Sunday, May 13, 2012

እስክንድር ነጋ
      በግሩም ተ/ሀይማኖት
    ትግል ውጤቱ መራር እና ጣፋጭ ነው፡፡ ጣፋጩን ለማግኘት ከባዱን ጎዳና መጓዝ ግድ ይላል፡፡ እስክንድር ነጋ የታገለበትን ውጤት አዝመራውን አጭዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ነፃ-ፕሬስ ጋር ከመጀመሪያው ጀምሮ የታገለ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አሁን የወያኔ መንግስት ‹‹አሸባሪ›› የሚል ታፔላ ለጥፎለት በእስር ላይ ቢሆንም ድሉን ማጣጣም የቻለው የፔን ኢንተርናሽናል ሽልማትን ለማግኘት በመብቃቱ ነው፡፡ እሱ በእስር ላይ ቢሆንም ባለቤቱ እና የልጁ እናት ሰርክዓለም ፋሲል ሽልማቱን ተቀብላለች፡፡ እጅግ ደስ የሚል ዜና ስንሰማ ይህ የመጀመሪያችን አልነበረም፡፡ የኢትኦጵ ጋዜጣ አሳታሚ ሲሳይ አጌና አምና ተሸላሚ ነበር፡፡ መንግስት ‹‹አሸባሪ›› ይላል አለም ግን በስራቸው ሽልማት እንደሚገባቸው አምኖ ይሸልማቸዋል፡፡ አለም የተቀበለውን የማይቀበል፣ ሁሉ ያየውን የሚክድ ምን አይነት ቀጣፊ ብድን እንደሆን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድራት ማወቅ አቅቷል፡፡ እንደ እስስት መልኩን እየቀያየረ እንደ እባብ ቆዳውን እየሸለቀቀ አጭበርብሮ ማለፍን ተግባሩ አድርጎታል፡፡  
      እስክንድር ነጋም ሆነ ሌሎች ጋዜጠኞች ‹‹አሻባሪ›› የሚል ምክንያት ተፈጥሮ የሀሰት ክስ መከሰሳቸውን ማንም የሚያውቀው  እውነት ነው፡፡ ቀጠሮ በቀጠሮ እየተራዘመ በእስር ላይ ሆነው ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጠረባቸው እስካሁን ውሳኔ ሳያገኙ አሉ፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በተደጋጋሚ ፍ/ቤት ሲቀርብም በሀሰት ስለመከሰሱ እየተናገረ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለፍ/ቤት ያቀረበውን ቃል እንደማጣቀሻ ላሳይ ወደድኩ፡፡ <<….አቃቤ ህግ ያቀረበብኝ የፅሁፍ ማስረጃዎች ሲቃኙ፣ በጋዜጣና በኢንተርኔት የወጡ 6 መጣጥፎች፣ በሀገር ውስጥ ከሚታተሙ ጋዜጦች ጋር ያደረኳቸው 2 ቃለ-ምልልሶች፣ በአሜሪካ፣ በካናዳና በስዊድን ሀገራት ካሉ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ፓልቶኮች ጋር ያደረኳቸው ቃለ-ምልልሶች ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም እንዴት እንደሚመለከተኝ ግልፅ ባይሆንልኝም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በስዊድን ሀገር ያደረጉት ንግግርና ይልማ በቀለ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር ያወጡት አንድ መጣጥፍም በማስረጃነት ተቆጥረውብኛል፡፡
    <<…እነዚህን ሁሉ በዝርዝር መቃኘት አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም፣ For the record በስሜ የወጡት መጣጥፎችና የሰጠኋቸው ቃለ-ምልልሶች የእኔ የሆኑና እስካሁን ድረስ ያለምንም ማሻሻያና መሸራረፍ ሙሉ ለሙሉ የማምንባቸው ናቸው፡፡ ዓላማቸው ብጥብጥ ማስነሳት አልነበረም፡፡ በሀገራችን የህልውና ጉዳይ የሆነውን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር የሚመክሩ፣ የሚማፀኑ፣ የሚገስፁ፣ የሚለምኑና መንገዱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የአውራ ፓርቲ ግንባታ ሙከራ በሀገሪቷ አንድነት ቁማር መጫወት ነው፡፡ እንደ አንድ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ዜጋና ጋዜጠኛ ድምፄን የማሰማት ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ኃላፊነቴንም ተወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእኔ የሚጠበቀው የምከፍለው ዋጋ ካለ በፀጋ መቀበል ብቻ ነው፡፡
     <<ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ አንድነትና ፍቅር ለሀገሬና ለህዝቧ እመኛለሁ፡፡>> ብሎ ነበር፡፡ እዚህውስጥ የነጠረ እውነት በጉልህ ይታያል፡፡ ሁሉም ልብ ሊለው ምን እየሰራሁ ነው ብሎ ዞሮ የሰራውንም ለሀገሩ ህዝብ ያደረገውንም ማያ አንገት ካለው እንዲያይ የሚያደርግ ነው፡፡ ለእኔ ወርቃማ አባባል ያልኩት
‹‹…እንደ አንድ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ዜጋና ጋዜጠኛ ድምፄን የማሰማት ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ኃላፊነቴንም ተወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእኔ የሚጠበቀው የምከፍለው ዋጋ ካለ በፀጋ መቀበል ብቻ ነው፡፡…›› ጣፈጠንም መረረንም እውነታው ይሄ ነው፡፡ ሌሎችም ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባው እውነታ ይህ መሆኑን ደጋግሜ አሰምርበታለሁ፡፡ ዝም ብለን ከማየት ውጭ እንደ አንድ ለሀገሩና ህዝቡ የሚቆረቆር ዜጋ የሚጠበቅብንን አድርገናል? ፍርሃት ሸብቦን ዝምታ ለጉሞን ከእውነታው ርቀን ቆመናል፡፡

     ሲሰደቡ፣ ሲገፉ፣ ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩ ዝም ማለት አላዋጣም፤ አያዋጣም፡፡ ሲያዋጣም አልታየም፡፡ ከፈሪነት ነው ያስፈረጀን፡፡ ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ ትዕግስት ነው ፍራቻ? ብሎ እንዲያስብ /ምን እየሰራሁ ነው ብሎ እንዲያጤን/ ሳይሆን እንደ ድርስ ጎረምሳ ጡንቻውን ወጥሮ በማን አለብኝነት እንዲኮፈስ ነው ያደረገው-ዝምታችን፡፡ በአገኘው ክፍተት እንደ እባብ ቆዳውን እየሸለቀቀ፣ እየለዋወጠ እና እያፈገፈገ የስልጣን ዘመኑን እንዲያራዝም ረድቶታል፡፡ አሁን ግን የዝምታ ጊዜ አይደለም፡፡ በቃ!...ግን በቃ የሚለውንም ከመፈክርነት አላቆ ታግሎ አታግሎ ፍሬያማ የሚያደርገው ነፃ እና ትኩስ አመለካከት ያለው ጠንካራ ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ በዛገ ቢላ መፈቅፈቅ፣ ቀደም ባለ ስልት መጓዝ፣ መታገል አያዋጣም፣ አላዋጣም፡፡

     በቱኒዚያ ተጀምሮ ማብቂያ የሌለው ተቀጣጣይ አብዮት የአረቡን አለም አምባገነኖች እንደገነደሰ ነው፡፡ እኛም የእኛን ልንገነድሰው ይገባል፡፡ አምባገነንነት ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአለም ሊጠፋ ይገባዋል፡፡

   የአምባገነኖች መጨረሻ ምን እንደሆነ በአረቡ አለም ከዳር ዳር ተቀጣጥሎ የነበረው አብዬት አሳይቷል፡፡ አምባገነንነት መድኃኒት ያልተገኘለት ጅምላ ጨራሽ በሽታ ነው፡፡ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ያልተገኘለት ሰውን ጨራሽ ሲሆን አምባገነንነት ህብረተሰብን፣ ሀገርን፣ባህልን አጥፊ ነው፡፡ ስለዚህ ልንታገለው ይገባል፡፡

    በአረቡ አለም ህዝቡ ያቀረበውን የስልጣን ለቀቅ ጥያቄን በንቀትና በስድብ ምላሽ ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ የሰደቡት፣ የናቁት ህዝብ ትግሉን አፋፍሞ ጥሏቸዋል፡፡ የእኛውም ሰውዬ ከዚህ ያልተለየ ንቀት የተሞላበት አነጋገር እንደተናገሩ እስከዛሬ አሉ፡፡ ዝምታችን የፍርሃት አዶከብሬ እየደለቅን አስመሰለን እንጂ ዞር ብለው እንዲያዩ፣ እንዲያስቡ አላረጋችውም፡፡ በማን አለብኝነንነት ተንፈራጠው እንዲቆሙ አድርጓቸዋል፡፡ አምባገነንነት ማክተሚያው እየቀረበ ነው ለማለት የሚያስደፍር ፍንጭ እየታየ ነው። ስልጣን ላይ ሙጥኝ የሚሉ፣ ሕዝብን በንቀት የሚያዩ ሁሉ በተራ በተራ እጣቸው ምን እንደሆነ እየታየ ያለበት የአረቡ አለም እንቅስቃሴ የህዝብን የበላይነት እያሳየ ነው።
                         ወይ ሽብር ሽብር፣ ዘንጋ..ዘንጋ
                         ይሄው በህዝብ ተሸንፎ ተዘረጋ
                         ያለ እኔ ለሀገሬ..ብለው ሲኮፈሱ
                         በተራ በተራ እያየን ፈረሱ
                         ተረኛ ነህና ከሆነ መዝሙሩ
                         አምባገነን ሁሉ ሞት ሲሆን ግብሩ
                         ማን ይሆን ቀጣይ ብለው ሲሸበሩ
                         አሸባሪ ብለው ስንቶችን አሰሩ?
                         የቱኒዚያ እሳት ስሩን ከሰደደ
                         ተረኛ እያለ ለእኛም ከወረደ
                         አምባገነን አለን 22 አመት ያሰረ
                         በድምጽ ስንጥለው ውጤቱን የሻረ
                         ወጣቱን ጨርሶ በደም የሰከረ…
   
      እኛም ቢሆን ጫንቃችን ላይ የተጎበረ በስልጣን ጥም የሰከረ ቡድን ለ22 ዓመት ተሸክመናል። እስከመቼ ነው ተሸክመን የምንኖረው? ምላሽ የናፈቀው ጥያቄ ነው። ሀበሻ ጀግና ነው እንላለን፡፡ በእርግጥ ለወራሪ አፍረን፣ ተንበርክከን አናውቅም፡፡ ለገዢዎቻችን ግን ጌታዋን እንዳየች ውሻ ስንሽቆጠቆጥ፣ ስንቅለሰለስ ነው የምንገኘው፡፡ በ1966ዓ.ም የተገኘ ወኔ ዛሬ የት ገባ? የእነ ማርታ፣ የእነ ዋለልኝ..ትውልድ አክትሞ ይሆን? አባት አያቶቻችን የሰሩትን አንቆለጳጵሶ እያወሩ ጀግና ነን ማለት ብቻ ውጤት የለውም፡፡ ጥቂት ጀግኖች የሚያደርጉትን ቅስቀሳ እንኳን ማስተዋል ያልቻለ ጀግንነት ይዘን እስከመቼ እንጓዝ? ይሄን በዝምታ የተሸበበ፣ መብቱን አጥቶ ተመስጌን ብሎ ያገኛትን ቆርጥሞ ማደር የተያያዘ ህዝብ ተው መብትህ ይሄ ነው…ብሎ እውነታ በማሳየቱ እና እውነትን በመፃፉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዛሬ በእስር ይገኛል፡፡ ጥቂት አሉን ከምንላቸው የዘመኑ ጀግኖች አንዱ ስለሆነው ስለእስክንድር ነጋ ጥቂት ነገሮች መናገር እችላለሁ፡፡ እኔ ቅርቡ ነኝ:: ውይ ነበርኩ ነው ማለት ያለብኝ ለካ!..ጊዜው ቆየ እኮ ከተለያየን፡፡

      8 አመት በላይ በጥሩ ቀረቤታ ዘልቀናል:: አለቃዬም ነበር ..ላመነበት አላማ ሟች መሆኑን ከማንም በላይ አውቃለሁ:: ጸሐፊ ነው ይጽፋል ብቻ ሳይሆን ይናገራል:: ገዢው ፓርቲ ያላውቀው ወይም አውቆ የተኛው እውነታን ማሳወቅ ሌላ ጉዳይ ማሸበር ሌላ ጉዳይ መሆኑን ነው:: መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚደንቅ ከመሆን ያለፈ ነው:: ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት መፈረጅ ምን የሚሉት አባዜ ነው? አሸባሪነትና ተቃዋሚነትን ምን አገናኘው? የተቃወመን ሁሉ አሸባሪ የሚል መንግስት ታቅፈን እስከመቼ እንጓዝ?
     
            እስከመቼ?
      በሀይል ተገዝተን እስከመቼ
      ሰላም ናፈቀን ወገኖቼ
      አረ! ዝምታው ምንድን ነው
      መብት ተገፈን የተኛነው?
              ወጥቶ መግባት ህልም ሆኖ
              መብት ጠፍቶ ተጨቁኖ
     ጎዳናዎች  በንጹሀን ደም ራሱ
     ዝምታው ይብቃ እንነሳ ተንሱ
             የወላድ እንባ ዋንጫ ሞልቶ
             ምሁራንን ከእስር ከቶ
             ነገር ዞሮ ፍርድ ተዛብቶ
      መብት ጠያቂ ሆኖ ወንጀለኛ
      አፋኝ ገዳይ ሲሆን ዳኛ
             ከዝንብ ማር አንጠብቅም
             በአድነት እንነሳ አማራጭ የለም
    ይሄ ነገር እስከመቼ  ይቀጥል? ወደተነሳሁበት ልመለስና እኔ እስከማውቀው እስክንድር ጥሩ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ግን ላመነበት ፖለቲካ ፓርቲ እንጂ ተቃዋሚ ስለተባለ በደመነፍስ አይሮጥም፡፡ ችኩልነቱ ለስራ እንጂ ለመናገር፣ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ምክንያታዊ ነው፡፡ አቃቢ ህግ የግንቦት ሰባት አባል የሚል ነገር ሲያቀርቡበት ተበሳጭቶ እንደነበር ሰርክዓለም ፋሲል ከፍርድ ቤት ሂደቱ በኋላ ተናግራለች፡፡ ያልሆነውን ነህ በመባሉ ሊበሳጭ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ቢሆን ኖሮ፣ ካመነበት ከዚህ ቀደም ያደርግ እንደነበረው ሲፅፍ ከስሙ ቀጥሎ ፓርቲውን ጠቅሶ ያሰፍር ነበር፡፡ እስክንድር ነጋ ከመኢአድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይል እንደነበረው ማለት ነው፡፡ ግንቦት ሰባት ስለተባለ መናደዱ መንግስት የሚያቀርበው ነገር ከእውነታ መራቁ እንጂ ፓርቲውን ጠልቶ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ እስከማውቀው ለመጥልትም ለመውደድም ምክንያት ይፈልጋል፡፡ እስክንድር ጋዜጠኛ እንጂ አሸባሪ አይደለም:: አይደለም ያልኩት እኔ ነኝ መንግስት ግን አሸባሪ ብሎታል፡፡  
   
   መታሰሩን በሰማሁ ጊዜ በእውኑ ያነባሁትን እንባ ፈጣሪ አይቆጥረው ይሆን? ለምን? አስቡት እኛ ሀገር እያለን ተሰደን በስው ሀገር የምንንከራተተው ይህ ጨቋኝ መንግስት ፕሬሱን ለማፈን ከወሰደው እርምጃ ሰለባ ከመሆን አምልጠን ነው:: እስር፣ ስቃይ፣ ስደት፣መከራ፣ የእነ አሰፋ ማሩ ሞት.. በዚህ አፋኝ መንግስት ምክንያት ለፕሬስ ነፃነት የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ ነካካሁት እንጂ አልጠቀስኩትም የተከፈለው መስዋዕትነት በዋዛ የሚወሳ አይደለም:: የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ሲጀመር መጀመሪያ ጋዜጣወጡት ውስጥ እስክንድር ነጋ አንዱ ነው::
    
     <<ኢትዮጲስ>> የምትባል ጋዜጣ ነበረች፡፡ ሁለት አመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ህይወቱን ሲገብርበት እስክንድር ነጋ ያኔ የጀመረውን ስቃይ በትጋት ቀጥሎ ዛሬ ላይ ደርሷል:: በእርግጥ ዛሬም ቢሆን የወያኔ መንግስት ብዕሩን እንደጦር በመፍራት ‹‹አሸባሪ›› ተብሏል፡፡ ግን በፔን ኢንተርናሽናል አሸባሪ ሳይሆን ደፋርና እውነታን ያነገበ ምርጥ ጋዜጠኛ እንደሆነ አምኖ ሸልሞታል፡፡ ለገዢው ፓርቲ ግን የደበቁትን የሚያወጡ የተጣሰውን የህዝብ መብት ተጣሰ ብለው ድምፅ የሚያሰሙ ድምጽ ለሌለው ድምፅ የሆኑ ጋዜጠኞች ውስጡን ስላሸበሩት፣ ተረግጦ ዝም ያለውን ህዝብ ንቃ! ስላሉበት ‹‹አሸባሪ›› ብሏቸው አሰረ፡፡ ውስጡ በተሸበረ፣ ነቁብኝ ብሎ በደነበረ ቁጥር የተቃወሙትን ሁሉ አሸባሪ እያለ የሚፈርጀው ወያኔ አስከመቼ ይጓዝ? ዝምታው ይሰበር፡፡

     በመጨረሻም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከተናገረው ልድገምና ልሰናበት፡፡ ‹‹…ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ኃላፊነቴንም ተወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ከእኔ የሚጠበቀው የምከፍለው ዋጋ ካለ በፀጋ መቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡….›› ሊሰመርበት የሚገባ እውነታ ስለሆነ በፅሁፍ እንደደጋገምኩት በውስጣችንም እንደጋግመው፡፡
                   ቀሪውንም ጊዜ ድል ለእስክንድር ነጋ እላለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment