Friday, May 4, 2012


ጥቁሯ ቦርሳዬ ክፍል 4
                     ወግ  በግሩም ተ/ሀይማኖት
   
 ሰላም ለምታነቡኝ፣ ሰላም ለምታዝናኑብኝ፣ ሰላም ለጓደኞቼ..ሰላም ለኢትዮጵያዊን ሁሉ...ምኞቴ ለሁሉም ሰላም ነውና ሰላማችሁ ይብዛ እላለሁ፡፡ ሰው ያለውን ከሰጠ ንፉግ አይባልም፡፡ ያለኝ አቅም መመኝት ነውና ተመኘሁላችሁ፡፡ ማየት መመኘት ማመንዘር ነው የሚለው እዚህ ጋር አይሰራም አትፍሩ፡፡ ከሰላም የበለጠ ምን አለ? ምነው በጥቁር ቦርሳ ተነሳህ የሚለኝ በዝቷል፡፡  የከለር ምርጫዬ ቀይ ቢሆንም ቦግ ብሎ መታየትን ስለማልሻ ሳይሆን ይቀራል? ብቻ እወዳታለሁ፡፡ ውስጧ ብዙ ምስጢር አለ፡፡ የጡረታ ጊዜዋ ቢያልፍም ፍቅር አስከ መቃብር ብዬ ሙጥኝታዬን አብዝቼባታለሁ፡፡ ለነገሩ ከሀገሬ ስወጣም ልክ የዚህችን አይነት ጥቁር ቦርሳ አንጠልዬ ነበር፡፡ እናቴም ሆነች እህቴ እኔና ጥቁር ቦርሳዬን ነው የሸኙን፡፡ ያቺ ቦርሳ ከእኔ ጋር ያላየችው ስቃይ የለም አንደበት ኖሯት አላወራችውም እንጂ...ደግነቱ እግዚአብሄር ይስጠኝ እኔ አውርቼላታለሁ፡፡ የአሁኗ ጥቁር ቦርሳ ከሀገር ስወጣ እንዳደረኩት ቡትቶ ሞልቼባት ሳይሆን ላፕቶፕ እና ወረቀታ ወረቀት ነው ያቆረችው፡፡ ስለያዘቻቸው ወረቀቶች እና መጣጥፎች ላወጋችሁ ነው፡፡

    ርዕሷን ግን ጥቁሯ ቦርሳዬ ያልኩበትን ምክንያትን መተንፈስ ግድ ይላል እና ላውጋዎ፡፡ የመብራት ችግር የመንን ከተጠናወታት ከረምረም አለ ከሚባለው አልፏል፡፡ አንድ አመት ከስድስት ውር ተጠግቶዋል፡፡..ያን የመብራት ችግር ለመቋቋም በተገኘው አጋጣሚ በቀን አንድም ሆነ ሁለት ሰዓት ብቅ ሲል ቻርጅ የሚደረገውን ሁሉ ቻርጅ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ እኔም ላፕቶፔን ይዤ መብራት ወዳለበት እብስስ....ቻርጅ አደርግና ለ3 ሰዓት ከተጠቀምኩ፣ ሞባይሌም ቻርጅ ከሌለው ከላፕቶፑ ካጋራሁ በኋላ ሌላ መብራት ወዳለበት...በቃ ምን አለፋችሁ እንደመድፍ አስተኳሽ ቦታ እየቀያየርኩ.. መዋጋት ነው፡፡ ታዲያ ቃታ ስቤ ጥይት አፈንድቼ አለመሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ እሷን ነገር አልወዳትም፡፡ ከመብራት ችግሩ ነው የምዋጋው፡፡ እንደዛ ሆኜ ነው ‹‹እኔ እና ጓደኞቼ››ን እና ‹‹ሀበሻ በየመን›› የሚሉ ጽሁፎቼን ያስነበብኩት፡፡ ለካ ያቺ የማንጠለጥላት ጥቁር ቦርሳ ተከራይቼ ያለሁበት አካባቢ ያሉ የመናዊያንን አይን ስባ ነበር፡፡ እኔን ሳትስብ የሌላውን መሳቧ ቢያስቀናኝም ቀናሁ አልልም፡፡ ቅናተኛ የሚል ታፔላ እንዳይለጠፍልኝ ፈርቼ ነው፡፡ ታዲያ አይናቸውን የሳበቻችው የመናዊያን  እኔ ሳልሰማ ‹‹አቡ አስወድ ሻንጣ›› ይሉኛል፡፡ ባለጥቁር ቦርሳው ማለት ነው፡፡

