Monday, April 23, 2012


 ስለሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የማውቀውን እውነታ ለማስጨበጥ አንድ ዙር ጫር..ጫር ያደረኩትን አቋድሻችኋለሁ፡፡ በቀጥታ ወዳቆምኩት ቃለ ምልልስ ከምሄድ ደጋግመን በመገናኘታችን ምክንያት በአንድ ወቅት አስቂኝ ገጠመኝ ነበረ፡፡ በገጣሚ እና የሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዘዳንት በወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን /አሁን ኢንተርፕሪነር ሽፕ ስራ ተሰማርተው በኢቲቪ የሚተላለፈው ስራ ፈጠራ እና ተነሳሽት ውድድሩ ላይ ዳኛ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ወ/ሮ ሙሉ በዛን ወቅት ነው የሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዘዳንት የነበሩት፡፡ በሌላ አባባል ብዙም ቅርርብ ስለሌለን ነው አንቱ ማለቴ እንጂ የየጥበብ ሰው አንቱ የሚባል ሆኖ አይደለም፡፡/ እና በወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን አስተባባሪነት ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቀዱ፡፡ በሰዓቱ የወ/ሮ ሙሉ አላማ አፈወርቅ ተክሌ ከመገናኛ ብዙሀን ብዙ የራቁ ስለሆነ ለማቀራረብ የተደረገ መንገድ ነው፡፡ ምን ያህል ስኬታማ ሆኗል የሚለውን አላውቅም፡፡ ስለ ስኬቱ እና አሁን ስለማቀርበው ገጠመኝ የሚያስታውሱት ካለ ወ/ሮ ሙሉ እዚህ ላይ ቢጨምሩበት እጠይቃለሁ፡፡

       ጋዜጣዊ መግለጫውን ሊሰጡን ተጠራን፡፡ በቪላ አልፋ ጊቢ ውስጥ ነው ጋዜጣዊ መግለጫው፡፡ በኢቲቪ የአውደሰብ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነ ስለሺ ይሁን ሽመልሽ..ስሙ ተረሳኝ በቴሌቪዥን ፕሮግራሜ ላይ ላቀርቦት ፈልጌ በደብዳቤ ጠይቄዎት እሺ አላሉም፡፡ ከመገናኛ ብዙሀን የሚርቁት እርሶዎ ነዎት አለ…፡፡ ለዘብ ባለ አነጋገር መጀመሪያም ከልብ አልነበረም አጠያየቅህ ጋዜጠኛ ቢጋበትም ያንኳኳል እኮ…አሁን ማነው ምኒልክ የሚባል ጋዜጣ አዘጋጅ አለ፡፡ ስለእኔ ተከታትሎ ነው የሚሰራው መረጃውን ከየት እንደሚያመጣ ሁሉ ይገርመኛል፡፡ አንተ ግን ..መቼ ስሜን እንኳን አስተካክለህ ጽፈህ ነው….እያሉ ሲናገሩ አቋረጥኩና አሁንም አለሁ ጥያቴ አለኝ ስላቸው ሁሉም በሳቅ አደመቁት፡፡

       ወደ ቀረው ቃለ-ምልልስ እናምራ እና በኋላ ትንሽ በሌሎች ጉዳች ላይ እመለሳለሁ፡፡  በዛን ወቅት ሳናግራቸው Great minds of the 21th century የሚል ሽልማት ነበር የተሰጣቸው የአለም ሎሬትነት ማዕረግ ቢሰጣቸውም በየትኛውም የመገናኛ ብዙሀን አለመነገሩ ይገርመኝ ስለነበር ‹‹የአለም ሎሬየት የሚለው ማዕረግ የተሰጠዎት ቅርብ ጊዜ ነው ሲሰጥዎትም ሆነ ከተሰጥዎት በኋላ በመገናኛ ብዙሃን የተሰማ ነገር የለም፡፡ ይታወቃል ብለው ነው ወይስ ያልተሰማበት መንገድ ይኖረዋል?..›› ስል ጠየኳቸው፡፡ መልሳቸውም ‹‹ይሄ ነገር ያልተሰማው እኔ እንደሚመስለኝ ከንቀት የተነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስት ቴሌቪዥንና ሬድዮ የሚያስተጋባው የሚታዘውን መሰለኝ፡፡ ያዘዘው ሰው ይኑር አይኑር አላውቅም፡፡ የአለም ሎሬት ለመሆኔ ክሪዲንሺያሉ /ማረጋገጫው/ ያው እዚህ የምታየው ነው..››

