Saturday, October 6, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር

  
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል 6ኛ
   እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ሁሉ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ
በግሩም ተ/ሀይማኖት

   ሰላም ወዳጆቼ ነዛር የተባለ ወዳጄ የሰጠው አስተያየት ላይ ...ወዳጄ ግሩም ባለህበት ቦታ ሰላምታዬ ይድረስ፡፡ /እፍኝ ሙሉ ስላምታህ ደርሶኛል/ በጽሁፍህ መግቢያ የገለጽከውን የኩዌት የሞተውን ልጅ ሀዘን ጨምሮ እስከመጨረሻው ያለው ጽሁፍ በጣም ያሳዝናል፡፡ በእርግጥ የኩዌቱ ልጅ ሞት የቅርብ ጊዜ ሀዘን ነው፡፡ እኛም እስከመጨረሻው የማንረሳው ወንድማችን ነበር፡፡ በሀዘን በመረረ ቃልም ነው ሞቱ እውን አልመሰል ቢለኝ በጽሁፍ ያቀረብከውን የሀዘን እሮሮ የጻፍኩት፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ወንድማችንን አጣነው፡፡ ይህ እንግዲ በኔ የደረሰ የቅርብ እውነታ ነው፡፡ ዛሬም ግን ኩዌት ውስጥም ሆነ የተቀረው አረብ ሀገር የዜጎቻችን ግፍ፣ በደል፣ ሞት፣ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሁኖ አንድም ጥሩ ነገር ለመሰማት ጆሮአችን አልታደለም፡፡ እኔማ አንዳንዴ በቃበሻ ዋጋው እንዲህ ሆነ፣ ማነው ይህንን በደል የሚያስቆም? መቼ ነውስ በየአረብ ሀገሩ ለሚንገላታው ዜጋ መላ የሚሰጠው? የውስጤ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡

 ከመቼውም በተለየ መልኩ እርስ በእርሳችን ተጨካከንን ድህነታችንም ከፋ፡፡ማንም አረብ መጫወቻ ሆንን፡፡ ታዲያ የዚህ ችግር መፍቻ ቁልፉ ምንድነው፡፡ በ2004 ወደ አረብ አገር የተሰደደውን ሰደተኛ ብዛት ለአንተ አልነግርህም፡፡ /እሱ ለእኔ ባይነግረኝም እኔ ልንገራችሁ፡፡ በ2011 ብቻ 103.000 ኢትዮጵያዊያን ወደ የመን ገብተዋል፡፡ ይሄ አንድ ሀገር ነው በአጠቃላይ አረብሀገር አስሉት፡፡/ ለኔ ጉድ ያሰባለኝ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ እየተመለስኩ ኤርፖርት ያገኘኋት አንድ የቅርብ ወዳጄ ግን ውስጤን ይበልጥ እንዲሰበር ነበር ያደረገችኝ፡፡ ነርሰ ናት፡፡ በሙያዋም ተቀጥራ ትሰራ ነበር፡፡ አንድ ወቅትም የድግሪ ትምህርቷን ቀጥላ እንደነበረ አጫውታኛለች፡፡ በዛን ሰዓት ሳገኛት ግን በሀገሯ መኖር አማሯት ሳውዲአረቢያ የቤት ሰራተኛ ሆና ለመሄድ ስትል ነበር ኤርፖርት የተገናኝ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንግዲ ምንም የለም፡፡ መጪው ጊዜ ግን እንዲህ አይነት የዜጎች ሰቆቃ የማናይበት እንዲሆን የዘውትር ምኞቴ ነው………ብሏል፡፡ የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡

ያን ተከትሎ አንዲት ልጅ ቻት ስታደርገኝ የመምህራን ኮሌጅ ዲፕሎማዋን ይዛ ታስተምርበት የነበረውን ትምህርት ቤት ተሰናብታ ወደ አቡዳቢ መንጎድዋን ስትነግረኝ መሪር ሀዘን ነው የተሰማኝ፡፡ ሀገር ውስጥ የተማሩት ስራ አጥተው ኮሊንስቶን ይሰራሉ ተብሎ በሚዲያዎች ገኖ መውራቱ ገርሞኝ ነበር፡፡ የገረመኝ መስራታቸውን ተቃውሜ አልነበረም፡፡ ሀገራቸው ሆነው ቢሰሩ ምናለበት በሚል ነው፡፡ ዲፕሎም እና ዲግሪ ይዘው እንደዚህ በሰው ሀገር መገረድን ሲሰማስ ምን ይባላል? በሀገር የተገኘውን መስራት ክብር መሆኑ ይሰመርበት፡፡ ጀምሬው የነበረውን ሀበሻዎች በሉብናን ያላቸውን ህይወት የሚዳስስ ታሪክ ልመለስበት ወደድኩ…. ከዛ በፊት ግን አዜብ የተባለች የፌዝቡክ አንባቢዬ ስልኬን አንኳኳች፡፡ ስከፍተው ጠላታችሁ ክፍት ይበል ልብ የሚያለሰልስ ብርጭቆ ወረቀት የሆነ ድምጽ በጆሮዬ ተንኳለለ፡፡ ‹‹ግሩም /ሀይማት ነህ?›› ስሜን ከእነአባቴ ግሩም /ሀይማት ብላ ስትጠራ../ቤት ክፍል ውስጥ የሚደረግ ስም ጥሪ መስሎኝ ‹‹አቤት!›› ብዬ በጩኸት ላደምቀው ስል ‹‹..ነህ..›› የሚለውን ጨመረችልኝ፡፡ አቤት የኔ ቆንጆ ቲቸር ማን ልበል? አልኳት፡፡ የተደወለልኝ ቁጥር ከየመን ስለሆነ የሚያውቁኝ ናቸው ብዬ ለመቀለድ፡፡

