Friday, July 27, 2012

Ethiopian refugee in Yemen



ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አለ ሌኒን፡፡
ጥቁሯ ቦርሳዬ ክፍል 5
ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት


የሰሞኑን ነገር ዝም ነው፡፡ ጉደ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አለ ሌኒን፡፡ ምን አሳቃችሁ ተሳሳትኩ እንዴ? ማን ነበር ያለው? ኤንግልስ?...ሼክስፔር? ሼክስፔር እንኳን አይልም፡፡ ጉድ የሚባለውን ሁሉ ጽፎታል፡፡ ታዲያ ማነው ይህን ያለው? ለነገሩ በደርግ ጊዜ ተረቱን ሁሉ ቀይረው አለ ሌኒን፣ አለ ማርክስ...የሚሉ ቀንደኛ ኢሠፓ ጎረቤታችን ነበሩን እና ያኔ የሰማሁትን አስታውሼ ነው መሰለኝ፡፡ የአባባሎችን ጉዳይ አንስተን ስንነጋገር አንድ ጊዜ ‹‹ወይ መዓልቲ..›› አለች ማዶና አለኝ አንዱ፡፡ ግራ ገባኝና ትግሪኛ እና ማዶናን ምን አገናኛቸው ብዬ አጥብቄ ጠየኩት፡፡ ማዶና ጣሊያናዊ ናት፤ ,ጣሊያን ኤርትራን በቅኝ ግዛት ገዝታለች...እያለ ቀመሩን በቅኝ ግዛት ስር አሳልፎ አባባላችንንም ቅኝ ተገዢ አደረገው፡፡

ጉድ ሳይሰማ...ወዳልኩበት ጉዳይ ልመለስ እና...ሙስና ሊያሰሩኝ!...ሆሆይ!...አንድዋ ታክሲ ላይ ወሬ ጀመረችኝ፡፡ ምን ነበር ያለችኝ? አዎ!.... መጀመሪያ ‹‹ሰላም! ደህና ዋልክ?›› ነበር ያለችኝ፡፡..ቁመትሽ ሎጋ ነው የእኔ አለም ሰንደቅ ያሰቅላል የሚባልላት አይነት ነች አረ ከዛም አልፎ በቃ!..ከርዝመቷ የተነሳ ባሏ ዛፍ ላይ ሲወጣ እንደሚያድር ነው ያሰብኩት፡፡ በፈገግታ አጥለቀለቀችኝ፡፡ እኔም የፈገግታ ሻወሬን ወስጄ ለሰላምታዋ ምላሽ ‹‹ሰላም!..እግዚአብሄር ይመስገን..›› ብያት በመነቸከው ጥርሴ...አገጠጥኩ፡፡ መሳቅና እኔማ ከተያየን ስንት ጊዜው ሰው ሲስቅ እንጂ እኔ ስቄ አልተገናኘንም፡፡ ካገኛችሁት ሰላም በሉልኝ፡፡

‹‹ሀበሻ ነህ?›› አስከተለችው፡፡ አሁን በእሷ ቤት ጫዎታ ማሳመሯ ነው....አንዳንዱ ሰው የሚያውራውን አያውቅም? ስል በውስጤ አንጎዳጎድኩ፡፡ ንዴት የሚያመነጨው እጢዬ ወዲያው ኦቨርታይም ሰራና በሰውነቴ ላይ አሰራጨው፡፡ በቃ ተናደድኩ፣ ቦግ አልኩ፣ ተንጨረጨርኩ፡፡ አስቡት ሰላምታ የተለዋወጥነው በአማርኛ...ታዲያ እኔስ ማነኝ ‹‹እቱ የአማርኛ ሶፍትዌር ተገጥሞልኝ ይመስላል በአማርኛ ያወራሁሽ?›› የበለጠ በፈገግታ አጥለቀለቀችኝ፡፡ የፈገግታ ማስቀመጫ ቁጠባ ባንክ ቢኖር ባስቀምጠው ለስንት ደመናማ ቀን የሚሆነውን አርከፈከፈችው፡፡ ንዴቴን የፈገግታ ጎርፍ ጠርጎት ሄደ፡፡ በሰዓቱ በፈገግታ ጠግቤ ራቴን ሁሉ የማልበላ መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ተገላብጦ ጨጓራዬ በደስታ ፈጭቶት ይሁን እንደ ርችት ተኩሶት ቶሎ እንደራበኝ አስታውሳለሁ፡፡

