Tuesday, July 31, 2012

ጥቁሯ ቦርሳዬ ክፍል 7
‹‹…ለአራጅነቱ ሪፈር ወደ ቄራ ››
ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት

ስላም ጤና ፍቅር ለእናንተ ይሁን! አሜን አትሉም፡፡ የእዚህ ክፍል ንዑስ መልዕክት ወይም ጥቅስ..‹‹በፍቅር፣ በመረዳዳት፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ በጋር ለመኖር በግልጽ እንነጋገር እንወያይ..›› የሚል ነው፡፡ ፍቅር እንዲያስተሳስረን በግልጽ መወያየት ግድ ይላል፡፡ በፍቅር የመኖርን ያህል ምን ነገር ያስደስታል? ታዲያ በፍቅር ስም ከሚነግዱ ስሙን ታዛ ከለላ አድርገው ከሚሸቅጡ አጭርባሪዎች፣ የፍቅር ሸቃጮች ራሳችሁን ጠብቁ…በየዋህነት በፍቅር ስም ራሳችሁን አትገብሩ፡፡ በየዋህነት በአስትሮሎጂ ምክንያት እንደጠፋው ድንግል እንዳትሆኑ….ኪኪኪኪ… ሳስበው ያ-ትዝታ ያስቀኛል፡፡ በእናንተ አትሮሎጂ ድንግሌን አጣሁ ብላ የመጣችው ልጅ ታሪክ ዛሬም ድረስ ስለ የዋሆች ሳስብ ጣፋጭ ትዝታዬ ነው፡፡

ራህዋ የምትባል ልጅ ናት አንድ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቢሮ ውስጥ በእንግድነት ጓደኛዬ ጋር ቁጭ ብዬ መጣች፡፡ ‹‹..በእናንተ አስትሮሎጂ ጉድ ሆንኩ ድንግሌን አጣሁ..›› ስትል ጥርሴ መጣብኝና ሳኩኝ፡፡ ሳቄ ሳያሸማቅቃት ቀጠለች፡፡ እዛ ዝግጅት ክፍል ስራተኛ ባልሆንም በእንግድነት ቁጭ ብዬ ይሄን ገጠመኝ ላጋጠመኝ አምላክ ምስጋና አቅርቤ ለመስማት የጆሮዬን ፍሪኩዌንሲ አስተካከልኩ፡፡ የሰማሁትን ሪከርድ ማድረጊያ ቅንጭላቴን ከፍቼ…ምን አለፋችሁ ብቻ ሬዲ የሚለው ላይ ክሊክ አደረኩና….ጀመረች፡፡ እኔም በራሴ አጻጻፍ ጀመርኩት…….

ልጅት ቀጠለች…ማን እንዳይሉኝ ስለ ራህዋ ነው የማወራው፡፡ አስትሮሎጂ አፍቃሪ ናት፡፡ አስትሮሎጂ አሳዳጅ ናት፡፡ የሚለው ሁሉ እውነት ይመስላታል፡፡ የአስትሮኖመሮች ግምት እና ቀመሩ በስሌት የሚመጣ መሆኑን ማን በነገራት፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ አስትሮኖመሮች የጻፉትን መተርጎም ብቻ ሳይሆን ጫቶኖመሮችም ይጽፉታል፡፡ እነዚህ ደግሞ ምንድን ናቸው ካላችሁ ጫት ላይ ቁጭ ብለው ደስ ያላቸውን ገምተው የሚጽፉ ናቸው፡፡ የሚገርመው ገጠመልን፣ ሆነልን የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ የጋዜጣውን ርዕስ የማልጠቅሰው ጋዜጣችንን አብጠለጠለ ብለው የኩርፊያ በትራቸውን እንደ ስኩድ ሚሳይል በስደት ያለሁበት ሀገር ድረስ እንዳያስወነጭፉብኝ ነው፡፡ እዚህ ጋር በፍቅር እንኑር እያልኩ ኩርፊያ ራሴ ላይ ማምጣት የለብኝም፡፡ ኩርፊያ ፍቅርን የሚያጠፋ ረመጥ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ስለዚህ ራሴ ላይ ኩርፊያ አልጋብዝም፡፡ ጋዜጣው ግን ሞቶ ነፍስ ይማር እየተባለ በነበር ሲጠራ ከርሟል፡፡ አሁን ግን አልጠራውም፡፡ ነፍስ ይማርም አልልም ዳግም ምጽዓቱን ያቅርብለት እንጂ..፡፡

