Wednesday, October 10, 2012

      ከክፍል ፡ ሶስት የቀጠለ ፡፡
ክፍል ፡ ሶስት የቆመው በተቀመጥኩበት ሺሻ ፡ ቤት ውስጥ ከነበረች ልጅ ጋር ለመተዋወቅ ፡ ወደ እሷ ሲሄድ ነበረ ፡፡  ታዲያ እንደተለመደው የሆነውን ነገር ሁሉ እኔ ለእናንተ አደርሳለው ፡፡ እናንተ ብቻ ባላችውበት ቦታ ተከታተሉኝ ፡፡
    አብረውኝ የነበሩት ጓደኞቼ እየሳቁብኝ ወደ ልጅቷ ጋር ሄድኩ ፡፡ ብዙም ድስ ባይልም እጇን ለሰላምታ ዘረጋችልኝ ፡፡ ወንበር እየሳብኩ ለመቀመጥ ፡ መቀመጥ ይቻላል አልኳት እኔ ከእሷ መልስ ሳልጠብቅ ለመቀመጥ እየተዘጋጀው ፡፡  ሁኔታዬ ሳይገርማት አልቀረም ፡ ትኩር ብላ እያየችኝ ፡
                                               መቀመጫ ፡ አጥተ ነው እዚ የመጣኽው ? አለችኝ አሁንም አይን አይኔን እያየች ፡፡
                                                አይደለም ፡ እዚ አንቺ ጋር መቀመጥ ፈልጌ ነው ፡፡ እዚ በመቀመጤ ይከፋሻል ?
   እረጅም ጸጥታ ሆነ ፡፡ እያሰበች እንደሆነ ገብቶኛል ፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በዋላ ፡ ምንም ችግር የለም ፡፡ ከፈለክ ብላ አንስታ የጀመረችውን ሺሻ ፡ መሳብ ቀጠለች ፡፡  አዎን እኔም መቀመጥ ነው ምፈልገው ፡፡ ሰለሀሳቧ እንድታወራኝ ፣ ፈቃደኛ ከሆነችም ሰለ እራሷ እንድታወጋኝ ፈልጌ ነው ወደ እሷ የቀረብኩት ፡፡

        አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ፡ ለምን ጒደኞችህን ጥላቸው መጣ ወደዚ ?
        ሁኔታሽ ትንሽ ለየት ሰላለብኝ ነው ፡፡ ለእረጅም ሰሀት በጣም በተደበላለቀ ሁኔታ ውስጥ ነበርሽ ፡፡ ዝምታሽ ፣ ሀሳብሽ ፣ አጠቃላዬ ቀልቤን ሳበው ፡፡ ሰለዚ ላወራሽ ፈለኩ ፡፡ ምንም ባላደርግልሽም ቢያንስ ፡ ሀሳብሽ ቀለል ይልሻል ብዬ ነው አልኳት ፡ ቀጥለ የምታወራውን ነገር ለመስማት እየቸኮልኩ ፡፡

      ስታየኝ ሀሳብ የበዛብኝ እመስላለው ? ደሞ ሀሳቤን ፣ ችግሬን ላንተ ብነግር ምን ትፈይድልኛለ ? ከንፈር መጦ ከማለፍ በስተቀር ፡፡  ብቻ ለሀሳብ አመሰግናለው ፡፡
     ምንም አይደለም ፡፡ ለማንኛውም  ሰምሽ ?
    ብዙ እንቆያለን እንዴ ?  ብዙ ሰለማንቆይ አንተ በተመቸ  ሰም ብጠራኝ ችግር የለም ፡፡
  እሺ ፡፡ አልኳት ምክንያቷ ባይዋጥልኝም ፡፡ ትንሽ እሷን ለማሳመን ግዜ እንደሚያሰፈልገኝ ገባኝ ፡ ትንሽ ማግባባትም ፡፡ የነበረኝ አማራጭ ወደተለመደ ጥያቄ እና መልስ ቀስ እያሉ መግባት ነበር ፡፡ የት ተወለድሽ ፤ የት ተማርሽ ? በመሳሰሉ ጨዋታ ጀምረን ትንሽ ፣ ትንሽ ወዸምፈልገው ነገር መግባት ጀምሬ ፡ ከብዙ ሰሀት ቆይታ በዋላ ፡ ወጣቷ ታሪኳን ማውራት ጀመረች ፡፡ እኔም በደንብ ለመስማት እንዲመቸኝ በመመሰል መልኩ አጠገቧ ተሰተካክዬ ቁጭ አልኩ ፡፡ ልጅት አራት አመታትን ወደዋላ ተጉዛ የተወሰነ ነገር እንዲ አለችኝ ፡፡

    እኔም ከእሷ ጋር ወደዋላ አብሬ ተጉዤ የእኔ ታሪክ ካለችው መነሻ ጀምሮ ያጫወተችኝ ይህ ነበረ ፡፡ ውልደት እና እድገቷ አዲሰ ፡ አበባ ጉለሌ ፡ የሚባል ሰፈር ነው ፡፡ ከልጅነት ጀምራ - ሁለተኛ ደረጃ ድረስም የተማረችው ብዙ እርቃ ሳትሄድ እዛው ጉለሌ ነበረ ፡፡ ቤተሰቦቿ ብዙም የተረፋቸው ባይሆኑም ለልጆቻቸው የሚበቃ ገቢ ግን ነበራቸው ፡፡ ታዲያ እሷም ልጅነት የሚባለውን ጊዜ ጨርሳ ፡ የአስራ ፡ ስምንተኛ አመት እድሜዋን ልታከብር ትንሽ ሲቀራት ፡ ሞት የተባለ ባለጋራ መጥቶ በድንገት አባቷን ወሰደባት ፡፡
   ሞት አባቷን ብቻ ወስዶ አይደለም ያቆመው ፡፡ ሙሉ የነበረውን ቤታቸውንም ማጉደል ፣ ሞቅ ካለ ኑሮአቸውንም ማቀዝቀዝ ነበረ መጀመሪያ ያደረገው ፡፡ ቤተሰቡ በዚ ሁኔታ የተጓዘው ለጥቂት ወራቶች ብቻ ነው ፡፡ ችግር የሚሉት ጣጣ የሚቋቋሙት አሎነላቸውም ፡፡ በቀናት አንዱ ታዲያ የእናቷ የቅርብ ዘመዶች ከጥቂት ጎረቤቶቻቸው ጋር ሁነው እቺን ወጣት ለአረብ ፡ አገር ሰደት አጯት ፡፡  ወጣቷ መጀመሪያ በዚ ሀሳብ ከው ብላ ቀረች ፡፡ ማመን የሚሉት ነገር አልሆነላትም ነበረ ፡፡

