Thursday, April 12, 2012

ጥቁሯ ቦርሳዬ

ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት

    ስደት ስደት ነው፡፡ ስሙን ብናሰማምረው፣ ብንኩለው፣ ብንኳኩለው ያው ስደት ነው፡፡ እዚህማ ያለነው በሁለት እንከፈላለን ይላሉ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ ሊያደርጉት፡፡ ገፈቱን እኩል እየተጎነጩት በባህር የገባ እና በአየር የገባ ብለው…ቂ…ቂ…ቂ…ቂ… አይ ወዳጄ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እግዚአብሄር ካንተ ጋር ሆኖ ከእስር ያውጣህ እንጂ ይቺ ቂ..ቂ.. የምትል ሳቅ በተጻፈች ቁጥር ትውስ ትለኛለህ፡፡ ትወዳት ነበር፡፡

    በዛ ያሉት አዳሜዎች፣ እና የአዳሜ እህቶች በአየር ነው የገቡት፡፡ ታዲያ አውሮፕላን ላይ ተሰቅላ የተጓዘችው በጉብኝት ቪዛ ይሁን እንጂ ቱሪስት ሆና አይደለም፡፡ ቦዶ ኪስ ቱሪስት ቢኮንስ የኔብጤ ይመስል የሰው እጅ እጅ ከማየት ይዘላል ብላችሁ ነው? ለነገሩ ቱሪስት አይሁኑ እንጂ የሰው እጅ ላለማየት መስራትን አማራጭ አድርገው የሚሄዱ ስለሆኑ ያኮሩኛል፡፡ ግን በኮንትራት ስራ አረብ ቤት ልትጠመድ ነው እያንዳንዷ አካሄዷ፡፡ የእኔው ለየት የሚለው ግን ባህር አቋርጨ..በየብስ በላብ ጨቅይቶ ብስብስ እስኪል ካልሲዬ…እግሬ እስኪላላጥ ተጉዤ ነው የመን ያለሁት፣ የገባሁት፡፡

   እይ!!!...ብቻ ተዉኝ እስኪ…ይሄን ለማንሳት አይደለም አነሳሴ፡፡ በስደቱ አለም ብቸኝነት ድቁስ ድቁስቁስ ያደረገኝ የዋዛ አይለም፡፡ እናቴ አሽቶ!..አሽቶ!! አድቅቆኛል፤ አልሞኛል፡፡ አንፍሶ፣ አንገዋሎ አንቀቀጥቅጦ…አበጥሮኛል፡፡ እንደ ወንደላጤ ካልሲ አዝረክርኮ..አልጋ ስር ባይሆንም እስር ቤት ወርውሮኛል፡፡ ስደት..የጨው ጆንያ አስመስሎ፣ አመድ ነዝቶ፣ በችግር ጠቅልሎ ጢባ ጢቢ…ጢባ ጢቢ ተጫውቶብኝ..ወዜን መጦ በጀሪካን ባዝሊን የማይመለስ ግርጣትና ንጣት አልብሶኛል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ፌድ ያደረገ ጅንስ መስዬ እንገላወዳለሁ በብቸኝነት ተተብትቤ፡፡

       ወዳጄ አሞህ ነው አጣሞህ? ከተማ እያለህ..በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደጉንዳን የሚርመሰመሱባት ሰነዓ ቁጭ ብለህ ብቸኝነት የሚያሰኝህ? ማለትዎ የማይቀር ቢሆንም ልክ መሆኖትን እኔም አሰምርበታለሁ፡፡ እኔ ግን ብቸኛ መሆንን መርጨ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ ሆኛለሁ፡፡ ብቸኝነትን እኔ ብቻ ፈልጌው ሳይሆን እሱ ፈልጎኝ እንደሆነስ የሙጥኝ ያለኝ? ይጣራልኝ ይመርመርልኝ፡፡