ስለ አስትሮሎጂ ሳወራ ትዝ የሚለኝ ብዙ ነገር አለ፡፡ ከሞያ ጓደኞቼ ውስጥ ደግሞ በተለያየ ገጠመኝ ሰለሞን ሙሉ ታፈስ እና ከበደ ደበሌ ሮቢ ትዝ አሉኝ፡፡ የት ይሆን ያላችሁት? ራህዋ እና አስትሮሎጂ ቁርኝታቸው መቼ እንደሚጀምር አላውቅም፡፡ ብቻ ጋዜጣ ስታገኝ ቶሎ፣ ገልብጣ ሊብራ የሚለው ስር የሰፈረውን ታያለች፡፡ ጥሩ ከሆነ ፈግጋ ሳቅ ሳቅ ሲላት፣ መጥፎ ከሆነ ደምና በኩርፊያ ተጠፍንጋ…ትውላለች፡፡ በቃ! የራህዋ የባህሪ እና የፊቷ ሁኔታ እንደ አየር ሁኔታ በሚትሪዎሎጂ ሳይሆን በአስትሮሎጂ የሚወሰን ነው፡፡

አንድ ቅዳሜ ጠዋት ፈገግ ኮስትር የሚያደርግ ነገር ገጠማት፡፡ እሷ ኮኮብ ስር ‹‹..የፍቅር ሰው የሆኑት ሊብራዎች በእዚህ ሳምንት የፍቅር ህይወታቸው ላይ የሚጋረጥ መሰናክል አለ፡፡ ብልጥ ከሆኑ የሚያልፉበት መንገድም አለ፡፡ ከፍቅረኛዎ የሚቀርብልዎትን ሀሳብ በእሺታ ያሳልፉት እቃወማለሁ ቢሉ የፍቅር ህይወትዎን ያበላሻሉ…›› ጭንቅ ጥብ ነገር ተፈጠረ፡፡ የሀሳብ ጥንግ ድርብ እሷ ላይ ሰፈረ፡፡ ፍቅረኛዋ ሁሌም እየጠየቃት የሚጣሉት ህብረ አንሶላ እንፍጠር ነው፤ ሴትነትሽን ልፈትሸው ነው፡፡ በሌላ አባባል ከልጃገረድነት ወደ ሙሉ ሴትነት ልለውጥሽ እያላት ነው፡፡ በአራዳ ልጆች አባባል እንደ ልብሽ እንድትሸኚ ላርግሽ እያላት ነው፡፡ ቆይ ግን ያልገባኝ ይሄ ነገር እንደልብ አያሸናም እንዴ? እውነት ከሆነ የሆኑት ተጨንቀዋላ?...

እሷ ደግሞ ጠብቃ ያቆየችውን ክብር መጠበቅ ነው ፍላጎቷ፡፡ ለባህልና ቅርስ ተንከባካቢ ኮሚቴ ትስጠው፣ ለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ታውርሰው፣ ለጋብቻዋ ገፀ- በረከት ታድርገው ሁሉም የራሷ ምርጫ ነው፡፡

አልሰጥም አትል ነገር ፍቅረኛዋን መለየት አትፈልግም፡፡ ትወደዋለች፡፡ እሱን ከምታጣ ‹‹…ክብሬን ሳትል ማዕረጌን አቤት ብቻ ነው ሲጣሩ እቴጌ…››የሚለውን ማቀንቀን ትመርጣለች፡፡ አጋጣሚ ነገር ሆነና እሱም ከዩነቨርስቲ ትምህርቱ እሷም ከስራዋ እረፍት የሚሆኑበት እና ዘውትር አብረው የሚያሳልፉት እሁድ ላይ ጠየቃት፡፡ እንዴት እንቢ ትበል? ታወሳት አስትሮሎጂው፡፡ ገጥሞላት የማያውቀው አስትሮሎጂ ገጥሞባት እጅ ሰጠች፡፡ ምን እጅ ብቻ እግርም ሰጠች፡፡ ሆነ….ጫጉላው አብቧል አልተባለ፣ ብራምባር ሰበረልሽ የለ…የቤርጎ አንሶላ አቅልተው የሳሙና ከፍለው ወጡ፡፡

