Monday, April 16, 2012


                         ግሩም ተ/ሀይማኖት
       እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬት አፍወርቅ ተክሌ..
                                         
      እረፍተ ዜናቸውን /የሞታቸውን ዜና/ ያረዳኝ ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ዘገባ ነው፡፡ አዘንኩ፡፡ በእውነት አዘንኩ ብቻ ሳይሆን አንጋፋዎቹ መከታተላቸው አስደነገጠኝ፡፡ በሰዓቱም ስለተደናገጥኩ የለጣፊውን ማንነት ልብ ስላላልኩ እገሌ ብዬ ማመስገን አልቻልኩም፡፡ ከዛ በኋላ በርካቶች ለጥፈውታል፡፡ ሁሉንም ላመሰግን ወደድኩ፡፡ ከምንም በላይ ያስደነገጠኝ የጥበብ ሰዎቻችን እና የኩዳዴ /የፋሲካ/ ጾም ቁርኝት ነው፡፡ ከሁሉም የከፋው የዘንድሮው ሁለት ወር ጸም ሶስት አንጋፋዎችን አሳጣን፡፡ ጾሙ ሲገባ በአጻጻፍ ስልቱ ከልጅነቴ ጅምሮ የምወደው ጋሽ ስብሀትን አጣን፡፡ እኩለ ፆሙ አካባቢ በትርጉም ስራቸው በርካታ የስለላ መጻህፍትን ያስነበቡን፣ በርካታ መጽሀፍትን የተረጎሙት ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ተርጓሚ ማሞ ውድነህን አጣን፡፡ የሁሉም ሲታሰብ ቤተሰብ የማጣት ያህል ነው የተሰማኝ፡፡
  
    ጋሽ ማሞ ውድነህን ከሁሉ በላይ የማውቃቸው ለሰርካለም አሳታሚ ድርጅት /ቢሮአችን/ በነበራቸው ቅርበት ነው፡፡ ሞታቸውን ስሰማ ቶሎ የታወሰኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሰርክዓለም ፋሲል ናቸው፡፡ በተለይ እስክንድር ነጋ ይወዳቸው ነበር፡፡ ያከብራቸዋልም፡፡ በእስር ሳለ ስለሆነ ስላልቀበራቸው ምን ተሰምቶት ይሆን? የተሰማውን አንድ ቀን ጽፎ እንደሚያስነብበን አምናለሁ፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በገዢው ፓርቲ ‹‹አሸባሪ..›› ተብሎ በእስር ላይ ነው፡፡ ቢሆንም ፔን ኢንተርናሽናል በምርጥ ጋዜጠኝነት ተሸላሚ አድርጎ ስለመረጠው ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ሲያንሰው ነው እንጂ የሚበዛበት አይደለም፡፡ አንድ ቀን እውነት ሲያሸንፍ፣ ስልጣን ኤስፓየርድ ሲያደርግ፣ ነገር ሲገለበጥ እስክንድርም ነፃ ይሆንና....እስከዛው ግን በቀጣይነት ስለ እስክንድር ነጋ በማሰፍረው ፅሁፍ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ወደ ጅምሬ ልመለስበት፡፡

   የእረፍተ ዜናቸው ያስደነገጠኝ እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬት አፍወርቅ ተክሌ አንድ ጊዜ ‹‹ለውዱ ግሩም ተ/ሀይማኖት ከመልካም ምኞት ጋርና ከወንድምነት ጋር..›› ብለው በእጅ ፅሁፋቸው ፅፈው ፊርማቸውን ያኖሩበትን ማስታወሻ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ይህ ማስታወሻ ከላይ ያስቀመጥኩት ፎቶዎች ያሉበት ነው፡፡  የእሳቸው፣ የቤታቸው እና አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ያኖሩት ድንቅ ስዕላቸው ያለበት ሆኖ ከውስጡ በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የተፃፈ የህይወት ታሪካቸው ያለበት ነው፡፡ ሰዓሊ ሆኜ አይደለም የተገናኘነው፡፡ ስለ ስዕል ምንም አይነት ግንዛቤ የለኝም፡፡ ቢያንስ ጥሩ ተመልካች አይደለሁም፡፡ በልጅነቴ በስዕል ፕሮፌሽናል ደደብ ከመሆኔ የተነሳ ጂኦግራፊና ባዮሎጂ በካርቦን ነበር የምገለብጠው፡፡ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግርማ የሚባል ካርቱኒስት የሚስላቸውን ካርቱኖች እያየሁ ትንሽ ሞካክሬያለሁ፡፡ ታዲያ በደፍተር ሉክ ላይ ከመሳል አልፌም አላውቅም፡፡

   ኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ጊዜ ለምኒልክ መጽሄት፣ ሌላ ጊዜ ለምኒልክ ጋዜጣ ቃለ-ምልልስ ሳደርጋቸው ነው የተቀራረብነው፡፡ የጋዜጣውን ቃለ-ምልልስ በኋላ አቀርበዋለሁ፡፡

   በአንድ ወቅት ቀንዲል ቤተ-ተውኔት ውስጥ በጥላሁን የህይወት ታሪክ ዙሪያ አንድ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ሳንዲያጎ ፕሮዳክሽን ወይም ሙዚቃ ቤት ነው ያዘጋጀው፡፡ ድንገት ጊዜው ከመርዘሙ ጋር ሳንዲያጎ ሙዚቃ ቤት ይባል ፕሮዳክሽን ከተሳሳትኩ ይቅርታ፡፡ በወዳጄ ጋዜጠኛ ወርቅአፈራሁ አሰፋ ጠሪነት ቦታው ላይ ተገኘሁ፡፡ ጋሽ አያልነህ ሙላትን ላናግረው ቢሮ ስገባ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን አገኘኋቸው፡፡ አጋጣሚው የገረመኝ ስለእሳቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መረጃ ነበረው እና ቃለ-ምልልስ ባደርጋቸው ጥሩ እንደሚሆን ጠቁሞኝ ነበር፡፡ በቀጥታ ራሴን አስተዋውቄ የአለም ሎሬትነት ማዕረግ ሊሰጣቸው እንደሆነ መረጃ እንዳለኝ ነግሬ ቃለ-ምልልስ እንድናደርግ ጠየኳቸው፡፡ ቀናት አመቻችተው ሲመቻቸው እንደሚደውሉልኝ ተነጋግረን ስልክ ቁጥሬን ሰጠኋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ካሉኝ የማስታውሰው ‹‹ሞባይል ስልክ የሚባል ነገር መያዝ አልወድም፡፡ ስራ ያስፈታል፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ እየሰራሁ ቢደወል እንዴት የምናደድ ይመስልሀል?›› አባባላቸው እውነት መሆኑን ጋሽ አያልነህ ሙላት ጠንቅቆ አስረዳኝ፡፡