     አንድ ቀን ተከራይቼ ያለሁበት ፎቅ ላይ ከእኔ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከሚስቱ ጋር የተከራየ ልጅ ሱቅ እቃ ሊገዛ ይሄዳል፡፡ ነጋዴው ‹‹ለአቡ አስወድ ሻንጣ መልዕክት እኔ ጋር አለውና ንገረው›› ይለዋል፡፡ አንድ ጓደኛዬ...እእ በዘልማድ ነው ጓደኛዬ ያልኩት፡፡ የመን ውስጥ የልብ የምለው ጓደኛ የለኝም፡፡ ከምር ነው ለጓደኛነት የሚሆን ማሰብ ሀጢያት ነው የሚመስለው፡፡ ለዚህም ሳይሆን ይቀራል ብቸኝነት ያለ ፍቃዴ፣ የቤት ኪራይ ሳይከፍል..ቂብ ብሎብኝ ያለው፡፡ እናላችሁ የተቀመጠልኝን መልዕክት እንድወስድ ላከብኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ስጠይቀው ባለሱቁ ሁሌ ጥቁር ቦርሳ ስለምይዝ እና ስሜን ስለማያውቁት እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እኔ ግን ስያሜዋን ወደድኳት፡፡ ተጠቀምኩባት፡፡ ጥቁሯ ቦርሳ የያዘችውን ምስጢር ቢያውቅ....አይ የኔ ነገር ልታውቁት አይደል?

       ከርዕስ ውጭ ጥቂት እናውራ፡- ቴዲ አፍሮ የአሁን ዕለቱ ትላንትና በለቀቀው አልበሙ ‹‹...ተናነቀኝ እንባ...ተናነቀኝ፣ ተናነቀኝ...›› የሚለው ዜማ በጥፊ ስትባል ከምትንኮራኮር ቴፔ ይንቆረቆራል፡፡ ቀልድ የማያውቀው አይኔ የምር አድርጎት እንባዬ ተናነቀኝ እና ቁጭ፡፡ ምክንያት ያደረገው ብቸኝነቴን ቢሆን ደግሞ ምን ትላላችሁ? የተናነቀኝ እንባ ግን ዝርግፍ ያለው ቆይቶ የሰማሁት ‹‹ስለፍቅር ሲባል ስለፀብ ካወራን ተሳስተናል አንድ ላይ ብንኖርም ተለያይተናል፤አጥተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል..›› ሲል ብሶታችንን እቅጩን ነው የነገረን እኮ ታዲያ እንዴት አልዘረግፈው? ሰው ብሶቱን ሲነግሩት አይደል..መጎዳቱን የሚያውቀው? ተቸግረን እናገኛለን በማለት ስንሰደድ አይደለም ባህር ስንቱን የዋጠው? ዋ! ወገኔ...መቼም ምስኪን ነኝ እና ቴዲን አስለቅሶኝ መረቅሁት፡፡ ሰው በልኬ ብለህ የለመንከውን የሰማና በልክህ የሰጠህ አምላክ ነገም ብንረዳህም ባንረዳህም ማንነታችንን፣ ችግራችንን፣ ታሪካችንን ፍቅራችንን፣ ማጣታችንን፣ አረንጓዴ መሬት ይዘን መራባችንን.. አንቆርቁረህ እንድታሰማን እድሜ ይስጥህ አልኩት፡፡ ምነው ፈጣሪ ምርቃቴን ሰምቶ እውን ባደረገለት? ዋይ ቢኖረኝ ላጥ አድርጌ ወርቅ ነበር የምሸልመው፡፡ ለነገሩ ያለኝን ሸለምኩት አይደል? ከወርቅ የበለጠ እድሜ ለምኜለታለሁ፡፡ ወርቁንም የሚያጌጥበት እድሜ ያስፈልገዋል እኮ...

