድ ከሆነ የእምነታችንን ክብር የሚያወርድ ነገር በሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረቡ እንዲጠየቅ..ይላል፡፡ በዚህ ክስ ቅሬታ የለኝም፡፡

ለመርማሪ ፖሊሱ ግን ገንዘብ ሰጥተው ትንሽ ቅጣትም ያሰፈልጋቸዋል፡፡ በደንብ መርምርልኝ ማለታቸው ከሀይማኖት አባት የሚጠበቅ ይሆን? ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀምብኝ አድርገዋል፡፡ ክትትል ሲደረግብኝ ቆይቶ ዘውዲቱ ሆቴል ራት እየበላሁ ሳለ ተያዝኩ፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ ገና ከመግባቴ ጀምሮ ዱላ ተቀበለኝ፡፡ ውብሸት የሚባል መርማሪ ወዲያው ስልክ ደውሎ መያዜን ሲናገር ከቢሮው ውጭ ብቀመጥም እየሰማሁት ነው፡፡ ቃል ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኔ ሶስት ፖሊሶችን ጠርቶ ከራሱ ጋር አራት ሆነው ሰማይ ምድሩ እስኪዞርብኝ አዞሩኝ፣ ቀጠቀጡኝ፡፡ በግድ ግን ቃሌን ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆንኩም፡፡ መረጃው አለህ? ያለህ መረጃ ፎርጅድ ነው ተብሏል፡፡ እላዩ ላይ ያለው ማህተም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አይደለም አለኝ፡፡ /አንድ ወረቀት ላይ ያረፈ ማህተም እያሳየኝ/ የእሳቸው ማህተም ይሄ ነው ..››ሲለኝ ግን እልህ ያዘኝ፡፡ ማህተሙን ከዚህ ወረቀት በኋላ መቀየራቸውን የሚያረጋግጥ ትንሳዔ ዘ ጉባኤ ማተሚያ ቤት ማህተም ያስቀረጹበት ማስረጃ እንዳለኝ ጭምር ቃል ሰጠሁ፡፡ ይህንን የሰጠሁትን ቃል ግን ወዲያውኑ ደውሎ የነገራቸው ፊቴ ነው፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ተከሳሽ የሆነው ዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴ ጉዳዩን እንዲከታተል በእሳቸው ፍቃድ ተላከ፡፡ በዛው ማታ መጣ፡፡ ይሄኔ ነገሮች ሁሉ ጎረበጡኝ፡፡ በጣም ተጠራጠርኩ፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ቤቴ ሄደን መረጃውን እንድናመጣ ፈለጉ፡፡ ግደሉኝ እንጂ አልሄድም እናቴ በዚህ ሰዓት እንድትደነግጥ አልፈልግም አልኩ፡፡ ሰበቤ በእናቴ ሆነ እንጂ እሳቸውስ መረጃው እንዲጠፋ ካልፈለጉ እንዴት ብሩን ያጨበረበረውን ሰው ይልካሉ? ለምንስ እሰኪነጋ መጠበቅ ሳይፈልግ ዲያቆን ደሳለኝ መጣ? ፍርድ ቤት ስቀርብ ካልሆነ ላለማቅረብ ወሰንኩ፡፡ ዳግም ዱላ ተጀመረ፡፡ እነሱ ሳይበቃቸው እኔ ተዝለፍልፌ ስለወደኩኝ መሰለኝ ድብደባው የተጠናቀቀው፡፡ ራሴን ስለሳትኩ እንዴት እንደነበር አላውቅም፡፡ ራሴን ሳውቅ ግን ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ሽንቴ ስለመጣ ካጋደሙኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ቀና ብዬ ሽንት ቤቱ የቱ ጋር እንደሆነ ተራኛውን ፖሊስ ጠየኩት፡፡ አሳየኝ እና ተነስቼ ስሄድ ውሻዋን ጃስ..ጃስ..ብሎ ሲያደፋፍራት እግሬን ዘነጠለችን፡ ወይም ዘነጠለኝ፡፡ የውሻውን ፆታ ስለማላውቅ ነው ሁለቱንም የተጠቀምኩት፡፡ እየተሳሳቁ ደግፈው አንስተውኝ ጊቢው ውስጥ ቆማ የበሰበሰች እና ሽንት የሚሸናባት አይጥ የሚርመሰመስባት አሮጌ መኪና ውስጥ ከተቱኝ፡፡ በማግስቱ ጓደኛዬ ዳንኤል የጋዜጣዬ ዋና አዘጋጅ ስለሆነ መታሰሬን ሰምቶ ፖሊስ ጣቢያ መጣ፡፡ ሳምንት ሙሉ እዛች የሚሸናባት መኪና ውስጥ አሳለፍን፡፡

ይህን ሁሉ የምለው ግን አስተያየት ሰጪዎቹ እና እሳቸው ይመሳሰላሉ ወይ? ወይስ አዲስ የሚመረጡትን ይሆን የሚያሞግሱት የሚለው እሳቤ መቶብኝ ነው፡፡ ምናለ እውነትን ለሰው ብለን ባንደፈጥጥ..ሰው ለማስደሰት ዋሽተን ፈጣሪን እያሳዘንን መሆኑን አትረሱ፡፡ ሙት አይወቀስም ብለንም ከሆነ ያልሆነ ቀባጥረን ከፈጣሪ ከምንጣላ ዝም ማለት አይቀልም?
ነብሳቸውን ይማር!!!!