Wednesday, August 1, 2012

ጥቁሯ ቦርሳዬ ክፍል 8
‹‹..ፍቅርን በአረቢኛ እንዴት ታነንሾካሹክለት ይሆን?.. ››
ወግ በግሩም ተ/ሀይማኖት

‹‹ሀሎ! ጤና ስጥልኝ!...›› አልኩ ሞባይል ስልኬን ከፍቼ፡፡ የደወለልኝን ሰው ቁጥር ከዚህ በፊት ባላውቀውም ተገቢው ሰላምታ ይድረሰው ብዬ ነበር ሰላምታ ማቅረቤ...

‹‹ምን ጤና ይሰጠኛል ጤና የነሳኝን ወሬ ላቀብልህ ነበር..›› ብስጭት የታከለበት ጎርናና ድምጽ ነው፡፡

‹‹ደስ ይለኛል ወዳጄ መቼ ላገኝህ እችላለሁ?›› ላልኩት ጥያቄ የሰጠኝ ምላሽ አሁኑኑ የሚል ሆኖ የት እንዳለሁ ጠየቀኝ፡፡ ነገርኩት፡፡ ሩቅ ቦታ ስለሆነ ከአንድ ሰዓት በኋላ እኔ ጋር እንደሚደርስ ነግሮኝ ተለያየን፡፡ እሱ እስኪመጣ ሰላምታዬን ለእናንተ ላድርስ፡፡ ሰላም ጤና ፍቅር ይስጣችሁ፡፡ የእዚህ ክፍል መርህ /መልዕክት/ ‹‹አስተውሎ መራመድ ብልህነት ነው..›› የሚል ነው፡፡ በእርግጥም አስተውለን የምናደርገው ነገር ፀፀት፣ ጉዳት፣ መጥፎ ስም፣ ህሊና የሚያስወቅስ ጭፍንነት.. የመሳሰሉትን ጉድፎችን አያስከትልም፡፡ አስተውሎ መራመድ ከግባችን መድረሻ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫችን ይሁን፡፡

ሀበሻ እና ቀጠሮ ፀባቸው የከረረ ይመስል እስካሁን አልታረቁም፡፡ በቀጠሮ ሰዓት መገኘት ክብር የሚቀንስ እየመሰለን ይሁን እንደ በሽታ ተጠናውቶን በማርፈድ ታውቀናል፡፡ ‹‹የሀበሻ ቀጠሮ..›› እያልን ተጠናውቶናል፡፡ ለነገሩ ‹‹ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው..›› እየተባለ የሚጻፍበት ግንብ እና በር ያለው ትምህርት ቤት ብንማርም ማርፈድ አርቆ የማሰብ ውጤት ነው የተባልን ይመስል በርትተን ተያይዘነዋል፡፡ አንዳንዱማ ለሁለት ሰዓት ቀጠሮ አራት ሰዓት ከቤቱ የሚነሳ አለ፡፡ ይህ ሰው ራሱን ይመርምር ዓለም ከሚጓዝበት ምህዳር በሁለት ሰዓት የዘገመ ሊሆን ይችላል፡፡ ጎበዝ ቀጠሮን እናክብር በሰዓት /በጊዜ/ ስንቀልድ በተገላቢጦሽ እየቀለደብን ነው፡፡

ከአንድ ሰዓት በኋላ ያለኝ ቀጣሪዬ ሶስት ሰዓት ከሀያ ደቂቃ ያህል ቆይቶ መጣ፡፡ ለምን አረፈድክ ብሎ መጠየቅም መቆጣትም አይቻልም፡፡ የሀበሻ ወጉ ማርፈድ ነውና ወግ ጠባቂ ብሎ ‹‹እንኳን ደህና መጣህ›› ብቻ ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ያለሁት ሱቅ ውስጥ ስለሆነ ቢመጣም ባይመጣም እዛው ነኝ የት መሄጃ አለኝ? ቁጭ ብለን አወጋኝ፡፡ ስስቅ፣ ሳዝን፣ በስራችን ሳፍር አዳመጥኩት፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን…የሚለውን ቀየር አድርጌ የሰማሁትን በፌዝቡክ ላይ ያኑርልኝ ብዬ አሳረፍኩት እነሆ፡-

