Monday, April 23, 2012


ልጅነትና ትዝታውን ማንሳት ከጀመርኩ የፓስቲ /የጉራጌ ብስኩት/ ለሰባት አመቴ ጥርስ መነቀል አስተዋጽኦ ያደረገውን ከተናገርኩ ለዛችው ፓስቲ ብዬ ሳንቲም ሰርቄ መገረፌን ሳላነሳት ማለፍ አልፈልግም። ቀበሌ ህብረት ሱቅ ግዛ ተብዬ ስላክ ሳንቲም መቀርጨጭን ስለለመድኩ ሁሌ እንድላክ የማላደርገው ጥረት የለም። ተሳክቶ ስላክ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጋር ወጣት አበባ ሻይ ቤትን የሚያውቅ እዛ ያለ ብስኩትን ያውቃል። ታዲያ አንድዋን ቀድሜ አጣጣምኩና ሄድኩ። ህብረት ሱቅ ግን የዛን ቀን ብጥብጥ ስለተነሳ ለልጆች አንሰጥም ተባለ እና መለሱኝ። ከተሰጠኝ ገንዘብ ደሞ አጉድያለሁ።

ነገር መጣ።

ቤት እንደገባሁ ከተላኩበት ብር ላይ ልጆች አንዱን ነጠቁኝ አልኩና የቀረችውን ደበኩዋት። ትንሽ ቆይቼ ወጣሁ እና ብስኩቴን ገዝቼ ሳሻምድ እናቴ ለካ ቀበሌ ህብረት ሱቅ ለመሄድ ወጥታለች። አየችኝ። ዱላው የጠበቀኝ ግን ማታ ነው።

እንደወናፍ ቆዳ ታሸሁ።

ከዛ በሁዋላ አልሰረኩም ማለት አይደለም። ብሰኩት ጠባሹ አረቦ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የዛ ቤት ቋሚ ተሰላፊ ነኝ። ክርስትና ስነሳ እንጃራ ይውጣልህ ተብዬ ሳይሆን የጉራጌ ብስኩት ይውጣልህ ተብዬ ነው መሰል የተመረቅሁት -እወደዋለሁ። አሁንም እወዳለሁ። የምትችሉ ላኩልኝ።

ትላልቅ ሴቶች ህጻናት ወንዶችን እንደሚያባልጉ ያወኩበት አጋጣሚ ደግሞ እነሆ፦ የምስራች ትባላለች ዛሬ..ዛሬ ትዳር ይዛ መውለድዋን አውቃለሁ። እሷ ትረሳው ይሆናል። እኔ ግን አልረሳትም። ጠባሳ የጣለብኝ ነገር አለውና ነው። አስታውሳለሁ ያኔ ገና ስምንት አመቴ ነበር እና ልላክህ ስትለኝ ቤታቸው ገባሁ። እኔ መግባቴን ያየው ዳንኤል እየጠራኝ ተከትሎኝ ገባ። ዳኒ የያኔውን ነገር ታሰታውሳለህ?/ዳኒ ሽኒ ዝተፈጠረ ትርሰኦ አይመስለን/ ቂጣ በዘይት እና በርበሬ የታሸ ለሁለታችን አበላችን። እያጫወተችን ያደረገችውን ነገር ዛሬ እዚህ ቦታ ላይ ባልጽፈውም ለሁላችሁም የሚገባ ነገር ነው። ድርጊቱ አስጠሊታ ስለሆነ ነው የደፈንኩት።

እኔ፣ ባይከዳኝ፣ ዳዊት፣ ተካልኝ፣ታምራት…ሌሎቹም በየጊቢው ያሉትን የኮክ እና የፖም ፍሬዎች በማደን ለራሳችን ደስታ እንፈጥር ነበር። ቅንጨ ጊቢ..አዳነች ጊቢ..የቀበሌው መዋለ ሀጻናት ጊቢ..ናዘሬት ት/ቤት አካባቢ ያሉ የሀብታም ጊቢዎች በየተራ እናዳርሳቸዋለን። ታዲያ አንዴ አዳነች ጊቢ የምንለው ጋር በአጥር ተንጠላጥለን ኮክ ዛፍ ላይ ወጣን። በርካታ ውሻዎች አሉ። እየጮሁ አስቸገሩን አንዱን ትል የበላው ኮክ ቀጠፍኩና ውሻው ላይ እወረውራለሁ ብዬ ካለሁበት ዛፍ ላይ ስቼ ወደኩ።

ውሻው ነከሰኝ።

ህክምና ስሄድ ውሻው ተገድሎ ለምርመራ እንዲመጣ ተባለ። ተደረገ። ለካ በሽተኛ ነው። ሆዴ ላይ 43 መርፌዬን ጠጣሁ። ለኮክ ተብሎ..አይ ልጅነት? ደስ ይላል። ሆዴን ሳይ ሁሌ አስበዋለሁ። ሌላው ደሞ እንደ ልጅ ሆያ ሆዬ መጨፈርም ሆነ ለአበባዮሆሽ አበባ መስጠት እከለከል ነበር። እናቴ ለምን እንደሆነ አላውቅም አትወድም። አንዴ ተደብቄ ስጨፍር ቆየሁና የተካፈልነውን ሳንቲም እንደሌላ ጊዜው በወረቀት ጠቅልዬ ሳልደብቅ ረስቼ ገባሁ። ሳንቲሙ ተገኘብኝና ተደበድቤ ሲበቃ በርበሬ ታጠንኩ። መቼም የደረሰበት ያውቀዋል። አቤት ስቃይ!! ከዛ በሁዋላ ሆያ ሆዬ የሚል ዘፈን እንኩዋን ሰሰማ ያቅለሸልሸኛል። በርበሬዋ ትዝ ትለኛለች።

ብዙውን ጊዜ እናቴን በስራ እረዳታለሁ። አባቴ ከሞተ በሁዋላ እንጀራ ሸጣ ስለሆነ ያሳደገችኝ አዝንላታለሁ። እንጨትና ቅጠል እገዛላታለሁ፤ እህል ገዝቼ አሰፈጫለሁ፤ እንጀራውን ተሸክሜ ያኔ ሺረጋ ሆቴል ይባል የነበረው አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አጠገብ እወስድላታለሁ። ጉሊትም አደርስላታለሁ። በዛ ያለ ጊዜዬን እስዋን ስራ ሳግዛት ደስ ይለኛል። ይህን በስራ ማገዝ እንጀራ መሸጡን እስካስቆምኩዋት ድረስ ዩንቨርስቲ ተማሪ ሆኜ ሁሉ አላቋረጥኩም።
ልጅነት፣ አይናፋርነት እና ፍቅርን በተመለከተ በክፍል 4 እመለስበትና እንሰነባበታለን።
ስላም ለእናንተ፣ ሰላም ለእኔ፣ ሰላም ለፌስ ቡክ ወዳጆቼ፣ ሰላም ለማውቃችሁ፣ ሰላም ለማላውቃችሁ…ሰላም ገና ወደፊት ለማውቃችሁ ሁሉ እንዲሆን እመኛለሁ።
ቸር እንሰንብት
 

No comments:

Post a Comment