አስቂኝ ነህ ለካ እንደምትፅፈው ነው የምትናገረው፡፡ ‹‹..አመጣችው..›› አለና ልቤ አልጎመጎመ፡፡ ታዲያ ከነፅሁፌ አውቃኝ ነው ‹‹ሀበሻ ነህ?›› ብላ ያናደደችኝ...መልስ አልቆብኝ ይሁን አጥሮኝ ዝምታን ለጊዜያዊ ኮንትራት ተያያዝኩት፡፡ ‹‹ጥቁሯ ቦርሳ ዛሬም አብራህ አለች?››

‹‹አዎ! ነገም ትኖራለች›› ዞር ብዬ አየኋት፡፡ ቦርሳዬን ማለቴ ነው፡፡ እንደ ታዘለ የበኩር ልጅ ጀርባዬ ላይ ተኝታለች፡፡

‹‹ጥሩ ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ ከማነባት ምናለ አንዴ ውስጧ ያለውን ብዘረግፈውና ብገላገል?...›› የፌዝቡክ ጓደኛዬ እንደሆነች ጭምር ተነፈሰችልኝ፡፡ እድሜና ቁመት ይስጣት..ከዚህ በላይ ለፀሀይ ቅርብ ትሁን፡፡ ግን ያልወደድኩት ጥቁሯ ቦርሳዬን ለመበርበር ማሰቧን ነው፡፡ ከታክሲ ወርደን ብዙ አወራን፡፡ የመጨረሻ ቃሏ ‹‹..ዛሬ እኛ ቤት ብንቅምስ? ባለቤቴ ነው ያንተን ፅሁፍ ፕሪንት እያደረገ የሚያመጣልኝ፡፡ እሱም ሊያወራህ ስለሚፈልግ ደስ ይለዋል...›› ነበር ያለችኝ፡፡ ሆሆይ ሙስና ሊያሰሩኝ? ቡና ጋብዘው ሊያነቡኝ? ጥቁሯን ቦርሳ ሊበረብሩ...በዛ ላይ የመን ያለ ትዳር የማሽላ እንጀራ ይመስል በቋፍ ነው-ይፍረከረካል፡፡ ደግሞ ነገ በሰው ትዳር ገባህ ልባል?...ብዙ አሰበ ውስጤ..ሰነዓ ትዳርና አዳር ባለየበት፣ መተማመን ባልነገሰበት መንደር ‹‹ጎመን በጤና...›› አለ ፀሀዬ..እውነቱን ነው፡፡ ጎዞዬን ቀጠልኩ፡፡ እዚህም ጉዞዬን ልቀጥል ወዳቆምነው ታሪክ እናምራ....

አሁንም እዛው ጫት የሚቃምበት የመስከረም ቤት ነኝ፡፡ የማልታያችሁ ከሆነ የሚያጨሱት ሺሻ ጭስ ከልሎኝ ነው እባካችሁ ፈልጉኝ፡፡ ስምጥ ካልኩበት ሀሳብ እያወጡ እነሱ የተጨናነቀ አለም ውስጥ የሚዶሉኝ በዙና ሰላሜን ነሱኝ፡፡ ‹‹ፀሀፊ ለመሆን ብዙ ማሰብ ያሰፈልጋል እንዴ?..›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡

‹‹ትንሽ ሀሳብማ መፅሀፍ አይሆንም ነገሮችን ትኩረት ሰጥቶ ማየት...›› ላስረዳት ስዘረዝር ካለችኝ እውቀት ላይ ሳልጨልፍላት ተቅለብልባ አቋረጠችኝ፡፡

‹‹ያ-ማነው የሚሉት ዙቤሪ ያለው ፀሀፊ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ታውቀዋለህ? አንድ ቀን መንገድ ላይ አሳዩኝ፡፡ ፊቱ ምን ያክላል?...›› እኔ ፀሀፊ ለመሆን ያሰፈልጋ ብዬ የማስበውን ስዘረዝርላት እሷ ሌላ ታወራኛለች፡፡ እሱ ለእኔ ምኔ ነው? የፃፈውን አላነበብኩ፣ እሱን አይቼ አይደል ፀሀፊ መሆን የፈለኩት ድሮም ፀሀፊ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ በእርግጥ አንድም ጽሁፍ ጋዜጣ ላይ አላተምኩም፡፡ አሁን ያለችው አናታም ጸሀፊ ተብዬ በኢንተርኔት ይጽፋል ይላሉ፡፡ አላየሁም፡፡ አላነበብኩለትም፡፡ ለነገሩ ኢንትኔት መክፈት ስችል አይደል?

ይህን ሁሉ የምታስብለኝ ሄለን ናት፡፡ ይለጥፋትና እንደተለጣፊ ሱቅ ጎኔ ተለጥፋ በነገር ወጋችኝ፡፡ አሁን እንደምንም ብላ መስከረም ወደጋራ ጫዎታ ቀየረችው እና ጣሂር ድምፁን ከፍ አድርጎ ያወራል፡፡ ሴቶቹ አፋቸውን ከፍተው ጭስና የተቃጠለ አየር እያስገቡ ይሰማሉ፡፡ ስለ አንድ ትውልደ ሀበሻ ደግነት ያወራል፡፡ ‹‹በል ዝም በል ጉረኛ ናችሁ፡፡ ከእናንተ ደግነት የማይጠበቅ ነው፡፡ ድፍን የሀበሻን ልጅ የምትጫወቱበት እናንተ አይደላችሁ? ስንቷን ሀበሻ የሰራችበትን አንጠፍጥፋችሁ ላካችሁ? ስንቷን ዲቃላ አሳቀፋችሁ...›› በዚህ ጩኸት ነበር ከሀሳቤ የወጣሁት፡፡ ሁሉም በዝምታ ሲሰሟት ቆይተው ሄለንም ነኢማም..የስድብ መዓት አወረዱበት፡፡ እነሱም ቁስሉ ስላለባቸው ነው እንጂ ያላስተዋሉት ጥሩዎችም መኖራቸውን ነው፡፡

የስድቡ በየአቅጣጫው መቀጠል ያሳሰባት መስከረም ጫወታውን መለወጥ ፈልጋ ነው መሰለኝ ‹‹ጣሂር አብዱል ባስጥን ታውቀዋለህ አይደል?

