Wednesday, August 1, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል አንድ
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ሴቶቻችን ለሱዳን ወንዶች ይታገላሉ….

ኢትዮጵያዊያን እንደ ጉድ እየጎረፉበት ስላለው የአረብ ሀገር ስደት እና እየተፈጸመባቸው ስላለው ግፍ ሁሌም አስባለሁ፡፡ እጨነቃለሁም፡፡ ግን ምንም ማድረግ የምችል አይነት አይደለሁም፡፡ አቅም የሌለኝ ልክ ክንፍ እንደሌላት ወፍ የምፍጨረጨር እኔም አረብ ሀገር ገብቼ ገፈቱን፣ የሚደርሰውን አሰቃቂ ግፍ እያየሁ፣ እየቀመስኩም ያለሁ ስደተኛ ነኝ፡፡ ቢሆንም ወገናችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለወገኔ አድርሼ የሚረዳ እንዲረዳቸው ከማድረግ በተጨማሪ የሚሰደደውን ቁጥር በአምስትና አስር ሰው ቁጥር እንኳን ብቀንስ ብዬ እጫጭራለሁ፡፡

በዚህ ዙሪያ ሁለት መጽሀፍትን ባዘጋጅም የማሳተም አቅሜን እስካደራጅ እና አቅሜ ፈቅዶ አስካሳትም የስደተኛው ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ መጣ፡፡ የሚደርስባቸውም ግፍ አሰቃቂነት አሳሳቢ እየሆነ፣ ሞት በየቦታው እየጠረጋቸው፣ የአካል መጉደል፣ መደፈር..የመሳሰሉት በእጥፍ እያደገ በመሆኑ ጊዜ ላለመስጠት በኢንተርኔት ጽሁፎቼን መልቀቁን አማራጭ አድረጌዋለሁ፡፡ እባካችሁ የሰማችሁ፣ ያነበባችሁ ለሌላው አሰሙ..አስነብቡ አንድም ቢሆን ወገን ይትረፍ፡፡ አረብ ሀገር ሆናችሁ የምታነቡም ለጥንቃቄም ሆነ ከአላማችሁ እንዳትዘናጉ ይሁናችሁ፡፡

በስደት ካሉ በጣም ከተለያዩ ሰዎች ጋር በደብዳቤ፣ በኢሜል፣ በስካይፒም የተለያየ ሀሳብ አካፍሉኝ እላለሁ፡፡ በርካቶች የማቀርብላቸውን ጥያቄ አቅም በፈቀደ ይመልሱልኛል፡፡ ከብዙዎቹ የምሰማው ግን አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ሀገር እያለን እንደሌለን ሆነን የሚፈጸምብንን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ችለን ያለንበት ህይወት ሰቅጣጭ ነው፡፡ ታንቀው የሚገደሉ፣ የሚደፈሩ ሴቶቻችን፣ ወንዶች እና ህጻናት ቁጥር የዋዛ አይደለም፡፡ ታንቀው፣ ተደብድበው፣ በእሳት ተቃጥለው፣ የሞቱ ወገኖቻችን በየአትክልቱ ስፍራ ተቀብረው በየቆሻሻ መጣያው ተጥለው ቀርተዋል፡፡ ቀባሪ አጥተው በየሆስፒታሉ ፍሪጅ ውስጥ በስብሰዋል፡፡ በህገ-ወጥ አጓጓዦች አጓጉል መንገድ ስንቶች ለሞት ተዳርገዋል? በየእስር ቤቱ ያሉ ወገኖች መጨረሻቸው ምንድን ነው? በየእስር ቤቱስ የሚደርስባቸው በደል ምንድን ነው? በዚህ ዙሪያ በተከታታይ እናወራለን፡፡ የስደት መንገዳችን እንዴት ነው? ተሰደንስ ምን አፈራን?

ዋናው ደግሞ እኛስ በስደት ሀገር ምን እየሰራን ነው? ወገን ወገኑን አሳልፎ የሚሸጥበት፣ ለአደጋ የሚያጋልጥበት፣ ጥቂቶች በሚሰሩት መጥፎ ተግባር ሁሉም የሚወቀስበት፣ የሚታሰርበት ሁኔታ የለም? አለ፡፡ ይህንንም ለማየት እንሞክራለን፡፡ በተያያዥነት እንዲረዳይ ወይም መገለጽ አለበት የምትሉት ሀሳብ/መረጃ/ ካለ ላኩልኝ፡፡ መረጃ ልትሰጡኝ የምትፈልጉ ለአማራጭ ኢሜል መጠቀም ከፈለጋችሁ girum_tekl@yahoo.com ብላችሁ ተጠቀሙ፡፡

የምንሰራው መጥፎ ስራ ከእኛ አልፎ ሀገር ዜጋ የሚያስወቅስ፣ የሚያሰድብ የሚሆንበት ጊዜ የለም ወይ? የሚለውን ለማየት ስንነሳ ሴቶቻችን በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው፤ ወንዶች በመጠጥና በሀሺሽ ንግድ በሌላም ህገ ወጥ ድርጊት ተሳትፈው የሚታዩበት ሁኔታ አለ፡፡ ሴቶቹ በሴትኛ አዳሪነት ተሰልፈው አሰደቡን፣ አዋረዱን የምንለውን ያህል ወንዶችም በዚሁ መስክ ተሰማርተው መገኘታቸው ያሳፈራል፡፡ ኩሉን ተኩሎ ሊፒስቲክ ተቀብቶ ታይት አድረጎ ለገበያ የሚቆም፣ ተደውሎለት ፒክ የሚደረግ ኢትዮጵያዊ አለ መባሉ ምን አይነት ስሜት ይጭርባችኋል? ዱባይ ካሉ ኢትዮጵያዊያኖች ጋር በዚህ ዙሪያም አውርቻለሁ፡፡ እመለስበታለሁ፡፡

ከዚህ ወጣ ብለን ተሰደን የሰራንበትን ቤተሰብ ለውጠናል ወይ? ለራሳችንስ ሆነናል፣ ጥሪት ቋጥረናል? የሚለውን ለማየት ስንሞክር ደስ የሚል እና የሚያሳዝን ነገር ልንሰማ እንችላለን፡፡ ጥቂቶች ደግሞ በሉብናን /ቤይሩት/፣ ዱባይ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን.. ኩዌት ያሉ ሴቶቻችን የሱዳን ወንዶች ሲሻሙ እና የለፉበትን አባክነው ቤት ተከራይተውላቸው ማስቀመጣቸው እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ እንዲያውም አንድ ቤይሩት ያለች ጓደኛዬን ሳዋያት ሁሉን ነገር ነገረችኝ፡፡ አከለችናም ‹‹ በአጠቃለላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ለሱዳን ወንዶች ይታገላሉ ማለት ያስችላል፡፡ ቤተሰቧ በርሃብ የሚቆላ ችግረኛ ሁሉ ስራ የጠላ በሴት ገንዘብ መቀመጥ የወደደ ሱዳናዊ ይዛ ቤት ኪራይ ከፍላ፣ አብልታ፣ አጠጥታ….አለችኝ ያሳፍራል፡፡ እዚህ የመንም ያለውን ሳይ በመውለድና በጋብቻ በኩል ሲታሰብ ከሀገር ያስወጣቸው የባል ችግር እስኪመስል ያገኙትን ሀገር ዜጋ አግብተው የሰሩበትን እያበሉ የሚኖሩ ያጋጥማሉ፡፡ አላማ መሳት ነው፡፡

ሰው ቤት፣ ድርጅት ውስጥ በጽዳት ተቀጥረው፣ አይገቡ ገብተው ገላቸውን ሸጠው ያገኙትን ለቁም ነገር ካላዋሉት ለምን መሰደድ አስፈለገ? ስትለፋበት የኖረችውን ገንዘብ ደግሳበት የሚበላው የሌለው ናይጄሪያዊ፣ ሶማሊያዊ..ህንድ፣ፓኪስታን…! ያገቡ እና ተያይዘው የእከክልኝ ልከክልህ ህይወት ሲመሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ደግሞ የሚገርመው የፎቶ እና ቪዲዮ ትዝታ ለማስቀረረት ያላቸውን አንጠፍጥፈው ደግሰው ማግባታቸው፡፡ የተሻለ ሲያገኝ አመት ሳይሞላው ጥሏት የሄደ ሞልታለች፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ እናወራልነአሁን የአፍሪካ ህብረትን አዲስ አበባ ላይ አድርገናል፡፡ ጎበዝ ከትንሽ አመት በኋላ ምን የአፍሪካ ህብረት ብቻ የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤትም ኢትዮጵያ እንዲሆን የምንጠይቅበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ ከአለም ያልወለድንለት ዜጋ ይኖር ይሆን? ቱቱ!!!...ቱቱ!.. ሴቶቻችን ማህፀናችሁ ይለምልም፡፡ አሜን በሉ!!

No comments:

Post a Comment