Wednesday, August 1, 2012

ጥቁሯ ቦርሳዬ
ክፍል 9
በግሩም ተ/ሀይማት

ሰላም ናችሁልኝ? ስላም ያድርጋቸሁ፡፡ የምመኝላችሁ ሰላም ነው፡፡ የዚህ ክፍል መልዕክት ‹‹አራዳ ለመሆን ከመፈንዳት ሰርቶ ይዞ መገኘት..›› የሚል ነው፡፡ አንኳር መልዕክቱን ወደታች ስንወርድ ፈረካክሰን እናያለን፡፡

አንድ በሉልን ፍቅር ልብስ የሚያስወልቀን አንሶ ሙቀትም ልብሳችንን እያስወለቀን ነው-የመን፡፡ ለስንቱ አውልቀን እንችላለን? ለፍቅር የምናወልቀው አንሶ ስል አሳብዶን እንዳይመስላችሁ..ያው ህብረ-አንሶላ ለመፍጠር..አይ እናንተ አሳፈራችሁኝ፡፡ ታዲያ በዚህን ሙቀት ቁም ነገር ብቻ ማውራት ሲያልብ በብርጭቆ ወረቀት እንደመጥረግ ይቆጠራል፡፡ ለነገሩ ብዙ ሲሪየስ ወግ አወጋኋችሁ፡፡ ድክም ያላችሁ ባይመስልም አረፍ እንድትሉ ፈለኩ፡፡ ምን መፈለግ ብቻ ከተመቻችሁ እና ጥርሳችሁ ከመጣ መሳቅ ይችላል፡፡ ታዲያ አደራ ሲትስቁ ንገሩን እኛም እናጅቦት፡፡ ምናለበት ዘንድሮ ሁሉን ነገር ቀየር አድርገን ባልተለመደ ሁኔታ ብንጓዝ? ብቻ ከማግጠጥ በአጃቢ መሳቅ ደስ ይላል፡፡ ከተቻለ አጀባውን በባንድ እናደርገዋለን፡፡ እንዳልኳችሁ ዘንድሮ ባልተለመደ መንገድ ብንጓዝ ምን ይመስላችኋል? ሀበሻ ምቀኛ ነው የሚለውን ለውጠን ሀበሻ የሚተጋገዝ፣ የሚረዳዳ ነው ለመባል እንጣር፡፡ ሀበሻ ምቀኛ ነው፣ ወሬኛ ነው፣ ተንኮለኛ ነው...እያለ የሚያወራው ራሱ ሀበሻ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ የሚያስገርመኝ ነው፡፡ እንዴት ሰው ራሱን ይሰድባል? ደሙን አላስወጣ፣ አላስለወጠ አፉን ሞጥሞጥ አድርጎ ብቻ ሀበሻ ሲባል…ይላል፡፡ ራሱን መስደብ ራሱን ማዋረድ የለመደ ህሊና እንዴት ራሱን ከፍ ማድረግ ያስብ..ባልተለመደ መንገድ እንጓዝ ያልኳችሁም ለዚህ ነው ይሄን ሰንካላ አባባል ጥለን እብስ….

ታዲያ ይህን ጥለን ስንጓዝ የአራዳ ልጅ ነን እያልን በባዶ መኮፈስንም አስቀምጠናት እንለፍ፡፡ ተግቶ በማስራት ስለሆነ መለወጥ የላጪን ልጅ ቅማል በላው እንደሚባለው ያራዳን ልጅ ፋራ በላው እንበል? ጎበዝ እንዳትጃጃሉ ግጥም አድረጎ በልቶታል፡፡ ፋራ የተባለው አቀርቅሮ ሲስራ አራዳ የተባለው ሙድ ሲይዝ ሙዱ ጉዱ ሆኖት ቀርቷል፡፡ አራዳ ማለት በልጦ መገኘት ነው፡፡ አራዳ ማለት ሰርቶ ማግኘት ይሁን እስኪ..አራዳ ማለት ይዞ መገኘት ነው፡፡ አራድነታችሁን ካልተጠቀማችሁበት እንደ እኔ ኑሩበት፡፡ እኔን ብታዩ በኑሮዬ አራዳ ነኝ፡፡ ያውም ሴንተሩ ላይ…ቤቴን ነው ያልኳችሁ፡፡ ማለቴ አራዳ ክ/ከተማ ነኝ፡፡ አሁን አራዳ ለክፍለ ከተማነት መጠሪያ ብቻ ቢያገለግል ነው የሚመረጠው፡፡ ልብስ ማንኳተት ቃላት ማንጋተት ጥቅም የለውም፡፡