     ለነገሩ እኛ እኮ ሽልማት የሚመስለን ቁሳቁስ ነው፡፡ ህሊና የሚያድስ እንደ ብርታት መርፌ የሚቆጠር ምስጋና እና አድናቆት ጥቅሙ አይገባንም፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› ስንባል ‹‹ምስጋና ኪስ አይገባም..›› ማለት ተዘውትሮ የሚሰማ እና ኪስ የሚገባ ብቻ ናፋቂነታችንን ያስመሰከረ ማንነታችን እየሆነ ነው፡፡ በምስጋና፣ በአድናቆት ህሊና መገንባትን እና ለህሊና መኖርን ጎበዝ እስኪ ከዛሬ እንጀምር፡፡ ህሊና ቢስ ሸቀጥ አምላኪ...በሸቀጥ የምንለካ፣ የምንመዘን.. ቁስ አንሁን፡፡ ሰው አድረጎ ፈጥሮናል እና ሰውን በሰውነቱ እንመዝን....

   አንዴ ይቅርታ ይደረግልኝ እና ቅድም እንባዬን አመጣው ካልኳችሁ ‹‹...ተናነቀኝ እንባ ተናነቀኝ..ተናነቀኝ እንባ ተናነቀኝ..›› ወደ ሚለው ዜማው ልመለስ፡፡ እዚህች ጋር ምስጢር ያላት ነገር የሰማሁ ስለመሰለኝ የእጅ ፍሬን ባይሆን የጆሮ ፍሬን ያዙና አስተውሏት፡፡
 
‹‹..የተለያየን ለት ልቤ አዝኖ ሊከፋ
ምወዳት ከልቤ ነበረ በተስፋ....›› እንደእኔ እንደኔ ይቺ ለሴት ነች ለሀገር? ለነገሩ ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ ሀገርም ሴትም እናት ናቸው፡፡ በማህጸናቸው ተሸክመው በጀርባቸው አዝለው...ከልብ የምንወዳት ሀገራችን ከልብ የምንወዳት እናታችን....ሁለቱም የተማስሎ ቁርኝታቸው ይበዛል፡፡ ስደት ሲወጣ እናቱን ሲሰናበት ያልከፋው ይኖር ይሆን? ሀገሩንስ? እኔ እናቴን ስሰናበታት የቤታችን ድንበር የሆነው በር ላይ፣ ሀገሬን ስሰናበት ድንደር የሆነው ወንዝ ድልድይ ላይ እንባዬን ጠብ አድርጌያለሁ፡፡ 

‹‹..ስትሰናበተኝ ላይቀር መተከዜ
ሰው አልሰማ እያልኩኝ በፍቅሯ መያዜ...
ይሄው ዛሬ ስትሄድ ሆዴ ባባ ተናነቀኝ..
ተናነቀኝ እንባ..ተናነቀኝ..›› በእሱ ዜማ ሂያጇ/ተሰናባቿ/ እሷ ሳትሆን ስሰማው ተገልብጦ ሀገሬን ተሰናባቹ እኔ ሆኜ እርፍ ነዋ! እኔ የማወራው የእኔን ነው የእናንተን እናንተ አስቡት፡፡ እንኳን የሰው የራሴንም የሚያስብ ጭንቅላት አጥቼ በጎረቤት/በየመን/ አዴንግ ማሽን ነው የምጠቀመው፡፡ እነዚህ ዘፋኞች ሲባሉ ነገረኞች ናቸው፡፡ አንድ ሰሞን ጎሳዬ እና ኤፍሬም ‹‹ኑ..ኑ..ተስብሰቡ›› እያሉ ምድረ ሀገሩን የረሳ ዲያስፖራ ሁላ አንቀዥቅዠው አስገቡት፡፡ የእኔም ልብ ብድግ ቢልም ፀሀዩ መንግስታችን ለመስተንግዶ ማረፊያ እንዳይቸግርህ ብሎ ኤርፖርት ጠብቆ ያንጠለጠልኳት ፌስታል ውስጥ ቦንብ ተገኘ ብሎ ‹‹አሸባሪ›› የሚል ታፔላ ለጥፎ ቃሊቲ ይልከኛል ብዬ ፈራሁና ቀረሁ እንጂ...ዋይ!! ተክልዬ..ወዲ ኮንካ ወዲ ዘይምኳን..አነስ ፈርሔ እንድዒ ንበር..
 