     እደውልልሀለሁ ብለው ስልክ ቁጥሬን የመውሰዳቸውን ነገር ግን ማንም ቢሯችን ሰዎች አልተዋጠላቸውም፡፡ ‹‹..እሳቸው እኮ የፈለገ መገናኛ ብዙሀን በደብዳቤ ጠይቋቸው እንኳን እሺ አይሉም...›› የሚለው ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ደካማ ጎኔ ጠንከር ብሎ ወይም ተጠራጣሪው ጎኔ አመዝኖ ሌላ አርቲስት ቃለ-ምልልስ አደረኩኝ፡፡ ከ13 ቀን በኋላ ግን በቢሮው ስልክ ሲደውሉ እኔ ስላልነበርኩ እስክንድር ይመስለኛል ወይም ሰርክዓለም መልዕክት ተቀበሏቸው፡፡ በማግስቱ አራት ሰዓት ቀጠሮ እንደተያዘልኝ ነው መልዕክቱ፡፡ በሰዓቴ ጦር ኃይሎች አካባቢ ያለው ቪላ አልፋ ቤታቸው ደረስኩ፡፡ ሰዓት ላይ የማያዛንፍ አቋም እንዳላቸው ሰምቼ ነበር እና በሰዓቱ ተጠንቅቄ ደረስኩ፡፡ ይህን ቤታቸውን ደርግ ወስዶባቸው እንደነበር ሲመለስላቸው ለማደስ ብቻ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳወጡበት ራሳቸው ነገሩኝ፡፡ በውበቱ ተማርኬ መፍዘዜን አውቀው ይሆን የነገሩኝ? እያንዳንዱ ነገር ጥበብ ወለድ ረቂቅ ስራ ነው፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ስገባ ግን ረጅም አመት ወደ ኋላ የሚመልስ እና የልጅነት ጊዜዬን የሚያስታውስ ምስል አየሁ፡፡ የአባታቸው ነው፡፡

    እዚህ ጋር አምሮ ተኩሎ ይሳል እንጂ በህጻንነቴ የማውቃቸው ሰው ምስል ጋር ተመሳሰለብኝ፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ከፍ ብሎ ያለ ካብ ጊቢ ውስጥ የነበሩ ‹‹የአፈወርቅ አባት›› ስንላቸው የሚያባርሩን ሰው ለመሆናቸው አልተጠራጠርኩም፡፡ ግን የወጣትነትና የሽምግልና፣ የመክሳትና የመወፈር ለውጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ የአባት ጡረተኞችን አይነት አለባበስ ከነ ኒሻናቸው እንደሚለብሱ እንኳን ያኔ አሁንም በአይነ ህሊናዬ ይታዩኛል፡፡ አርባ ደረጃ..ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ፣ ቅ/ማርያም፣ አራት ኪሎም በተወሰነ ቦታ ያደጋችሁ እኝህን ሰው ታውቋቸው ይሆናል፡፡

   ከሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ጋር ሻይ ጠጥተን ከስቱዲዮ ጀምረው ቤታቸውን እያዞሩ ሲያሳዩኝ በመሀል ብልጭ እያለ ደስታዬን ሰልቦኝ የሚሄደው ‹‹ለምንድን ነው የአፈወርቅ አባት..›› ሲባሉ ያባርሩን የነበረው? ይሄን የመሰለ የሚያኮራ ልጅ እያላቸው? ችግሩ ምንድን ነው? የሚል ሀሳብ ነበር፡፡ የአንድ ሰው ጊቢ፣ የአንድ ሰው ስቱዲዮ የምጎበኝ አልመሰለኝም፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም ነው የሆነብኝ፡፡ ይሄ እንደ ፕላዝማ ስክሪን የሰፋ ፊቴ ስሜቴን ያሳብቃል መሰለኝ፣ አለያም ጥሩ አንባቢ ናቸው ማለት ነው፡፡ ይሄ የመጀመሪያዬ ቤት ስለሆነ ነው ቪላ አልፋ ያልኩት እንጂ መገናኛ እና አዋሳም ከዚህ የማይተናነሱ ቤቶች አሉኝ ሲሉ በግርምቴ ላይ ግርምት እንድጨምር አድርገው ነገሩኝ፡፡ የሽልማታቸው ብዛት ዛሬ ላይ ሆኜ ማስታወስ የሚከብድ ነው፡፡ የልብሶቹ ለብቻ ዋንጫዎቹ፣ ኒሻኖቹ.. ሁሉም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ እንደ ቢሮ የሚጠቀሙበት ቦታ ላይ በትልቅ ወረቀት ላይ ያገኙትን ሽልማቶች፣ መቼ እንደ ተሸለሙ፣ የሸላሚው ድርጅት ወይም ሀገር ዝርዝር ተመዝግቦ ተቀምጧል፡፡ አስታውሳለሁ ሰባ ሁለት አካባቢ ነበር፡፡

     ስላየሁትም፣ ስለሰማሁትም፣ ስናወራ ስለታዘብኩትም ለመጠየቅ መቅረፀ ድምፄን አስተካክዬ ተቀመጥን፡፡ በመጀመሪያ የጠየኳቸው ጥያቄ ከስማቸው በፊት ስለሚገቡት የማዕረግ መጠሪያዎች እና ሙሉው ካልተጠራ ስለሚሉበት ምክንያት ነበር፡፡ ይህን ቃለ-ምልልስ ሐምሌ 6 እና 13 1993 ዓ.ም ለንባብ በበቃው ‹‹ምኒልክ›› ጋዜጣ ላይ ነበር ያሰፈርኩት፡፡ በአጋጣሚ ካስመጣኋቸው መረጃዎቼ ጋር መጥቶ እጄ ላይ ስላለ  የሰጡኝን ምላሽ ላስነብባችሁ፡፡