    ቀናቶች እየነጎዱ ሲሄዱ እና የቤተሰቡም ችግር ሲጨምር ግን ለወጣቷ የነበራት አማራጭ ፡ ሰደትን አሜን ብሎ መቀበል ነው ፡፡ መጀመሪያ የገፋችውን ሀሳብ ተሰማማችበት ፡፡ የቀራት ምንም አልነበረም ፡፡ የውጭ ፕሮሰሷን ለመጀመር ከአንድ የቅርብ ሰው ጋር ሁና ፡ አቅራቢያቸው የሚገኝ ኤጀንሲ ፡ ቢሮ ተገኝች ፡፡ በቢሮው የነበራትን ቆይታ ስታጠናቅቅ ጠብቂ ፡ ቪዛሽ የሚመጣ ቀን እንጠራሻለን ተባለች ፡፡
ፕሮሰሷን ከጨረሰች በዋላ ፡ አኳሏ አዲስ አበባ ቢቀመጥም ፡ ልቧ ግን የማታውቀው ኩዌት አንዱ አረብ ፡ ቤት ነበረ የተገኝው ፡፡ ሁሌም ታስባለች ፣ ሰርታ ቤተሰቧን መለወጥ ታናናሾቿን ማሰተማር ፍላጎቷ ሆነ ፡፡ሲመሽ ፣ ሲነጋ አምላኳን መጨቅጨቅ ያዘች ቪዛዋ ቶሎ እንዲመጣ ፡፡

     ቀኑ ማክሰኞ ነበረ አለች ፡፡ በትውሰታ ፡ ከጎረቤት ያቃጨለ ስልክ ኦሷን የሚፈልግ ይሆናል ብላ አስባ አታውቅም ፡፡ ድንገት ስልክ ይፈልግሻል ስትባል ሳታውቀው ልቦ ደንገጥ አለ ፡፡ በሰልኩ ጫፍ የሰማችው ድምጽ ፡ ሰለቷ እንደሰመረ የሚያበስር የቪዛሽ ፡ መጥቶአል የምስራች ተበሰራት ፡፡  እሮጣ ሂዳ እናቷን አቀፈቻቸው ፣ ደስ አላት ፡፡ እንደገና ደሞ ለቅሶ ፣ የመለያየት ለቅሶ በቤቱ ተተካ ፡፡
  ወጣቷ አጠቃላይ የሚያሰፈልጋትን ውጣውረድ አጠናቃ ፡ ለመጨረሻ በረራ ቦሌ አለም ፡ አቀፍ ኤርፖርት ስትገኝ ፡ በተደበላለቀ የሰሜት ባህር ውስጥ ነበረች ፡፡ እናቷ ያለቅሳሉ ፣ እህቶቿም ያነባሉ ፣ ይህ ሁሉ መለያየት የመጣው በአባቷ ሞት እንደሆነ የምታሰበው እሷ ደሞ ድርብ ሀዘን ሆኖባታል ፡፡ ብቻ ሁሉንም ችላ  እንደቀልድ አገሯን ጥላ ወጣች ፡፡

               ኩዌት ፡፡

  ከአዲስ ፡ አበባ በትንሽ ተነስተን ፡ ዛሬ እዚ የመገኛዋን ጅሜሬ አይተን አሁን ወደዋናው ጉዳያችን ኩዌት ደረስን ፡፡ ኩዌት ለወጣቷ ብዙ ነገር ነች ፣ ብዙም ሆናለች ፡፡ ከቤተሰብ መለየት ፣ ሰራ፣ ናፍቆት ፣ ሲልም ፍቅርን የችው እዚው በስደት የተገኝችበት ኩዌት ነበረ ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥታ የገባችበት ቤት በጣም ታሰታውሰዋለች ፡፡ጥሩ የሆኑ ሰዎች ጋር ነው የተቀላቀለችው ፡ ሁለት አመትም የቆየችው በፍቅር ነበረ ፡፡ ታዲያ መጥፎ ዕድል ሁኖባት ነው መሰል አሰሪዎቿ ወደሌላ ሀገር ለመሄድ ሲነሱ ፡ እሷም ሳትፈልገው ሌላ አሰሪ ጋር መግባት እጣ ፈንታዋ ሆነ ፡፡

   አሁን የገባችበት ቤት በጣም ከባድ ፣ ሰራ ጭቅጭቅ የበዛበት ፣ ምንም ሰላም የሌለው ሆነባት ፡፡ የነበረኝ አማራጭ ዝም ብሎ መስራት ነው ፡፡ ልውጣ ብል ወዴትም አልሄድም ፣ አገሬ የእኔን እጅ የሚጠብቁ ብዙ ቤተሰቦች አሉ ፡፡ ከአውን በዋላ ደሞ አገሬ ገብቼ መኖር አልሻም ነበረ ፡፡  ያለኝ አማራጭ እየተበደልኩ ፣ እየተገፋው መኖር ነው ፡ ብዬ አመንኩ ፡፡  እንደገና በመሀል ዝምታ ሆነ ፡፡ ለምን ግን እንደዚ ታሪኬን ታሰለፈልፈኛለ ?
   እያሰለፈለፍኩሽ አይደለም ፡፡ ዝምታሽ ውስጥ ብዙ ነገር እንዳለ ነግሬሽ ነበረ ፡፡
   ሳቅ አለች ፡፡ « እንዴት አወክ » ?
   ለብዙ ሰሀት ሰከታተልሽ ነበረ ፡፡ እኔ ደሞ የሰወች ዝምታ ፣ ድርጊት ፣ ይሰበኛል ፡፡ በተለይ እንደአንቺ በዝምታ ውስጥ ሁነው ከራሳቸው ጋር የሚያወሩ ሰዎች ይማርኩኛል ፡ እኔ የማላየው ፣ የማልሰማው አንድ ነገር እንዳለ ይገባኛል ፡፡ ከዚ ነገር ውስጥ ደሞ ብዙ ተቃሚ ፣ አሰተማሪ፣ አንዳንዴ አዝናኝ ነገርም አይጠፋም ፡፡
   ልክ ነህ ፡፡ ሀሳብ ይገርማል ፡፡« አንተ አታስብም ? »
    አስባለው ፡፡ የኔ ነገርም ለራሴ ያሰተምረኛል ፣ ሀሳቤ ለእኔ በዙ ነገሬ ነው ፡፡
    እንጃ ምን እንዳሰገረማት ፡ በጣም ሳቀች ፡፡ ሰምህ ማነበር ያልከኝ ?
     ኒዛር ፡፡ ኒዛር እባላለው ፡፡
    « ኒዛር .....  ሰለኔ ከማውራቴ ጥቂት ሰለአንተ ልጠይቅ ?»
    ይቻላል ፡፡ የቻልኩትን እመልሳለው ፡፡
   «   ኩዌት ውስጥ ፡ ቤተሰብ አለ ማለቴ አግብተሀል » ?
       የለኝም ፡፡ ሰራተኛ ነኝ ፡አላገባውም  ፡፡
    « እሺ ፍቅረኛስ ? ፍቅረኛ የት ነች ? »
  ለመመለስ ትንሽ ከበደኝ ፡፡ የምናወራው ወሬ እኮ ሰለፍቅር አይደለም ፡ እኔ ሌላ ነገር ላዋራሽ አይደለም ፡ ፍቅረኛዬ እዚ የለችም ፡ ሌላ ሀገር ናት ፡አልኩአት አይን አይኗን እያየው  ፡፡
      በቃኝ ብዙም ጥያቄ አልጠይቅህም ፡፡ አውን አንተ የፈለከውን ነገር መጠየቅ ትችላለ ፡፡
     እኔም የምጠብቀው ይህንን ነበር ፡፡ ኩዌት ለአንቺ ምንድነች ? በኩዌት እንደምትፈልጊው አልፈሻል  ኖረሻል ?  አንቺ ውስጥ በኩዌት ሰላለው ህይወት ማወቅ እፈልጋለው ፡፡