‹‹...ሰው ልኬ አታውራ ተው ሲለኝ ያኔ..
ሲነግረኝ ሰው ፈርቶ አኳኻናን አይቶ
ለእኔ እደማትሆነኝ አልሰማም አልኩና...›› ይሄ ደግሞ የመናገር እና የመፃፍ መብት ተሰጠ ብለን፣ እውነት መስሎን ስንቶች መከራ ያየንበትን...ብቻ ይሄ ቴዲ አፍሮ የመሳለሚያ አካባቢ ልጅ ነው መባሉን አልቀበልም ነበር፡፡ አባቱ ካሳሁን ግርማሞን፤ አክስቱ ገነትን፣ ጓደኛው ቴዎድሮስን..ያደገበት ቀስተደመና ት/ቤትን ባላውቅ ኖሮ የጎጃም ቆሎ ተማሪ ነው ብዬ እሟገት ነበር፡፡ የዋዛ ይመስጥረዋል እንዴ....የቅኔ እርጎ እየጋተን.... እይ! የኔ ነገር በዘፈኑ ተመስጨ ያሻኝን ስል ዝም ትሉኛላችሁ? 

    ፀሀፊው ብቻ ነው መብት ያለው? ከዚህ በላይ ያለው እኔን አይመለከትም፡፡ የፈጣሪዬ የአቶ ፀሀፊ ሀሳብ ነው፡፡ እኔ ቀጠልኩ....ስለላቡ ስለምኑ እያሰብኩ..እያሰብኩ ሳላጠናቅቅ ‹‹ተጫወት እንጂ ምነው ዝም አልክ?›› ሄለን ናት ያለችኝ፡፡ አየኋት አየችኝ፡፡ አይኗ አቀጣሪ ነገር ነው ሳልጠይቀው ጫዎታ መፈለጓን ቀድሞ አሳበቀልኝ፡፡ ቁልጭልጭ አለ፡፡ እንዴት አባቱ ያምራል አይኗ እባካችሁ? የአስራሁለት...ኤጭ ደርዘን ማለት እችል ነበር ለካ...የደርዘን ቻይናዎች አይን ቢደምር አይወዳደረውም፡፡ እንዴት እስከዛሬ ልብ ብዬ አላየሁትም? ለነገሩ እንዴት ይታያል፡፡ ይሄ እንደቀለበት መንገድ የተሟለለ ፊቷ በቡግር ተንቆጥቁጦ ኮረኮንች መንገድ ስለሚመስል የሰውን አይን ከሩቅ ይመልሳል፡፡ ምቀኛ ፊት አላት አይን የማያስገባ...ገበያ ከልክል ነው፡፡ ደግሞ እኮ ዘመናዊ ልሁን ባይ ነች፡፡ ከአለባበሷ ጀምሮ ስልጣኔ የፈነጠቀባት፣ አወቀች..ዘመነች የተባለች እንድትሆን ትፈልጋለች፡፡ ወርቅ ብትለብስ ዘምና ሙትት ብትል የሚያሳብቅ ገጠሬነት አላት፡፡ ጥርንቅ ባለ፣ ሞልቶ በፈሰሰ የገጠር ባህል እና ወግ ተኮትኩታ ማደጓ ያስታውቃል፡፡ ራሱ ውበት እንደሆነ ሳታውቅ ባላገርነትን ነውር አድረጋው እሷም ‹‹ባላገር›› ብላ ትሳደባለች፡፡ ዝንጀሮ የራስሽን መቀመጫ ሳታይ...ያስተርታል፡፡ ለእኔ ግን በባላገርነቱ የሚኮራ ወዳጄን ያስታውሰኛል፡፡ አይ! ሰማኸኝ በለው፡፡ እባካችሁ የምታገኙት ይህችን ፅሁፍ አሳዩት ላስፍራት፡፡