‹‹የእነ መሀመድ አልራሚ ወንድም?..››

‹‹እ..እ..›› አለችና ሁሉም እንዲሰሟት በመፈለግ አይነት ዙሪያዋን ቃኘች፡፡ ‹‹ቅድም ከሀዳ ስመጣ ደባብ ላይ ነው /እንደ ውይይት ታክሲ ተሳፋሪዎች ፊት ለፊት የሚፋጠጡበት ነው/ አንዱ የመኒ ፊት ለፊቴ ተቀምጦ ቀሚሱን እየገለበ ሊያሳየኝ ሲታገል በአጋጣሚ አብዱልባስጥ ታክሲው ላይ ወጣ፡፡ ስነግረው ተናደደና ካሳየሽ እንትኑ ላይ እርገጭው ከዛ በኋላ እኔ አለሁ አለኝ፡፡ ለካ አማርኛ ይሰማል፡፡ አሮሻን ጋር ሲደርስ ወረደ እና ‹ሞኛችሁን ፈልጉ› በሎን ሄደ፡፡›› ቤቱ በሳቅ ተናጋ፡፡ እኔም ሳቅ አዋጥቻለሁ፡፡ በቋንቋ ጉዳይ ብዙ ገጠመኝ ስለማውቅ ነው ያሳቀኝ፡፡ በአንድ ወቅት አንዷ ስትሰራ ውላ ምግብ ቀርቦ ‹‹ኩሊ..›› ስትባል ስቅስቅ ብላ አልቅሳ ጎረቤት ያለችው ሰራተኛ ተጠርታ መጣች፡፡ ምነው ስትባል ‹‹ስሰራ ስደክም ውዬ እህል ሲቀርብ ኩሊ ይሉኛል..›› ብላ ታለቅሳለች፡፡ ወይ ትርጉም አለማወቅ!!.. አኩሊ.. ብይ..ማለት እና ሲናገሩ ‹‹አ›› ፊደልን ዋጥ አድርገው እንደሆነ ማንም ካልነገራት ምን ይደንቃል?.... በዛው የመናዊያን በሙሉ አማርኛ ይችላሉ በሚል ነገር ተገልብጦ በየተራ ሁሉም ሊያወሩ አቆበቆቡ፡፡

አሁን ‹‹...ተረኛ ነኝና..›› የሚለውን ለማቀንቀን ከወደ ጥግ የተቀመጠችው አስቴር ቀጠለች፡፡ ማንም ሊሰማት ያሰበ የለም፡፡ እንትን እንደነካው እንጨት ፊት የነሳት በዝቷል፡፡ እንደ አልጋ ልብስ ፈርጀ ብዙ ዘርፍ ያለው ታሪክ አላት፡፡ የስደት፣ የብልግና፣ የስርቆት፣ የሰው ባል መቀማት...የውሸት፣....አሁን ግን ሁሉ እንትን የነካው እንጨት ያደረጓት...እንትን የምለው ፈርቼ ሳይሆን ስሙ ይደብረኛል እንዳትጠሩት አደራ! ሁሉ ፊቱን ያዞረባት ጉድ እንዲህ ነው......

አንድ ልጅ አላት፡፡ በቃ!...አላት አላት ነው፡፡ አጠራጣሪው አባቱ ነው፡፡ አታስቡ ግን ባል አላት፡፡ ያውም ካገባች አስራ አንድ አመት ሆኗታል፡፡ የልጅ አባት ነኝ ባዮች ግን ፍርድ ቤት ተዳርሰዋል፡፡ የመን ያሉ ሀበሾች በትዳር ዙሪያ ከሚሉት እዚሀ ጋር አንዱን ልጥቀስ...‹‹የምናገባቸው ቀን..ቀን የአረብ ማታ ማታ የእኛ ናቸው..›› ይላሉ፡፡ /ይህ አባባል ሁሉንም የሚመለከት አይሆንም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀጥለው ክፍል ላይ እውነተኛ ታሪክ አቀርባለሁ፡፡ ስማቸውን ስለቀየርኩት እንጂ ይህም እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ለመጠቅስ እወዳለሁ፡፡/