    ተነስቼ ዲፕሎማው ወዳለበት በመሄድ አየሁት፡፡ ከበርካታ ሽልማቶች መካከል ልክ እንደ ሌሎቹ ለራሱ በተሰጠው ዙሪያው ወርቅማ ከለር ባለው መስታዎት ፍሬም ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ሽልማቶቹን ሳይ ስለ እሳቸው እስክንድር ነጋ የነገረኝ መረጃ ታወሰኝ እና በፍጥነት ዞርኩ፡፡ መጠየቅ ያለብኝ ሰዓት ነበረ እና ጠየኳቸው፡፡ ‹‹ዓለም አቀፋዊ ጉባዔ ላይ ለመገኘት ከነገ ወዲያ ወደ እንግሊዝ ይሄዳሉ በዚህ ጉባዔ መዝጊያ ላይ በታወቁት የታሪክ ተመራማሪ በአርነስት ኪም ስም የተሰየመ ሽልማት አለ፡፡ ለእዛ ሽልማት እጩ ነዎት ይህ ሽልማት ምን አይነት ነው?›› አልኳቸው፡፡

    ‹‹ይህ ሽልማት ክብር ነው፡፡ በገንዘብ በኩል የገንዘብ ተሸላሚነት የለውም፡፡ ለምን አብዛኛውን ጊዜ በሰው አእምሮ ውስጥ የሚኖረው እንደ ኖቬል በብዙ ሚሊዮኖች እና በሺህዎች የሚገኝ ነገር እንዳለ ነው፡፡ አስተዋፅዖው ስምህ ሪኮግናይዝድ መሆኑ ብቻ ነው..›› አሉኝ፡፡ በዚህ ዙሪያ ባለኝ መረጃ መሰረት ‹‹..እርስዎ በዚህ ጉባኤ ላይ አራት ወጥ የፈጠራ ስራዎትን ከ40 ምርጥ የስላይድ ስዕሎች ጋር ይዘው ይሄዳሉ ተብሏል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው? ከስራዎችዎ ውስጥስ ለዚህ ጉባኤ እንዲሆኑ ብለው የመረጡበት መስፈርት እንዴት ነው? ከታሪክ፣ ከፈጠራ ምሉዕነት፣ ወይስ ከእነሱ አላማ ጋር የሚሄዱትን አስበው ነው?...›› የሚል ጥያቄዬን ሰነዘርኩ፡፡

     ‹‹ስለአፍሪካ ምንድን ነው አስተዋጽኦ የማደርገው? ስለሀገሬስ ምንድን ነው አስተዋጽኦ የማደርገው? በምልበት ጊዜ መጀመሪያ የኢትዮጵያን ስነ-ጥበብ ታሪክን ማጎልበትና አንዲት ስራ ዛሬ ላይ እንደ ወሬ እንደጫዎታ ሆኖ እኛ ካለፍን በኋላ ስለ እኛ ዘመን አንድ አስተዋጽኦ አድርጌ ማለፍ፡፡ እንደ አክሱም፣ ላሊበላ እንደ ቅርሳችን የሚሆን አንድ ነገር ለማውረስ ነበር፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ አጋጣሚ ሆኖ አፍሪካውያኖች ለነፃነታቸው የሚታገሉበት ጊዜ ነበር፡፡ እና በዚህ ላይ እኔ ምን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ? በምልበት ጊዜ ያው በአፍሪካ አዳራሽ የሚገኘው የመስታዎት ስዕል (ዘስትራግል ኤንድ ኦስፕሬሽን ዘ አፍሪካ ፒፕል) የሚለውን ሰራሁ፡፡…›› ይህን አባባላቸውን አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እውነት ለታሪክ፣ ለሀገር የሚቀር ነገር ስርተው አልፈዋል የሚለውን በድፍረት መናገር ያስችላል፡፡

