Sunday, April 22, 2012


 ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት
(ክፍል 3)

   መጥቻለሁ ወዳጆቼ…የእኔ ነገር መጣሁ ብዬ አስጠበኳችሁ አይደል? ምን  ብዬ ነበር ያቋረጥኩት? ‹‹…ምን ባጠፋሁ ነው የእናቴን ገበር ምጣድ በሚያክል እጁ በጥፊ የከደነብኝ፡፡ አሁን ሳስበው ያኔ ይቺ ድንቡሎ ፊቴ እሱ እጅ ላይ ስታርፍ የቡሄ ሙልሙል መስላ ይሆን? ምነው ያኔ ፎቶ ባነሱኝ ነበር፡፡ እኔ ወድቄ እሱ ለያዥ ገናዥ አስቸገረ…›› ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡

    ተጣጥቤ ስመለስ ከንፈሬ ከበደኝ፡፡ አብጦ ማር የተሞላ ስልቻ መስሎ ተወጠረላችሁ፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ ነው ነገሩ..እንኳን ቡጢ አርፎበት ቀድሞም ደባደቦ ከንፈር የሚባለው አይነት ነበረ፡፡ ኪሎ ስጋ አፌ ላይ ለጥፌ የምዞር ያህል ከበደኝ፡፡ አይ የኔ ነገር መቼም አያምርብኝ..እኔን ብሎ ጠባሽ፡፡ ምነው ባልጠብስስ..ራሴ በቦክስ ከምጠበስ? ተጣጥቤ እንደመጣሁ ሳየው ይባስ ብርክ ያዘኝ..ፈርቼ እንዳይመስላቸሁ ወንድነቴ መጥቶብኝ ነው፡፡ ታዲያ ሰው ፊት ያን የሚያክል ቡጢ አሳርፎብኛል አይደል? /ቡጢ ይሁን ጥፊ  ስለተምታታብኝ እናንተ ደስ ያላችሁን በሉት/ የሰዉ ሁሉ አይን እኔ ላይ ሲያርፍ እንድደባደብ እየተበቁ መሆኑ ገባኝ፡፡ ሊገላግሉ የተዘጋጁ ሁሉ ነበሩ…

     ፈሪ ለእናቱ በውስጤ ያዜምኳት ዜማ ነች፡፡ ‹‹እንገናኛለን አሁን የሰው ሰርግ አልበጠብጥም..›› ብዬ ዛትኩና ወደ ጭፈራዬ ላመራ አሰብኩ፡፡ በኋላማ ስሰማ ለካ ፍቅረኛው ነች፡፡ እሷ ቹዝ ዘ ቤስት ልትል ማማረጫ ይሁን አጫፋሪ ብቻ ያጨችኝ እሷ እና ፈጣሪ ይወቁት፡፡ ልጨፍር ስሞክር ጉልቻ ያከለው ከንፈሬ ወደ ፊት ሊደፋኝ አዘነበለ፡፡ ቅሌት ብርቄ አይደል ብዬ ከሚሳቅብኝ ሹልክ ብዬ ወደቤቴ ነዋ!...፡፡ ብቸኝነቴ ይሻላል ከቡጢ አልኩና ለእራት የሚሆን ፎሰሊያ በእንቁላል /ማልቤድ/ ገዝቼ ገባሁ፡፡ እናንተዬ ቤት ስገባ ጭር ብሎ አሳነባሪ ሆድ ውስጥ የምገባ መሰለኝ፡፡ ቅዝቃዜው ፍሪጅ ውስጥ የማድር ቢያስመስለኝ አይፈረድም፡፡ የሙቀት ሞተር የምትሆን ‹‹ፍቅሬ›› ብላ እቅፍ የምታደርግ የግራ ጎኔን አጠንክሬ ማፈላለግ እንዳለብኝ ግን አመንኩ፡፡

    በሳምንቱ ፍለጋው አያልቅም እያልኩ አንድ ሀሙስ ሀሙስ እየተሰባሰቡ የሚቅሙበት ቤት ሄድኩ፡፡ አንድ ክፍል ቤቷ ተጨናንቃለች፡፡ ዛሬ ቀኑ ሀሙስ በመሆኑ በርካታ እንግዶች አሉባት፡፡ ሀሙስ ሀሙስ የእሷ ቤት ሁሌም በሰው እንደተሞላ ነው፡፡ የመን ውስጥ ከቀኖች ሁሉ ሀሙስ ልዩ ማዕረግ አለው፡፡ ‹‹አሊዮም ከሚስ›› ይላሉ የመናዊያኑ፡፡ ዛሬ ሀሙስ ነው ማለታቸው ነው፡፡ በዚህ እለት ሚስቶች ለባሎቻቸው የማይሆኑት የለም፡፡ በየቤቱ በየቀኑ የሚቃም ቢሆንም የሀሙሱ አቃቃም ይለያል፡፡ ይህን ባህል ሀበሻው ለመቀበል አልከበደውም፡፡ እኛ ዘንድስ ሀሙስ የቀን ቅዱስ እያልን እናንቋለጳጵሰው የለ? ደግሞስ የትኛውም ቦታ ላይ መጥፎ ነገር እንጂ ጥሩ ነገር አንኮርጅም እኮ!!!