አስቴርና ሁሴን ከተጋቡ አስራአንድ አመት ሆኗቸዋል፡፡ በተጋቡ አምስተኛ አመታቸው ልጅ ተወለደ፡፡ ምስጢረ የተባለችው ልጃቸው ዛሬ ስድስት አመት ሆኗታል፡፡ ሁሴን ልጄ ብሎ እያሳደጋት ያለችው ምስጢረን ልጄ ናት እስከዛሬም ማሳደጊያዋን እየሰጠሁ ነው ያሳደኳት ሚስቴ መውለድ ስላልቻለች ልጄን እወስዳለሁ የሚል አረብ መጣ፡፡ በእርግጥም ሁለቱም የጥቁር ጠይሞች ሆነው ሳለ የምስጢረ አረብ መምሰል ለ የሚገርመው ለብዙ ሰው ነበር፡፡ ሁሴን ቦታ ሆናችሁ አስቡት እስኪ ልጄ ብላችሁ ለስድስት ያሳደጋችሁትን አባት ነኝ የሚል ሲመጣ፡፡ ያውም እስከዛሬ ማሳደጊያ በየወሩ መቶ..መቶ ዶላር እየሰጠሁ ነው ብሎ...ምን ታደርጋላችሁ? አስቴር ስምንት አመት የሰራችበት ቤት አሰሪዋ ነው የልጄን ይሰጠኝ ጥያቄ ያቀረበው...የእነሱ በፍ/ቤት ስለተያዘ አነሳሁ እንጂ አጠራጣሪ ልጆች የያዙ...ብዙ ሞልተዋል፡፡

‹‹ዝምታህ ውበት አለው..›› ሄለን ከማስበው ሀሳብ እየመነጠቀች ማውጣቱን ተያይዛዋለች፡፡ አቋራጭነቱን መስከረም ተረክባለች፡፡ እዚህ የተፋፈገ ቤት ውስጥ ምናቸውም አልተመቸኝ፡፡ ጫቴን ኪሴ ከትቼ ውልቅ.....በቀጥታ ወደ ቤቴ ነው ያመራሁት፡፡ ጭር ሲል አልወድም የሚለውን ዜማ እያቀነቀነ የጠበቀኝ ኦና..ኦና የሚል ቤቴን ለማሟሟቅ ከሰል ማቀጣጠል ጀመርኩ፡፡ ስረጉት ምስኪን ጎረቤቴ ነች፡፡ ትመቸኛለች፡፡ ቆንጅዮ ናት፡፡ ቅብጥብጥና አተራማሽ ብትመስልም አይደለችም፡፡ ተግባቢ፣ ተጫዋች..ሁሉን ነገር በስርዓት የምታከናውን ናት፡፡ በሯን ከፍታ ብቅ ስትል ልቤ ድንግጥ አለብኝ፡፡

‹‹ምን ልታደርግ ነው? የተቀጣጠለ ከሰል እኔ ጋር አለልህ..››

‹‹እየቃምኩ ስለሆነ እጣን ላጨስ ፈልጌ ነው..›› ታዲያ ብቸኝነቴን፣ ኦናው ቤቴን..እምቅ እምቅ የሚለውን በጭስ ላጥነው ነው ልበላት?

‹‹ቡና ላፍላልህ?›› አትቅም፣ ሽሻም አታጨስ ከሁሉ ቁጥብ ነች፡፡ ቡና ማፍላት ግን አንደኛ ናት፡፡ ቤቷ ከጥቂት ሴት ጓደኞቿ ውጭ ብቅ የሚል ወንድ አላየሁም፡፡ ፍለጋው አያልቅም ብዬ ስዞር ‹‹አምላኬ ሰው ስጠኝ በልኬ..›› እያልኩ ሳቀነቅን ከዚሁ ሊቀናኝ ይሆን? ማን ያውቃል እጣ ፋንታዬም ትሁን እጣ ጦሴ ብናዬን ላጣጥም ገባሁ፡፡ ማን ያውቃል ለእናንተ የገጠመው ይግጠመኛ....

/እስከ አሁን ያቀረብኩት ትዝብት ብዬ ከፃፍኩት አጭር ወጣጥፍ ነበር፡፡ እዚህ ሀገር ያለውን የፍቅር ሁኔታ በተመለከተ ከላይ በገባሁት ቃል መሰረት በእውነተኛ ታሪክ ላይ ያቀነቀነ ወጌን ይዤ ብቅ እላለሁ እስከዛው ግን...........
የነገ ሰው ይበለን