Monday, April 23, 2012


ፍል ሁለት
አቦ ተመቸኝ

<<የአንተ አባት ምን አይነት ነው? የእኔ አባት ቀይ ረጅም ሽበታም ነው..የአውራ ጎዳና መኪና ይነዳል ትልቅ የነዳጅ ቦቲ..>> በጥሞና ሲያዳምጠኝ ቆይቶ <<የእኔም አባት አንተ እንደምትለው ነው ብዙ ጊዜ ክፍለ ሀገር ነው።ግን ትላንት ማታ መጥቶ ነበር።..>> አለና የቲቸር ሳያንስ እሱም ጥርጣሬ አርሶ ስለዘራብኝ ቤቴ ልወስደው አሰብኩ። ወደቤት ስወስደው ነገር ተገለብጦ ..ለእሱ እኔ ውጭ የተወለድኩ ወንድሙ ነኝ። እሱ ለእኔ ከውጭ የተወለደ ወንድሜ ነው። አራዳው ፋዘር አራርቆ መውለድ ሲባል ተሸልቅቆ አቀራርቦ አንድ ሰፈር በስድስት ወር ልዩነት ከች አርጎናል። ታላቅነቴን ግን አልተነጠኩም። ብራቮ አባቴ ብኩርናዬን ስላላስነጠከኝ።
በቃ!! ተዋደድን ምንስ ቢሆን ወንድሜ አይደል? የአንዱ ሲገርመኝ እሱስ ታናሽ ወንድምም አለው።አንድ ብቻ የነበረው ታላቅ ወንድሜ ታናሾቹ በረከትንለት።ያኔ ነው አሁንማ ታላቅ ወንድሜ በስደት እያለሁ በሞት ተለየኝ።ድምጻችሁን ዝቅ አድርጋቸሁ ነፍስ ይማር በሉ። ውሎዬ ከጓደኞቼ ይልቅ ከወንድሜ ጋር ሆነ። ከወንደሜም ጋር ሆኜ ተካልኝ ተክሌ፣ታምራት ተክሌ፣ባይከዳኝ..የአባቱን ስም አላውቅም እሱም ሲናገር ሰምቼው አላውቅም። ቅዳሜ..ቅዳሜ መርካቶ እንሄድና ሲኒማ አዲስ ከተማ እንገባለን። በ50 ሳንቲም ሶስት ፊልም እናያለን፤ብዙ ስቃይ እንቅብላለን። ወረፋ ላይ ዱላ እንቀምሳልን፤መሬት ተቀምጠን ሽንት በቂጣችን ስር ሲሽኳለል ይውላል። የሲጋራ ትርኳሽ ሲወረወር ላያችን ካረፈ እንቃጠላለን። ብቻ ሁሉም ያኔ አሁን ያራዳ ልጅ ትሪፕ እንደሚለው ነው።

ፊልሙ አልቆ ስንወጣ ስለፊልሙ አክተሩ እንዲህ አለና እንዲህ ብሎት..አይደለም እንዲህ ነው ያለው/ትርጉም በራሳችን ክርክር ለመንገዳችን/ እየተዳረቅን በሲኒማ ራስ ቴያትር በኩል አቋርጠን ወደ ሰፈር በእግር እንጓዛለን።ሁሌም ከፊልም መልስ በሲኒማ ራስ በኩል የምንሄደው በአምስት ሳንቲም የምትሸጥ ሳንቡሳ ስላለ እሱዋን ለመብላት ነው። የቻልነውን ያህልም እንሰርቃለን። እኔ ግን ከሳንቡሳ ስርቆት ይልቅ አራዳ ጊዮርጊስ ጋር የመጽሐፍ ስርቆት ይቀናኝ ነበር። አነብና መልሼ ሸጨ ለቅዳሜ ፊልሜ እና ለሳንቡሳ አውለዋለሁ። ሳንቡሳ መብላት ውድድርም አለ። ግን የሪኮርዶ ባለቤት ባይከዳኝ ነው።የበላውም መጠን ብረሳውም 20 ይመስለኛል።ካሳነስኩት ግን ይቅርታ ባይኬ…ይህን ስላችሁ አፉን ሸፈፍ ድርጎ <<ኤኔ ሲሜ ባይኬ..>> የሚላት አባባል ታወሰችኝ።

አንድ ጊዜ ቀኑ ቅዳሜ ስለሆነ ተካልኝ እና ወንድሙ ታምራት እናታቸው ለፊልም ሰጥታቸው ሊሄዱ ነው። እኔ፣ባይከዳኝ፣ዳዊት..የምንገባበት የለንም። ቅዳሜ..ቅዳሜ ድሞ ሰፈራችን ያለ ሻፊ የሚባል ከሰል ነጋዴ ንፍሮ አስለምዶናል። ንፍሮው ዝም ብሎ እንዳይመስላችሁ። ዘይት አለው ስንኩርት አለው። ከፈለጋችሁ እናንተ ነፍሮ ወጥ በሉት። እኛ ጥሞን ተጋፍተን ነው አንዳንድ ጭልፋ በሹራባችን ተቀብለን ድጌ ሁላ የምንሄደው። ችግሩ ሻፊ አይሸለቀቅም።