   ታዲያ ይህን ግርጣትና ንጣት ያመጣ ብቸኝነት ለመቅረፍ ስትራቴጂያዊ ጥናት አደረኩልዎት እና ‹‹ጥንድ..ጥንድ ሆነው ሲሄዱ ባይ ለካስ..›› የሚለውን ለማቀንቀን አሰብኩ፡፡ ባዝሊን፣ ቅባት ይዛ መጥታ ልታወዛኝ አስቤ አይደለም፡፡ እንዲያውም የቀረውን ወዝ አንጠፍጥፋ የምትወስድ መሆኗን መቼ አጥቼ? ሰው ትሁን ብቻ!...በቃ የሚፈለገው ሰው መሆን ነው፡፡ ግን ዝም ብሎ ሰው መሆን ብቻ መስፈርት አይደለም፡፡ ፤ሌላ መስፈርት ያስፈልገዋል፡፡  ማሟላት ያለባት አልኩ እና መሰፈርት ብጤ በውስጤ ከተብኩ፡፡ አሁን ቀሪው ነገር ቅኝት የተባለ ፕሮግራም ዘርግቶ ማጧጧፍ ነው…‹‹ፍለጋው አያልቅም..›› የሚለውን እያቀነቀንኩ ተሰማራሁ፡፡..ውሀ አጣጬን ፍለጋ..ውይ የኔ ነገር እዚህ የመን ውሀ አጣጭ ሳይሆን ለስላሳ አጣጭ ነው የሚፈለገው ቢባል ያስኬዳል..የሚረክሰው ለስላሳው ነዋ!...ውሀ 70 የየመን ሪያል  ሲሸጥ ፔፐሲ 50 ሪያል ነው፡፡
    
    ለቅሶ ቤትም፣ ሰርግ ቤትም ብቻ የሄዋን ዘር የምታተኩርበት ቦታ ሁሉ አይኔን ማተርኩ፡፡ አንዴማ በቃ! ደም ግባትዋ ይጣራል ብዬ አስኔን ስባው..ስባው ሊወጣ ጥቂት ሲቀረው ፈገገች፡፡ ተመስጌን ብዬ ፈጣሪዬን በሆዴ አመስግኜ እኔም ፈገግሁ፡፡ ልብ ስል እይታዋ ከኔ የዘለለ መሆኑን አወኩ እና አይንዋን ተከትዬ ላኩት አይኔን፡፡ እኔ በአካል ኦርጅናሉ ቁጭ ብዬ እስዋ ለካ የምትፈገው ግርግዳ ላይ ከተለጠፈ የፈረንጅ ፎቶ ኮፒ ጋር ነው፡፡ አስቡት እሲኪ አያናግራት፣ አይመልስላት እሱ ላይ የምታፈጠው ምነው፡፡ እኔ በአካል ያለሁትን ትታ....ካንተ ይልቅ የተለጠፈ የፈረንጅ ፎቶ ይሻላል ማለቷ እንደሆን የገባኝ ረፍዶ ነው፡፡ ፍለጋው አያልቅም ብዬ ብነሳም አሰልቺ ሆነብኝ እና እስኪ ሀሳብ የሚጋራ የወንድ ጓደኛ ልያዝ..የሚል ሀሳብ መጣብኝ፡፡

በእርግጥ የወንድ ጓደኛ የሚሆን ማግኘት ይቸግራል፡፡ እዚህ ያለ ወንድ ሁሉ ሴት ነው እያሉ ሴቶቹ በአደባባይ ሲያውካኩ ስሰማ ተጠራጥሬ እንትኔን ሁሉ ፈልጌያለሁ፡፡ ተመስጌን በእሱ ከሆነ አለኝ፡፡ ሌላው ስለሌለው ይሆን ሴት ያስባለው? እንጃ!!! ምን ይሆን ሴት ያስባላቸው? ታዲያ ክንክን ቢለኝ፣ ሴት ለመባላቸው ሰበብ ምህኛቱ ቢያጥረኝ…ጥሪው ቢጎስጠኝ፣ ቢጎረብጠኝ…መንስዔውን ለማወቅ ዳከርኩ፣ ተውተረተርኩ…በዚህ የተነሳ በእኔው ጥናት እንኳን ሁለት ነገር አገኘሁ፡፡

     ‹‹የታዘሉ ወንዶች..›› የሚል ስያሜ የሰጠኋቸውን እና ‹‹ባልጦ የለበሱ ወንዶች›› የሚል ስያሜ የሰጠኋቸውን ግሩፖች ለየሁ፡፡ ‹‹የታዘሉ ወንዶች..›› ያልኳቸው የሴት እጅ ጠብቀው ጉርሳቸውንም፣ ጫታቸውንም፣ ልብሳቸውንም..የሚሸፍኑ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ በአንድ ያልተወሰኑ እንደ እሳት አደጋ ሰራተኛ ስሜት በተቀጣጠለበት ዞረው አስክነው የሚኖሩም አሉበት፡፡

      ‹‹ባልጦ የለበሱ ወንዶች..›› ባልጦ የሚባለው እዚህ የመን ውስጥ ሴቶች የሚለብሱት ጥቁር ቀሚስ ነው፡፡ ያን- ቀሚስ ሳይለብሱ መውጣት ነውር ነው፡፡የሴትነታቸው  መገለጫ ነው፡፡ ወሬ ቀደው ወሬ ሰፍተው..ወሬ ደርተው ወሬ በልተው..የሚኖሩ በመሆናቸው ባልጦ የለበሱ ወንዶች ብያቸዋለሁ፡፡

      ሳስበው እና ሳስባቸው የሚገርሙኝ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ዘይገርም ሻሸመኔ ይባል ነበር አሁን ዘይገርም ሰነዓ ልል ነው፡፡ ስደት ከገባሁ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ስለምታዘብ ከላይ የጠቃቀስኳቸውን እና ሌሎች ነገሮችን መታዘብ ቻልኩ፡፡ ያለውን የፍቅር ሁኔታ ሳጠና ግን ሜትሪዎሎጂው የሚያመለክተው እንደሚከተለው ሆኖ አገኘሁት፡፡ ታዲያ ልብ ይበሉ ይህ የፍቅር ሜትሪዎሎጂ በየመን ያለ ሀበሻን ትኩረት አድርጎ የተጠና የእኔ ምስኪኑ ጥናት ነው ..….ከፈለጉ ሜትሪዎሎጂ ሚለውን ትተው ሚስኪኖሎጂ..ሊሉትም ይችላሉ፡፡
                      የፍቅር ሜትሪዎሎጂ በሰነዓ