    « ኩዌትን እኔ እንዴት ብዬ እንደምነግር አላውቅም ፡፡ በኩዌት ብዙ ሁኜ አልፌአለው ፣ ኩዌትን እንዲ ነው ብዬ የማወራበት ቃል የለኝም ፡ ከአገሬ መነሻዬን ነግሬሃለው ፡፡ አውንም ያለውት እዚው ነው ፡፡ ብቻ ጥያቄህን መመለስ ሰላለብኝ ፡ ኩዌት ለኔ ...... »  ወጣቷ ታሪኳን ስትጀምር እኔ ደሞ በህሊናዬ ለመያዝ እራሴን አዘጋጅቼ ወጋችንን ቀጠልን ፡፡
      « ለመጀመሪያው ሁለት አመታት ያሳለፍኩት ሀይወት መልካም ነበረ ፡፡ የነበሩኝ ጥሩ አሰሪዎች ከተሳፈሩ በዋላ በጣም ብዙ ችግር ውስጥ ገባው ፡፡» አውንም በትዝታ ወደዋላ ነጎደች ፡ ከትዝታዋም የኔ ያለችውን በወዳጃዊ ጨዋታ ቀጠልን ፡፡

       ህይወት ዝብርቅርቅ ብሎባት በነበረችበት የመጀመሪያ ጊዜ ላይ አንድ አዲስ ነገር ተፈጠረ ፡፡ እዛው ኩዌት ከሚኖር አበሻ ፡ ጋር ተዋውቃ ፍቅር ጀመሩ ፡፡ እሱን ባገኝችበት ሰሀት ታዲያ የነበረችበት ቤት በጣም ከባድ ነበረ ፡፡ ሰቃዩ እና በደሉ እያንገፈገፋት ነበረ የተቀመጠችው ፡፡ በመሀል ታዲያ ከኔ ያለችው ሰው የተሰጣት ነገር ግን ከነበረችበት ሰቃይ የሚያወጣት ሰለነበረ ያለአንዳች ማቅማማት ተቀበለችው ፡ ከምትሰራበት ቤት ጠፍቶ መውጣት ፡፡  ከምትሰራበት ቤት ያሰጠፋትን ፍቅረኛዋን ተማምና በማታውቀው መንደር በአንድ ቤት ውስጥ ሐዋሊ ተገኘች ፡፡

    « ምናለ ሰው ፍቅርን ሲጀምር እንደነበረው መዋደድ እስከፍጻሜው ቢቀጥል ? » ከትውስታ ወጥታ ለጠየቀችኝ ጥያቄ መልስ አልነበረኝም ፡፡    ፍቅረኛዋ ማዳም ቤት በነበረችበት ወቅት የሚወዳትን ያህል አልሆነላትም ፡፡ እሷን የተከራየው ቤት ውስጥ አሰቀምጦ እሱ ውሎው ደጅ ነው ፡ ሲለውም አዳር አይመጣም ፡፡  ብዙ ጠብቃ የነበረችው የውጭ ኑሮም ፈታኝ ሆነባት ፡፡   ሰራ የላት ፣ የመኖሪያ ፈቃድ የላት ፣ እንደልብ ወጥታ አትገባ ፣  ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቿን መደጎም የማትችልበት ሁኔታ ላይ ደረሰች ፡፡
     ፍቅረኛዋን በጣም ነው የምተወደው ፡፡ ብዙ ነገር ከእሱ ጋር ታስብ ነበረ ፡፡ በአካል እና በቅርብ ስታገኝው ግን እንደጠበቀችው አሎነላትም ፡፡ ታዲያ የታሪኬ መቀየሪያ የምትለው ጊዜ ላይ ፡ ስልኩንም አድራሻውንም እስከነአካቴወ አጠፋባት ፡፡ የቤት ኪራይ ፣ ምግብ ፣ ወዘተ ማንም የሚሸፍነው አጣች ፡፡ ውጩንም አታውቀውም ወጥታም ሰራ ለመስራት  ድፍረት አልነበራትም ፡በዚ ሁኔታ ወራት አለፈ ፡፡

    አንድ እንጻላይ የምታውቃትን ኢትዮጵያዊት ለመቅረብ ወሰነች ፡፡ ቢያንስ እንደዚ ሁኜ ከምኖር በውጭ ከማውቀው ሰው ጋር የመጣው ይምጣ ብላ በራሷ ወሰነች ፡፡ የመጀመሪያ ምርጫዋ የነበረው እጇን ለፖሊስ መስጠት ነበረ ፡፡ ከዛም አገር ቤት ገብቶ የመጣውን መቀበል ፡፡ ሆኖም ከአሰሪዎቻ ቤት ሳትወጣ ብዙ ልጆች በውጭ ጠፍተው እንደሚሰሩ ሰምታለች ፡ የተሳካላቸውም  አግብተው ወልደው ፡ እነሱ ያዩትን ህይወት ደሞ
ማየት እና መጋፈጥ እንደማያቅታት እራሷን አሳምናለች ፡፡ ጊዜ መግደል አልፈለገችም አብራት አንድ እንጻ ላይ ወደምትኖረው አበሻ ፡ ቤት ሄዳ በሩን አንኳኳች ፡፡   እሷ ወደውስጥ ገብታ እስክትወጣ እኛ ደሞ እረፍት አድርገን ሳምንት ታሪኩን እንጨርሰዋለን ፡፡ 