       ከምሰራባቸው ጋዜጣና መፅሔቶች መካከል አንዱ ለሆነው ዜጋ መፅሔት ጥበብ አምድ ቃለ-ምልልስ ልናደርግ እኔ እና ሰማኸኝ በራሱ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገናኝተናል፡፡ ሜዳውም ፈረሱም ያው ተብለን ግን ብቻችንን ወጋችንን መጠረቅ አልቻልንም፡፡ የአዲስ አልበም ስራ ስለነበረው ታዋቂው የባህል ዘፈኖች ግጥም ደራሲ ግሩም ኃይሌ፣ ሙዚቃ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ፣ ለሰማኸኝ ጥሩ ጥሩ ግጥሞችን የሰራለት ገጣሚ አባተ ማንደፍሮ፣ የሰማኸን ሚስት ገበያነሽ..ሌላ ማን ነበር? ሌላ ማን ነበር?..በቃ! ጊዜው ስለረዘመ ረሳሁት የረሳኋችሁ ይቅርታ አለን ብላችሁ እጅ አውጡ...ስሜ ሳይጠቀስ ብላችሁ ሆድ እንዳይብሳችሁ ፈጣሪ አይርሳችሁ፡፡ ብቻ ተሰባስበን አርጋን ይጠቀጠቃል፣ ዜማ ይዜማል፣ ግጥም ይታረማል..ጥሎብኝ ደግሞ የሰማኸኝን ነጎድጓዳማ ድምፅ እወደዋለሁ፡፡ የምንቅም ሰዎች እየቃምን ነው፡፡ ላብ እንጠርጋለን፣ ቡና እንጠጣለን፣ ሲጋራ እናጨሳለን፡፡ በመሀል ላይ የሰማኸኝ በለው ስልክ ደግሞ ደጋግሞ አንቃጨለ፡፡ አነሳው እና ‹‹ሀሎ!›› ሲል ጀመረ፡፡ሁላችንም በትኩረት እንድናዳምጥ በምልክት ነገረን፡፡ ያ- ወቅት ሰማኸኝ ምሽት ከሚሰራበት ሸዋጌጥ ሆቴል /ጭፈራ ቤት/ ወጥቶ የራሱን ጭፈራ ቤት ካሳንቺስ መናኽሪያ ጋር የከፈተበት ወቅት ነበር፡፡

       ታዲያ ረጅም ጊዜ የሰራበት ሸዋ ጌጥ ሆቴል ሌላ የባህል ሙዚቃ ተጫዋች ተክቶላቸው እንዲወጣ ስለለመኑት አሁን ስሙን ለክብሩ ስል የማልጠቅሰውን ታዋቂ ድምፃዊ ወስዶ ያነጋግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስሙን የማለጠቅሰው ድምፃዊ በአንድ ወቅት ቅ/ማርያም አካባቢ ቡና ቤት ውስጥ የራሱን ካሴት ከኪሱ አውጥቶ ይከፈትልኝ ብሎ ለብቻው ሲጨፍር ስላመሸ ዘገባ አድርጌው ነበር፡፡ በራሱ ሂሳብ እየጠጣ በነፃ ጭፈራ ቢያስኮመኩመንም በወራዳ ተግባሩ ተጣልተናል እና ስሙን የማልጠቅሰው በቀል እንዳይመስልብኝ ነው፡፡

     እንተደለመደው ምሽት ላይ ተቀናጅቶ ለማቅረብ ልምምድ ሊያደርጉ በጊዜ ተሰባሰቡ፡፡ ያ ለቤቱ አዲስ ድምፃዊ ሲንጠባረርባቸው ምን ሆነህ ነው ይልና ሙሉጌታ ቦርጋ ይጠይቀዋል፡፡ እኔ እኮ ታዋቂ ዘፋኝ ነኝ ብሎ የማይሆን ነገር ይናገራቸዋል፡፡ ከመሀላቸው አንዱ ‹‹ሂዲ አንተን ብሎ ታዋቂ የባላገር ዘፋኝ..›› ይለዋል ይህን ተባልኩ እኔ እዛ አልሰራም ለማለት ነበር ወደ ሰማኸኝ የደወለው፡፡ ይህን የሰማው ሰማኸኝ ታዲያ ምን አለበት ባለ-ሀገር ነን እኮ..እያለ አረጋግቶት ስልኩን ዘጋው፡፡ ሰማኸኝ ባለ-ሀገር!...ባለ-ሀገር!!!! እያለ ሲደጋግም ቆይቶ ባላገር /ባለ-ሀገር/ ማለት ስድብ ነው? እኔ ባላገር ባላገር..ሰሜ ባላገር ባላገር እያለ እያጠና በነበረበት ዜማ አንጎራጎረ፡፡ ደስ የሚል ቅላፄ አለው፡፡ ወዲያው ለአባተ ማንደፍሮ እና ለግሩም ሀይሌ እሰኪ ለዚህ ግጥም ስሩልኝ አለ፡፡ ተሰራ ለዝናው እርከን ከፍ ማለት ብቻ ሳይሆን ለእሱነቱ መታወቂያ ሆነው፡፡ ባላገርነት ውበት ነው....ለሰሜ ባላገር
   
     ወደ ወጌ ስመለስ ሄለን ባላገርነቷ ውበቷም ድም ግባቷም መሆኑን ባወቀች ምንኛ ደስ ይል ነበር? ለነገሩ ትራንዚት አድርጎ አዲስ አበባ ከረም ያለ ሁሉ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ ይላል፡፡ አዲስ አበባ ከተባለ ሁሉ የአራዳ ልጅ እየመሰላቸው ነው፡፡ ስንት ጀንፈል እና ጀዝባ እንዳለ ቢያውቁ አፋቸውን በቆጠቡ፡፡ ሄለንም አዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ ያለች ዘመዷ አገናኝታት ፓስፖርት አውጥታ ወደ የመን ስትመጣ ሀብታም ስትሆን ታይቷት ነበር፡፡ እንዲያውም ሀብታም ስትሆን በምናቧ ያቀናበረችውን ፊልም እንደ ራንቦ ክፍል ስድስት ድረስ በተኛች ቁጥር በህልሟ አጣጥማዋለች፡፡ በኮንትራት ሁለት አመት ከሰራችበት ከወጣች ስድስት አመት አስቆጥራለች፡፡ በአጠቃላይ ስምንት አመቷ ነው፡፡ በያን ሰሞን ቀኑን እረሳሁት እንጂ ቤቷ እንድቅም ጋብዛኝ ሳለ ብዙ አውግታኛለች፡፡ አስታውሳለሁ ኮንትራት ቤት በገባች በ15 ቀኑ አሰሪዋ አስገድዶ ከደፈራት በኋላ በተደጋጋሚ ያስተኛት ነበር፡፡ በመሀል ፀንሳ ስለነበር አስወርዳለች፡፡ እድለኛ ነች፡፡ ስንቷ ስታረግዝ ሆዷ ሳይገፋ ተጠርዛ ወደ ሀገር ቤት ገብታለች? ስንቷ አስወርዳለሁ ብላ ሞታለች? ስንቶቹስ እዚህ አባት የሌለው ልጅ ይዘው ያሳድጋሉ? ለነገሩ ማህጸናቸውን ያለምልመውና ሀበሻ ለሀበሻ የተጋቡት ሁሉ የህዝብ ቁጥርን ከፍ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ይሁን መዝናኛቸውን አልጋቸው ላይ አድርገው ልጅ በልጅ ናቸው፡፡

     ‹‹ሁሌም እንደዚህ ነህ?››  ምን አይነቷ ናት? ሄለን አሁንም አቋረጠችኝ፡፡ እነዚህ እያሉ ሰው በነፃነት ሀሳቡን ማንሸራሸር እንዴት ይችላል? አቋራጭ የበዛበት ዘመን፡፡

     ‹‹እንዴት?›› አፈጠጥኩባት፡፡

      ‹‹ስትቅም ዝምታ ታበዛለህ?››

     ‹‹ታዲያ ዝም ብዬ ልዘላብድ?››

     ‹‹ምን እያሰብክ ነው?››                    
  
     ‹‹ባክሽ ምን የሚታሰብ ይጠፋል? አንድ ቀን ፀሀፊ ለመሆን አስባለሁ፡፡ ልፅፍ የምችለውን አስባለሁ፡፡ አወጣለሁ፤ አወርዳለሁ፡፡››
      
      ከሄለን አጠገብ የተቀመጠችው ሰናይት ‹‹ፀሀፊ ለመሆን ብዙ ማሰብ ግድ ነው እንዴ?›› እዚህ ቤት ውስጥ መገኘቷ ያስገረመኝ ሴት ነች፡፡ ከመስከረም ጋር በአንዱ ተጣልተው ነበር፡፡ ሰናይት አግብቶ መፍረታት ሪኮርድ ሳይኖራት አይርም፡፡ ትዳርና አዳር ተምታቶባታል፡፡  በሰባት አመት ውስጥ 5 ጊዜ አግብታለች፡፡ አጠገቧ የተቀመጠው ኩኩሻ እዚህ ሀገር ከመጣ አራት ረመዳን ቆጥሯል፡፡ እኛ ሀገር ቢሆን አራት ደመራ ለኩሷል ነበር የሚባለው፡፡ እዚህ ደመራ ስለሌለ በአመት አንዴ በሚመጣው ረመዳን ነው የሚቆጠረው፡፡

    ኩኩሻን አልረሳለትም አንድ ቀን ነጭ ቅፈላ ቀፈለኝ፡፡ ድርቅ ያለ ቅፈላ..እኔ ደግሞ አውቄ ተቀፈልኩለት፡፡ጫት ገዝቼለት አብረን ቁጭ ብለን ስንቆረጣጥም ብዙ አወጋኝ፡፡ ‹‹ከልጅነቱ ጀምሮ አባቱ የሚሰሩበት ቦታ እየሄደ አብሯቸው ቀለም እንደሚቀባ ነገረኝ፡፡ ኢን አዘር ሀንድ.... በሞቴ እንዳታሳበፍሩኝ አንዳንዴ ምናለ ጉራማይሌ ባወራ?..ነውርነት የለው እንደሞባይል ካርድ አይጠይቅ፡፡ አይከፈልበት...በቃ ይቺን ስለማውቃት ተጠቀምኳት፡፡ የካበተ ልምድ ስላለው አሁን በጥሩ ክፍያ በዚህ ሞያ እንደሚሰራ ሲነግነኝ ከእኔ እጥፍ እያገነ ለምኖ መቃሙ ገረመኝ፡፡ ለነገሩ እዚሀ ሀገር መለማመጥና የሰው ኪስ..ኪስ ማየት የሁሉ ባህሪ እንዲሆን በአዋጅ የታዘዘ ነው የሚመስለው፡፡ ብቻ ጥሩ ይለብሳለ፤ አምሮበታል፡፡ ፊቱ ግን ቡግር ጥሎት በሄደው ጥቁር ጥቁር ነጠብጣብ ተዥጎርጉሯል፡፡ እንዲያውም አፍንጫው ላይ ካለው ማዲያት ጋር ሲታይ የቀለም መቀባት ችሎታውን ተጠቅሞ አብስትራክት ለመስራት ያዥጎረጎረው ይመስላል፡፡ ቡሬ አልኩት በሆዴ...

                                  ሰላም፣ ሻሎም፣