ውይ የእኔ ነገር ንፍሮው ታወሰኝ እና ተዘናጋሁ። እናላችሁ የለመድነውን ንፍሮ እሱ ሊሰጠን አኛም ልነቀበል የሰጪና ተቀባይ ፕሮሰስ ላይ እያለን ገንዘቡን ፊት ለፊት በጣሳ ተቀምጧል። ለባይከደኝ እኔ ሸፈንኩለት አነሳው። ሸኛ ፊልም ገብተን ሻፊ ምን ተረፈኝ ታንቄ እሞታለሁ ብሎ እንደነበር ስሰማ ተጸጸትኩ።

ያኔ አባቴ በህይወት እያለ ነው። ጓደኞቼ ሞጋ/በረባሶ/ የሚባለውን ከጎማ የሚሰራ ጫማ ፊት በር ገበያ እየሄዱ ያሰራሉ። እኔም ቀናሁና አሰራሁ። አቤት የተመታሁት? ለስፖርት ሸራ ጫማ አስገዝቼ አባቴ እናቴን የተቆጣትን አልረሳውም። ሌላ ጊዜ ግን እሱ ሞቶ አድርጌያለሁ። የጉራጌ ብስኩት ነብሴ እስከወጣ እወዳለሁ፡፡ሳንቲም እሰርቅና እገዛለሁ። ከዚህ ጋር የተያያዘ ገጠመኜ ሰባት አመቴ ላይ እንደ ልጅ በወግ ጥርሴ ተነቃንቆ በክር ተጎተቶ አይደለም የወለቀው ፓሰቲ የሚባለውን ደቡልቡል ኳስ የሚመስል የጉራጌ ብስኩት ስገምጥ ስክት ብሎ ቀረ። ጣጣ የለ ፈንጣጣ ውልቅ..ብቻ ብስኩቴን ደም ነካውና ጨርሼ ላጣጥም አልቻልኩም::እሷ ትቆጨኛለች::
ወደ ት/ቤት ገጠመኜ ስመለስ
አንድ ጊዜ ከምንቀርባቸው ውስጥ አንዷ እወድሀለሁ ብላኝ አስታውሳልሁ ሁለት ቀን ከት/ቤት ቀርቻለሁ። ብትስመኝ ኖሮ ከት/ቤት ከናካቴው ሳቋርጥ አይታያችሁም? በጣም አይናፋር ነበርኩ-የዛሬን አያርገውና። ዛሬ እሷ በውጭው አለም ታዋቂ ሞዴሊስት ሆና ፌስቡክ ዳግም አገናኝቶናል። ለነገሩ ከልጅነት ጓደኞቼ መካከል ከጌትሽም፣ከተካልኝም፣ከካሳሁን የሺጥላ ጋርም ፌስቡክ አገናኝቶናል። ተካልኝ ስዊዲን፣ካሳሁን አሜሪካ ከትመዋል።
ወደ ያኔ ወጌ ስመለስ…ያኔ ጓደኛ እንባባላለን እንጂ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ነበር። ሳባን የእህቴ ያህል እወዳታለሁ። ዛሬ የልጆች እናት መሆኗን ከመስማት ውጭ የት እንዳለች አላውቅም። ኮኮበ ጽብሃ ከገባን ጊዜ ጀምሮ አላገኘዋትም።
ኮኮበ ጽበሃ ስንማር ለአውቶቡሰ የሚሰጠንን ቀበና ያለችው ሻይ ቤት የጉራጌ ብስኩት እንበላባትና በእግር <<እሰኪ ልወዝወዘው ልወዝወዘው በእግሬን..>> አያንጎራጎርን እናስነካዋለን፡፡ እኔና ጌትሽ ያችን ብስኩት ለመብላት ብቻ ሳይሆን ከሳምሶም ዳቦ ቤት ባለ 20 ሳንቲም ዳቦ ገዝተን ልክ እንደኬክ በወረቅት ይዘን እያጓመጥን መንገዱን እናስነካዋለን::ዳቦ በሙዝ..ሎሚ በከረሜላ..የማይታወሰው አለ ይሆን?

የልጅነት ታሪካችን ቢውራ..ቢወራ የሚያልቅ አይደለም። ቀጣዩን ክፍል ሶስት እመለስበታልሁ። ከደበራቸሁ ግን አስተያየት መስጫው ላይ x ምልክት አስቀምጡ::ከተመቻቸሁ ጭብጨባችሁን አሰሙኝ። ወደፊት እንላለን።
ቸር እንሰንብት
 —

No comments:

Post a Comment