     ‹‹አንዴ ለአንባቢህ ሙሉ ስሜን ከነማዕረጌ መስጠት አለብህ ከዛ በኋላ ግን እየደጋገምክ ያንን ማለቱ የሞኝ ለቅሶ ነው፡፡›› አሉኝ በዚህ ብስማማም አንዴ ሲናገሩ ‹‹ስትጠሩ አንጠልጥላችሁ በግማሽ አትጥሩኝ ከጠራችሁ ሙሉውን ጥሩ ካልሆነ ግን በስሜ ብቻ ጥሩኝ..›› ሲሉ ሰምቻለሁ ስለዚህ አሁን ካሉኝ ጋር አይቃረንም? ወይስ ይህ ነገር ተደጋግሞ አሰልችቶት ነው ይህን ያሉት? አልኳቸው፡፡ አይኔ ግን ትርጉማቸው ያልገባኝ አብስትራክት ስዕሎች ላይ ይንከራተታል፡፡ ‹‹ምን መሰለህ..›› ሲሉ ጀመሩ፡፡

    ‹‹ምን መሰለህ በፅሁፍ ለሚደረግ ነገር ሲጀመር ሙሉ አርዕስቱ መጠራት አለበት፡፡ ማለት እጅግ የተከበሩ ሜተር አርቲስት የአለም ሎሬየት አፈወርቅ ተክሌ የሚለው መስፈር አለበት፡፡ እነዚህ አርዕስቶች...አንተ አጋጣሚ እዚሁ ክፍል ውስጥ ነው ያለኸው አንኳር..አንኳር የሆኑ ዲፕሎማዎችና የምስክር ወረቀቶች አሉ፡፡ ይህንን አይተህ ሁሉንም ነገር መረዳት ትችላለህ፡፡እነዚህ ነገሮች ሲሰጡ ሴኔት ተቀምጦ፣ ኮሚቴ ተቀምጦ ወይም የአካዳሚ አባላት ተቀምጠው ይህ ሰው እስካሁን ድረስ በሰራው ስራ ይህ ማዕረግ ይገባዋል ብለው ነው የሚሰጠው፡፡ በስራህ በድካምህ የመጡ ናቸው፡፡›› ሲሉ ውስጤ ተፀንሶ የሚላወስ ብልጭ ያለ ጥያቄ ነበርና የእነዚህ ነገሮች /ሽማቶች/ ዋጋቸው ወይም ጥቅማቸው ምን ያህል ነው? አልኩኝ፡፡

     ሲመልሱልኝ ‹‹..እነዚህ ነገሮች ከዩንቨርስቲ ዲግሪ በላይ ናቸው፡፡ ሲሰጡህ እኛ ለዚህ በቂ ነህ ብለን እናምናለን ትቀበላለህ ወይ ብለው ይጠይቁሀል፡፡ እቀበላለሁ ካልክ ያንን ስም ማክበር ማስከበር ግዴታህ ነው፡፡ እኔ ይሄ ይጠራ፣ ይሄ ይጠቀስ የምለው ለዛ ነው፡፡ ካልሆነ አፈወርቅ ተክሌ በቂዬ ነው፡፡ ለማናም አርቲስት ለማንም የፈጠራ ሰው ስሙ በቂው ነው፡፡ እነፒካሶ እርዕስት ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ ግን በጽሁፍ ከሆነ ያ-ያገኙትን እርዕስት መፃፍ አለበት፡፡ በመናገር ከሆነ ግን ፒካሶ ነው የምትለው፣ ዳቪንቺ ነው የምትለው፣ እከሌ ነው የምትለው፡፡ እኔንም አፈወርቅ ልትለኝ ትችላለህ፡፡

     ግን በሀገራችን የሆነው ምንድን ነው፡፡ መንግስት የሰጠህ አርዕስት ካልሆነ በስተቀር የተከበሩ፣ ክቡር መባል አትችልም የሚል መንፈስ ጭቅላታቸው ውስጥ ገብቷል፡፡ እንጂ ለእኔ አፈወርቅ የሚያሰኘኝ ስራዬ ነው፡፡ እሱ ይበቃል፡፡ ግን ለምንድን ነው ይሄን የሚቃረኑት?..›› አሉኝ፡፡ በዚህ አይደለም ያበቃነው፡፡ ጠቅለል አድርጌ እመለስበታለሁ፡፡
                        ቸር እንሰንብት፡፡      


Thursday, April 12, 2012

ጥቁሯ ቦርሳዬ

ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት

    ስደት ስደት ነው፡፡ ስሙን ብናሰማምረው፣ ብንኩለው፣ ብንኳኩለው ያው ስደት ነው፡፡ እዚህማ ያለነው በሁለት እንከፈላለን ይላሉ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ ሊያደርጉት፡፡ ገፈቱን እኩል እየተጎነጩት በባህር የገባ እና በአየር የገባ ብለው…ቂ…ቂ…ቂ…ቂ… አይ ወዳጄ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እግዚአብሄር ካንተ ጋር ሆኖ ከእስር ያውጣህ እንጂ ይቺ ቂ..ቂ.. የምትል ሳቅ በተጻፈች ቁጥር ትውስ ትለኛለህ፡፡ ትወዳት ነበር፡፡

    በዛ ያሉት አዳሜዎች፣ እና የአዳሜ እህቶች በአየር ነው የገቡት፡፡ ታዲያ አውሮፕላን ላይ ተሰቅላ የተጓዘችው በጉብኝት ቪዛ ይሁን እንጂ ቱሪስት ሆና አይደለም፡፡ ቦዶ ኪስ ቱሪስት ቢኮንስ የኔብጤ ይመስል የሰው እጅ እጅ ከማየት ይዘላል ብላችሁ ነው? ለነገሩ ቱሪስት አይሁኑ እንጂ የሰው እጅ ላለማየት መስራትን አማራጭ አድርገው የሚሄዱ ስለሆኑ ያኮሩኛል፡፡ ግን በኮንትራት ስራ አረብ ቤት ልትጠመድ ነው እያንዳንዷ አካሄዷ፡፡ የእኔው ለየት የሚለው ግን ባህር አቋርጨ..በየብስ በላብ ጨቅይቶ ብስብስ እስኪል ካልሲዬ…እግሬ እስኪላላጥ ተጉዤ ነው የመን ያለሁት፣ የገባሁት፡፡

   እይ!!!...ብቻ ተዉኝ እስኪ…ይሄን ለማንሳት አይደለም አነሳሴ፡፡ በስደቱ አለም ብቸኝነት ድቁስ ድቁስቁስ ያደረገኝ የዋዛ አይለም፡፡ እናቴ አሽቶ!..አሽቶ!! አድቅቆኛል፤ አልሞኛል፡፡ አንፍሶ፣ አንገዋሎ አንቀቀጥቅጦ…አበጥሮኛል፡፡ እንደ ወንደላጤ ካልሲ አዝረክርኮ..አልጋ ስር ባይሆንም እስር ቤት ወርውሮኛል፡፡ ስደት..የጨው ጆንያ አስመስሎ፣ አመድ ነዝቶ፣ በችግር ጠቅልሎ ጢባ ጢቢ…ጢባ ጢቢ ተጫውቶብኝ..ወዜን መጦ በጀሪካን ባዝሊን የማይመለስ ግርጣትና ንጣት አልብሶኛል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ፌድ ያደረገ ጅንስ መስዬ እንገላወዳለሁ በብቸኝነት ተተብትቤ፡፡

       ወዳጄ አሞህ ነው አጣሞህ? ከተማ እያለህ..በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደጉንዳን የሚርመሰመሱባት ሰነዓ ቁጭ ብለህ ብቸኝነት የሚያሰኝህ? ማለትዎ የማይቀር ቢሆንም ልክ መሆኖትን እኔም አሰምርበታለሁ፡፡ እኔ ግን ብቸኛ መሆንን መርጨ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ ሆኛለሁ፡፡ ብቸኝነትን እኔ ብቻ ፈልጌው ሳይሆን እሱ ፈልጎኝ እንደሆነስ የሙጥኝ ያለኝ? ይጣራልኝ ይመርመርልኝ፡፡

   ታዲያ ይህን ግርጣትና ንጣት ያመጣ ብቸኝነት ለመቅረፍ ስትራቴጂያዊ ጥናት አደረኩልዎት እና ‹‹ጥንድ..ጥንድ ሆነው ሲሄዱ ባይ ለካስ..›› የሚለውን ለማቀንቀን አሰብኩ፡፡ ባዝሊን፣ ቅባት ይዛ መጥታ ልታወዛኝ አስቤ አይደለም፡፡ እንዲያውም የቀረውን ወዝ አንጠፍጥፋ የምትወስድ መሆኗን መቼ አጥቼ? ሰው ትሁን ብቻ!...በቃ የሚፈለገው ሰው መሆን ነው፡፡ ግን ዝም ብሎ ሰው መሆን ብቻ መስፈርት አይደለም፡፡ ፤ሌላ መስፈርት ያስፈልገዋል፡፡  ማሟላት ያለባት አልኩ እና መሰፈርት ብጤ በውስጤ ከተብኩ፡፡ አሁን ቀሪው ነገር ቅኝት የተባለ ፕሮግራም ዘርግቶ ማጧጧፍ ነው…‹‹ፍለጋው አያልቅም..›› የሚለውን እያቀነቀንኩ ተሰማራሁ፡፡..ውሀ አጣጬን ፍለጋ..ውይ የኔ ነገር እዚህ የመን ውሀ አጣጭ ሳይሆን ለስላሳ አጣጭ ነው የሚፈለገው ቢባል ያስኬዳል..የሚረክሰው ለስላሳው ነዋ!...ውሀ 70 የየመን ሪያል  ሲሸጥ ፔፐሲ 50 ሪያል ነው፡፡
    
    ለቅሶ ቤትም፣ ሰርግ ቤትም ብቻ የሄዋን ዘር የምታተኩርበት ቦታ ሁሉ አይኔን ማተርኩ፡፡ አንዴማ በቃ! ደም ግባትዋ ይጣራል ብዬ አስኔን ስባው..ስባው ሊወጣ ጥቂት ሲቀረው ፈገገች፡፡ ተመስጌን ብዬ ፈጣሪዬን በሆዴ አመስግኜ እኔም ፈገግሁ፡፡ ልብ ስል እይታዋ ከኔ የዘለለ መሆኑን አወኩ እና አይንዋን ተከትዬ ላኩት አይኔን፡፡ እኔ በአካል ኦርጅናሉ ቁጭ ብዬ እስዋ ለካ የምትፈገው ግርግዳ ላይ ከተለጠፈ የፈረንጅ ፎቶ ኮፒ ጋር ነው፡፡ አስቡት እሲኪ አያናግራት፣ አይመልስላት እሱ ላይ የምታፈጠው ምነው፡፡ እኔ በአካል ያለሁትን ትታ....ካንተ ይልቅ የተለጠፈ የፈረንጅ ፎቶ ይሻላል ማለቷ እንደሆን የገባኝ ረፍዶ ነው፡፡ ፍለጋው አያልቅም ብዬ ብነሳም አሰልቺ ሆነብኝ እና እስኪ ሀሳብ የሚጋራ የወንድ ጓደኛ ልያዝ..የሚል ሀሳብ መጣብኝ፡፡

በእርግጥ የወንድ ጓደኛ የሚሆን ማግኘት ይቸግራል፡፡ እዚህ ያለ ወንድ ሁሉ ሴት ነው እያሉ ሴቶቹ በአደባባይ ሲያውካኩ ስሰማ ተጠራጥሬ እንትኔን ሁሉ ፈልጌያለሁ፡፡ ተመስጌን በእሱ ከሆነ አለኝ፡፡ ሌላው ስለሌለው ይሆን ሴት ያስባለው? እንጃ!!! ምን ይሆን ሴት ያስባላቸው? ታዲያ ክንክን ቢለኝ፣ ሴት ለመባላቸው ሰበብ ምህኛቱ ቢያጥረኝ…ጥሪው ቢጎስጠኝ፣ ቢጎረብጠኝ…መንስዔውን ለማወቅ ዳከርኩ፣ ተውተረተርኩ…በዚህ የተነሳ በእኔው ጥናት እንኳን ሁለት ነገር አገኘሁ፡፡

     ‹‹የታዘሉ ወንዶች..›› የሚል ስያሜ የሰጠኋቸውን እና ‹‹ባልጦ የለበሱ ወንዶች›› የሚል ስያሜ የሰጠኋቸውን ግሩፖች ለየሁ፡፡ ‹‹የታዘሉ ወንዶች..›› ያልኳቸው የሴት እጅ ጠብቀው ጉርሳቸውንም፣ ጫታቸውንም፣ ልብሳቸውንም..የሚሸፍኑ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ በአንድ ያልተወሰኑ እንደ እሳት አደጋ ሰራተኛ ስሜት በተቀጣጠለበት ዞረው አስክነው የሚኖሩም አሉበት፡፡

      ‹‹ባልጦ የለበሱ ወንዶች..›› ባልጦ የሚባለው እዚህ የመን ውስጥ ሴቶች የሚለብሱት ጥቁር ቀሚስ ነው፡፡ ያን- ቀሚስ ሳይለብሱ መውጣት ነውር ነው፡፡የሴትነታቸው  መገለጫ ነው፡፡ ወሬ ቀደው ወሬ ሰፍተው..ወሬ ደርተው ወሬ በልተው..የሚኖሩ በመሆናቸው ባልጦ የለበሱ ወንዶች ብያቸዋለሁ፡፡

      ሳስበው እና ሳስባቸው የሚገርሙኝ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ዘይገርም ሻሸመኔ ይባል ነበር አሁን ዘይገርም ሰነዓ ልል ነው፡፡ ስደት ከገባሁ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ስለምታዘብ ከላይ የጠቃቀስኳቸውን እና ሌሎች ነገሮችን መታዘብ ቻልኩ፡፡ ያለውን የፍቅር ሁኔታ ሳጠና ግን ሜትሪዎሎጂው የሚያመለክተው እንደሚከተለው ሆኖ አገኘሁት፡፡ ታዲያ ልብ ይበሉ ይህ የፍቅር ሜትሪዎሎጂ በየመን ያለ ሀበሻን ትኩረት አድርጎ የተጠና የእኔ ምስኪኑ ጥናት ነው ..….ከፈለጉ ሜትሪዎሎጂ ሚለውን ትተው ሚስኪኖሎጂ..ሊሉትም ይችላሉ፡፡
                      የፍቅር ሜትሪዎሎጂ በሰነዓ

    ፍቅር ፍቅር ነው፡፡ፀባዩም ተለዋዋጭ ነው..ልክ እንደዘመኑ ሰው፡፡ እንደ ሌባ ኪስ ኪስ የሚያይ ፍቅር አለ፡፡ እንደታክሲ./ከፒያሳ ቄራ..ከአጣና ተራ ኮተቤ../ የሚያዞር ፍቅር አለ፡፡ እንደ ዲጄ ቴፕ የሚያስጎረጉር፣ ካሴት ሲያስመርጥ የሚያስውል ፍቅር አለ፡፡ እንደ አልቃሽ አስለቅሶ እንደኮሜዲ የሚያስቅ ፍቅር አለ፡፡ እንደጨጓራ በሽታ እህል የማያስበላ፣ እንደመጥፎ ህልም እንቅልፍ የሚያባርርም ፍቅር አለ፡፡ እንደ 15 ልጆች አባት መንገድ ለመንገድ ለብቻ የሚያስወራ፤ እንዳልተያዘ የቤት ጣጣ ጨርቅ የሚያስጥል፤ እንደትራፊክ መንገድ አስገትሮ የሚያውል ፍቅር አለ፡፡ እንደ ፓስታ የሚያምዝለገልግ፣ እንደ ፔፕሲ የሚያገነፍል፣ የሚያስቆዝም የሚያስተክዝ ፍቅር አለ፡፡ እንደጥፍር መቁረጫ ጥፍር የሚያስከረክም ፍቅር አለ፡፡ አይኑካ የሚባል በአይን የሚገባ ፍቅርም አለ፡፡ ፍቅር አይነቱ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ዘመን እየጠበቀ እንደዘመኑ ከሰዉ ጋር ይለዋወጣል፡፡ እንደ አየር ሁኔታው ይሞቃል ይቀዘቅዛል፤ ይበርዳል፡፡ ታዲያ ብርዱ በ60 መርፌ አይመለስም፡፡ በ60 ዙር አልጋ መውደቅ ላይም ፤ላይመለስ ይችላል፡፡ ስለፍቅር ሁሉም ያስባል ያልማል፤ ይፈላሰፋል፡፡ ከዱብዳው ግን ማምለጥ የሚቻለው የለም፡፡ ሲመጣ ማጣጣም እና መጣጣም ነው ዋናው፡፡ መኝታ ቤት፣ መናፈሻ፣ መዝናኛ ቦታ፣ ፊልም ቤት፣መንገድ ላይ ፣ ጓሮ ፣ቢሮ ውስጥ …ብቻ ቢያሻዎት ሽንት ቤትም ቢሆን ሊያጣጥሙት ይችላሉ፡፡ እንደ ፍላጎትዎ..እንደመሩት እንደመራዎት እንደ አመቺነቱ እንደቀልብያዎ..ሊያጣጥሙት ፣ ሊያጣጥሞትም ይችላል፡፡ ስለዚህ የፍቅር ሜትሪዎሎጂውን ማውቁ……

  ፍቅር በተመላላሽ፡-የሰነዓን አየር በአማከለው ሁኔተታ..ስራ አዳሪ ተቀጥረው እየሰሩ..የፍቅርን ንፋስ ሀሙስ እና አርብ ብቻ ለሚያጣጥሙትን ነው የሚመለከተው  ስራ በአዳሪ ፍቅር በተመላላሽ የሚባለው፡፡