« ሐዋሊን ፡ ሳስበው ፡ ሳስበው » ሁለት ፡፡

by Nezar Dage on Sunday, June 3, 2012 at 5:20am ·
                                   ሐዋሊን ሳስበው ፡ ሳስበው ፡፡

                                     ሁለት ፡፡
   ባለፈው የቆመንነው ወደ ሐዋሊ ለመግባት እየተንደረደርን ፡ በተለያዩ ታክሲ እና መንገዶች ሰለሚገጥማችው ገጠመኞች አውግተን ነው ፡፡  ያለነው አውን ገና ከ ሐዋሊ ደጃፍ ነን ፡፡ ዛሬ ዘው ብለን ወደ ሐዋሊ ከመግባታችን በፊት አንድ የምናየው ቦታ አለ ፡፡ አናንተ ባላችውበት ሆናችው እንድትከተሉኝ ለጊዜው አካላችውን ከተመቻችው ቦታ አንዱ ጋር አሳርፉት አና በህሊናችው ግን እኔን ተከተሉኝ ፡፡
    መንገዱን ጀምረናል ፡፡ የምንሄደው ወደማናውቀው ቦታ ወይም ዐገር አይደለም ፡፡ ተወልደን ወዳደግንበት ፣ ከፉ ደግ ወዳየንበት ፣ በጣም ወደምንወዳት ዐጋረችን ነው ፡፡ እዛ የተወሰነ ቆይታ አድርገን እንመለሳለን ፡፡ መቼም ሰለ ሐዋሊ አያወራን ወደ ኢትዮጰያ መሄዳችን ያሰገርማችው ይሆናል ፡፡ የምናየውን እና የምንታዘበውን ነገር አይተን ስንጨርስ ወደ ኢትዮጵያ የመሄዳችን ሚስጥር ይገባችዋል ፡፡

    እይታችንን እንጀምራለን ፡፡ አዎ ብዙዎች ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለባቸውን ችግር ሊፈቱ ፣ ሰርተው ሊለወጡ አስበው ፡ ሰደትን መፍቴ አድርገው እራሳቸውን ለሰደት ያዘጛጁ ወጣቶችን ፡ በተለይም ሴት እህቶቻችን ዋናውን ቦታ ይይዛሉ ፡፡   ሁሌም በሚኖሩበት ነገር ያለው ሀቅ ቢከብዳቸው ፣ በአቅማቸው ሊጋፈጡት የሚችሉት ነገር  ሰደት ነው አና. እራሳቸውን በሰደት መንገድ ላይ ሲያቀርቡ ያለምንም ማመንታት ነው ፡፡
  በፍቅር የኖሩበት የቤተሰባቸው ህይወት ፈርሶ ፣ ብዙ ያሰለመዳቸው የአባታቸው እጅ ታጥፎ ፣ ወደር የሌለው የእናታቸው ደግነት በችግር ተሸንፎ ማየት የሚከብዳቸው ፡ ወንድሞቻቸው ፣ እሆቻቸው ፣ ሲልም ፍቅረኞቻቸው እና የትዳር አጋራቸውን የጎበጠ ኑሮ ለመለወጥ ፡ ከማንም በፊት የሰደትን መንገድ ጀማሪዎች
የዛሬ የሐዋሊ እውነታወች ናቸው ፡፡

    በአገራቸው ቆመው ያሰቡትን ለማሳካት ፡ ሰርተው ጥረው ቤተሰብን ለመቀየር ካላቸው ፍላጎት አንጻር ፡ ምንም ባህላቸው ከባህላቸው ከማይዛመድ ህዝቦች ጋር
ቋንቋቸው ፡ ምንም ከማያውቁት ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር ለመኖር ወስነው በአይናቸው እንባ እያነቡ ሲወጡ ያኔ የድህነት መጥፎ ጎኑ ቁልጭ ብሎ ይታያል ፡፡  እያየን ያለነው ከመነሻው እዛው አገራችን ያለወን የዜጎቻችን የኑሮ ነጸብራቅ ነው ፡፡ በዚ አድካሚ የህይወት ጉዞ ፡ መድረሻቸውን ሳያውቁት ፡ ሻንጣቸውን አንጠልጥለው ፡ ከፈጣሪ ጋር ወደማያውቁት አለም ፡ አረብ ፡ አገር የሚጓዙትን   ህልመኞች እናስባቸው ፡፡
      ከአገራቸው ሁሉም ሰደተኞች ሲወጡ ይዘው የሚወጡት ተሰፋ ነው ፡፡ የነገ ትልቅ ህልም ፡፡ ይህንን ህልም ለማሳካት መውተርተር ፣ መባዘን ፡፡ ከምንም በላይ የሚያማቸው ቃል አለ ፡፡ በነሱ አንደሻማ መቅለጥ ፡ ብርሃን ሊሆኑት ያዘጋጁት ቤተሰበብ ፣ አደራ ፣ ፍቅር ፡፡  የእውነታው ግብ ግብም እዚ ይጀምራል ፡፡
    አውን ያለነው አንድ በችግር የተጎሳቆለ ቤተሰብ መሀል ፣ ድህነተ/ የበዛበት ሰፈር ውስጥ ነን ፡፡ እናንተ ህሊናችው የፈቀደውን ቦታ እዩ ፡፡ በዚ በችግር በተጎሳቆለ ቤተሰብ ማህል ፣ ችግር የውቂያኖስ ያህል የሰፋበት ማህበረሰብ ፡፡   ከዚ ማህበረሰብ ውስጥ   በአረብ ፡ አገር ሰደት ፡ ለመለወጥ ያኮበኮበች የትንሽ ልጅ ልብ ፡፡

     በማታውቀው አገር ልትኖር የገዛ ዐገፘ እንጀራ እናት ሰትሆንባት ፡ የማታውቀውን ያን ማዶ አዚ ሁና ዘውትር በሀሳብ አየቃኝችው ፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር በሰደት ሃሳብ ኖራ በሰደት ታደራለች ፡፡ የዛች እጻን የልብ ትርታ ሚስጥሩን የሚያውቀው የቅርቧነው ፡፡ እሷ ግን በዚ ሁኔታ ማለፍ አትፈልግም ፡፡ እንደ ጉም ለተነነው ለቤተሰቦቿ ማንነት ሰትል በማታውቀው አገር ጅብ ቢበላትም ትመርጣለች ፡፡ ከፊትም ከዋላም ያለው ነገር ሁሉ አሰፈሪ ነው ፡፡
    ዐገሯን ማሰብ አትሻም ፡፡ በአገሯ የመኖር ህልመም የላትም ፡፡ አሁን አሁን የእሷ አ.ኩያዎች ኢትዮጵያ የነሱ አትመስላቸውም ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት አገር ፡፡ በታላቅ ህዝብ መሀል ታናናሽ ህዝቦች የሚኖሩባት አሰከፊ ኢትዮጵያ ፡፡   እዚ ጋር ቆም ብለን ፡ ለደቂቃ የሐዋሊ ወጣት ሴቶችን እናስብ ፡ ከነሱ ውስጥ ደግሞ ትናንሽ ህጻናት ፡፡ 