     ስለዚህ ስዕል እና ስለሌሎች ስራዎቻቸው ቀጥለው ያሉኝ ‹‹..በውስጡ ያለው ፍልስፍና፣ የትግሉን ወደ ፊት ተስፋ ምን እንደሆነ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ያሳያል ብዬ ከማምነው ስራዬ አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ እኔ በሰዓሊነቴ ምንድን ነው አስተዋተጽዖ የማደርገው? ይሄው ተማርኩ፣ ታለንትም አለኝ፡፡ ነገር ግን ተመልሼ ሀገሬ በምሰራበት ጊዜ ምንድን ነው አንዱ በሀገር ውስጥ መገኘት ነው፡፡ ሁለት የሀገርን ታሪክ አውቆ ከዚህ ውስጥ ምን መጨመር ይቻላል ብሎ መስራት ነው፡፡ ያንን እውን ለማድረግ መስራት እና በስራዬ መግለጽ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ አንኳር አንኳሩን በዘመናችን መታሰብ ያለባቸውን ወደ 28 ያህል ቴምብሮች ህዝቡም የሚያየው የእኛን ታሪክ በውጭ የሚያሳይ ፣በቀላሉ ሰው እጅ የሚገባ እነሱን መስራት ጀመርኩ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከሚታዩት አንዱ ይሄ ኮሌክሽን ስታምፕ ያለበት ነው፡፡

   ‹‹…ከዚህ በላይ ደግሞ አፍሪካን በሚመለከት ደግሞ እንደዚሁ የአፍሪካ ቅርስ ምንድን ነው? ምንድን ነው የወረስነው? እንዴትስ ነው የምናስተዋውቀው? ወደ ፊትስ ምን መጨመር አለብን? የሚለውን አክዬ የአፍሪካ ቅርፅ (አፍሪካን ሄርቴጅ) የተባለው ዋናው ስራዬ አሁን በብሄራዊ ሙዚየም የሚገኘው ነው፡፡ አፍሪካኖች የታሪክ ደሀ አለመሆናችንን በስራዎቼ ሊያዩ እንዲችሉ፤ የፀሀይ መብራት ሲበራበት የሚታየው ስራዬ ብዙ ሰዎች ከውጭ ሀገር እየመጡ የሚመለከቱት እሱን ነው፡፡
 
     ከዚህ ቀጥሎ ምንድን ነው ሌላው ስራዬ ኮንሰርን ያደረገው የአፍሪካን አንድ መሆን፣ አንድ በመሆን ሰላምን አግኝተን፣ ራሳችን አውቀን፣ እያንዳንዱ ስራ ተገኝቶለት፣ በእኩልነት እና በህብረት፣ ፍቅር የሚጎለብትበት ዘመን ለማየት በስራዬ ጥረት ያደረኩበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ስራዬ ኦ.ኤ.ዩ ከተመሰረተ በኋላ ኤምብለም ይውጣ በተባለ ጊዜ ያደረኩት ሶስት እጆች የጥቁሩ፣ የጠይሙ፣ የነጩ ተባብሮ አንድነትን ሲፈጥር የፀሀይ ብርሃን ይወጣል፡፡ የፀሀይ ብርሃን የህይወት ዋናው መንቀሳቀሻው ስለሆነ የሚል እሳቤ ነበረኝ፡፡ ከቆየሁ በኋላ ግን የአፍሪካ ህብረት ብቻ መች ይበቃል? የአለም ህብረት መኖር አለበት በሚል ያው እንደሚታየው አራቱ እጆች ተባብረው ሲተሳሰቡ አዲስ ብርሃን ይመጣል፡፡ ይህን እና ይህን የመሳሰሉትን ስራዎቼን በማየት ነው እነዚህ ሰዎች የጋበዙኝ፡፡›› የሚል ምላሽ ሲሰጡኝ ሌላ ጥያቄ አቀበልኳቸው፡፡

   ‹‹..እነዚህ አሁን የጠቃቀሱልኝ ስዕሎች ከእነሱ አላማ ጋር ይዳል ብለው ነው የመረጧቸው? ሽማቱንስ አገኛለሁ ብለው ያስባሉ? ብዬ ጠየኳቸው፡፡ በእርግጥ በነበረኝ መረጃ መሰረት ያ-ፋውንዴሽን በቂ ያለውን ሰው ያጫል ድምጽ ይሰጣሉ፣ ይሸልማሉ፡፡
 