ፌዝቡክ ላይ የምትፅፋቸውን እከታተልሀለሁ፡፡ የመን ያሉ አስገራሚ እና አሳዛኝ ታሪኮችን ስታነሳ የእኔ ቢቀርብ ብዬ ነው አለኝ፡፡ ወደ ዋናው ወሬ ሲገባ ደግሞ ‹‹..ከሚስቴ ጋር የተዋወቅነው ቤት ልትከራይ መጥታ ነው፡፡..››ሲል ትረካውን ጀመረ፡፡ ያው ወሬው አደባባይ ሊውል ከተጀመረ ወደኋላ ምን ያደርጋል? ፍርጥርጥ እንዲያደርገው የሚል እሳቤ መጣብኝና ‹‹እንዴት?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡

ያው ታውቀዋለህ እዚህ ሀገር ሶስት ክፍል ቤት ነው የምትከራየው ከዛ የምትይዘውን ክፍል ትይዝና ቀሪውን ለሌላ ማከራየት ነው፡፡ ለደላላዎች ነግሬ ስለነበር ለኮንትራት ስራ መጥታ ሁለት አመት ሳትሰራ በሚደርስባት በደል ተማራ የጠፋች ልጅ በደላላው አድራሽነት እኔ ጋር ያለውን ቤት ልትክራይ መጣች፡፡ ተስማማን እና ኪራዩን ከፍላኝ እቃ ልግዛ ብላ ስትሄድ ሀገሩን ስለማታውቅ ላጋዛት ሄድኩ፡፡ ፍራሽ ብቻ ነው የገዛችው፡፡ ማደሪያ ስለ ሌላት ልታድርበት ነው ፍላጎቷ፡፡ አንሶላ የለ ብርድ ልብስ..አሳዘነችኝ፡፡ እዚህ ላይ እንዴት ትተኛለሽ እኔ ጋር ግቢ እና አልጋው ላይ ተኚ እኔ መሬት እተኛለሁ አልኳት፡፡ ተስማማን አደረች፡፡ በማግስቱ ስራ ስለሌላት ቁልፉን ሰጥቻት ሄድኩ፡፡ ምክንያቱም ቴሌቪዥን እንኳን እያየች ትዋል ብዬ ነው፡፡ ጊዜው ባዶ ቤት ውስጥ እንዴት ይሄድላታል? ምግብም አብስላ ብትበላ ትንሽ እቃ ስላለኝም ብዬ ነው፡፡ እኔው ቤት ዋለች ከስራ ስወጣ ምሳ የምትበላው ነገር እና ጫቴን ይዤ ሄድኩ፡፡ ቡና አፈላችልኝ…እኔው ጋር ዳግም አደረች፡፡ አሁን ግን አልተላለፍንም፡፡ በዛው ገባች በቃ!..ኪራዩ ቀረና ሌላ ሰው ተከራየው…ስራፈልጌ አስገባኋት፡፡

አልጋ ላይ ደስ የሚል ወሲብ ጣር አላት፡፡ በስሜ እየጠራች ‹‹ኡህ..ውይ..››በሚል ይጀመርና የእኔ ፍቅር፣ የእኔ ማር፣ የእኔ አንበሳ…ፍቅር ነህኮ ኡህ…ደስታን ካንተ አገኘሁ…›› ብዙ ብዙ ትላለች፡፡ ይህ ነገሯ ከለስላሳ ሙዚቃ የበለጠ ተመቸኝ፡፡ በጣምም ወደድኳት፡፡ ለሁለት አመት አብረን ኖርን፡፡ ጭፍን ያለ ፍቅር ውስጥ ገባሁ፡፡ ነገሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ከምትሰራባቸው ሰዎች ሴት ልጅ ጋር ሲላመዱ ምስጢር ይገላለጡ ጀመር፡፡ የወንድ ጓደኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንደነበረ እና እንደተጣላት ነገረቻት፡፡ በባህላቸው ሴት ስታገባ ልጃገረድ ሆና ካልተገኘች ‹‹ጃንቢያ›› በሚባለው ሆዳቸው ላይ በሚታጠቁት ስለት እንዲገላት የሚፈቀድለት ወንድሟ ስለሆነ..እንዴት ጓደኛ ልትይዝ እንደቻለች የእኔዋ ልጅቷን ጠየቀቻት፡፡ በዛ ላይ ወንድና ሴት አንድ ላይ መሄድ አይቻልም እንዴት ትገናኛላችሁ? አለቻት፡፡