    ፍቅር ፍቅር ነው፡፡ፀባዩም ተለዋዋጭ ነው..ልክ እንደዘመኑ ሰው፡፡ እንደ ሌባ ኪስ ኪስ የሚያይ ፍቅር አለ፡፡ እንደታክሲ./ከፒያሳ ቄራ..ከአጣና ተራ ኮተቤ../ የሚያዞር ፍቅር አለ፡፡ እንደ ዲጄ ቴፕ የሚያስጎረጉር፣ ካሴት ሲያስመርጥ የሚያስውል ፍቅር አለ፡፡ እንደ አልቃሽ አስለቅሶ እንደኮሜዲ የሚያስቅ ፍቅር አለ፡፡ እንደጨጓራ በሽታ እህል የማያስበላ፣ እንደመጥፎ ህልም እንቅልፍ የሚያባርርም ፍቅር አለ፡፡ እንደ 15 ልጆች አባት መንገድ ለመንገድ ለብቻ የሚያስወራ፤ እንዳልተያዘ የቤት ጣጣ ጨርቅ የሚያስጥል፤ እንደትራፊክ መንገድ አስገትሮ የሚያውል ፍቅር አለ፡፡ እንደ ፓስታ የሚያምዝለገልግ፣ እንደ ፔፕሲ የሚያገነፍል፣ የሚያስቆዝም የሚያስተክዝ ፍቅር አለ፡፡ እንደጥፍር መቁረጫ ጥፍር የሚያስከረክም ፍቅር አለ፡፡ አይኑካ የሚባል በአይን የሚገባ ፍቅርም አለ፡፡ ፍቅር አይነቱ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ዘመን እየጠበቀ እንደዘመኑ ከሰዉ ጋር ይለዋወጣል፡፡ እንደ አየር ሁኔታው ይሞቃል ይቀዘቅዛል፤ ይበርዳል፡፡ ታዲያ ብርዱ በ60 መርፌ አይመለስም፡፡ በ60 ዙር አልጋ መውደቅ ላይም ፤ላይመለስ ይችላል፡፡ ስለፍቅር ሁሉም ያስባል ያልማል፤ ይፈላሰፋል፡፡ ከዱብዳው ግን ማምለጥ የሚቻለው የለም፡፡ ሲመጣ ማጣጣም እና መጣጣም ነው ዋናው፡፡ መኝታ ቤት፣ መናፈሻ፣ መዝናኛ ቦታ፣ ፊልም ቤት፣መንገድ ላይ ፣ ጓሮ ፣ቢሮ ውስጥ …ብቻ ቢያሻዎት ሽንት ቤትም ቢሆን ሊያጣጥሙት ይችላሉ፡፡ እንደ ፍላጎትዎ..እንደመሩት እንደመራዎት እንደ አመቺነቱ እንደቀልብያዎ..ሊያጣጥሙት ፣ ሊያጣጥሞትም ይችላል፡፡ ስለዚህ የፍቅር ሜትሪዎሎጂውን ማውቁ……

  ፍቅር በተመላላሽ፡-የሰነዓን አየር በአማከለው ሁኔተታ..ስራ አዳሪ ተቀጥረው እየሰሩ..የፍቅርን ንፋስ ሀሙስ እና አርብ ብቻ ለሚያጣጥሙትን ነው የሚመለከተው  ስራ በአዳሪ ፍቅር በተመላላሽ የሚባለው፡፡

    ፍቅር በአዳሪ፡- ሀሙስ እና አርብ አይበቃም ብለው ተመላላሽ ለሚሰሩ ቤታቸው ለሚያድሩ የሚያንዣብብባቸው ጠንካራ ሀሳብ ነው፡፡

    ፍቅር በኮንትራት፡- ጠንከር ብሎ አላስበላ፣ አላስጠጣ ሲል እና ስራ አስትቶ ቤት ሲያስውል ነው፡፡…ስንፍና ሲጨመርበት እና እጅ እጅ ሲያሳይ ባለው ሁኔታ ተጠቂዎቹ ወንዶች ናቸው፡፡

   ፍቅር በቶክ ሾው፡- እየተገናኙ ለረጅም ሰዓት በወሬ ብቻ የሚያሳልፉ ፍቅረኞችን የሚያመላክት ነው፡፡ጀማሪዎች ላይ ይጠረነክራል፡፡

እግረኛው ፍቅር፡- በእግር ጉዞ ተጀምሮ ዛል እስኪሉ ወክ የሚገባበዙትን ያማከለ ነው፡፡

ፍቅር በቀን ስራ፡- ተባራሪ ለአንድና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜያዊ መውደቅ የሚሞከር …በድንገተኛ የስሜት ተጠቂዎች ላይ ያንዣብባል፡፡

    ውጤት ተኮር ፍቅር፡- የሚያስገኘው ጥቅም ከግምት ውስጥ ገብቶ ያዋጣል አያዋጣም ተብሎ በውጤት ተኮር ጥናት የሚመሰረት ነው፡፡ውጤት ካላስገኘ ምላዕተ ጉባዔው ይወስን፣ ርቄን ማቄን፣ አስቸኳይ ስብሰባ ሳይባል አዲስ ስልት ሊያስቀይስ ወይም ማፈግፈግን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ‹‹…የተሸለ..ካገኘ ድርጅቱ በጨረታው አይገደድም›› እንደሚለው ማስታወቂያ ማለት ነው፡፡ ይሄ እንደነጋዴ ጥቅም ብቻ ታርጌት ያደረገ ነው፡፡

ወጪ መጋራት፡- ይሄኛው ሁሉን በጋራ ለማድረግ የሚፈልጉት ላይ የሚታይ መተሳሰብ የሞላበት ነው፡፡

ቱሪዝም፡ በውጭ ዜጋዎች ላይ ያተኮረ ሀብተም ከደሃ ያለየ ብቻ ነፍስ ኖሮት የሚንቀሳሰቀስ የውጭ ዜጋ ላይ የሚያተኩር ቢያንስ ከሀገር እንዲያስወጣ የሚያገለግልበት ሁኔታ የሚጠናበት ነው፡፡

  11ኛው ሰዓት፡- እድሜ ነጉዶ ከሽበት ጋር ያጣመዳቸው ሹገር ዳዲ እና ሹገር ማሚን እያሳደዱ ማጣጣም ላይ ተመሰረተ ነው፡፡

አይኑካ፡- እስር ቤት ውስጥ ከወንዶች ክፍል ወደ ሴቶች ክፍል ወይም በተቃራኒው መስመር የሚወረወር ምልከታ ብቻ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በተረፈ በዚህ ሳምንት እንደ ወትሮው ከፊል ደመናማ/ፀባማ/ ከፊል ፀሀያማ/ፍቅራማ/ ሆኖ ይሰነብታል፡፡
 ብዬ ተነተንኩት እና እርፍ ማንም ልክ ነህም አይደለህም ሊለኝ ይችላል፡፡ ግን ማን በእኔ እይታ አየው? ስለዚህ…..   
   
    አፈር ስሆን እስካሁን ማነህ አላላችሁኝ እኔም እገሌ ነኝ አላልኩ፡፡ ይህ ታሪክ የጸሀፊው አይደለም፡፡ ፀሀፊው የፈጠረኝ የእኔ የፍጡሩ ታሪክ ነው፡፡ አንተ ማነህ ካላችሁ ለስሜ አልጨነቅም፡፡ ከበደም በሉኝ በለጠ፣ መሀሙድ በሉኝ እንድሪስ…መጠሪያው አያጨቃጭቀንም፡፡ ለእኔ ስሜ ምግባሬ ነው፡፡ አልዳሰስ አልከሰስ…ሳልፈጠር በፍጡር የተፈጠርኩ፡፡ ያለነበርኩ በእሱ ዘንድ የኖርኩ፡፡ ለእናንተ እንግዳ ነኝ፡፡ ለፀሀፊው እስኪፈጥረኝ አርግዞ እስኪወልደኝ ምንያህል እንዳማጠኝ እሱኑ ጠይቁት፡፡ ለስሜ አልጨነቅም ማንነቴን የምነግራችሁና ምግባሬ ይገልጸዋል እውነቱን ይዞ መሄድ ነው ፍላጎቴ፡፡ ለስሙ ከሆነ በፈለጋቸሁት ጥሩኝ ግን ማን ብባል ነው ደስ የሚላቸሁን? ስም ነገሩኝ እስኪ…  በዚህ ዘመን ለበዛ ትርጉም አልባ ስም ችግር አንዱን ለጥፉልኝ እግር የለም አትከፍሉበት፤ አይፈልጣችሁ አይቆርጣችሁ ደስ ያላችሁን አንሱ እና…
ትርጉም ያለው ቢሆን ግን ደስ ይለኛል፡፡
    
የከርሞ ሰው ይበለን እንጂ ጥቁሯ ቦርሳዬ ውስጥ ስላለው ነገር እናወራለን ገና፡፡                            
                            
                                   ቸር እንሰንብት