    ‹‹እንግዲህ እዚህ ላይ ግልጽ ይመስለኛል›› አሉ እና በስላይድ ካዘጋጁት ስዕል ውስጥ የተወሰነውን አሳዩኝ፡፡ ቡርሽ ቤቷን አውቃ ገብታለች የሚል እሳቤ ውስጤ ተላወሰ፡፡ ልክ ነበርኩ፡፡ እሳቸው የተጠበቡት እያሉ እኔ ለማየት በመብቃቴ ኮራሁ፡፡ የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ውስጤ ያልነበረ ስዕል የመስራት ፍቅር ያኔ ተወልዶ አደገ፡፡ ለነገሩ የአለም ዋንጫ ሰሞን ሁሉ ኳስ ተጫዋች መሆን ያስብ የለ? የእኔም ሀሳብ ከዛ አልዘለለም፡፡ ያሳዩኝን ሲጨርሱ የሰጡኝ መልስ….

   ‹‹እነሱ እኔን ለመጋበዝ ያላቸው ምክንያት ስራዎቼ ከእነሱ አላማ ጋር የገጠመ በመሆኑ እና አሁንም ይሄ ሰውዬ ራሱ/አርነስት ኪይ/ የአለምን እንደዚህ አይነት ነገር አስተዋፅዖ የሚያደርጉትን ሰዎች በመብራት እየፈለገ ታሪካቸውን ይፅፍ ስለነበር እሱ በአረፈ ጊዜ በስሙ ይሄ ፋውንዴሽን ተመሰረተ፡፡ በኮንግተረሱ ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ኢንቨስትጌትድ ናቸው፡፡ በእነሱ መካከል ይሄን አላማ በፈጠራ ስራው ያራምዳል የሚሉትን የዛ ፋውንዴሽን ሴኔት ሽልማት ይሰጣል፡፡ እኔ ራሴም ኮንግረሱ ላይ እሄዳለሁ እንጂ ለዚህ ሽልማት እበቃለሁ ብዬ በሀሳቤ የለም፡፡›› አሉኝ፡፡ ቢሆንም ግን ሽልማቱን ተቀብለው ከመጡ በኋላ ተገናኝተን ‹‹ይበልጥ እንድሰራ ያበረታታኛል እንጂ አያሰንፈኝም፡፡›› ብለውኛል፡፡ ቃለ-ምልልሱን በደረግንበት ወቅት እስካሁን ከተሸለሙት ውስጥ የትኛውን ይበልጥ ይወዱታል? የትኛው ነው የበለጠ ክብርስ ያለው? ብያቸው ነበር፡፡ ማበላለጥ ይከብዳል ሁሉም የሚሸልሙህ ስራህን ወደው አክብረውህ እስከሆነ ድረስ አንተም የሸለሙህን ልታከብረው ግድ ይላል፡፡ ቢሆንም ግን ዋጋቸው /ክብራቸው ይለያያል፡፡ እኔ በመሸለሜ ይበልጥ ደስ ያለኝ.. The International Biographical Center of Cambridge በስነ ሙያ ጥበብ የመጨረሻ ሽልማት የሆነውን Davinci Diamond የደቬንቺ አልማዝ የተባለው ሽልማት ለእኔ ልዩ ነው።

    ከዛ በላይም The United Cultural Convention of the United States of America የተባለው ማዕከል International Peace Prize ልዩ ሽልማትና፣ የክብር የሰላም አምባሳደርነትን ሰጥቶኛል፡፡ Great minds of the 21th century የሚል ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ ይህም ትልቅ ክብር ያለው ነው፡፡ በተቀረ የምጠላው ሽልማት የለኝም፡፡ ቢኖር አልቀበልም ነበር፡፡ ይህች አባባላቸው ፈገግ አድረጋኛለች፡፡

    እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እንደ ጥበብ ሰውነታቸው በጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ነጻነት፣ ባሕልና ሥልጣኔ እንዲሁም በግዕዝ ቋንቋ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታቸው አስተምህሮ፣ ትውፊትና ስርዓት በእጅጉ የሚኮሩ ናቸው፡፡ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታቸው የነበራቸውን ጥልቅ ፍቅርና ክብር ከገለጹባቸው መካከልም የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመቅደሱ፣ ግድግዳዎች የሌሎችም በርካታ አድባራት የእሳቸው የጥበብ ትሩፋታቸውን ያረፉባቸው እንደሆን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ባሳተሙት የህይወት ታሪካቸው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
           እግዚአብሄር ነፍሳቸውን በገነት ያኑራት

1 comment: