Tuesday, August 27, 2013

ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ፈተና

ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ፈተና…
የዲግሪ ምሩቁ ስቃይ
   በግሩም ተ/ሀይማኖት
ነሀሴ 20 ቀን 2005 ጠዋት ላይ ነው፡፡ ያለሁበት ሱቅ በር ላይ ቁመታም ጠይም ሀበሻ መጥቶ ቆመ፡፡ ምንም መናገር የፈለገ አልመሰለኝም፡፡ ዝም በዝምታ እቃ ሊገዛ ስሎኝ ምን ፈለክ አልኩት፡፡ ምግብ እንደሚፈልግ በእጅ ምልክት ነገረኝ፡፡ መናገር የማይችል መስሎኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ እንዴት እኔ ጋር ልትመጣ ቻልክ? ስለው ሳልፍ ሱቁ በር ላይ የተቀባውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ስንደቅ አላማ ሳይ ሀበሻ ናቸው ብዬ መጣሁ አለ፡፡ አጠገቤ ካለ የየመናዊያን ምግብ ቤት አምጥቼ ሰጠሁት፡፡ይስሀቅ መብራቱ ይባላል የመቀሌ ልጅ ነው፡፡በልቶ ሲጨርስ አዲስ ነህ? በየት መጣህ? ስንት ጊዜ..ሆነህ?…የሚሉ ጥያቄዎችን ደረደርኩለት፡፡ ሲነግረኝ ጅማ ዩንቨርስቲ በቢሮ አስተዳደር (በኦፊስ ማንጅመንት) ባችለር ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ አዲስ አበባም ሆነ መቀሌ ለእሱ የስራ በራቸውን ሊከፍቱ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሳዑዲ አረቢያ የሚመላለስ ልጅ እዛ ስራ ብትሞክርስ አብረን እንሂድ ይለዋል፡፡ ስራ ካልተገኘስ ብሎ ስጋት ስላደረበት ዘመዱ ቀድሞ ሄዶ ስራ ካገኘ እንዲጠራው ይነጋገራሉ፡፡ በተነጋገሩት መሰረት ልጁም ቀድሞ ይሄድና ሳዑዲያ ውስጥ አንድ ድርጅት ያለው የሚያውቀው መጠጥ ይገዛው የነበረ ደንበኛውን ወንድሜ ተምሮ ተመርቆ ስራ አጣ ይለዋል፡፡
    ‹‹ይምጣ ኢንሽ አላህ ስራ እናስገባዋለን…›› ይለዋል፡፡ ደውሎ ና ስራ ተገኝቷል ይለዋል፡፡ ትንሽ ገንዘብም ልኮለታል እሱም ፈላልጎ ሳንቲም ጨምሮ በጅቡቲ ይመጣል፡፡ ‹‹..ችግር የገጠመኝ ከድሬደዋ ነው…›› ሲል አጫወተኝ፡፡ ድሬ ደሞ ምን አጋጠመህ አልኩት፡፡ የሆነች ልጅ አይቶ እንደወደዳት…እሷን ለማናገር ሶስት ቀን ሁሉ አድሮ ጉዞውን ሊያስተጓጉል ፈልጎ ነበር፡፡ ግን የስራውን መግኘት ሁኔታ አስቦ ልቡን ድሬ ላይ ጥሎ ወደ የመን ነጎደ፡፡ እንደሌሎቹ ሁሉ ከባህር ሲወርድ በአጋቾቹ ተያዘ፡፡ ስልክ ቁጥር አምጣና ደውለህ የሳዑዲያ 1500 ሪያል አስልክ ተባለ፡፡ ቁጥር የለኝም በማለቱ ያየውን ስቃይ ሲነግረኝ በጣም የከፋ እና አሳዛኝ ነበር፡፡ እንዴት ላሳይህ ሰውነቴ ላይ በሙሉ በሲጋራ እያጠሉኝ 13 ቦታ ጠባሳ በጠባሰ ሆኛለሁ፡፡በዛ መቼ በቃ ብለህ ነው፡፡ አንገቴ ውስጥ ገመድ ከተው አንጠለጠሉኝ፡፡ ሁለቴ አንጠልጥለው አወረዱኝ፡፡ ልሞት ብዬ አጣጥሬ ነቃሁ፡፡ እጄን በገመድ አድርገው መኪና ላይ አስረው መሬት ለመሬት ጎተቱኝ፡፡ እጄን ሰበሩኝ፡፡ የያዝኩትን ብር መጀመሪያ ሲፈትሹኝ ወስደውበኛል፡፡ ዱላው ሲበዛብኝ ይልክልኘል ያልኩት ሳዑዲ አረቢያ የለው ልጅ ደውዬ ነበር፡፡ አንዴ አንስቶ አወራኝ እና በኋላ ስልኩን ከነአካቴው አላነሳም አለኝ፡፡ ደበደቡኝ..ደበደቡኝ፡፡ እይ…(የተሰበረ እጁን ገልጾ አሳየኝ፡፡)
   በሲጋራ 13 ቦታ እንዴት እንዳቃጠሉት ጠየኩት፡፡ ብልቱ ላይ፣ መቀመጫው ላይ ደረቱ እና ሆዱ ላይ እንዳቃጠሉት ነገረኝ፡፡ አሁን ምን ታስባለህ ወደ ሀገር መመለስ ወይስ ሳዑዲ ትሄዳለህ ስለው ‹‹..ኧረ.! ሀገሬ ነው የምፈልገው..›› ሲናገር እያንገፈገፈው ነው፡፡ታዲያ ወደ ሀገር መመለስ ከፈለክ ሀረድ IOM ካምፕ ለምን አልገባህም? አልኩት፡፡ እውነትም ሀገር ለመግባት ከሰነዓ ከተማ ከመሞከር ይለቅ ካምፑ ይቀላል ብዬ ነው፡፡እዛም ችግር እንዳለ እና ቶሎ እንደማይመልሷቸው አውቃለሁ፡፡
   ‹‹መጀመሪያማ እዛ ነው የገባሁት፡፡ ግን ከእኔ በፊት የገቡ በጣም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሉ፡፡ ሶስት አመት የተቀመጡ አሉ፡፡ እዛም አድሜ መፍጀት ነው የሆነብኝ፡፡ እዚህ ያለውን አማራጭ መሞከር ፈልጌ ከመጣሁ ሶስት ቀኔ ነው፡፡..›› አለኝ፡፡ ካምፕ ውስጥ ብልቱ የተቆረጠ ልጅ ነበር ብለውኛል አንዱም ራሱን አጠፋ ብለውኛል አይተሀቸዋል? አልኩት፡፡ ካምፕ ውስጥ ብቻ አይደለም ያየኋቸው ስንያዝም አብረን ነበርን፡፡ ሲቆረጡም አይቻለሁ፡፡…የምናገረው ጠፋኝ፡፡ አፌን ደም ደም አለኝ፡፡ በሰፊው ላውራው ፈለኩ፡፡ ሻይ እንጠጣ አልኩትና የምሄድበትን አስተጓጉዬ ወደ ቤተክርስቲያኑ መታጠፊያ ላይ ያለ ቁርስ ቤት ተቀመጥን፡፡ ላወራ የፈለኩት ሁሉ ጠፋብኝ፡፡ እንደምንም ብዬ እስኪ ስለሁኔታው ንገረኝ አልኩት፡፡ የታሪኩን ፍሰት ሳልስት ለመያዝ በንቃት እየጠበኩት፡፡
    ‹‹ነገሩ ሰቅጣጭ ነው፡፡ በሁለት ጀልባ የተጫነው 80 አካባቢ እንሆን ሆናል፡፡ ከበዛ 90 ብንሆን ነው፡፡ገና መሬት ከመርገጣችን ወዲህ ኑ..እያሉ አዋክበው መኪና ላይ ጫኑን፡፡ የሆነ ጊቢ ውስጥ አጎሩን፡፡ ፍተሻ ጀመሩ፡፡ ብር ብቻ አይደለም የሚፈትሹት፡፡ ሳዑዲ ማን ነው የሚቀበላችሁ? ስልክ ቁጥሩን አምጡ..እያሉ ቁም ስቅል አሳጡን፡፡ እኔ ስልክ ቁጥር ጽፌበት የነበረውን ብጫቂ ረቀት አኘክ አኘክ አድርጌ ጆሮዬ ውስጥ ተፍኩት፡፡ ሲፍትሹ ያገኙትን ገንዘብ ወሰዱብኝ፡፡ ድብደባው ተጀመረ ልብሳችሁን እያወለቃችሁ ለየብቻ መሬት ላይ አስቀምጡ ተባልን፡፡ የሚገርመው ነገር ይህን አይነት ነገር የሚሰሩት ኢትዮጵያዊያ ናቸው፡፡ ብጫቂ ወረቀት ይሰጡህና ስምህን ጽፈህ ያወለከው ልብስ ላይ ታደርጋለህ፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ራቁትህን ትገባለህ፡፡ አስብ ያሳፍራል ሴቱም ወንዱም ፓንት እንኳን ሳታደርግ አንድ ክፍል ውስጥ መለመላህን መታጎር፡፡
   ‹‹..ፈትሸው ሲጨርሱ ወጡ ተባልን፡፡ ከያዛት ብጫቂ ወረቀት ላይ ‹ፋኖስ› ብሎ ተጣራ፡፡ ኢትዮጵያ ነው የሚጣራው፡፡አንዲት ከ16 ዓመት የማትበልጥ ልጅ ራቁትዋን ብድግ አለች፡፡ሰውነቷ በፍርሃት ይንቀጠቀጣል፡፡ በሁለት እጆችዋ ሀፍረቷን ሸፍና ጭንና ጭንዋን እያፋተገች ወደ እሱ ሄደች፡፡ ‹ነይ ወደዚህ አንቺ ብልጥ ሆነሽ ልታታልይን ነው? ስልክ ቁጥሩን በየቦታው ደብቀሽ የጻፍሽው? ብሎ ከየልብሷ ላይ የሰበሰበውን ቁጥር አገጣጥሚ እና ደውይ..› ብሎ ወረቀቱን ሰጣት፡፡በሁለት እጇ ሸፍና የነበረውን ሀፈረቷን እንዴት ለቃ ትቀበለው እፍረትም ይዟታል፡፡ ለቃ እንዳትቀበለው…ብቻ በጥፊ ሲያጎናት ድንጋጤው ነው መሰለኝ ለቀቀችና በአንድ እጇ ወረቀቱን በአንድ እጇ ሞባይል ስልኩን ተቀበለችው፡፡ ያኔ ነጻ አገኛት በታጡ ነካካት፡፡ ዋይ ብላ እሱን ለማስተው ወደኋላ ስታፈገፍግ ›..ዝም ብለሽ ደውይ ብሎ በጥፊ መታት፡፡ ብልቷ አካባቢ እያቆጠቆጠ ያለውን ፀጉር በያዘው ሲጋራ አቃጠለው፡፡ በዚህን ሰዓት ‹.አአአ!…› ብላ ወደ ላይ ስትዘል የያዘችውን ሞባይል ለቀቀችው፡፡ አረቦቹ ደስ ብሏቸው በትዕይንቱ ይስቃሉ፡፡ ይሄ ሙክታር ዪባል የጅማ ልጅ ግን ልጅቷን በዱላ አላስተረፋትም፡፡ በጠረባ ጣላትና ጣቱን እንትኗ ውስጥ ለመክተት ሲታገል አንዱ አላስችል አለውና ‹ምነው አንተ ከሰውም አልተፈጠርክ ሴት ልጅ ያውም ያገርህን ልጅ እንዴት እንዲህ ተደርጋለህ?..ነውር ነው፡፡..› ይለዋል፡፡    
   በቀጥታ ቁጭ ብለው ከሚስቁት የትዕይንቱ ታዳሚዎች የመናዊያን ቀጣሪዎች ወገባቸው ላይ ከሚታጠቁት ስለት ነገር (ጃንቢያ ይባላል) ተቀብሎ መጥቶ ና ወደዚህ ብሎ ጠራው፡፡ ፈራን ሁላችንም ፈራን፡፡ እነዚህ ሰዎች ደም የለመዱ ደም የጠማቸው ናቸው፡፡ ምንም አማራጭ ስለሌለው እሱም ሀፍረቱን በእጆቹ ሸፍኖ ተጠጋው፡፡ አዘንክላት? እዚሁ እያየንህ አርጋት(ተገናኛት) አለው፡፡ፈጽሞ አላደርገውም ከፈለክ ግደለኝ፡፡ ወገኔ ናት እኮ አለው፡፡ ናጥ ያደርገው የነበረውን ስሜት ስታይ የማናዊያኖቹ ክላሽ ስለያዙ ባይፈራቸው የያዘውን ስለት ነጥቆ አሩን የሚያበላው ይመስል ነበር፡፡ በእርግጥም ተናነቁ..የመናዊው ተነስቶ ክላሽ ደቀነበት፡፡ በዚህን ጊዜ እጁን ወደላይ አለ፡፡ ሙክታር ተብዬው የልጁን ብልት በእጁ ይዞ ‹እኔ ላይ ወንድ ልትሆን አይደል ወንድነትህን እንዳውቅልህ ካላደረካት እቆርጥልሀለሁ› አለው፡፡
   ‹‹ወንድነቴን ግፍ በመስራት አይደለም የማሳይህ ይሄን የደቀናችሁብኝን መሳሪያ አውርዱትና ላሳይህ፡፡ ያለበለዚያ ቁረጠኝ እንጂ እሷንስ አላደርግም..› አለው፡፡ ጭካኔውን ተወኝ ሙሽልቅ ሲያደርገው ሁላችንም ደነገጥን፡፡ አንደኛው ግን ከመሀላችን አአአአአአ!!!! ብሎ ዛር እንዳለበት አጓራ፡፡ ድምጹን ከፍ አድርጎም ‹..እናንተ አውሬዎች..› እያለ ተሳደበ፡፡ እሱንም ጠርቶ ተገናኛት ያለበለዚያ እቆርጥሀለሁ ሲለው ፈራ፡፡ ልጅቷ መሬትእንደወደቀች በፍርሃት ትንቀጠቀጣለች፡፡ ብልቱን ተቆረጠው ልጅ ይንደፋደፋል፡፡ ይኛውንም ብልቱን ይዞታል፡፡ ቆረጠውም፡፡ በዚህን ጊዜ   ካሳሁን የተባለ የሮቤ ልጅ የሚደፋደፉትን ለመርዳት ሲጠጋቸው በደም ማፍሰስ ደስታ ላይ የነበረው ሙክታርት በጥፊ ብሎት ከእጁ ስለቱን ሊነጥቀው ሲል ያኛው ባለመሳሪያው በሁለት ጥይት ደረቱን ብሎ ደፋው፡፡ ሌላኛው ደንግጦ ይሁን እንጃ ብድግ ሲል እሱንም በጥይት መታው፡፡ ‹..እስኪ ወንድ ናችሁ አስጥሏት ብሎ ያችን አንድ ፍሬ ልጅ ራቁቷን እንደተኛች በጣቱ ይጫወትባት ጀመር፡፡ ምን እናድርግ ዝም አልን፡፡….በኋላ ቅበሩ ብለውን ከጊቢ ውጭ መሳሪያ ደግነው ቆፍረን ቀበርን፡፡ ልጅቷን ግን ከዛ ጊቢ እስክንወጣ እየተፈራረቁ ተጫወቱባት፡፡ ሌሎቹንም ሁሉ ተጫወቱባቸው፡፡››
   ‹‹..ከዛ መዓት ውስጥ አንተ እንዴት ወጣህ?›› አልኩት፡፡
   ‹‹ ይሄውልህ..ሳዑዲ የጠራኝ ዘመዴ ስልኩን ሲዘጋብኝ በድብደባ ልሞት ነበር፡፡ አማራጭ ሳጣ ከ20 ቀን በኋላ ቤተሰብ ጋር ደወልኩ፡፡ ቀጥታ ከኢትዮጵያ አንቀበልም ስላሉ ሳዑዲ ያለ ሰው ተፈለገና የእኔ ቤተሰቦች ገንዘቡን ለእሱ ቤተሰቦች ሰጡ፡፡ እሱ ልዋጩን ከሳዑዲ በሪያል ላከ፡፡ በጨለማ ብልታቸውን ከተቆረጡት ልጆች ጋር አውጥተው ካምፑ አካባቢ ጥለውን ሄዱ፡፡...ካምፕ ከገባን ከ24 ቀን በኋላ ያች ህጻን ልጅ ደብድበዋት ፊቷ ሁሉ አባጦ መጣች፡፡…››የሚነግረኝ ነገር ሁሉ ውስጤን የሀዘን ከል ቢያለብሰውም፡፡ ብቻዬን ምን ማድረግ እችላሁ?

No comments:

Post a Comment