እናቷ በአደጋ ምክንያት አይናቸውን ሲታወሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሚፈልጉበት ቦታ እንዲያንቀሳቅሳቸው በሾፌርነት ተቀጠረ፡፡ ገብቶ ሲላመዱ እንደ ጀመሩ ነገረቻት፡፡ እናቷ አይኗን በመታወሯ ምክንያት አባትየው ስለፈታት ለብቻዋ ነው የምትኖረው፡፡ ልጅትም እሷ ጋር እሄዳለሁ ብላ ትሄዳለች፡፡ እሱ እዚያ በሾፌርነት ስለሚሰራ እዛው ይገናኛሉ..ሌላውንም ሌላውነም ብቻ ምስጢሯን ሁሉ አጫወተቻት፡፡ አያይዛም ሀበሻ ለፍቅር እንደሚሆን በትውልደ ሀበሻው እንዳየችና አንድ ሀበሻ እንድታስተዋውቃት ጠየቀቻት፡፡ ከመሳሳም ውጭ ምንም ማድረግ እንደማትፈልግ አሳወቀቻት፡፡ ወሮታውን 200 ዶላር ልትከፍል ለውንዱም የፈለገውን ልታደርግለት ስለተስማማች የእኔዋ ሚስት እድሉ ለሌላ እንዳይወጣ ፈልጋ አማከረችኝ፡፡ እኔም በጽዳት ሰርቼ የማገኛት ከሲጋራ፣ ጫት ሱሴ እና የቤት ኪራይ የማትዘል ሳንቲም ይልቅ በዚህ ጥሩ ልጠቀም እንደምችል ገምቼ ተስማማሁ፡፡..አለኝ ታሪኩን የሚያወጋኝ ወጣት፡፡

እዚህ ጋር የፍቅርን ህልውና እንድጠራጠር አደረገኝ፡፡ ሰው የሚወደውን ሰው እንዴት ለጥቅም ብሎ አሳልፎ ከሌላ ሰው ጋር እንዲሳሳም ያቀራርባል? የምወደውን ሰው እንኳን ለሌላ ማሳለፍ ቀርቶ ቅንጣት የጸጉሯን ስባሪ እንዲነኩብኝ አልፈልግም፡፡ ለነገሩ እዚህ አረቡ አለም ላይ ያሉ ጥቂት በጣም ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ወንዶች ሴቷ ገላዋን ሸጣ የምታመጣውን ጠብቀው የሚኖሩ አሉ፡፡ እነዚህ ጥቅም ፈላጊዎች እንጂ ፍቅር ናፋቂዎች አይደሉም፡፡ ወይ ፍቅር…..

ከሱ ጋር ወዳወራሁት ስመለስ…. በስምምነታችን መሰረት የልጅቷ እናት ጋር በሳምንት ሶስት ቀን የጊቢውን አትክልት መንከከባከብ በሚል ሰበብ ተቀጠርኩ፡፡ ከልጅቷም ጋር እንደ ተባልኩት ተግባባን፡፡ ተጀመረ፡፡ ህሊናዬ ባይቀበለውም ከሚስቴ ጋር የማደርገው እያስመሰልኩ ህሊናዬ እየተሟገተ ገባሁበት፡፡ ከመሳሳም ያልዘለለ ግንኙነታችን ለትንሽ ጊዜ እንደተጓዘ መግባባት ስንጀምር በማይሆን ሁኔታ እንድንወስብ ጠየቀችኝ፡፡ ይህን አይነት ድርጊት እኔ ተጠቅሜ አላውቅም አንቺ ለምን በኋላ ማድጉን ፈለግሽ አልኩ፡፡ ስታገባ ድንግል ካልሆነች እንደሚገሉዋት እና በፊት ከነበረው ጓደኛዋ ጋር እንደዚህ እንደነበር የሚጠቀሙት ነገረችኝ፡፡

ከድርጊት በኋላ ተጋድመን ስታውራኝ ከእኔ ጋር ደስ የሚል ጊዜ ልታሳልፍ እንደፈለገችና የጠየቀችኝን እንቢ ማለቴ እንዳስከፋት ነገረችኝ፡፡ ስትቀጥልም..ሀበሻ ለፍቅር አመቺ እንደሆነ እሷ ብቻ ሳይሆን አባቷም ያውቃሉ፡፡ ሚስታቸውን የእሷን እናት መሆኑ ነው ከፈቱ ጀምሮ ከሰራተኛቸው ጋር እንደሚቀብጡ ታውቃለች፡፡ እንደተመቸቻቸውም ነግረዋታል፡፡ ልቤ ቀጥ አለ፡፡ የምሰማው ቅዠት እንጂ እውነት አልመስልህ አለኝ፡፡ ጆሮዬን የመስማት ጉጉት አርገበገበው፡፡ ለነገሩ በየቤቱ ሁለት ሶስት ሰራተኛ ሲለሚኖር ሌላዋን ይሆናል እንጂ የእኔዋን ውድ አይሆንም ሲል ውስጤ ውስጤን አጽናናው፡፡ ጠይቄ ቁርጡን ማውቅ ፈለኩኝ፡፡ ልቤ ግን ምቱን ጨምሮ ጉሮሮዬ ስር ተወተፈ፡፡ የሚገርም ነው በተፈጥሮዬ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከዳት እንባ ተናነቀኝ፡፡ አላለቅሰው ምኔ ናት ልበላት? በምን አለቀስኩስ ብዬ ሰበብ ልስጥ? የእኔን በዝምታ ተለጉሜ መቆየት ሰብራ ወደ ወሬያችን እንድንመለስ ስትል ሳልጠይቃት ዘረገፈችው፡፡

ከሰራተኛቸው ፋጡማ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እና በጣም እንደተመቸቻቸው የነገሯትን አወራችኝ፡፡ ግንባሬ ላይ ችፍ ያለው ላብ ይሁን አይኔ፤ ላይ ታቁሮ የነበረው እንባ አላወኩም ጉንጬን ሰንጥቆ ወረደ፡፡ እልህ ተናነቀኝ፡፡ ግጥም አድርጌ መሳም ሳይሆን የመንከስ ያህል ትንፋሽ እስኪያጥራት ሳምኳት፡፡ በሁኔታዬ ግራ ተጋብታለች፡፡ ለፍቅሬ መታመን ስል ከመሳሳም ውጭ ሌላ ነገር ውስጥ እንዳልገባ ስታገል መቆየቴ አናደደኝ፡፡ ለፍቅሬ መታመን ስል ነበር ጠቀም ያለ ገንዘብ ልትሰጠኝ እናድርግ ያለችኝን እንቢ ያልኩት፡፡