አቤት ይሄን የሚያነቡ የአራዳ ልጅ ተብዬዎች…ልመቻችሁ ብሎ…ማለታችው አይቀርም….በቃ አኩርፈውኝ አጠገባቸው ሆኖ ላጤናቸው ፊታቸው ለጉድ ተዘፍዝፎ ይታያል፡፡ ይህቺ ፊትህን ዘፈዘፍከው፣ ጣልከው የአንድ ሰሞን ቋንቋ ነበረች፡፡ የአራዳ ልጆች የተሻሻለች ስድብ ናት፡፡ አሁንም ትሰራለች፡፡ በቃ! እነዚህ እነ እንትና አራዳ ነን ብለው ሞራላችን ላይ እቃ..እቃ ተጫወቱብንኮ የምሬን ነው፡፡ እርድና ቋንቋ ማበላሸት ነው እንዴ? አንዱ አንድ ቀን ምን አለኝ መሰላችሁ? ምነው ጣልከው አለኝ፡፡ ዞር ብዬ የጣልኩት ነገር እንዳለ ስፈልግ ሳቀ፡፡ እምቢኝ ብሎ ከከንፈሩ አምልጦ ውጪ ያደረ ጥርሱን የበለጠ አስገጥጦ ተንከተከተ፡፡ እንሹካ የተገተረ ጥረሱን ለመሰብሰብ እየሞከረ ‹‹ፊትህን ጣልከው ነው ያልኩህ..›› አለኝ እና አረፈው፡፡

በእውነት ፋራ አይደለሁ ጣልከው ሲለኝ ላነሳ መዞሬ? አሁን በእናታችሁ የእኔ ፊት ጣልከው የሚባል ነው? መደመሪያውኑ የሰላሌን ሜዳ መስሎ ወድቆ የለ? የፊቴን ስፋት ልብ አላለውም እንጂ ከመስፋቱ የተነሳ ግማሹን አሳርሼ ግማሹ ላይ የሪል ስቴት ግንባታ መጀመሬን ቢያውቅ ጣልከው ባላለ፡፡ ውይ የእኔ ነገር ፊቴ የሚታያችሁ መስሎኝ ነው እኮ፡፡ እውነትም ፋራ ነኝ አይደል? እኔ የምለው ከምር እንነጋገር እስኪ ፀጉር ካላሳደኩ፣ የተንጀላጀለ ሱሪ ካለበስኩ፣ መርገጫው ሸክም የሆነ መጫሚያ ካልተጫማሁ፣ ቋንቋ ካላንሸዋረርኩ አራዳ አልባልም ማለት ነው?

አንድ ሰሞን ብቅ የሚሉ አባባሎችን እንመልከት እስኪ..ይመችህ ይመችሽ፣ አይ-ደል? የራስሽ..የራስህ ጉዳይ፣ ንገረው ለእገሌ ንገሪው ለእገሌ፣ ሲላጥ ሲላላጥ../ሰው እንደ ድንች እንደ ሽንኩርት ሲላጥ ይታያችሁ../ ደሞ እነሱ እንደሚያደርጉት ቃላትን ያለቦታቸው ሸጉጠን የአነጋገር ፋሽን ካልተከተልን አራዳ አይደለንም ማለት ነው? እኔን የፈለገ ፋራ ይበለኝ እንጂ አልጠቀምም፡፡ ከዚሁ አንድ ሰሞን ብቅ ከሚሉ ሰሞነኛ ቃላት ዙሪያ ሳልወጣ ‹‹ፍንዳታ›› ስለምትለው ቃል አስባችሁ ታውቃላችሁ? ፈነዳ፣ ፈነዳች..ፍንዳታ! ሆሆይ..በቃ! ፈነዳ የሚለው ቃል እኮ ትርጉም አጣ ማለት ነው፡፡ የተስፋዬ ካሳ ቀልድ ላይ ፈንዱ..የምትለውን የእንግሊዘኛ ቃል ታካ ‹‹..ካልፈነዳን አትረዱንም?..›› የምትል አባባል አለች፡፡ አስቃን አልፋለች፡፡ የአሁን ፍንዳታ ትርጉም ግን የተለየ ነው፡፡

እስኪ በእናታችሁ አንድ ነገር ላስቸግራችሁ፡፡ ብዙ አይደለም የማስቸግራችሁ አይናችሁን ጨፈን አድርጉ እና በምናባችሁ ሰው ሲፈነዳ ለማየት ሞክሩ፡፡ አያችሁ? ቆይ አረ እኛም ፈንድተን ነበር እንዴ? ወይ ጉድ ለካ ሳናውቀው ፈንድተን አልፈናል፡፡ ንገሩኝ እስኪ ፍንዳታ የሚለው ፊቱ ላይ ቡግር ወጥቶ የፈነዳለት ነው? ያኔ ነው ሀገሬ እያለሁ ፍንዳታ የሚባሉት ምን አይነቶች እንደሆኑ ለማወቅ ዳዳሁና አንድ የሰፈሬን ጎረምሳ /በእነሱ አጠራር ፍንዳታ ልበለው?/ ጠየኩት፡፡ የተለያዩ ምልክቶችን እና የሚያሳዩትን ባህሪ ነገረኝ፡፡ ለምሳሌ እንደ እገሊት ብዬ የሆነች ልጅ ጠቀስኩለት፡፡ ‹‹ውይ እሷማ ፈንድታ ጨርሳ ስትፈነዳ ያዝረከረከችውን አሁን እየሰበሰበች ነው..›› አለኝ፡፡ ድንቅ አነጋገር ነው፡፡ ሲፈነዱ ያዝረከረኩትን ሲያልፉ መሰብሰብ መቻሉም ጥሩ ነው፡፡ ግና እንዴት?

እዚህ ጋር ከአንድ ቴያትር ላይ የመዘዝኩትን አባባል ላዳምቅበት፡፡ ‹‹ከዘጠኝ ቀሚስ ለበስ ፈላስፋ ጋር ቁጭ ብሎ ከማውራት ኩንታል ድማሚት ላይ ተቀምጦ መፈንዳትን እመርጣለሁ…›› ከዳንዲዬ ጨቡዴ ቴያትር ላይ ነው የወሰድኩት፡፡ ከፈለገ እሱ ይፈንዳ እንጂ ፈንዱ ለማለት ሳይሆን መዝዤ ያወጣሁት መፈንዳት ድማሚት ላይ ተቀምጦ እንጂ እንዲሁ እንዴት ይፈነዳል? የሚለውን እንድታስቡት ነው፡፡ ጃክ ኤንድ ፋት ማን ፊልም ላይ የሚሰራው ፋትማን ፈንድቶ ነው የሞተው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እሱስ ውፍረትም ነበረው የእኛን እኮ ዝም ነው፡፡ የምር ቋንጣም ይፈነዳል እንዴ? ነገሩ እንደዛ ነው የሆነብኝ፡፡

እዚህ የመን ግን ነገር ተገልብጧል፡፡ ፍንዳታውንም፣ ማፈንዳቱንም፣ መፈንዳቱንም በደንብ ያውቁታል፡፡ ትላንት እንኳን አንዱ የታጠቀውን አፈንድቶ እሱም ፈንድቶ አስር ሰዎችን አስከትሎ ነጎደ፡፡ አሸባሪዎቹ ይህን ፍንዳታ እና ማፈንዳት ይዘውታል፡፡ ፍንዳታ ማለት እንሱ ናቸው፡፡ የፈነዱ የሚፈነዱ….ሜይ 21 ቀን ወታደሮች ሰልፍ ልምምድ ላይ እያሉ ያፈነዳው 103 ወታሮችን በታትኗል፡፡ ስጋቸው እንደ አሸዋ ክምር በአካፋ እስኪዛቅ፡፡ ግሩም ፈነዳ ቢሏችሁ ጎረመሰ መስሏችሁ ዝም እንዳትሉ፡፡ አንድ ፎቅ የሚበታትን ፈንጂ የታጠቀ ከገጠመኝ ነው፡፡ አይግጠም ነው፡፡ እዚህ እውነተኛው ፍንዳታዎች ናቸው፡፡

ልጄ ለአቅመ ሔዋን ደረሰች፣ ልጄ ለአቅመ አዳም ደረሰ በማለት ፋንታ ልጄ ፈነዳ/ፈነዳች/ ልንል ነው? ስለ ፍንዳታዎች ባህሪ የምታውቁ እስኪ ጻፍ ጻፍ አድረጉና አስነብቡን፡፡ በአንድ ወቅት የቡሄ ሰሞን በየመንደሩ ርችት የሚያፈነዱ በዝተው ነበር፡፡ ሽማግሌው ኪስ፣ ጫማ..ውስጥ እየከተቱ ‹‹ጧ!..›› ያደርጋሉ፡፡ ያፈነዳሉ እንጂ አይፈነዱም፡፡ ሰው ያስደነግጣሉ፣ ጆሮ ያደነቁራሉ፡፡ ታዲያ ማን ይሙት እነዚህን ልጆች እደጉ ተመንደጉ አመት አመት ያድረሳችሁ ብሎ የሚመርቃቸው ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ ? ወይድ በአጭር ያስቀርህ፣ ያፈንዳህ ከማለት የዘለለ ማን ሊቸራቸው? ያፈንዳህ እየተባሉ ይሆን ፍንዳታ የሆኑት? እንጃ ብቻ እንጃ፡፡ ‹‹ከመፈንዳት አካባቢን ማጽዳት›› የምትል ጽሁፍ አካባቢያቸውን ያሳመሩ ልጆች ጽፈው አይቻለሁ፡፡ አሪፍ አይደለች? አራዳነት በስራ የሚለውን አይጠቁምም ብላችሁ ነው? ድሮ ድሮ አራዳ ማለት ያለውን የሚያካፍል እንጂ ቁጭ ብሎ የሰው እጅ የሚጠብቅ አይደለም፡፡ እንደዛማ ከሆነ በልመና የተሰማሩ ሁሉ አራዳ ናቸው ማለት ነው፡፡ የሰው እጅ ከማየት ሰርቶ ማግኘት፡፡ አራዳነት ይዞ መገኘት፤ ሰርቶ መለወጥ ከሆነ ቆየ ያላወቃችሁ አራዶች ንቁ!!!!...
ሰላም ሁኑ!!..

No comments:

Post a Comment