   የሄድኩባት ልጅ መስከረም ትባላለች፡፡ የአመት መጀመሪያ ሳይሆን መጨረሻ ነው የሚመስለው ፊቷ፡፡ ጨፍጋጋ ነገር ነች፡፡ ህይወቷ በተደጋጋሚ በአንድ ምህዋር የሚሽከረከር ነው፡፡ጠዋት ወደ ስራ ትሄዳለች፣ ከስራ ስትመጣ ጓደኞቿ ጋር እየዞረች ጫት ትቅማለች፣ሺሻ ታጨሳለች ሲነጋ ስራ ትሄዳለች፡፡ በቃ! ሁሌም ይሄው ነው፡፡ ሀሙስ እሷ ቤት ነው ተራው፡፡ ሀሙስ ሀሙስ ሁሌም የቤቷ እና የእሷ ንጽህና የተለየ ነው፡፡ እንደ እድል ሆኖ የእሷ ሀሙስ ፍቅረኛም ሆነ የትዳር ጓደኛ አላመጣላትም፡፡ ቢያመጣላትም አልበረከተላትም፡፡ ለትዳር ሳይሆን ለአዳር ህብረ አንሶላ የሚፈጥር ግን ደጋግሞ ገጥሟታል፡፡ ‹‹ይሄንንስ ማን አየው? ጦም ከማደር ያገኙትን መቀርቀር..›› የምትለው ፍሬከርስኪ አባባል አላት፡፡ የየእለቱን ስታሳድድ ሳይነጋ እየጨለመባት እድሜዋ ሽምጥ እየጋለበባት መሆኑ አልታወቃትም፡፡ የኋላ ኋላ ከፀፀት ጋር የምታኝከው ቁጭት እያጠራቀመች መሆኑ መች ገባት? ቢገባት በነቃች፡፡ ነቅታ ለነገ ህይወቷ ራሷን ባዘጋጀች፤ ወይ ትዳሯን አጥብቃ በያዘች፡፡ ይሄ ደግሞ የአብዛኛዎቹ ሴት እህቶች ችግር ነው፡፡ ባክነው ኖረው ባክነው ይቀራሉ፡፡ እድሜ ሲያልፍ ‹‹እህህ!..››ን እያንጎራጎሩ የፀፀትን ሸማ አጣፍተው ይቀመጣሉ፡፡

   ‹‹ቡናውን ተቀበላት!..እየቃምክ ታንቀላፋለህ እንዴ?..›› የመስከረም ድምጽ ነው ከሀሳቤ ያባነነኝ፡፡ ጭልጥ ብዬ በሀሳብ ባህር መዋኘቴን መቼ አወቀች? ስንቱ ጋር ደርሼ፣ ስንቱን አውርጄ፣ ስንቱን ሰቅዬ፣ ስንቱን ሸፍኜ፣ ስንቱን ገልቤ፣ ስንቱን አስሼ..፣የእሷን ህይወት ዳስሼ መመለሴን ብታውቅ ታንቀላፋለህ እንዴ? ባላለችኝ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠችው ሶስና የዘረጋችልኝን ቡና የተሞላ ሲኒ ተቀበልኳትና ቀመስ አድርጌ አስቀመጥኩት፡፡ የአንዳንዱን ቡና አጠጣጥ ስሰማ አስጠላኝ፡፡ አንዱ ፉት አባባሉ የሚያፏጭ ይመስላል፡፡ ሶስና ስታጣጥም በነጠላ ጫማ የምትራመድ ትመስላለች፡፡  ምላሷን ላንቃዋ ላይ  አጣብቃ ‹‹ጧ!›› ታደርጋለች፡፡