        እቺን መሰል የአገራችን የዘመን ውጤቶች ፡ ቦሌ ኤርፖርት ሲገቡ የሚያነቡት በቃ ተለያየን እንባም ፡ ሳይፈልጉ መለየትን ፣ የወዶ ማጣትን ህመም እያሳየን ፡ አላማ ነው እና አገራቸውን እንደዘበት ጥለው ይወጣሉ ፡፡ አገራቸውን ጥለው በሚወጡ ዜጎች ልክ ፡ ብዙ ችግር ፣ ብዙ ስቃይ አለ ፡፡  በየቤቱ በየጓዳው እውነት የማይመሰል ፡ አሰከፊ ድህነት አለ ፡፡  የዚ ድህነት ቀንበር ተሸካሚዎች ደግሞ እነዚው እንቦቅቅላ ህጻናት እና ወጣት ሴቶች ናቸው ፡፡
      ሰለምታውቁት ኑሮ ብዙ አልልም ፡፡ ሁላችንም በየቤታችን ያለውን ድህነት እናውቀዋለን ፡፡ የዚ ድህነት ዋጋ ከፋይ ማን እንደሆነም እንረዳለን ፡፡ የማንረዳው ነገር ቢኖር ዋጋ የሚከፈልበት ገንዘብ አንዴት እንደሚመጣ አለማወቃችን ነው ፡፡
     አውን ወደዋናው ሀሳባችን ልንመጣ ነው ፡፡ የቤተሰብን ኑሮ ለመቀየር በየአረብ አገሩ የሚኖሩ ዜጎቻችን ፡ አንደምን እየኖሩ እንደሆነ ገንዘቡንስ እንዴት እያመጡ እንደሆነ ምን ያህሉ ቤተሰብ ያውቃል ፡፡ የዛን ማዶ እውነታ ሳያውቅ ፡ እህቴ በደወለች ፣ ፍቅረኛዬ በላከች እያለ ምንዱባን እየጠበቀ የሚኖረው ወጣትስ ፡ እውን ገንዘቡ እንዴት እንደሚመጣ ያስበዋል ?
  ልጄ በአመቷ አረብ ፡ አገር ሂዳ ታከሲ ገዛች ፣ ቤት ሰራች ፣ ወርቅ በወርቅ ፣ ገንዘብ በገንዘብ አንበሻበሸችኝ ብሎ የሚኖረው ቤተሰብስ ፡ የአረቦች ምድር ብር የሚፈልቅበት አገር አድርጎ ነው የሚያየው ወይስ እውነታውን እያወቀ ፡ «  የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው »  በሚል ተረት የልጆቹን የደም ደሞዝ እየበላ ነው ? የተቀመጠው ፡፡ በርግጥ በልጆቹ ብዙ ቤተሰብ አልፎለታል ፡፡ ከትላንት ጨለማ ወጥቶ ብርሃን አዮቶ ይሆናል ፡፡ ልጆቹ የሚኖሩበትን ህይወት ባያይም ፡ ባይሰማም ፡፡
   የዛሬ የኢትዮጵያ ቆይታችን በተከታታይ ለምናየው ሐዋሊ መሰረት ይሆን ዘንድ ነው ፡፡ በርግጥ የቆይታችን ሚስጥር ከገባችው ፣ አሁን ከሀሳባችው ነቅታችው ፡ ሐዋሊን ማየት አንጀምራለን ፡፡ አደራ የምላችው ግን እስከመጨረሻው የዛሬ ቆይታችንን እንዳትረሱት ነው ፡፡ ሐዋሊ ላይ በቆየን ቁጥር ከፊት እና ከዋላችን የምናያቸው ነገሮች በጠቅላላ መሰረቱ የት እንደሆነ ይገባችዋል ፡፡ 
    በአንዱ ሺሻ ቤት ቁጭ ብላ በሀሳብ የምትናውዝ ፣ በተሰፋ መቁረጥ ማንነት ውስጥ ያለችን አንድ ምስኪን ስታዩ በኢትዮጵያ ካየናቸው አንድ ደሀ ሰፈር ውስጥ ፡ ወደ አረብ ፡ አገር ልትሰደድ ያለችን  ህጻን አስታውሱ ፡፡  ከዛም እሰከመጨረሻው አብረን ከቆየን ፡ ሁሉንም እናያለን ፡፡ ከዛ በፊት ግን አንደዛሬው ድንገት ወደ ኢትዮጵያ አንሄድም ፡፡ ጽሁፉን ከማብቃታችን በፊት ፡ ኢትዮጵያ እንቆያለን ፡፡  እሰከዛው ግን ከዛሬ መልስ ጀምረን ሐዋሊን እናያለን ፡፡  የሐዋሊ ኮከቦች የተባሉትንም ፡ የአገራችንን ልጆች አፍ ለአፍ ገጥመን ሁሉንም ከነሱ እንሰማለን ፡፡  ለአሁን ባለንበት ቦታ ሁነን ቢበቃን እና ሳምንት ብንመለስስ ?
                      መልካም ፡ ሳምንት ፡፡

Saturday, October 6, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር

  
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል 6ኛ
   እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ሁሉ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ
በግሩም ተ/ሀይማኖት

   ሰላም ወዳጆቼ ነዛር የተባለ ወዳጄ የሰጠው አስተያየት ላይ ...ወዳጄ ግሩም ባለህበት ቦታ ሰላምታዬ ይድረስ፡፡ /እፍኝ ሙሉ ስላምታህ ደርሶኛል/ በጽሁፍህ መግቢያ የገለጽከውን የኩዌት የሞተውን ልጅ ሀዘን ጨምሮ እስከመጨረሻው ያለው ጽሁፍ በጣም ያሳዝናል፡፡ በእርግጥ የኩዌቱ ልጅ ሞት የቅርብ ጊዜ ሀዘን ነው፡፡ እኛም እስከመጨረሻው የማንረሳው ወንድማችን ነበር፡፡ በሀዘን በመረረ ቃልም ነው ሞቱ እውን አልመሰል ቢለኝ በጽሁፍ ያቀረብከውን የሀዘን እሮሮ የጻፍኩት፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ወንድማችንን አጣነው፡፡ ይህ እንግዲ በኔ የደረሰ የቅርብ እውነታ ነው፡፡ ዛሬም ግን ኩዌት ውስጥም ሆነ የተቀረው አረብ ሀገር የዜጎቻችን ግፍ፣ በደል፣ ሞት፣ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሁኖ አንድም ጥሩ ነገር ለመሰማት ጆሮአችን አልታደለም፡፡ እኔማ አንዳንዴ በቃበሻ ዋጋው እንዲህ ሆነ፣ ማነው ይህንን በደል የሚያስቆም? መቼ ነውስ በየአረብ ሀገሩ ለሚንገላታው ዜጋ መላ የሚሰጠው? የውስጤ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡

 ከመቼውም በተለየ መልኩ እርስ በእርሳችን ተጨካከንን ድህነታችንም ከፋ፡፡ማንም አረብ መጫወቻ ሆንን፡፡ ታዲያ የዚህ ችግር መፍቻ ቁልፉ ምንድነው፡፡ በ2004 ወደ አረብ አገር የተሰደደውን ሰደተኛ ብዛት ለአንተ አልነግርህም፡፡ /እሱ ለእኔ ባይነግረኝም እኔ ልንገራችሁ፡፡ በ2011 ብቻ 103.000 ኢትዮጵያዊያን ወደ የመን ገብተዋል፡፡ ይሄ አንድ ሀገር ነው በአጠቃላይ አረብሀገር አስሉት፡፡/ ለኔ ጉድ ያሰባለኝ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ እየተመለስኩ ኤርፖርት ያገኘኋት አንድ የቅርብ ወዳጄ ግን ውስጤን ይበልጥ እንዲሰበር ነበር ያደረገችኝ፡፡ ነርሰ ናት፡፡ በሙያዋም ተቀጥራ ትሰራ ነበር፡፡ አንድ ወቅትም የድግሪ ትምህርቷን ቀጥላ እንደነበረ አጫውታኛለች፡፡ በዛን ሰዓት ሳገኛት ግን በሀገሯ መኖር አማሯት ሳውዲአረቢያ የቤት ሰራተኛ ሆና ለመሄድ ስትል ነበር ኤርፖርት የተገናኝ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንግዲ ምንም የለም፡፡ መጪው ጊዜ ግን እንዲህ አይነት የዜጎች ሰቆቃ የማናይበት እንዲሆን የዘውትር ምኞቴ ነው………ብሏል፡፡ የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡

ያን ተከትሎ አንዲት ልጅ ቻት ስታደርገኝ የመምህራን ኮሌጅ ዲፕሎማዋን ይዛ ታስተምርበት የነበረውን ትምህርት ቤት ተሰናብታ ወደ አቡዳቢ መንጎድዋን ስትነግረኝ መሪር ሀዘን ነው የተሰማኝ፡፡ ሀገር ውስጥ የተማሩት ስራ አጥተው ኮሊንስቶን ይሰራሉ ተብሎ በሚዲያዎች ገኖ መውራቱ ገርሞኝ ነበር፡፡ የገረመኝ መስራታቸውን ተቃውሜ አልነበረም፡፡ ሀገራቸው ሆነው ቢሰሩ ምናለበት በሚል ነው፡፡ ዲፕሎም እና ዲግሪ ይዘው እንደዚህ በሰው ሀገር መገረድን ሲሰማስ ምን ይባላል? በሀገር የተገኘውን መስራት ክብር መሆኑ ይሰመርበት፡፡ ጀምሬው የነበረውን ሀበሻዎች በሉብናን ያላቸውን ህይወት የሚዳስስ ታሪክ ልመለስበት ወደድኩ…. ከዛ በፊት ግን አዜብ የተባለች የፌዝቡክ አንባቢዬ ስልኬን አንኳኳች፡፡ ስከፍተው ጠላታችሁ ክፍት ይበል ልብ የሚያለሰልስ ብርጭቆ ወረቀት የሆነ ድምጽ በጆሮዬ ተንኳለለ፡፡ ‹‹ግሩም /ሀይማት ነህ?›› ስሜን ከእነአባቴ ግሩም /ሀይማት ብላ ስትጠራ../ቤት ክፍል ውስጥ የሚደረግ ስም ጥሪ መስሎኝ ‹‹አቤት!›› ብዬ በጩኸት ላደምቀው ስል ‹‹..ነህ..›› የሚለውን ጨመረችልኝ፡፡ አቤት የኔ ቆንጆ ቲቸር ማን ልበል? አልኳት፡፡ የተደወለልኝ ቁጥር ከየመን ስለሆነ የሚያውቁኝ ናቸው ብዬ ለመቀለድ፡፡

     የሆነ ደስ በሚል ቅላፄ ‹‹አታውቀኝም እዚህ የመን መጥቼ ነው፡፡ ችግር ገጥሞናል፡፡…›› ሳግ ነገር የተናነቃት መሰለኝ፡፡ ‹‹..ሸሽሽ…›› የሚል ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ‹‹..የለ ተሀረኩ..የለ..›› የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ ‹‹አናግሪው ቶሎ በይ..›› የሚል ድምጽ ከጀርባ በደከመ ሁኔታ ይሰማል፡፡ ‹‹ሄሎ ከኤርፖርት ይዘውን ሚግሬሽ እስር ቤት ሊወስዱን ነው፡፡ ምን ትረዳናለህ..እባክህ እርዳን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው፡፡ መመለስ አልፈልግም እባክህ…›› በለቅሶ ታጀበ፡፡ አይኔ ባያነባም ውስጤ ግን አብሯት አነባ፡፡ ቢሆንም መጠየቅ ስለነበረብኝ ከየት ኤርፖርት ነው የያዟችሁ ወዴት ስትሄዱ..