    ፍቅር በአዳሪ፡- ሀሙስ እና አርብ አይበቃም ብለው ተመላላሽ ለሚሰሩ ቤታቸው ለሚያድሩ የሚያንዣብብባቸው ጠንካራ ሀሳብ ነው፡፡

    ፍቅር በኮንትራት፡- ጠንከር ብሎ አላስበላ፣ አላስጠጣ ሲል እና ስራ አስትቶ ቤት ሲያስውል ነው፡፡…ስንፍና ሲጨመርበት እና እጅ እጅ ሲያሳይ ባለው ሁኔታ ተጠቂዎቹ ወንዶች ናቸው፡፡

   ፍቅር በቶክ ሾው፡- እየተገናኙ ለረጅም ሰዓት በወሬ ብቻ የሚያሳልፉ ፍቅረኞችን የሚያመላክት ነው፡፡ጀማሪዎች ላይ ይጠረነክራል፡፡

እግረኛው ፍቅር፡- በእግር ጉዞ ተጀምሮ ዛል እስኪሉ ወክ የሚገባበዙትን ያማከለ ነው፡፡

ፍቅር በቀን ስራ፡- ተባራሪ ለአንድና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜያዊ መውደቅ የሚሞከር …በድንገተኛ የስሜት ተጠቂዎች ላይ ያንዣብባል፡፡

    ውጤት ተኮር ፍቅር፡- የሚያስገኘው ጥቅም ከግምት ውስጥ ገብቶ ያዋጣል አያዋጣም ተብሎ በውጤት ተኮር ጥናት የሚመሰረት ነው፡፡ውጤት ካላስገኘ ምላዕተ ጉባዔው ይወስን፣ ርቄን ማቄን፣ አስቸኳይ ስብሰባ ሳይባል አዲስ ስልት ሊያስቀይስ ወይም ማፈግፈግን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ‹‹…የተሸለ..ካገኘ ድርጅቱ በጨረታው አይገደድም›› እንደሚለው ማስታወቂያ ማለት ነው፡፡ ይሄ እንደነጋዴ ጥቅም ብቻ ታርጌት ያደረገ ነው፡፡

ወጪ መጋራት፡- ይሄኛው ሁሉን በጋራ ለማድረግ የሚፈልጉት ላይ የሚታይ መተሳሰብ የሞላበት ነው፡፡

ቱሪዝም፡ በውጭ ዜጋዎች ላይ ያተኮረ ሀብተም ከደሃ ያለየ ብቻ ነፍስ ኖሮት የሚንቀሳሰቀስ የውጭ ዜጋ ላይ የሚያተኩር ቢያንስ ከሀገር እንዲያስወጣ የሚያገለግልበት ሁኔታ የሚጠናበት ነው፡፡

  11ኛው ሰዓት፡- እድሜ ነጉዶ ከሽበት ጋር ያጣመዳቸው ሹገር ዳዲ እና ሹገር ማሚን እያሳደዱ ማጣጣም ላይ ተመሰረተ ነው፡፡

አይኑካ፡- እስር ቤት ውስጥ ከወንዶች ክፍል ወደ ሴቶች ክፍል ወይም በተቃራኒው መስመር የሚወረወር ምልከታ ብቻ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በተረፈ በዚህ ሳምንት እንደ ወትሮው ከፊል ደመናማ/ፀባማ/ ከፊል ፀሀያማ/ፍቅራማ/ ሆኖ ይሰነብታል፡፡
 ብዬ ተነተንኩት እና እርፍ ማንም ልክ ነህም አይደለህም ሊለኝ ይችላል፡፡ ግን ማን በእኔ እይታ አየው? ስለዚህ…..   
   
    አፈር ስሆን እስካሁን ማነህ አላላችሁኝ እኔም እገሌ ነኝ አላልኩ፡፡ ይህ ታሪክ የጸሀፊው አይደለም፡፡ ፀሀፊው የፈጠረኝ የእኔ የፍጡሩ ታሪክ ነው፡፡ አንተ ማነህ ካላችሁ ለስሜ አልጨነቅም፡፡ ከበደም በሉኝ በለጠ፣ መሀሙድ በሉኝ እንድሪስ…መጠሪያው አያጨቃጭቀንም፡፡ ለእኔ ስሜ ምግባሬ ነው፡፡ አልዳሰስ አልከሰስ…ሳልፈጠር በፍጡር የተፈጠርኩ፡፡ ያለነበርኩ በእሱ ዘንድ የኖርኩ፡፡ ለእናንተ እንግዳ ነኝ፡፡ ለፀሀፊው እስኪፈጥረኝ አርግዞ እስኪወልደኝ ምንያህል እንዳማጠኝ እሱኑ ጠይቁት፡፡ ለስሜ አልጨነቅም ማንነቴን የምነግራችሁና ምግባሬ ይገልጸዋል እውነቱን ይዞ መሄድ ነው ፍላጎቴ፡፡ ለስሙ ከሆነ በፈለጋቸሁት ጥሩኝ ግን ማን ብባል ነው ደስ የሚላቸሁን? ስም ነገሩኝ እስኪ…  በዚህ ዘመን ለበዛ ትርጉም አልባ ስም ችግር አንዱን ለጥፉልኝ እግር የለም አትከፍሉበት፤ አይፈልጣችሁ አይቆርጣችሁ ደስ ያላችሁን አንሱ እና…
ትርጉም ያለው ቢሆን ግን ደስ ይለኛል፡፡
    
የከርሞ ሰው ይበለን እንጂ ጥቁሯ ቦርሳዬ ውስጥ ስላለው ነገር እናወራለን ገና፡፡                            
                            
                                   ቸር እንሰንብት

Wednesday, December 21, 2011


                  ሀበሻ በየመን
     ለመሆኑ እንዴት ናችሁ? አቀማመጣችሁን አላልኩም። ኮምፒዩተራችሁ ላይ አፍጥጣችሁ ይመስለኛል የምታነቡት። እሺ በስደት ያላችሁ..የስደት ኑሮ ቅብብሎሹ እንዴት አድርጓችሁዋል? እንዴ ምነው ተገረማችሁ? ልክ ነኝ እኮ ኑሮ ቅብብሎሽ አይደል እንዴ? ሰኞ ወደ ማክሰኞ ሲጠልዘን፤ ማክሰኞ ተቀብሎ አባብሎ ወደ ረቡዕ ሲወረውረን .. መስከረም ወደ ጥቅምት ሲጠልዘን፤ ጥቅምት ለህዳር፣ ህዳር ለታህሳስ…እያለ ቅብብሎሹ በርትቶ ጠውለዛው ደርቶ እዚህ ደርሰን የለ? አሁንም ቅብብሎሹ አንዱ ወደ አንዱ መለጋቱ  እንደቀጠለ ነው። ገና እንለጋለን፤ እንጠለዛለን። ስንት አመት ይሆን በቅብብሎሹ ውስጥ የምናሳልፈው?...