   ሴቶቹ፣ ወንዶቹ ሁለት ሶስት ቦታ የሺሻ እቃ ጥደው ያንቦለቡሉታል፡፡ ጫቱን አቃቃማቸው በሆዳቸው ትተው በጉንጫአቸው ማርገዝ የጀመሩ እስኪያስመስላቸው ወጥቀውታል፡፡ በዝና የሚወራለትን የመስከረምን ቤት የሀሙስ ቃሚዎችን ፕሮግራም ለማየት ነው ጫቴን አንጠልጥዬ የመጣሁት፡፡ በእርግጥም ከጠበኩት በላይ ብዙ ሰው አለ፡፡ ስለዚህ ሁሉ ሳስብ ነው ‹‹ተኛህ እንዴ ያለችኝ..›› የሁሉ አዚም ተሰብስቦ ይተኛባትና በዚህ ሁሉ ጫጫታ መሀል ጫት እየቃምኩ የምተኛው ተንቀሳቃሽ በድን አደረገችኝ? ያቋርጣትና አቋረጠችኝ፡፡  ቅድስትና አብደላ የጀመሩትን ፍቅር አቋረጠች፤ ጎረቤቶቿን አጣልታ አቆራረጠች፡፡ እሷ ራሷ ከአንዱ ጋር የጀመረችውን ፍቅር አቋረጠች፡፡ ቅድም ራሱ ጣሂር እና አሰፋ ሲያወሩ አቋረጠች፡፡ አሁን እኔን ከሀሳቤ…በቃ!..ማቃረጥና ማንቋለጥን ቋሚ ስራዋ አደረገችው?

     ቁመናውም ሆነ ነገረ ስራው በጣም የሚያስገርመኝ ቀጭኑ አሰፋ በሩ ስር ተቀምጧል፡፡ በዛ ቁመቱ ተጣጥፎ ሲቀመጥ ያሳዝናል፡፡ ሰዓሊ ነኝ ቢልም የረባ ነገር ሰርቶ /ስሎ/ ያየው የለም፡፡ ድንገት የሚስለው ሸራ ወጥሮ ቡርሽ ወድሮ ሳይሆን በጫት እንጨት..ጫት ቅጠል ላይ ነው መሰለኝ የሚስለው፡፡ጫት ይዞ፣ ጫት ወድሮ፣ ጫት ጎርሶ ነው ሁሌ የማየው፡፡ አሰፋ ስደት መቼ እንደወጣ የሚያውቅ የለም፡፡ አንዳንዴ ሳስበው እሱ ራሱ የሚያውቀው አልመሰለኝም፡፡

     አጠገቡ ካለ ሰው ጋር የጦፈ ወሬ ይዟል፡፡ ጫቱን እያነሳ በጣትና ጣቱ መሀል እያስገባ አሸት..አሸት ያደርገዋል፡፡ ወዲያው ወደ አፉ ከቶ ሌላ ያነሳል፡፡ ሂደቱ አያቋርጥም፡፡ የሚቋረጠው ቶሎ ቶሎ አፉ ላይ የሚለጉመውን ሲጋራ የያዘ እንደሆን ነው፡፡ አጠገቡ የተቀመጠው የጣሂር ወሬ የሰለቸው ይመስላል፡፡ ጣሂር እሱ ሲያወራ እንጂ ሰው ሲያወራ ማዳመጥ አይወድም፡፡ ቀለብላባ አይን እና ቀለብላባ ምላስ ለጉድ ታድሎታል፡፡ ወሬው ማቋረጫ የለውም፡፡ የአሁንለቱ በቀደምለት ታክሲ ስጠብቅ አገኘሁትና ለአፍታ ጆሮዬ ግሎ እስኪገለማ ሁለት ነጥብ፣ አራት ነጥብ..የሌለው ወሬውን አንቆረቆሮብኝ አደነዘዘኝ፡፡ ጆሮ ስትራፖ ሲይዘው አይታችሁ ታውቃላችሁ እኔ ግን የዛን ቀን አየሁ፡፡ ዳግም ሳየው እንደተበደረው ሰው መንገድ አቋርጨ እብስ…ዳግም ጆሮዬን ስትራፖ ቢይዘው በምን ይለቀኛል? ይሄ ቋንቋው የማይገባኝ የአረቦቹ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ እንኳን እንደሱ አይታክትም፡፡ እማማ ትሙት! እላችኋለሁ ስለምን እንዳወራኝ አላውቅም፡፡ በእርግጥ እናት ኖሮኝ አይደለም እማማ ትሙት ያልኩት፡፡ መቼም ፈጣሪዬ /ፀሀፊው/ ያለ እናት ነው የፈጠረኝ ማለት ይከብደኛል፡፡ ግን እስካሁን አላውቃትም ወይም አላስተዋወቀኝም እናቴን፡፡