     የሆነ ደስ በሚል ቅላፄ ‹‹አታውቀኝም እዚህ የመን መጥቼ ነው፡፡ ችግር ገጥሞናል፡፡…›› ሳግ ነገር የተናነቃት መሰለኝ፡፡ ‹‹..ሸሽሽ…›› የሚል ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ‹‹..የለ ተሀረኩ..የለ..›› የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ ‹‹አናግሪው ቶሎ በይ..›› የሚል ድምጽ ከጀርባ በደከመ ሁኔታ ይሰማል፡፡ ‹‹ሄሎ ከኤርፖርት ይዘውን ሚግሬሽ እስር ቤት ሊወስዱን ነው፡፡ ምን ትረዳናለህ..እባክህ እርዳን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው፡፡ መመለስ አልፈልግም እባክህ…›› በለቅሶ ታጀበ፡፡ አይኔ ባያነባም ውስጤ ግን አብሯት አነባ፡፡ ቢሆንም መጠየቅ ስለነበረብኝ ከየት ኤርፖርት ነው የያዟችሁ ወዴት ስትሄዱ..

   ‹‹ሰነዓ ኤርፖትርት ላይ ነው የያዙን ወደ ቤይሩት እየሄድን ነበር…›› ተቋረጠ፡፡ ሜግሬሽን ሄጄ ላገኛቸው ፈለኩ፡፡ ያለሁበትን ሱቅ የሚጠብቅልኝ ሰው ስፈልግ ቆየሁና አገኘሁ፡፡ በዚህ አገር አጠራር ጀዋዛት የሚባለው እስር ቤት ሄድኩ፡፡ አሁን ስላወኩት ከፊት ተጠቀምኩኝ እንጂ በሰዓቱ ስሟን ስላልነገረችኝ ማን ብዬ ላስጠራት፡፡ ተጠጋሁና ተደወሎልኝ ነበር ማን ነው የደወለልኝ ስል ‹‹አዜብ..›› አሉ እና ጠሯት፡፡ ትንሽዬ ልጅ መጣች፡፡ እድሜዋ ያለማጋነን 16 ወይም 17 ቢሆን ነው፡፡ ግራ መጋባትና ፍርሃት የተራኩቱት ፊቷን ሳይ አሳዘነችኝ፡፡ ተጨባበጥንና ‹‹ስሜ አዜብ….ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ጓደኛህ ነኝ፡፡ የምትጽፋቸውን ባይም ያለኝ አማራጭ ነው እና ቤይሩት ለመሄድ መጥቼ ኤርፖርት ላይ የእናንተ ቪዛ የተስተካከለ አይደለም ብለው 15 የምንሆነውን ያዙን አሁን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው እባክህ አግዘኝ ስንት ከስክሰን…›› እንባ ቀደማት፡፡ ለስደት ህይወት ማጀቢያው እንባ፣ ብስጭት፣ ፀፀት እና ጭንቀት ናቸው፡፡ የጀመረችውን ትጨርስ ብዬ በዝምታ ዝምታ ውስጥ ሰፍሬ አይኔን ከአንዳቸው አንዳቸው ላይ እያንቀዋለልኩ ጠበኳት፡፡ ብዙ አወራን፡፡

    ይመለከተዋል ያልኩትን ሰው ፈልጌ ላናግር ሞከርኩ፡፡ እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ፡፡ እዚህ ሀገር ግልጽ ሙስና ነው ያለው፡፡ ያበደረህን ገንዘብ የሚጠይቅህ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹ለአንድ ሰው 400 ዶላር ክፈል እና እፈታልሀለሁ..›› ተባልኩ፡፡ ኪሴ ያለችኝ 4000 ሪያል ናት፡፡ በዶላሪኛ ስትሰላ 20 ዶላር ማለት ነው፡፡ አስቡት ልዩነቱን፡፡ ተመለስኩኝ እና ያሉኝን ነገርኳት፡፡ የሚበሉ የሚጠጡት ነገር ገዛዝቼ አቀበልኳቸው እና ብር ከላኩልኝ ደውልላቸው ላለችኝ ሰዎች ደዋወልኩኝ፡፡ አንድ ብር ያሰከረው ጉንጩን በጫት የወጠረ ሰው መጣና ‹‹አንተነህ ያናገርከው?›› አለኝ፡፡ ቢጨንቀኝ እንጂ የማወጣበት ገንዘብ እንደሌለኝ ነገርኩት ‹‹…ሁሉን ከፍዬላቸዋለሁ ማታ ወደ ቤይሩት ይሄዳሉ…›› ማንም አይወጣም ሲል ድንፋታ የምትመስል ነገር ወርውሮልኝ ሄደ፡፡

   ውስጤ እያዘነ ተሰናብቻቸው ከሚግሬሽን እስር ቤት ወጣሁ፡፡ መቼ ነው ፈጣሪ የሚሰማን? መቼ ነው እንባችን ስፍሩን የሚሞላው? መቼ ነው በቃ! የሚለን? እውን መንግስት ቤይሩት መሄድን አስቦበት ነው የከለከለው? ከሆነ ይህን አይነት ድርጊት ሲፈጸም እንዴት አያውቅም? በኬንያ ቪዛ እንዴትስ የመን ሊመጣ ይችላል? የመሳሰሉትን አሰብኩ፡፡ ከማሰብ ውጭ ግን ምን አመጣለሁ? በቀረችኝ ሳንቲም ታክሲ ተሳፍሬ ጉዞዬን ስቀጥል ስለ ቤይሩት የሰማሁትን ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ያሰላሰልኩት ብዙ ነው ባለፈው ወደጀመርኩት ታሪክ ልንጎድ…..     
          
   በተከታታይ በቻት ሳጥኔ ሳትታክት እየጻፈችልኝ ያለችውን እህታችን ደግሜ ላመሰግናት ወደድኩ፡፡ ቀጠልኩ.. ከላይ እንደገለጽኩልህ ልጅቷ የተሰጣት መልስ ጥሩ ስላልሆነ መፍትሄም ስላጣች ያላት አማራጭ መጥፋት ነበርና ጠፋች፡፡ ጠፍታም ለረጅም ጊዜ የተለያየ ቤት ሰርታለች፡፡ ካንዱ ስትወጣ ስራ አጥታ ረጅም ጊዜ ስትቀመጥ ብዙ ተቸግራለች፡፡ አሁን ያለችበት ቤት ሁለት አመቷ ነው፡፡ ሰውዬው ደስ ሲለው ይከፍላታል ሲያጣ ይከለክላታል፡፡ እንደዛም ሆና እንደነገረችኝ ልጅዋን በጥሩ ሁኔታ እያስተማረች ነው፡፡ ወላጆች ግን ልጄ ምን ሰርታ ነው ብሩን ያመጣችው አይሉም፡፡

   የእኔውን ቤት ጉድ ደግሞ ልንገርህ…እኔ የነበርኩበት ቤት 3 ሰው ብቻ ነው ያለው፡፡ ቀን ቀን አይውሉም፡፡ ሴትዮዋ መጥፎ የምትባል አይደለችም፡፡ ልጁ ተማሪ ነው፤ እሷ ስራ አላት፡፡ ወንድሟ ደግሞ የቤተሰብ ድርጅት ውስጥ ይሰራል፡፡ ታዲያ ግን ቤት ውስጥ ስራው ማለቂያ የለውም፡፡ የምተኛው ሌሊት 7 ሰዓት ነው፡፡ የቀኑን ወደ ሌሊት ገልብጠውታል፡፡ ቀን ቀን ቤት ስለማይውሉ ስራ ብዙም አያስቸግረኝም፡፡ ከ10 ስዓት በኋላ ግን መቀመጥ እስኪያቅተኝ በስራ ያጣድፉኛል፡፡ በዛ ላይ ከ7 ሰዓት በኋላ ያለውም ቢሆን መተኛት አትበለው፡፡ ልጇ ቀበጥ ነገር ነው፡፡ የ11 አመት ልጅ ቢሆንም አጠገቡ ያለውን ውሀ ማንሳት አይፈልግም፡፡ መጥሪያውን ተጭኖ ይጣራል፡፡ እንደሰው መተኛት ያለብኝ አይመስለውም፡፡ እሱስ ባልከፋ እንቅልፍ ነው የነሳኝ ሱሰኛ የሆነው ወንድሟ ሌላ ፈተናዬ ነበር፡፡ ፍላጎቱ የተወጠረ ስሜቱን ማርገብ ነው፡፡ ለእኛ ያለው አመለካከት በንቀት የተሞላ ነው፡፡ በቃ! ለስሜት ማስከኛ የተፈጠርን እቃዎች ነው የምንመስለው፡፡

    አንዳንዶቹ በፍርሃትም ይሁን በፍላጎት ፍቃደኛ ስለሚሆኑላቸው መሰለኝ ‹‹..አንቺ ከሌሎቹ በምን ትበልጫለሽ? በፊት ከነበሩት ውስጥ እከሊትን..እከሊትን እንዲህ አደርግ ነበር ይለኛል ስማቸውን እየጠራ፡፡ እሺ እንደማልለው ሲያውቅ ሁሌም ይዝትብኛል፡፡ ለሴትዮዋ የሆነ ያልሆነውን ይነግራታል፡፡ በዚህ ምክንያት ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ቤት ትቆልፍብኝ ነበር፡፡ በዚህ በጣም ስማረር ቢሮ ሌላ ቦታ እንዲቀይሩኝ ነገሬ ተቀየርኩ፡፡ የተቀየርኩበት ቤት የሚገርምህ ጥቁር አትወድም፡፡ የወሰደኝ ባልዋ ነበር፡፡ ከእኔ በፊት የነበረችው ማዳጋስካራዊ ቀላ ያለች ነበረች፡፡ ከእኔ ጋር አንድ ፊሊፒኒሳዊ ተቀጥራለች፡፡ ሁለት ነን ማለት ነው፡፡ እኔ 4 ልጆቿን እይዛለሁ ፊሊፒንዋ ቤት ታጸዳለች፡፡ ምግብ ቤት ውስጥ አይሰራም፡፡ እዛ ፎቅ ላይ ያሉት ሁሉ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ልጆቹ አያቶቻቸው የሰሩትን ነው የሚበሉት፡፡ አባትየው የት እንደሚበላ አናውቅም፡፡ እሷ ከልጆቹ ጋር ትበላለች፡፡ እኔና ፊሊፒኗ በመሀል ፍዳችንን በላን፡፡ አንድ ሴጣናም ልጅ አላቸው እሱን ይዤ ስንቀዋለል ነው የምውለው፡፡ ከፊሊፒንስዋ እንዲያውም እኔ እበላለሁ፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ አያት ቤት ያለችው ሀበሻ ነች፡፡ እስዋ ትሰጠኛለች፡፡ የምግቡ እና የልጁ ሁኔታ ሲመረኝ ጠፋሁ፡፡

    ከመጥፋቴ በፊት እሰራበት የነበረው ቦታ ከፊት ለፊት ያለው አፓርትማ ላይ ያለችው ደግሞ ጠዋት11 ሰዓት ተነስታ ስራ ትጀምር እና ሌሊቱን ሁሉ አትተኛም፡፡ ስራ ባይኖር እንኳን እህቶቿ ጋር ትወስዳታለች፡፡ ሌላም እታች ያለች ኢትዮጵያዊት አለች፡፡ እሷ ደግሞ ከማንም ጋር እንድትገናኝ አትፈቅድላትም፡፡ መውጫ ሰዓታቸውን ጠብቃ ነው ወደ እኛ የምትመጣው፡፡ የእሷ አሰሪ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ፓንቷን እንኳን ማውለቅ አትፈልግም፡፡ ለሁሉ ነገር ጥሪ ነው፡፡ ቤቱን ካጸዳች በኋላ ሴትዮዋ ቼክ ታደርጋለች፡፡ በዚህን ጊዜ አውቃ ግርግዳው ላይ ወይም ሶፋ ስር ቆሻሻ ታደርግና አልጸዳም ብላ ታሰቃያታለች፡፡ ከጨረሰች እኛ ያለንበት አፓርትማ ላይ እህቷ ስላለች እሷም ጋር ታሰራታለች፡፡ ከጠፋሁ በኋላ ግን ምን ላይ እንዳለች አላየኋትም፡፡

     አሁን የምሰራው ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ ነው፡፡ ያለሁበት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ስራቸው ግን ያስጠላል፡፡ ሴትነታቸውን ይሸቅጣሉ፡፡ ከተማውን እንደጨረስክ ያለው ቦታ ነው የሚሰሩት፡፡ እዚህ ያሉት ሶሪያዊያን ሲነግሩኝ በ50.000 የሉብናን ገንዘብ ነው የሚሰሩት፡፡ ይህ ማለት 27 ዶላር አካባቢ ባለ ዋጋ ራሳቸውን ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዴ ግን ቢዝነስ ቢሰሩ አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱን ቤት ሰራተኛነት ከጀርባው ያለውን ችግር ስታይ የግድ የሚገፋቸው ነገር ታያለህ፡፡ የዛኑ ያህል የሚያናድዱኝ በነጻ ቪዛ መጥተው በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩት ናቸው፡፡ አሁን የምሰራበት ቦታ ሶስት ወንዶች ናቸው የሚሰሩት እኔ ብቻ ነኝ ሴት በየአመቱ ለሶስት ወር የሚያግዛቸው አንድ ሴት ይቀጠርላቸዋል፡፡ ልክ አሁን እኔ እንደተቀጠርኩት፡፡ ታዲያ ከባንግላዲሾች እና ሶሪያዎች ጋር በማይረባ ብር ይተኛሉ፡፡ ሁሉ እንደ እነሱ ስለሚመስላቸው በእርካሽ ትገኛላችሁ ይላሉ፡፡

   ይወራ ከተባለ ለጉድ ይወራል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ካሉት መካከል ወገናቸውን የሚሸጡ የመኖራቸውን ያህል ለሰው ችግር ቆዳቸውን የሚገፈፉ ጥሩ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ኤቢ ደመቀ በአብዛኛው የመን ባለ እና የመን በነበረ ሰው ዘንድ የሚታወቅ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ዮሀንስ ተስፋዬ /ጆኒ/ የሚባል ልጅ አለ፡፡ ከረንቦላ ቤት ስለነበረው ጆኒ ከረንቡላ ይሉታል፡፡ ከባህር የመጡትን ከረንቡላ የሚያጫውትበት ቤት ውስጥ ከማሳደር አንስቶ የማይሰራው በጎ ስራ የለም፡፡  በተጨማሪ ኩሩቤል የሚባል ኢትዮጵያዊ UNIDOM የተባለ ድርጅት አዋቅሮ ብዙዎችን ለመርዳት ሞክሯል፡፡ ስለእነዚህ ሰዎች በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ አሁን ያነሳኋቸው ቀጣይ ለማቀርበው ታሪክ ምክንያት ስለሆኑኝ ነው፡፡ በሚቀጥለው በቀጠሮ እንገናኝ
                        ሰላም ሰንብቱ 

Tuesday, August 28, 2012

የአቡነ ጳውሎስን ሞት ስሰማ ሶስት ነገሮች ታወሱኝ
የአምላክስራ ግሩም

ከፈጣሪያቸው ይልቅ ቀጣሪያቸው መለስን ይፈራሉ የሚባሉት የአቡነ ጳውሎስን ሞት ስሰማ ሁለት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ቀጣሪያቸውን ያልኩት በአንድ ወቅት ጳጳሱ የሲኖዶሱን ህግ ሊቀይሩ ፈልገው በተነሳው ውዝግብ ዙሪያ አለቃ አያሌውን ቃለ-ምልልስ ስሰራ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖና ውጭ ጳጳስ በህይወት እያለ በመንግስት የተቀጠሩ ቀኖና የሻሩ ናቸው ስላሉኝ ነው፡፡

የአቡነ ጳውሎስም ሞት ስሰማ ትዝ ያሉኝ ሶስት ነገሮች…አንደኛ ተወልጄ ያደኩበት ሰፈር ቅ/ማሪያም ቤተክህነት ፊት ለፊት በመሆኑ ሲወጡ ሲገቡ ወታደራዊ ሰላምታ እየሰጡ ‹‹ታጋይ ጳውሎስ!..›› የሚሉዋቸው ሁለት ልጆች ታወሱኝ፡፡ ሁለተኛው በሳቸው ጠባቂዎች እንደተገደሉ የሚነገረው ባህታዊ እና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መጥተው ከፊቴ ድቅን አሉ፡፡ ሶስተኛው በጎንደር ሀገረ ስብከት ውስጥ የተሰራውን ሙስና አጋልጨ በእሳቸው እና በዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴ ከሳሽነት ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እኔና ጓደኛዬ ላይ የተፈጸመብን ግፍ ታወሰኝ፡፡ ለሶስቱም ትዝታዎቼ ምክንያት አለኝ፡፡ በተለይ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የተደረገብኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከህሊናዬ የሚፋቅ አይደለም፡፡

በዕለተ ሀሙስ አረብ ሳይት ላይ ብቅ ጥልቅ የሚጫወተው ኢቲቪ ድብብቆሽ ጫዎታውን ስለቀጠለ ሀገሪኛ መረጃ የሚያቀብለን ብቸኛው ኢቢኤስን እያየሁ ነው፡፡ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው በተፈጸመበት ወቅት ብዙ እውነት የማይመስሉ ሙገሳዎች ከአስተያየት ሰጪዎች ሰማሁ፡፡ እውነት ለእሳቸው ነው ሌላ የማላውቀው አቡን ሞተዋል ያስብላል፡፡ መቼም ከተጠናወተን መጥፎ አመል ውስጥ ሰው ሲሞት ጨካኙን ደግ ሌባውን ንጹህ ማድረግ፣ ሰው ያልሆነውን ነው ብሎ መካብ ዋነኛው በሽታችን ነው፡፡ ምናለ ዋሽተን ያልሆኑትን ከምንቀባጥር ዝም ብንል በዝምታ፡፡ መቼ ይሆን አካፋን አካፋ የምንለው? ‹‹..ካልሆነም ዝም አይነቅዝም..›› ይባላል እኮ፡፡ በተለይ አንድ መምህር/ሰባኪ/ ነኝ ያለ ሰው አድርባይነቱ ሳይሆን በዚህ ውሸትን ባዘለ አንደበቱ የሚሰብከው እንዴት ይሆን? የሚል እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ በቲቪው ፕሮግራም ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ መሰራት ያለበትን ነው የሰሩት፡፡ የሰዎችን ሀሳብ መገደብ የለበትምና..ስለሳቸው ግን ከተባለው ውጭ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እኔ ግን የማስታውሰው እና የማውቀው እውነታ ተቃራኒ ነው….

ትዝታ አንድ፡- በቅጽል ስማቸው ፑሲ እና ነጬ በመባል የሚታውቁት ልጆች በይፋ ወታደራዊ ስላምታ እየሰጡ ‹‹ታጋይ ጳውሎስ!!›› ይበሉ እንጂ የአካባቢው ሰውም ሆነ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና የሚያውቁ በድብቅ ይህን ከማለት ወደኋላ አላሉም ነበር፡፡ በወያኔ መመረጣቸው ብቻ ሳይሆን በፖሊስ ዲፌንደር መኪና ከፊት ከኋላ መሳሪያ ባነገቡ ጠባቂዎች ከመታጀባቸው ጀምሮ ታጋይ ጳውሎስ የተባሉበትን ነገር ከዘረዘርኩት ጊዜም ቦታም አይበቃም፡፡ በቲቪ ካየኋቸው አስተያየት ሰጪዎች መካከል ‹‹..ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ፣ ለጋስ፣ ደሀ ረጂ..፣..›› ምንትሴ..ቅብርጥሴ የሚሉ ግነት የሞላቸው ነገሮች ናቸው ይህን እንዳስታውስ ያደረገኝ፡፡ በተለይ ‹‹..ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ…›› የምትለው ነገር አልዋጥልህ አለኝ፡፡ ገዳማት ሲፈርሱ የታገሉት ትግል ስለመኖሩ መረጃ ስላጣሁ ነው አልዋጥልህ ያለኝ፡፡ ለቅዳሴ ጧፍ የሚያጡ ደብሮች ባሉዋት ኦርቶዶክስ ባጀት ጥይት የማይበሳው ፍሪጅና ስቶቭ ያለው ሶስት መኪና ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተው ሲያስመጡ ይህም ሀይማኖትን መውደድ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው በእሱ ቤት ያደረ አገልጋይስ በጋርድና መሳሪያ መጠበቁ ሀይማኖቱን ወይስ ራሱን መውደዱን ያሳያል? ለነገሩ ራሳቸውን መውደዳቸው አይደል የራሳቸውን ሀውልት ሲኖዶሱ ሳይፈቅድ እየተቃወማቸው ያቆሙት?

