Saturday, May 4, 2013

ታዳጊዋን የደፈሩ አዛውንት 11 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

ታዳጊዋን የደፈሩ አዛውንት 11 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ግራባ ፊላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣የ14 ዓመቷን ታዳጊ አስገድደው የደፈሩ የ60 ዓመት አዛውንት፣ የ11 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡ የታዳጊዋ ወላጆች በእርሻ ሥራ ላይ የቀጠሯቸው አዛውንት፣ ወሲባዊ ጥቃቱን የፈፀሙት ቤተሰቧ‹‹ቤት ጠብቂ›› ብለው ወደ ገበያ መሄዳቸውን አረጋግጠው እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል። ታዳጊዋ የደረሰባትን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ወዲያው ለቤተሰቦቿ አልተናገረችም፡፡
ወራት እየተቆጠሩ ሲሄዱ ግን ሰውነትዋ እየወፋፈረ፤ ሆድዋ እየገፋ መሄዱን የተረዱ ቤተሰቦችዋ ጥርጣሬ አድሮባቸው ጠየቋት፡፡ ታዳጊዋ የደረሰባትን ተናገረች፡፡ ያኔ የአምስት ወር እርጉዝ ነበረች። ቤተሰቦችዋ ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከቱና ክስ ተመሠረተ፡፡ ከትናንት በስቲያ በዱግዳ ወረዳ የዋለው ችሎት፤ተከሳሹ ድርጊቱን መፈፀማቸውን በማረጋገጡ የ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንደፈረደባቸው፤ የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር አስቻለው አለሙ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡


ከአዲስ  አድማስ ጋዜጣ የተወሰደ