ውስጤ ሌላ ሀሳብ አፈለቀ፡፡ ያለችኝን እንቢ ስለላኩዋት ሌላው ሀበሻ ያደርጋል ብላ ለማሳመን ውሸቷን ቢሆንስ? ደግሞ አባትስ ከእናቷ ውጭ ሌላ ሴት ማድረጋቸውን እንዴት ሊነግሩዋት ቻሉ? ውሸቷን ነው የሚል ሀሳብ ነበር፡፡ ምነው እንዳሰብኩት ውሸት በሆነና እፎይ ባልኩ፡፡ ያሰብኩትን ሀሳብ አቀረብኩላት፡፡ ምን አቀጣቅጧት እቴ…ምን ታድርግ ቁስሌ አልገባት..የፍቅሬ መናድ አያሳዝናት….ለምኗ ብላ ትሸሽገው? እንኳን እኔ አንዱ ደካማ ሰው ይቅርና ወገኔ ያልኩት ሁሉ የማይችለውን ጉድ ዘረገፈችልኝ፡፡ ከሀያ ቀን በፊት እሷ ራሷ በዚህ ተግባር ላይ እያሉ ይዛቸው ስትቆጣ አባቷ ከእናቷ ፍቺ በኋላ ፋጡማ ስለተስማማቻቸው እንደሆን ቶሎ ማግባት ያልፈለጉት እንደነገሯት ጭምር ስትነግረኝ የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ እሷ ግን ቀጠለች፡፡ እንዳይወልድ መጠንቀቅ እንዳለበት ለስሙ ጥሩ አንዳልሆነ ስነግረው ‹‹..ከዚህ በኋላ እጠነቀቃለሁ፡፡ ባለፈው አርግዛ እንድታስወርድ አደረኩኝ..›› አለኝ፡፡ እሱ ወንድ ስለሆነ ነው የሚናገረው እኔ ብሆን ግን ይገሉኛል ለዚህ ነው…እያለች ታወራልች፡፡ እኔ ግን አስብ የነበረው ሳንደራጅ፣ ተቀማጭ ሳይኖረን፣ በዚህ ኑሮ መውለድ የለብንም ብላ አሳምናኝ ያደረገችው ውርጃ የአባቷ ጽንስ ቢወለድ ኖሮ የሚከሰተውን ነው፡፡

ክዳቷ ውስጤን በቁጭት አርመጠመጠው፡፡ የጠየቀችኝን ተቀብዬ ስንተኛ ወዴ ፍቅሬ በ200 ዶላር አሳልፍ እንደሸጠችኝ እያሰብኩ ነበር፡፡ በእልህ የጀመርኩት ነገር ግን ባላሰብኩት ሁኔታ ቀጠለ፡፡ ከኋላ ትቼ በተፈራው ቦታ ገባሁበት፡፡ ከዚህ በኋላ ህይወቴ አደጋ ላይ እንደሆነ አውቃልሁ ያወቁ ቀን ይገሉኛል፡፡ ያለኝ አማራጭ ወደ ሳዑዲያ መጥፋት ብቻ ነው፡፡ ሀገሬ የምገባበት ፓስፖርት የለኝ፡፡….አይኖቹ እንባ አቅርረው ስለነበር ጥያቄ ቢኖረኝም የባሰ ሆድ ማስባስ ስለሆነብኝ ተውኩት፡፡ እሱ ግን ‹‹..እሷ እኔ አለሁ አይነኩህም ብላ እንደሰጠችኝ ተስፋ በተስፋ ተሰንጌ መኖር አለበለዚያ በተለያየ መንገድ ከዚህ የምውጣበትን መፈለግ ካልሆነም ሞት መጠበቅ ነው እጣዬ…ይሄው ነው ከፈለክ ጻፈው፡፡ ካፈለክ…›› ብሎኝ ሊሄድ ተነሳ፡፡ ሚስትህስ አሁን በምን ሁኔታ ናት? መለስ ብሎ ስልኬን ከእጄ ወሰደ እና ቁጥሯን ጽፎ ‹‹..ያን ዜና ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ አላየኋትም፡፡ ከፈለክ ደውልና ጠይቃት፡፡ ላንተም ይደርስህ ይሆናል..›› ብሎኝ ወጣ፡፡ ስርዓት ያጣው አነጋገሩ ቢያናድደኝም ምላሽ አልሰጠሁትም፡፡ ሆድ የባሰው በመሆኑ የሚናገረውን አያውቅም ወይ ስሜታዊ ሆኖ ነው ብዬ አለፍኩት፡፡

ባለፈው ልጇ እና ባሏ ላይ የፈላ ዘይት የደፋችው ሴት በፍርድ ቤት የተፈረደባትን ፍርድ በቀጣዩ አሳውቃለሁ ብዬ ነበር፡፡ ፍርዱ ሞት ነው፡፡ ግን ፍርዱ የሚፈጸመው ህጻኑ ባለበት መሆን ስላለበት ልጁ 18 አመት እስኪሞላው እስር ቤት እንድትቆይ ተውሰኗል፡፡
በቀጠይ ዘና በሚያደርግ ጽሁፍ እንገናኛለን፡፡
ቸር ይግጠመን፡፡

No comments:

Post a Comment