   ‹‹ሰነዓ ኤርፖትርት ላይ ነው የያዙን ወደ ቤይሩት እየሄድን ነበር…›› ተቋረጠ፡፡ ሜግሬሽን ሄጄ ላገኛቸው ፈለኩ፡፡ ያለሁበትን ሱቅ የሚጠብቅልኝ ሰው ስፈልግ ቆየሁና አገኘሁ፡፡ በዚህ አገር አጠራር ጀዋዛት የሚባለው እስር ቤት ሄድኩ፡፡ አሁን ስላወኩት ከፊት ተጠቀምኩኝ እንጂ በሰዓቱ ስሟን ስላልነገረችኝ ማን ብዬ ላስጠራት፡፡ ተጠጋሁና ተደወሎልኝ ነበር ማን ነው የደወለልኝ ስል ‹‹አዜብ..›› አሉ እና ጠሯት፡፡ ትንሽዬ ልጅ መጣች፡፡ እድሜዋ ያለማጋነን 16 ወይም 17 ቢሆን ነው፡፡ ግራ መጋባትና ፍርሃት የተራኩቱት ፊቷን ሳይ አሳዘነችኝ፡፡ ተጨባበጥንና ‹‹ስሜ አዜብ….ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ጓደኛህ ነኝ፡፡ የምትጽፋቸውን ባይም ያለኝ አማራጭ ነው እና ቤይሩት ለመሄድ መጥቼ ኤርፖርት ላይ የእናንተ ቪዛ የተስተካከለ አይደለም ብለው 15 የምንሆነውን ያዙን አሁን ወደ ሀገር ሊመልሱን ነው እባክህ አግዘኝ ስንት ከስክሰን…›› እንባ ቀደማት፡፡ ለስደት ህይወት ማጀቢያው እንባ፣ ብስጭት፣ ፀፀት እና ጭንቀት ናቸው፡፡ የጀመረችውን ትጨርስ ብዬ በዝምታ ዝምታ ውስጥ ሰፍሬ አይኔን ከአንዳቸው አንዳቸው ላይ እያንቀዋለልኩ ጠበኳት፡፡ ብዙ አወራን፡፡

    ይመለከተዋል ያልኩትን ሰው ፈልጌ ላናግር ሞከርኩ፡፡ እንደጅብ ቆዳ ቅኝቱ ‹‹እንብላው..እንብላው..›› ብቻ ሆንብኝ፡፡ እዚህ ሀገር ግልጽ ሙስና ነው ያለው፡፡ ያበደረህን ገንዘብ የሚጠይቅህ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹ለአንድ ሰው 400 ዶላር ክፈል እና እፈታልሀለሁ..›› ተባልኩ፡፡ ኪሴ ያለችኝ 4000 ሪያል ናት፡፡ በዶላሪኛ ስትሰላ 20 ዶላር ማለት ነው፡፡ አስቡት ልዩነቱን፡፡ ተመለስኩኝ እና ያሉኝን ነገርኳት፡፡ የሚበሉ የሚጠጡት ነገር ገዛዝቼ አቀበልኳቸው እና ብር ከላኩልኝ ደውልላቸው ላለችኝ ሰዎች ደዋወልኩኝ፡፡ አንድ ብር ያሰከረው ጉንጩን በጫት የወጠረ ሰው መጣና ‹‹አንተነህ ያናገርከው?›› አለኝ፡፡ ቢጨንቀኝ እንጂ የማወጣበት ገንዘብ እንደሌለኝ ነገርኩት ‹‹…ሁሉን ከፍዬላቸዋለሁ ማታ ወደ ቤይሩት ይሄዳሉ…›› ማንም አይወጣም ሲል ድንፋታ የምትመስል ነገር ወርውሮልኝ ሄደ፡፡

   ውስጤ እያዘነ ተሰናብቻቸው ከሚግሬሽን እስር ቤት ወጣሁ፡፡ መቼ ነው ፈጣሪ የሚሰማን? መቼ ነው እንባችን ስፍሩን የሚሞላው? መቼ ነው በቃ! የሚለን? እውን መንግስት ቤይሩት መሄድን አስቦበት ነው የከለከለው? ከሆነ ይህን አይነት ድርጊት ሲፈጸም እንዴት አያውቅም? በኬንያ ቪዛ እንዴትስ የመን ሊመጣ ይችላል? የመሳሰሉትን አሰብኩ፡፡ ከማሰብ ውጭ ግን ምን አመጣለሁ? በቀረችኝ ሳንቲም ታክሲ ተሳፍሬ ጉዞዬን ስቀጥል ስለ ቤይሩት የሰማሁትን ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ያሰላሰልኩት ብዙ ነው ባለፈው ወደጀመርኩት ታሪክ ልንጎድ…..     
          
   በተከታታይ በቻት ሳጥኔ ሳትታክት እየጻፈችልኝ ያለችውን እህታችን ደግሜ ላመሰግናት ወደድኩ፡፡ ቀጠልኩ.. ከላይ እንደገለጽኩልህ ልጅቷ የተሰጣት መልስ ጥሩ ስላልሆነ መፍትሄም ስላጣች ያላት አማራጭ መጥፋት ነበርና ጠፋች፡፡ ጠፍታም ለረጅም ጊዜ የተለያየ ቤት ሰርታለች፡፡ ካንዱ ስትወጣ ስራ አጥታ ረጅም ጊዜ ስትቀመጥ ብዙ ተቸግራለች፡፡ አሁን ያለችበት ቤት ሁለት አመቷ ነው፡፡ ሰውዬው ደስ ሲለው ይከፍላታል ሲያጣ ይከለክላታል፡፡ እንደዛም ሆና እንደነገረችኝ ልጅዋን በጥሩ ሁኔታ እያስተማረች ነው፡፡ ወላጆች ግን ልጄ ምን ሰርታ ነው ብሩን ያመጣችው አይሉም፡፡

   የእኔውን ቤት ጉድ ደግሞ ልንገርህ…እኔ የነበርኩበት ቤት 3 ሰው ብቻ ነው ያለው፡፡ ቀን ቀን አይውሉም፡፡ ሴትዮዋ መጥፎ የምትባል አይደለችም፡፡ ልጁ ተማሪ ነው፤ እሷ ስራ አላት፡፡ ወንድሟ ደግሞ የቤተሰብ ድርጅት ውስጥ ይሰራል፡፡ ታዲያ ግን ቤት ውስጥ ስራው ማለቂያ የለውም፡፡ የምተኛው ሌሊት 7 ሰዓት ነው፡፡ የቀኑን ወደ ሌሊት ገልብጠውታል፡፡ ቀን ቀን ቤት ስለማይውሉ ስራ ብዙም አያስቸግረኝም፡፡ ከ10 ስዓት በኋላ ግን መቀመጥ እስኪያቅተኝ በስራ ያጣድፉኛል፡፡ በዛ ላይ ከ7 ሰዓት በኋላ ያለውም ቢሆን መተኛት አትበለው፡፡ ልጇ ቀበጥ ነገር ነው፡፡ የ11 አመት ልጅ ቢሆንም አጠገቡ ያለውን ውሀ ማንሳት አይፈልግም፡፡ መጥሪያውን ተጭኖ ይጣራል፡፡ እንደሰው መተኛት ያለብኝ አይመስለውም፡፡ እሱስ ባልከፋ እንቅልፍ ነው የነሳኝ ሱሰኛ የሆነው ወንድሟ ሌላ ፈተናዬ ነበር፡፡ ፍላጎቱ የተወጠረ ስሜቱን ማርገብ ነው፡፡ ለእኛ ያለው አመለካከት በንቀት የተሞላ ነው፡፡ በቃ! ለስሜት ማስከኛ የተፈጠርን እቃዎች ነው የምንመስለው፡፡

    አንዳንዶቹ በፍርሃትም ይሁን በፍላጎት ፍቃደኛ ስለሚሆኑላቸው መሰለኝ ‹‹..አንቺ ከሌሎቹ በምን ትበልጫለሽ? በፊት ከነበሩት ውስጥ እከሊትን..እከሊትን እንዲህ አደርግ ነበር ይለኛል ስማቸውን እየጠራ፡፡ እሺ እንደማልለው ሲያውቅ ሁሌም ይዝትብኛል፡፡ ለሴትዮዋ የሆነ ያልሆነውን ይነግራታል፡፡ በዚህ ምክንያት ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ቤት ትቆልፍብኝ ነበር፡፡ በዚህ በጣም ስማረር ቢሮ ሌላ ቦታ እንዲቀይሩኝ ነገሬ ተቀየርኩ፡፡ የተቀየርኩበት ቤት የሚገርምህ ጥቁር አትወድም፡፡ የወሰደኝ ባልዋ ነበር፡፡ ከእኔ በፊት የነበረችው ማዳጋስካራዊ ቀላ ያለች ነበረች፡፡ ከእኔ ጋር አንድ ፊሊፒኒሳዊ ተቀጥራለች፡፡ ሁለት ነን ማለት ነው፡፡ እኔ 4 ልጆቿን እይዛለሁ ፊሊፒንዋ ቤት ታጸዳለች፡፡ ምግብ ቤት ውስጥ አይሰራም፡፡ እዛ ፎቅ ላይ ያሉት ሁሉ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ልጆቹ አያቶቻቸው የሰሩትን ነው የሚበሉት፡፡ አባትየው የት እንደሚበላ አናውቅም፡፡ እሷ ከልጆቹ ጋር ትበላለች፡፡ እኔና ፊሊፒኗ በመሀል ፍዳችንን በላን፡፡ አንድ ሴጣናም ልጅ አላቸው እሱን ይዤ ስንቀዋለል ነው የምውለው፡፡ ከፊሊፒንስዋ እንዲያውም እኔ እበላለሁ፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ አያት ቤት ያለችው ሀበሻ ነች፡፡ እስዋ ትሰጠኛለች፡፡ የምግቡ እና የልጁ ሁኔታ ሲመረኝ ጠፋሁ፡፡

    ከመጥፋቴ በፊት እሰራበት የነበረው ቦታ ከፊት ለፊት ያለው አፓርትማ ላይ ያለችው ደግሞ ጠዋት11 ሰዓት ተነስታ ስራ ትጀምር እና ሌሊቱን ሁሉ አትተኛም፡፡ ስራ ባይኖር እንኳን እህቶቿ ጋር ትወስዳታለች፡፡ ሌላም እታች ያለች ኢትዮጵያዊት አለች፡፡ እሷ ደግሞ ከማንም ጋር እንድትገናኝ አትፈቅድላትም፡፡ መውጫ ሰዓታቸውን ጠብቃ ነው ወደ እኛ የምትመጣው፡፡ የእሷ አሰሪ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ፓንቷን እንኳን ማውለቅ አትፈልግም፡፡ ለሁሉ ነገር ጥሪ ነው፡፡ ቤቱን ካጸዳች በኋላ ሴትዮዋ ቼክ ታደርጋለች፡፡ በዚህን ጊዜ አውቃ ግርግዳው ላይ ወይም ሶፋ ስር ቆሻሻ ታደርግና አልጸዳም ብላ ታሰቃያታለች፡፡ ከጨረሰች እኛ ያለንበት አፓርትማ ላይ እህቷ ስላለች እሷም ጋር ታሰራታለች፡፡ ከጠፋሁ በኋላ ግን ምን ላይ እንዳለች አላየኋትም፡፡

     አሁን የምሰራው ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ ነው፡፡ ያለሁበት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ስራቸው ግን ያስጠላል፡፡ ሴትነታቸውን ይሸቅጣሉ፡፡ ከተማውን እንደጨረስክ ያለው ቦታ ነው የሚሰሩት፡፡ እዚህ ያሉት ሶሪያዊያን ሲነግሩኝ በ50.000 የሉብናን ገንዘብ ነው የሚሰሩት፡፡ ይህ ማለት 27 ዶላር አካባቢ ባለ ዋጋ ራሳቸውን ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዴ ግን ቢዝነስ ቢሰሩ አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱን ቤት ሰራተኛነት ከጀርባው ያለውን ችግር ስታይ የግድ የሚገፋቸው ነገር ታያለህ፡፡ የዛኑ ያህል የሚያናድዱኝ በነጻ ቪዛ መጥተው በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩት ናቸው፡፡ አሁን የምሰራበት ቦታ ሶስት ወንዶች ናቸው የሚሰሩት እኔ ብቻ ነኝ ሴት በየአመቱ ለሶስት ወር የሚያግዛቸው አንድ ሴት ይቀጠርላቸዋል፡፡ ልክ አሁን እኔ እንደተቀጠርኩት፡፡ ታዲያ ከባንግላዲሾች እና ሶሪያዎች ጋር በማይረባ ብር ይተኛሉ፡፡ ሁሉ እንደ እነሱ ስለሚመስላቸው በእርካሽ ትገኛላችሁ ይላሉ፡፡

   ይወራ ከተባለ ለጉድ ይወራል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ካሉት መካከል ወገናቸውን የሚሸጡ የመኖራቸውን ያህል ለሰው ችግር ቆዳቸውን የሚገፈፉ ጥሩ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ኤቢ ደመቀ በአብዛኛው የመን ባለ እና የመን በነበረ ሰው ዘንድ የሚታወቅ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ዮሀንስ ተስፋዬ /ጆኒ/ የሚባል ልጅ አለ፡፡ ከረንቦላ ቤት ስለነበረው ጆኒ ከረንቡላ ይሉታል፡፡ ከባህር የመጡትን ከረንቡላ የሚያጫውትበት ቤት ውስጥ ከማሳደር አንስቶ የማይሰራው በጎ ስራ የለም፡፡  በተጨማሪ ኩሩቤል የሚባል ኢትዮጵያዊ UNIDOM የተባለ ድርጅት አዋቅሮ ብዙዎችን ለመርዳት ሞክሯል፡፡ ስለእነዚህ ሰዎች በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ አሁን ያነሳኋቸው ቀጣይ ለማቀርበው ታሪክ ምክንያት ስለሆኑኝ ነው፡፡ በሚቀጥለው በቀጠሮ እንገናኝ
                        ሰላም ሰንብቱ