Thursday, April 18, 2013

“ማሪያም ነኝ” ባዩዋ ተፈረደባት

“ማሪያም ነኝ” ባዩዋ ተፈረደባት

በአሸናፊ ደምሴ
የፌዴራሉ አቃቤ ህግ የማይገባትን ጥቅም ለማግኘት
በማሰብ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በመንቀሳቀስ
ሰዎችን በማታለል “እኔ ማርያም ነኝ፤ እንደኢየሱስም
በጅራፍ ተገርፌያለሁ፤ ከሞትም ተነስቻለሁ፤
የወለድኳቸውንም ልጆች ያገኘሁት በመንፈስ ነው”
ስትልና የዓለም ፍፃሜ ደርሷል በሚል የሰዎችን የግል
ሀብት ለራሷ ስታደርግ ደርሼባታለሁ ሲል ክስ
የመሰርተባት የ34 ዓመቷ ትዕግስት ብርሃኑ ወ/
ጊዮርጊስ፤ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል
ችሎት ፊት ቀርባ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ በ2 ዓመት
ከ4 ወራት ፅኑ እስራትና በአንድ ሺ ብር የገንዘብ
መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ባሳለፍነው ሳምንት ወሰነ።


እንደአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ከሆነ ግለሰቧ በአራት የተለያዩ ክሶች የተወነጀለች ሲሆን፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት
“ለሰው ህይወት ማለፍ ሳቢያ ነች” ሲል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ ያልተሟላ ነው ሲል ውድቅ ሲያደርገው በተቀሩት
ሶስት ክሶች ግን ጥፋተኛ ነች ብሎ እንድትከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር።
ተከሳሿ ጥፋተኛ የተባለችበት አንደኛ ክስ በየካቲትና በመጋቢት ወራት ውስጥ 1999 ዓ.ም የማይገባትን ጥቅም

ለማግኘት አስባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 21 ልዩ ቦታው ኪዳነምህረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ300 በላይ
ሰዎችን በመሰብሰብ “እኔ ማርያም ነኝ፤ እንደኢየሱስም በጅራፍ ተገርፌ፤ ከሞትም ተነስቼያለሁ” የሚል የሀሰት ወሬ
በመንዛትና የዓለም ፍፃሜ ደርሷል ንብረት አያስፈልግም በሚል ያላችሁን ንብረት አምጡ ስትል ከተለያዩ የግል
ተበዳዮች ጥሬ ገንዘብና ወርቅ የተቀበለች ሲሆን፤ በአጠቃላይም 40ሺ ብር ለግል ጥቅሟ አውላለች ሲል በክስ መዝገቡ
ያስረዳል።
እንደአቃቤ ህግ ቀጣይ ክስ ደግሞ ተከሳሿ በሰኔ 1 ቀን 1999 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16 ልዩ ቦታው
ላምበረት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 50 የሚደርሱ ሰዎችን በመያዝ ወደደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በመጓዝ ወንጭ
ገዳም ተብሎ ወደሚጠራው መንፈሳዊ ቦታ በመውሰድ በፆምና ፀሎት ሰበብ አብረዋት የነበሩት ሰዎች ለአምስት ቀናት
ምግብ እንዳይበሉ በማድረግ እንዲዳከሙና ለከፋ ጉዳት እንዲዳረጉ አድርጋለች ሲል በክሱ ያትታል።
በሌላም በኩል ግለሰቧ በጥር 24 ቀን 2003 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11 ልዩ ቦታው ተክለሃይማኖት ቤተ-
ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ ወደ 20 የሚጠጉ ህፃናት ልጆችና ሴት ተከታዮቿን በመያዝ፣ “እኔ ማርያም ነኝ፤ ልጆቼን
የወለድኳቸውም በመንፈስ ነው እንጂ ከወንድ ጋር ተኝቼ አይደለም” በማለትና ተከታዮቿም እርሷ ማርያም ነች።
ሞታም ተነስታለች እንዲሁም 40 ቀን ያለምግብ ትፆማለች በማለት ሀሰተኛ ወሬዎችን እንዲነዙ በማድረግ
ስታስተምር እንደነበር ከፖሊስ የምርመራ መዝገብ ደርሶኛል ያለው ዐቃቤ ሕግ፤ በዚህም ምክንያት በቤተ-ክርስቲያኗ
ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ምዕመናን “ ሀሰት ነገር አትናገሪ” ሲሉ በመቃወማቸው ወደሁከት ውስጥ እንዲገቡ
ያደረገች በመሆኑ በፈፀመችው የሀሰት ወሬዎችን በማውራትና ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል ተከሳለች ይላል።
ጉዳዩን ሲመረምረው የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል ችሎትም የዐቃቤ ሕግን ክስ ተከሳሿ
ማስተባበል ባለመቻሏ ጥፋተኛ ሆና አግኝቻታለሁ ሲል፤ መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም በ2 ዓመት ከ4 ወር ፅኑ
እስራትና በ1000 ብር እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል።¾
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