በቀጣዩ ቅዳሜ እዛው ጋዜጣ ላይ ‹‹..ሰሞኑን በሚገጥሞት ነገር አይደናገጡ፡፡ ባለፈው ሳምንት በሰሩት ነገርም አይፀፀቱ በዚህ ሳምንት ከፍቅረኛዎ ደስ የማይል ዜና ይሰማሉ…›› እያለ ይወርዳል፡፡አልቀረም እሁድ እሁድ የሚገናኙበት ቦታ የለም፡፡ ጭንቅ ጥብ ሆነ፣ ተስፋ መቁረጥ የተከመረበት ፍርሃት ነገሰባት፡፡ ፍለጋው አያልቅም የሚለውን እያዜመች ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ ተገኘ ልጁ ተገኘ የሚለውን ለልቧ አዚማ ‹‹..ምነው? ሆዴ ባልተለመደ ሁኔታ…›› ብትል እንደማይፈልጋት ነገሯት ቁጭ፡፡ እሷ ስትናገር ምነው ስለው….ነው ያለችው ባልተለመደ ሁኔታ የሚለውን በሀሳብ ስስላት የጨመርኩት ነው፡፡ ጠብቃ ያቆየችውን በአስትሮሎጂ ተማርካ አስረከበች፡፡ ከእንዲህ አይነት ገጠመኝ ይሰውራችሁ…..፡፡

የየዋሆቹን ትቼ ወደ የመን ሀበሾች ስመለስ ባለፈው ካሰፈርኩት ታሪክ ስር ቅድስት ተክሌ የተባለች ልጅ ‹‹..ለሁላችንም የልብ ድንግልና ይስጠን::…›› ብላለች፡፡ በትልቁ አሜን ከተገኘስ የልብ ድንግልና ይሰጠኝ ብያለሁ፡፡ እናንተም ለራሳችሁ አሜን በሉ፡፡ ሁለት ይሁኑ ሶስት ሰዎች የጭን ድንግልና ከሌለ እንዴት የልብ ድንግልና ይኖራል፣ የጭን ድንግልና ይበልጣል ያሉ አሉ፡፡ ሁሉም በራሱ አመለካከት ልክ ነው፡፡ ግን አስተውሎ መራመድን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ከልብ ይልቅ የጭን ድንግልና የመረጠውን ደም ለማፍሰስ አምሮቱ፣ ለአራጅነቱ ሪፈር ወደ ቄራ ቢላክ ያዋጣዋል፡፡ ሄለን የተባለች የመን ያለች ስደተኛ ‹‹..ባሏን ስለገደለችው ሴት ለምን አትጽፍም ብላኝ ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ዜና ሰርቼው ነበር፡፡ ልመለስበት ወደድኩ፡፡

የመን በተለይ ሰነዓ ጆሮ እንስጥ እንጂ የማይሰማ የለም፡፡ እንኳን ሰዉ ንፋሱ ወሬ ያመጣል፡፡ አሁን የምናገረው እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ታዲያ ሚስቶቻችን ቀን ቀን የአረብ ማታ ማታ የእኛ የሚለውን የአንዳንድ ባሎች አባባል አስታውሱልኝ፡፡ አሚናት ትባላለች ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ቆንጆ ባትሆንም አስጠሊታ አይደለችም፡፡ አስጠሊታው ውስጣችን እንዳይሆን እንጂ ውጫችን እንዳይሆን መጠንቀቅ የለብንም፡፡ ውበት ከውስጥ ነው፡፡

ከያሲን ጋር አብረው መኖር ከጀመሩ አምስት ዝርክርክ አመታትን አሳልፈዋል፡፡ በጭቅጭቅ፣ በቅናት..በኩርፊያ የታጀቡ 5 አመታት፡፡ ተነጋግሮ መረዳዳት፣ መተማመን ባለመቻላቸው የቅናት ዛር አዶከብሬውን ይዞ ጎጇቸው ላይ ይጨፍር ጀመር፡፡ ቅናት እንዲያጠፋ ይሁን ቅናት እንዲያፋፍም ልጅ ወለዱ፡፡ ባልተረጋጋ የትዳር ህይወት ላይ ያሉ ሰዎች መውለድን ባያስቡት እንዴት ደስ ይላል? ወልደው ለእነሱ ያልጣመቸውን ህይወት በቆርፋዳ መልኩ ሊያጋፍጡት መውለድ ብልግና ነው፡፡ ከእደዚህ አይነት ቤተሰብ ተወልደው ለጭንቅ ጥብ የተዳረጉ ስንት ዜጎቻችን ይሆኑ?

ገባ ወጣ../ሌላ ነገር አላልኩም/ አመሸህ፣የት ነበርክ?…አቤት ቅናት ያበቀለ ትዳር እንኳን ልጅ ሊወለድበት ጎረቤትም አይኖርበት፡፡ አሚናት የፈሲታ ተቆጢታ እንደሚሉት አይነት ባሏ በወጣ በገባ ቁጥር ትነዘንዘው ጀመረች፡፡

ከዕለታት አንዱ በተረገመ ፍጻሜ እለት አገር አማን ብሎ ልጁን ታቅፎ የተኛ ባለቤቷን እና የዘጠኝ ወር ህፃን ልጇን ቁርስ ትሰራላቸዋለች፡፡ የሚበሉት ቁርስ ሳይሆን ሞትን የሚያጣጥሙበት ቁርስ፡፡ ዘይት አፍልታ ደፋችባቸው፡፡ ተሰውራ ከረመች፡፡ ልጇም ሆነ ባሏ ያሲን በህክምና ቢረዱም ባሏ ከፍተኛ አደጋ የደረሰበት በመሆኑ አልተረፈም፡፡ ያሲን ጁሜሪ የሚባለው ሆስፒታል ገብቶ ለሁለት ቀን እርዳታ ቢደረግለትም ራስ ቅሉ ላይ በደረሰው ከፍተኛ አደጋ ምክንያት ሊተርፍ አልቻለም፣ ሞተ፡፡ ትንሽ ልጃቸው አሁን ከፍተኛ ህክምና ተደርጎለት በአንድ በጎ ምስኪን ሴት እናትነት እያደገ ነው፡፡ ፊቱን ራስ ቅሉ ብሎም ጀርባው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ህጻን ገና ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል እየተባለ ነው፡፡ ደብዛዛ ቢሆንም ከላይ ያለውን ፎቶ ይመልከቱ፡፡ በወቅቱ ፊቱ በመጎዳቱ ምክንያት ፕላስቲክ ሰርጅሪ መደረግ እንዳለበት የህክምና ባለሞያው ገልፀው በዛው ቀረ፡፡ ዛሬ ግን ከፍተኛ ህክምና ማግኘት ቀርቶ ለነፍስ ያሉ አሳዳጊው የሚበላውንም እየተቸገሩ ነው የሚያሳድጎት፡፡

ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ፈጽማ የተሰወረችው አሚናት ከወር በኋላ ተያዘች፡፡ ዘይት አፍልታ የደፋችበትን ምክንያት ስትናገር ‹‹አናዶኝ ነው እኔ ተቃጠልኩ አልቻልኩም፡፡ ሌላ ሴት ጋር እየሄደ አስቸገረኝ፡፡ አልፎ ተርፎ እጅ ከፍንጅ ያዝኩት..ይህን ድርጊት የፈጸምኩት ተናድጄ ነው..››አለች፡፡ ይሄኛው አዲስ ግኝት ሳይሆን አይቀርም ለንዴት ማብረጃ ዘይት አፍልቶ…ሆሆይይይ…የጉራጌ ብስኩት አደረገችው እንዴ በዘይት የምትጠብሰው? ደግሞ እኮ ሰነዓ የሰው ሚስት ይዞ፣ የሰው ባል ይዞ ተኝቶ መገኘት አዲስ እና የሚያሳፍር አይደለም፡፡ አንዳንድ ገገማ ደግሞ አለላችሁ ፍጥጥ… ምንም አላረግንም፡፡ አስቡ እስኪ ልብስ አውልቀው በር ዘግተው እየተያዙ ምንም አላረግንም…ታዲያ ለፀሎት ነው በር የዘጉት? በር መዝጋቱ ለጸሎት ይሁን ልብስ ማውለቁስ? ለምንድን ነው ለምርመራ!. ኪኪኪከኪ…