    ስለዚህ ጣሂር ያለውን ስላልሰማሁት ያን ሁሉ ቃላት ዝም ብሎ ለአየር ዘረገፈው፡፡ ኪሳራ ነው፡፡ ለነገሩ የእሱ ወሬ ዞሮ ዞሮ ስለየመናዊ አባቱ እና ስለኢትዮጵያዊ እናቱ ነው፡፡ 20 ጊዜ ባገኘው ሀያ ጊዜም ያወራልኛል፡፡ አረብ የጠበሱት የእሱ እናት ብቻ ናቸው እንዴ? ‹‹ባሌ ምን የሚያክል እርሻ አለን መሰለህ..›› ሲል ሁሌ ይጀምራል፡፡ አረብ ሀገራትን በስደት ያጥለቀለቀው ወንድ ሁላ መሳ ለመሳ የእርሻ መሬት ነበረው፡፡ ለኢትዮጵያ የእሱ አባት ብቻ ከየመን ሄደው ያረሱላት ይመስል ይንጦረጦራል፡፡ ጣሂር ከቁመቱ ማጠር ጋር ጉራው ሲነፃፀር ጉራው መቶ ሺህ ጊዜ ይበልጣል፡፡ ወደፊት ሾል ያለ አፍንጫው እያሸተተ ያለ ቀበሮ ያስመስለዋል፡፡ እኔ ግን ከአይኑ ማነስ እና መቁለጭለጭ ጋር አይጠመጎጥ ነው የሚመስለኝ፡፡ ያለ ቅጥ የወጠቀው ጫት ጉንጩን እባጭ አስመስሎታል፡፡ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው ጫቱ፡፡ ሶፍት ወረቀቱን እያነሳ አፉን በጠረገ ቁጥር ንጣቱን በአረንጓዴነት ያቀልመዋል፡፡ አሁንም አሁንም አፉን ቢጠርግም ፊተኛ ጥርሱ ላይ ከተለጎደው ጫት ጋር ሲታይ የተዝረከረከ የገልቱ ቡሀቃ መስሏል፡፡ መዝረክረኩን አልኩ እንጂ አረንጓዴ ሊጥ የለም፡፡

   ‹‹ቡናው ቀዘቀዘ እኮ አትጠጣም እንዴ?..››አለችኝ መስከረም፡፡ ደህና ከምኮመኩመው ሀሳብ አላቀቀችኝ፡፡ ይቺ ልጅ ለማቋረጥ ብቻ ነው የተፈጠረችው? ትቀናለች መሰለኝ ሰው ጥሩ ነገር ሲያስብ አትወድም አስሬ ትጠራኛለች፡፡ ስሟን ቄስ ይጥራውና..ለካ ደግሞ የመን ቄስ ቢኖርም ስም አይጠራም፡፡ ፍታት የለ! ክርስቲያን ሲሞት የሚሰልምበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ክርስቲያን ሲባል መቃብር የለም፡፡ ቦታ አንሰጥም ይባልና ሬሳ ፍሪጅ ውስጥ ከቶ ለማውጣት ከላይ እታች መንጦልጦል ነው፡፡ ለዚህ ሲባል ወንደሰን ከማል፣ ማንያህሉሽ ሀቢባ እየተባሉ ስም ገለባብጦ አፈር መቅመስ ነው፡፡ ፍታት የለ ሰዓታት..ታዲያ በምን ቦታ ቄስ ስሟን ይጥራው? ቄስ ባይሆንም ሴጣን ይጥራው፡፡ አቤት ብላ ስትወጣ እስክትመለስ ብዙ አስባለሁ፡፡ ለካ ቄስ ይጥራው ሲባል ትሙት ማለት ነው? ይሄ ነገር ይለፈኝ፡፡
       
    ሀሳብ ማመንዠጌን እንደጣሂር ወሬ አራት ነጥብ ከማሳጣው ፉልስቶፕ አደረኩና ቀዝቅዞ ወዘናው የረገበ ቡናዬን መጠጣት ጀመርኩ፡፡ ቤቱ በጭስ ታፍኗል፡፡ በኩር ተበክሯል፡፡ ሺሻው ይጨሳል፤ ግማሹ ሲጋራውን ለጉሞ ያንቦለቡላል፡፡ የሽታው ነገር መላ ቅጥ የለውም፡፡ የቡና ሽታ፣ የጫት ሽታ፣ የብብት ሽታ፣ የጫማ ሽታ፣ የአፍ ሽታ፣ የእንትን ሽታ፣ የሽታዎች ሽታ፣ ይፈሳል፣ ይገሳል፡፡ እኔም እያላበኝ ስለሆነ የሰውነቴን ቢያንስ የብብቴን ሽታ አዋጥቻለሁ፡፡

                   እመለሳለሁ፡፡