      አቦ ዛሬ ጣፋጭ ወግ እናውጋ ነው የሚባለው የብሶት ቁስል እንከክ እንበለው? ስለስደት ብናወራ አይመቻችሁም? ከስደትም ስደት አስከፊውን የአረብ ስደት…ከአረብ ሀገርም ስለየመን እናውራ። ምነው  ፊታችሁ ጨፈገገ? የስደት ነገር ሲነሳ ቤተሰብ ትዝ አላችሁ? ወደ እውነታው እንምጣ ከኑሮ ጋር ያለውን ትግል ለማሸነፍ ፣ ለመሸነፍም ቢሆን የትግል ሜዳ አድረጋችሁ የመረጣችሁት የመንን ነው እንበል። የመንን በሀሳብ ለመቃኘት ተዘጋጁልኝ። የመን ደሞ ጥሩም አለ መጥፎም አለ። ሞቱም፣ ዱላውም፣ መደፈሩም፣ ማግኘት፣ ማጣቱም ሁሉም አለ። ከሌሎች በከፋ ሁኔታ አለ።

      የመንም ይኖራል። ለጉድ!!..ይኖራል። ኑሮ ከተባለ ሀበሻ በየመንም እየኖረ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ስደት ነው። ወደ ተሻለው ሳይሆን…ብዙ ብዙ እውነት የማይመስሉ እውነቶች የተሰገጡበት ህይወት ነው በየመን ያለው። ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል ኮካኮላን ያስተረተው በየመን ያለ ሀበሻን ኑሮ ታይቶ ነው ማለት ይቻላል። አይደለም ካላችሁም አሁን እኔ ብያለሁ። ማነው የሚከራከረኝ? ከየመን በከፋ ሁኔታ ላይ ሱማሊያ የሚኖሩ መኖራቸውን ሳትረሱ ማለት ነው። አትቸኩሉ እኔው እነሱንም አሳያችሁዋለሁ።

      ችግር የማይነቅለው የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም ተሰዷል። ነብዩም ተሰደዋል። አረ ቆራጡ እና ተፈጥሮን በቁጥጥር ስራ እናውላለን ያሉት ኮረኔል መንግስቱም ተሰደዋል። እኛ ለስደት አዲስ አደለንም። አለም ለስደት አዲስ እንዳልሆነ ሁሉ እኛም እየተሰደድን ነው። ተሰደናልም ገናም እንሰደዳለን።

    ሀበሻ በየመን እጅጉን አሰልቺ የሆነ ደግሞም ያልሆነ ዝብርቅርቅ ህይወት ከጥሩ ጎኑ መጥፎው ያመዘነበት ኑሮ መሀል ተሰንጎ ነው የሚኖረው። እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት፣ ጥርጣሬ.. የበዛበት ነው ህይወቱ። መሰደብ.. <<ያ-ሀበሺ..ሸቃላ..ኦሪያ..ያ ሱማሌ..ያ አስወድ..>> የዘውትር መጠሪያ ኤጭ!..ድሮስ ክብር በሀገር አይደል? ነው እንጂ። ክብር በሌለበት ተንቆ፣ ተዋርዶ መኖር ያውም ከራስ ባልተሻለ ሰው። የመን ያለ የሀበሻ ቁጥር እንዲህ በዋዛ የሚሰላ አይደለም። በህጋዊ መንገድ ያለውና ህጋዊ ያልሆነው ከ70- 80 ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ታዲያ ይገመታል ነው። ይበልጣል እንጂ አያንስም። ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጓዡም ቀላል ተብሎ የሚጠራ አይደለም።

     በእናታቸው፣ በአባታቸው፣  አልፎም በአያታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ…ግማሽ ጎናቸው የመናዊ ትውልደ ሀበሻ 5.000.000/ አምስት ሚሊዮን/ አካባቢ ናቸው። ይህ የሚያሳየው የየመንና ኢትዮጵያ ትስስር የጥንት መሆኑን ነው። በፊት የመኒዎች በችግር ወደ ሀገራችን ይሰደዱ ነበር። ዛሬ ነገር ተገልብጦ እኛ ወደ እነሱ  ሆኗል። አሁንም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ ያለው የመናዊ ቁጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ነው። ከዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የመን ከአረቢኛው ቀጥሎ አማርኛ በሰፊው ይነገራል።

    <<ገንዘብ ካለ…>> ሁሉም የመናዊያን የሚያውቋት ተረት ናት።<<እወዲሻሎ..ኢንደሚኖ…አንቺ..>> በሁሉም ዘንድ የተለመደች ቃል ነች። ልክ እኛ ጋር ማዘር ፋዘር..እንደተለመደ ሁሉ። ጫት ሲነሳ ሐረርን የማያነሳ የመናዊ የለም።

    የዛሬዋ የመን ጥንት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ <<ሀገረ ናግራን>> እንደምትባል ታሪክ ያስረዳል።በመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ <<ኤደን>> ደግሞ <<አደን>> ተብሎ መለወጡን አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋና ከተማዋ ሰነዓ ጥንታዊነቷን ለማስረገጥ ከንግስት ሳባ የንግስና ዘመን ጋር ቁርኝት እንዳለው ይጠቀሰል። የመናዊያን ንግስት ሳባ ኢትዮጵያዊ ሳትሆን የመናዊ ነች ብለው ያምናሉ። ግብጾች የእኛ ናት እንደሚሉት ማለት ነው። ሳባ የመን ውስጥ ማሪብ የተባለ ቦታ ቤተመንግስት አላት። ምክምያታቸው ይህ ብቻ ነው። አባቷ ማነው? እንዴት ንግስት ሆነች ምላሽ የላቸውም። ምሁሮቻቸውም ሳባ ኢትዮጵያን አስተዳድራለች እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለችም ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው…ሽንጥ አላቸው እንዴ? እንጃ!.. ብቻ ለአባባሉም ቢሆን እንበለውና ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ።