ትልቁ ችግር እኛ ንጹህ ነን ወይ የሚለውን ሳይሆን ሁሉም የሰው ነው የሚያብጠለጥለው፡፡ አሚናትም ይህን አስባ ራሷን ብትፈትሽ ለዚህ አይነት ጭካኔ ባልተዳረገች፡፡ እሷስ ለትዳሯ ታማኝ ነች ወይ? ብለን ብናስብ ሊከብድ ይችላል፡፡
ይህን ቃል አጥብቀን እንደያዝን ወደ ታሪካችን እንመለስ፡፡ የሚያሳዝነው እና አሳዛኙ ድርጊት የተፈጸመው ያለ ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ያሲን እሷ ያለችውን አላረገም ማለቴ አይደለም፡፡ ማድረጉንም አላውቅም፡፡ ግን አደጋውን አድርሳ ለአንድ ወር ያህል ራሷን ደብቃ ከረመች፡፡ ጠፍታ የተሰወረችበት ቦታ ድረስ መርቶ ያሲያዛት ከበፊት ጀምሮ በውሽምነት ይዛው የነበረ የመናዊ መሆኑ ነው ደግሞ ዝንጀሮ የራሷን መቀመጫ ሳታይ የሚያስብለው፡፡ ለዚህም ነው ያለ ምክንያት ያልኩት፡፡ ራሷ እየተሰረቀች እሱ አደረገ ብሎ መንጨርጨር….

አዲስ ሲም ካርድ ገዝታ ከመናዊው የባል ተደራቢ ጋር ብቻ ለመገናኘት አስባ ትደውልለታለች፡፡ በድርጊቷ ተናዶ ስለነበር የት እንዳለች ጠይቆ ሲያበቃ እንዲገናኙ እንደምትፈልግ ስትነግረው ቀጠራት፡፡ ቦታው ድረስ ፖሊስ ይዞ በመሄድ አስያዛት፡፡ በባሏ ላይ የሸረሞጠች ሴት በውሽሟ ላይ..እንደሚባለው ባሏን የገደለች ነግ ለእሱም የማትመለስ መሆኑን በየመኒኛ አስልቶት ይሆን ያስያዛት? ወይስ በስርቆት የሰራውን ሀጢያት በዚህ አካክሶ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ሊል ?

ሰው አብሮ የበላው፣ አብሮ የጠጣውን ትዳሬ አካሌ፣ አምሳሌ ያለው ላይ ይህን መሳይ አሰቃቂ ድርጊት ለመፈጸም እንዴት ይነሳል? ያውም እሷ ያልጠበቀቸውን እምነት አጎደለ ብሎ…ሰማንያ ሲያደርጉ እሱ በአክሲዮን ግዢ መልክ /ወይም ጨረታ/ ሊጠቀም እሷ በሞኖፖል ልትጠቀልለው ነው የተስማሙት?

እሺ ባሏ አጥፍቶ ሊሆንም ላይሆንም ቢችል እንኳን የዘጠኝ ወር ህፃን አብሮ እንዲቃጠል የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? አልተገለፀም፡፡ መጨካከን ካልሆነ እናት የፈለገ ብትናደድ ለልጇ ብላ አትተውም? <<..ጎሽ ለልጇ ስትል…›› ብለው የተረቱት እናቶች ይህን እንዴት ይሰሙት ይሆን? ወይስ ‹‹ጎሽ ለባሏ ብላ ልጇን ቀቀለች..›› ብለው ይቀይሩታል፡፡

ፍ/ቤት የወሰነባትን በሚቀጥለው አስነብባለሁ፡፡ እርሶ ቢሆኑ ምን ይፈርዱባት ነበር?
አንድ ጣትህን ወደ ሰው ስትቀስር ሶስቱ የታጠፉት ወደ አንተ ማመልከታቸውን አትርሳ የሚለውን አስበን እንሰነባበት፡፡
በፍቅር እንሰንብት