ትዝታን ትዝታ ሲስበው ከእሳቸው በፊት በነበሩት በአቡነ ተ/ሀይማኖት ጵጵስና ዘመን ለዘመን መለወጫ ገብቶ ገንዘብ ያልተቀበለ የአካባቢው ልጅ የለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጳጳስ ምን እንደሆነ እንኳን በማላውቅበት ሰዓት ነፍሳቸውን ይማረውና ልጆች እንግባ…እንግባ ብለውኝ ቤተክህነት ገባን፡፡ አሁን ስማቸውን የማላስታውሰው..ዘበኛ አሰላፊነት ተሰልፈን አቡነ ሰላማ ይመስለኛል ስማቸው ይዘውን ገቡ፡፡

ክስት ባለ ሰውነታቸው ላይ ልዩ ግርማ ሞገስ የተላበሱት ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ተ/ሀይማኖት መስቀል እያሳለሙ የክርስትና ስም ይጠይቁን ጀመር፡፡ ተራዬ ደርሶ ክርስትና ስሜን ተናግሬ መስቀል ተሳለምኩ፡፡ ከእየሩሳሌም የመጣ መስቀል በክር በክር ተደርጎ አንገታችን ላይ እያጠለቁልን አስር አስር ብር ሰጡን፡፡ እንደ ሀይማኖት አባትነታቸው..እኛም እንደ ልጅነታችን ማን እንደጀመረ ባላስታውስም ዝቅ ብለን እግራቸውን እየሳምን ወጣን፡፡ በዚህ ጊዜ ያስተዋልኩት አሁንም የማስታውሰው ጫማ አለማድረጋቸውን እና እግራቸው ልስልስ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ነገር ሲገርመኝ ስላደኩ ነው መሰል በአንድ ወቅት ቤተክህነት ይሰሩ የነበሩ የጓደኛዬን እናት ጠየኳቸው፡፡ ደርግ ይሰሩልኛል ብሎ ቢመርጣቸውም እንደፈለገው ሳይሆን እንዳልፈለገው ሆነው ተገኙ፡፡ የአራት ኪሎው ቅዱስ ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ደውል ፓርላማ ውስጥ ስለሚበጠብጥ ተብሎ እንዳይደወል ታገደ፡፡ ቀጠለናም መውጫ በሩ በግንብ ተዘጋ፡፡ ለማስከፈት ያደረጉት ትረት ሰሚ አጣ፡፡

በዚህን ጊዜ ያ-የተዘጋ የቤተክርስቲያን በር እስኪከፈት ጫማ ላለማድረግ እና ከጥራጥሬ ውጭ እህል ላለመብላት ቃል ገብተው እስከሞቱበት ዕለት የተዘፈዘፈ ሽንብራ እና ጥራጥሬ እየበሉ ኖሩ፡፡ ታዲያ ትዝታዬ ብቅ ያለው የአሁኑ ደግ ለሀይማኖታቸው ተቆርቋሪ የተባሉት ዋልድባን የሚያክል ገዳም ሲጠረመስ እንኳን ድምጻቸውን አልሰማሁም፡፡ አቡነ ተ/ሀይማኖት በደሞዛቸው የሚያስተምሯቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ልጆች ነበሩ፡፡ በአካባቢያችን ልጁን ማስተማር ያልቻለ ሰው ማመልከቻ አጽፎ ሲሄድ ይረዱ ነበር፡፡ አሁን ደግ፣ ለጋስ ሲባሉ የሰማሁት አቡነ ጳውሎስ ግን ደሞዛቸውን ከአቡነ ተክለሀይማኖት በሶስት እጥፍ ቢያሳድጉም ባጀት የለም በሚል ግንፍሌ ድልድይ ጋር የነበረው የልጆቹን መኖሪያ የአቡነ ገሪማን ፊርማ ባዘለ ደብዳቤ ከረቸሙት፡፡ ቦታው ለቢሮ እና ለተለያየ ነገር እንዲውል ሆነ፡፡

ትዝታ ሁለት፡-እለቱ ሀሙስ መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ ቦሌ ማተሚያ ቤት ጋዜጣ ለማሳተም ልሄድ ስል ግርግር እስጢፋኖስ ጋር አየሁ፡፡ ዕለቱ የእሲጢፋኖስ በዓል የሚከበርበት በመሆኑ ብዙም ትኩረት ሳልሰጠው ነበር ያለፍኩት፡፡ ቦሌ ማተሚያ ቤት ስደርስ ግን ጳጳሱ አንዱን ባህታዊ ገደሉ የሚል ግነት የተሞላበት መረጃ ደረሰኝ፡፡ ለማተሚያ ቤቱ ካሜራ ክፍል የምሰጠውን ሰጠሁና ለማጣራት ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ተመለስኩ፡፡ ሰዉ ሁሉ የሚያወራው የተምታታ ሆነብኝ፡፡ ቦታው ላይ ከነበረ ሰው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አቃተኝ፡፡ አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይደግመውም፡፡ ጠባቂያቸው እንጂ እሳቸው አይደሉም የሚለው ሀሳብ ደጋግሞ ደረሰኝ፡፡ ወደ ቦሌ ማተሚያ ቤት ተመልሼ የጋዜጣውን ህትመት እየተከታተልኩ ሳለ ድካም ተሰማኝ እና ማሙሽ የሚባል ልጅ፣ ጌታመሳይ ገ/መስቀል ማራቶን የሚባል የስፖርት ጋዜጣ የሚከታተል ልጅ ወደ ተቀመጡበት ተቀላቀልኩ፡፡ ወሬው ስለዚሁ ጉዳይ ነበር አንድ በትክክል ቦታው የነበረ ልጅ ስለነበር ትክክለኛ መረጃ ሰጠን፡፡ በጠባቂዎቻቸው ነው ባህታዊው የተገደሉት መባል ብቻ ሳይሆን የብረት አንካሴያቸውን እየወዘወዙ ወደ ጳጳሱ በማምራታቸው እንደሆነ ችግሩ የተከሰተው ሰማሁ፡፡

ዋናው ነገር ግን ይህ አልነበረም፡፡ የተገደሉትን ባህታዊ ማንኛውም ቤተክርስቲያን ለቀብር ቦታ እንዳይፈቅድ ተወገዘ፡፡ እኝህ ባህታዊ ጳጳሱን እንኳን ሊገድሉ አስበው ቢሆን በቀልን ምን አመጣው? በቀል ካልሆነስ የሚቀበሩበትን ቦታ መከልከሉ ምን ይሆን ጥቅሙ? ፈረንሳይ ለጋሲዮን እየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ራስ ካሳ ቤት ተገኝቶ ህዝቡ በዘልማድ ጭቁኑ ሚካኤል የሚለው ቤተክርስቲያን የቀብር ቦታ ፈቀደ፡፡ የደብሩ አስተዳደር ተወገዙ፤ ቤተክርስቲያኗ ከሲኖዶስ ትዕዛዝ አፈንግጣለች ተባለ፡፡ በመወገዝ ብቻ አልበቃም አመታዊ የጥምቀት በዓልን ታቦቱ ከሌሎቹ ታቦታት ጋር ጃንሜዳ እንዳይወጣ ታገደ፡፡ ሐምሌ አስራዘጠኝ ማናፈሻ ጀርባ በቀበሌ 22 መዝናኛ ገባ ብሎ የማርያም ፀበል ያለበት ቦታ ከአድባራቱ ተነጥሎ አደረ፡፡ የሚገርመው ግን የኢየሱስ ደብር ታቦት ሚካኤልን ጥሎ ከሌሎቹ ጋር ጃንሜዳ አላደረም፡፡ እዛች አነስተኛ ቦታ ላይ አብረው አደሩ፡፡ ህዝቡም በእልህ አድምቆት አደረ፡፡ አስታውሳለሁ እኛም ጃንሜዳ ቢሆንም ያመሸነው አዳር ያደረግነው እዛ ነው፡፡ እንኳን ሰው ታቦት በሚያግዱት ጳጳስ ማን አስተዳድሩ አላችሁ ብለው ለእየሱስ ደብር ካህናት ዋጋቸውን ሰጡዋቸው፡፡

ትዝታ ሶስት፡- ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በጦርነቱ ለተጎዱ ቤተክርስቲያናት ማደሻ ከጎንደር አገረ ስብከት ጽ/ቤት ጥያቄ ቀረበ፡፡ በወቅቱ ጠ/ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ነበር ጥያቄው የቀረበው፡፡ ምንም አይነት ባጀት የለንም 10 ቶን ቡና ተፈቅዶላችኋል እሱን ወስዳችሁ ሽጡና በትርፉ የተወሰኑትን አድሱ ተባለ፡፡ ይሄን ቡና ወስዶ የመሸጡን ሀላፊነት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴን ወከሉ፡፡ ቡናው ተሸጦ ግን ለቤተክርስቲያኗ ማደሻ ሳይሆን ለአፍ ማሰሻ፣ ለኪስ ማደለቢያ ነው የሆነው፡፡

ቢታይ ቢታይ ሁሉም ዝም..ሆነ፡፡ ነገሩ የከነከናቸው አንዳንድ ካህናት ቤተክህነት ድረስ ለክስ ከጎንደር መጡ፡፡ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ተባሉ፡፡ መፍትሄም ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በዚህን ጊዜ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ አሳትም ነበረ እና ሙሉ መረጃውን ሰጡኝ፡፡ አጣርቼ ትክክለኛ ማስረጃ በመሆኑ ለህዝብ አቀረብኩት፡፡ የመረጃውንም ኮፒ ጋዜጣው ላይ አቀረብኩ፡፡ ወዲያው በብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ክስ ተከፈተብኝ፡፡ የክሳቸው ፍሬ ሀሳብ ትክክለኛ እና መጠየቅ ያለበትን ነው የጠየቁት፡፡ ‹‹ገመና›› የተባለ ጋዜጣ ያወጣውን ዘገባ አይተን ሁኔታውን ለማጣራት ሞክረናል፡፡ የተጠቀሱት ግለስብ የቀረበብኝ ማስረጃ ፎርጅድ ነው እኔ ስለሁኔታው አላውቅም ስላሉ ጋዜጠኛው ላይ ክስ ተመስርቶ ያለው ማስረጃ እንዲረጋገጥ፡፡ ትክክለኛ ከሆነ የጉዳዩ ባለቤቶች እንዲጠየቁ፡፡ ያቀረበው ማስረጃ ትክክለኛ ካልሆነ እና ፎርጅድ ከሆነ የእምነታችንን ክብር የሚያወርድ ነገር በሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረቡ እንዲጠየቅ..ይላል፡፡ በዚህ ክስ ቅሬታ የለኝም፡፡