      በአንድ ወቅት ፋጡማ ሁሬቢ… ከተባለች እንጋፋ የየመን ጋዜጠኛ ጋር የጦፈ ክርክር አድርገናል።
   
    <<ለመሆኑ ኢትዮጵያ በውጭ ንጉስም ይሁን ንግስት የተዳደረችበት አጋጣሚ አለ ወይ? እንደዚህ አይነት ታሪክ አንብበሽስ ታውቂያለሽ? ካልሆነ ግን ድንገት አለም ያለወቀው ታሪክ ልናገኝ ነው ማለት ነው እና ማስረጃውን ስጭኝ?>> አልኳት። <<እምቢኝ!...ያባ ቢላዋ ልጅ ለማን ተገዛንና የመንን የእኛ ንጉሶች ማስተዳደራቸውን እንጂ እኛ በየመናዊያን ስለመተዳደራችን ማን ተናገረና ያለመረጃ ልቀበል?እምቢኝ……የአባት፣ አያቴን ታሪክ መድገም ቢያቅተኝ ጠብቄ እኖራለሁ>> እያለ ውስጤ ፉከራ ይሁን ቀረርቶ ብጤ ፎካከረ። ከሌሎች ጋርም እንዲሁ ተከራክሬያለሁ። እነሱን ለመርታት ከመሞከር ይልቅ ድንጋይ መፍለጥ ይቀላልና በእንጥልጥል እተወዋለሁ።

      ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በ575 ዓ.ም ጀምሮ ንጉስ አብርሃ ለ50 ዓመታት ልጆቹ 20 አመት የመንን ባስተዳደሩበት ወቅት አሁን ያለንባት ሰነዓ ከተማ ለአቢሲኒያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። በዛ ዘመን የተገነቡ ቤቶች ዛሬ ባብል የመን /የየመን በር/ በሚባለው ኦልድ ሰነዓ አካባቢ አሉ። የየመን ዋና የቱሪስት መስህብ ነው። በፎቶው ላይ የምታዩት ማለት ነው። ከአንድ ሺህ አመት በላይ ያስቆጠሩ 14000 ቤቶች አካባቢ አሉ። ሌላው ስለየመን አንስቶ ሳይወሳ የማይታለፍ የእርሻ ዘዴያቸው ነው። ለም አፈር የወርቅ ያህል ውድ ነው። ከመሬቱ ደረቃማነት የተነሳ የሚታዩትን አትክልቶች፣ የእህል አይነቶች ሲያዩ የመናዊያን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ ምስክሮች ናቸው። ለም የሆነውን አፈር ከሩቅ ቦታ ፈልገው ጭነው ያመጣሉ፣ ውሀ ከመሬት ለማውጣት እስከ 300 ሜትር ይቆፍራሉ።ያወጡትን ያጠጡታል፣ የፈለጉትን ይዘሩበታል። ያ- ደረቅ ድንጋያማ መሬት ህዝቡን አጥግቦ ያድራል።

     ሌላም ስለየመን ሲነሳ ሳይወሳ የማይታለፍ አለ።

    ጫት…….ጫት የህዝቡ መንቀሳቀሻ የደም ሴል ነው ማለት ይቻላል። ያለ ጫት ህይወት ያለ የማይመስላቸው ያገኙትን ሁሉ ለጫት የሚያውሉ ጥርሳቸው አልቆ ተፈጭቶላቸው በማንኪያ ሁሉ የሚወስዱ አሉ። በቀን ከ25000 ሺህ ሪያል በላይ /ከመቶ  አስር ዶላር በላይ/ ለጫት ወጪ የሚያደርግ ቤተሰብ በብዛት እንዳለ በአንድ ወቅት የመን ታይምስ ለንባብ ያበቃ መሆኑን አስታውሳለሁ።

    የመን ያለ ሀበሻ ባህሪውን፣ አብሮነቱን፣ መተሳሰቡን፣ ፍቅሩን፣ መተዛዘኑን፣ መደጋገፉን፣ መነቃቀፉን፣ ወሬ መውደዱን፣ ተንኮሉን፣ አብሮ መብላት መጠጣቱን፣ ሀሜቱን፣ በነገር መነቋቆሩን…ይዞ ነው የተሰደደው። ሀበሻ እርስ በእርሱ ፍቅር አለውም የለውምም የሚያሰኙ ብዙ እንከኖች አሉት። እዚህ ያለ ሀበሻ የወሬ ፍቅር አለው።

     ወሬ ይወዳል።

     የምን ወሬ ይወዳል ብቻ ነው? ወሬ በልቶ ወሬ ጠጥቶ፤ ወሬ ቀዶ ወሬ ሰፍቶ ነው የሚኖረው ያሰኛል። የመን ውስጥ ሀበሻ በገንዘብ እና ዕቃ ስርቆት አይደለም የሚታወቀው። ብዙም አይጠረጠርም። ስልክ ሰርቆ በመደወል ግን የሚያህለው የለም። ሱሱ ወሬ ነዋ!! ያማል ያሳማል።

    እዚህ ያለ ሀበሻ ሁሉ ህጋዊ አይደለም። በህጋዊ መንገድ የገባም አይደለም። አገባቡ በሁለት መንገድ የተከፈለ ነው። በባህር እና በአየር ነው የሚገባው። በባህር የሚገቡት የሚደርስባቸውን ስቃይ በተመለከተ ጥቂት ልበል።      
   
      ስለ የመን አሰቃቂ ጉዞ ከዚህ በፊት በባህር ስለሚደረግ ጉዞ፣ ሬሳው በየቦታው ውደቆ፣ የባህሩ ውሀ ሰውነት ላይ የሚፈጥረው ችግርን በተመለከተ …ያሰባሰብኩትን መረጃ በቪዲዮ መልክ አዘጋጅቼው ስለነበር እንድታዩት አስቀምጨዋለሁ። እዩት…
    
                                         በቀጣዩ እንገናኝ……….