ለመርማሪ ፖሊሱ ግን ገንዘብ ሰጥተው ትንሽ ቅጣትም ያሰፈልጋቸዋል፡፡ በደንብ መርምርልኝ ማለታቸው ከሀይማኖት አባት የሚጠበቅ ይሆን? ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀምብኝ አድርገዋል፡፡ ክትትል ሲደረግብኝ ቆይቶ ዘውዲቱ ሆቴል ራት እየበላሁ ሳለ ተያዝኩ፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ ገና ከመግባቴ ጀምሮ ዱላ ተቀበለኝ፡፡ ውብሸት የሚባል መርማሪ ወዲያው ስልክ ደውሎ መያዜን ሲናገር ከቢሮው ውጭ ብቀመጥም እየሰማሁት ነው፡፡ ቃል ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኔ ሶስት ፖሊሶችን ጠርቶ ከራሱ ጋር አራት ሆነው ሰማይ ምድሩ እስኪዞርብኝ አዞሩኝ፣ ቀጠቀጡኝ፡፡ በግድ ግን ቃሌን ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆንኩም፡፡ መረጃው አለህ? ያለህ መረጃ ፎርጅድ ነው ተብሏል፡፡ እላዩ ላይ ያለው ማህተም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አይደለም አለኝ፡፡ /አንድ ወረቀት ላይ ያረፈ ማህተም እያሳየኝ/ የእሳቸው ማህተም ይሄ ነው ..››ሲለኝ ግን እልህ ያዘኝ፡፡ ማህተሙን ከዚህ ወረቀት በኋላ መቀየራቸውን የሚያረጋግጥ ትንሳዔ ዘ ጉባኤ ማተሚያ ቤት ማህተም ያስቀረጹበት ማስረጃ እንዳለኝ ጭምር ቃል ሰጠሁ፡፡ ይህንን የሰጠሁትን ቃል ግን ወዲያውኑ ደውሎ የነገራቸው ፊቴ ነው፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ተከሳሽ የሆነው ዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴ ጉዳዩን እንዲከታተል በእሳቸው ፍቃድ ተላከ፡፡ በዛው ማታ መጣ፡፡ ይሄኔ ነገሮች ሁሉ ጎረበጡኝ፡፡ በጣም ተጠራጠርኩ፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ቤቴ ሄደን መረጃውን እንድናመጣ ፈለጉ፡፡ ግደሉኝ እንጂ አልሄድም እናቴ በዚህ ሰዓት እንድትደነግጥ አልፈልግም አልኩ፡፡ ሰበቤ በእናቴ ሆነ እንጂ እሳቸውስ መረጃው እንዲጠፋ ካልፈለጉ እንዴት ብሩን ያጨበረበረውን ሰው ይልካሉ? ለምንስ እሰኪነጋ መጠበቅ ሳይፈልግ ዲያቆን ደሳለኝ መጣ? ፍርድ ቤት ስቀርብ ካልሆነ ላለማቅረብ ወሰንኩ፡፡ ዳግም ዱላ ተጀመረ፡፡ እነሱ ሳይበቃቸው እኔ ተዝለፍልፌ ስለወደኩኝ መሰለኝ ድብደባው የተጠናቀቀው፡፡ ራሴን ስለሳትኩ እንዴት እንደነበር አላውቅም፡፡ ራሴን ሳውቅ ግን ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ሽንቴ ስለመጣ ካጋደሙኝ አግዳሚ ወንበር ላይ ቀና ብዬ ሽንት ቤቱ የቱ ጋር እንደሆነ ተራኛውን ፖሊስ ጠየኩት፡፡ አሳየኝ እና ተነስቼ ስሄድ ውሻዋን ጃስ..ጃስ..ብሎ ሲያደፋፍራት እግሬን ዘነጠለችን፡ ወይም ዘነጠለኝ፡፡ የውሻውን ፆታ ስለማላውቅ ነው ሁለቱንም የተጠቀምኩት፡፡ እየተሳሳቁ ደግፈው አንስተውኝ ጊቢው ውስጥ ቆማ የበሰበሰች እና ሽንት የሚሸናባት አይጥ የሚርመሰመስባት አሮጌ መኪና ውስጥ ከተቱኝ፡፡ በማግስቱ ጓደኛዬ ዳንኤል የጋዜጣዬ ዋና አዘጋጅ ስለሆነ መታሰሬን ሰምቶ ፖሊስ ጣቢያ መጣ፡፡ ሳምንት ሙሉ እዛች የሚሸናባት መኪና ውስጥ አሳለፍን፡፡

ይህን ሁሉ የምለው ግን አስተያየት ሰጪዎቹ እና እሳቸው ይመሳሰላሉ ወይ? ወይስ አዲስ የሚመረጡትን ይሆን የሚያሞግሱት የሚለው እሳቤ መቶብኝ ነው፡፡ ምናለ እውነትን ለሰው ብለን ባንደፈጥጥ..ሰው ለማስደሰት ዋሽተን ፈጣሪን እያሳዘንን መሆኑን አትረሱ፡፡ ሙት አይወቀስም ብለንም ከሆነ ያልሆነ ቀባጥረን ከፈጣሪ ከምንጣላ ዝም ማለት አይቀልም?
ነብሳቸውን ይማር!!!!