Wednesday, August 1, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል ሁለት
በግሩም ተ/ሀይማኖት

በዚህ ርዕስ የመጀመሪያውን ፅሁፍ እንደለቀኩ ኢ-ሜሌም ሆነ ስልኬ የግል መልዕክቶች በመቀበል ተወጠሩ፡፡ ከ142 በላይ ሰዎች ቻት ያደርጉኝ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን አብዛኛዎቹ ያስተላለፍኩትን መልዕክት በትክክል ካለመረዳት የመነጨ ጭንቀት ነበር ያማከሩኝ፣ የወቀሱኝ፡፡ ካስተላለፍኩት መልዕክት ባፈነገጠ መልኩ የተረዱኝ የተረጎሙብኝ አሉ፡፡ ከዛም ተነስተው የሰደቡኝ ሞልተዋል፡፡ ስድብ ለብስልት መገለጫ አይሆንም፡፡ እውነታ የያዘ ሰው ይሄ ይሄ ነው እውነታው ቢለኝ የማልቀበልበት መንገድ የለም፡፡ አስተውላችሁ በማንበብ ወገን ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃ
ቂ ግፍ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሰሩ ስህተቶችን ብንነጋገር እና መፍትሄ ካገኘንም፣ መርዳት የምንችለውን ብንረዳ ቀና ወገናዊነት ነው፡፡

‹‹..ሴቶቹ በሴትኛ አዳሪነት ተሰልፈው አሰደቡን፣ አዋረዱን የምንለውን ያህል ወንዶችም በዚሁ መስክ ተሰማርተው መገኘታቸው ያሳፈራል፡፡ ኩሉን ተኩሎ ሊፒስቲክ ተቀብቶ ታይት አድረጎ ለገበያ የሚቆም፣ ተደውሎለት ፒክ የሚደረግ ኢትዮጵያዊ አለ መባሉ ምን አይነት ስሜት ይጭርባችኋል? ዱባይ ካሉ ኢትዮጵያዊያኖች ጋር በዚህ ዙሪያም አውርቻለሁ፡፡ እመለስበታለሁ፡፡ …›› ነው ያልኩት፡፡ ይሄ ማለት ዱባይ ያሉ ሴቶች በሙሉ ይሸረሙጣሉ ማለት ነው? በየትኛው ስሌት እና አባባል እንደተተረጎመ ዲክሽነሪ ላይ ቢፈለግ አይገኝም፡፡

ስለ ወንዶቹ ድርጊት ተወያይቻለሁ ነው ያልኩት፡፡ ቢሆን እንኳን ዱባይ ያሉ ጥቂት ሴቶቻችን የሚሰሩት ነገር የለም? ወገኖቻችን ላይስ ግፍ አልተፈጸመም? በቅርቡ ተጫውተውባት ዛፍ ላይ አንጠልጥለው ራሷን ሰቀለች የተባለች የለችም? በደረሰባቸው ግፍ አብደው ኮሚኒቲ ውስጥ የነበሩ የሉም? አሁንስ አይኖሩ ይሆን? ለሶስት ተጫውተውባት የፌስቱላ ችግር ገጥሟት አዋጡላት ተብሎ የታከመች የለችም? በስም ብቻ ሳይሆን በፎቶ ጭምር የማውቃቸው ወንዲኛ አዳሪዎች የሉም? /ለሴቶች ሴተኛ አዳሪ ከተባለ ለወንዶች ወንዲኛ አዳሪ የሚለውን ልጠቀም እንጂ እስከዛሬ ስላልተለመደ ቃል ያለው አልመሰለኝም፡፡/ ጥቂት በጣም ጥቂት እህቶቻችን ለሚያገኟት ሳንቲም ብለው በቪዲዬ ተቀርጸው መጠቀሚያ አልሆኑም?

እንዲያውም እዚህ ጋር አንድ ገጠመኜን ላሰፍር ወደድኩ፡፡ አንድ ፈረንሳያዊ ተጓዥ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የመን የጋዜጠኞች ማህበር ስብሰባ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩና ስሄድ አገኘሁት፡፡ እሱም ተጋብዞ ስለነበር ሁለታችንም የተጋባዥ ወንበር ላይ ነው ያለነው፡፡ ከየት እንደመጣሁ የጠቀኝ እና ወሬ ተጀመረ፡፡ በወሬያችን መካከል እዚሁ እንደምኖር ተነፈስኩ፡፡ የመን ትንሽ ጊዜ ስለሚቆይ አብራው የምትዝናና ሀበሻ ሴት እንዳስተዋውቀው ጠየቀኝ፡፡ አንደኛ እኔ አቃጣሪ ደላላ አለመሆኔን ሁለተኛ ማንኛዋም ሀበሻ የእንደዛ አይነት ፍላጎት እንደሌላት እና ለስራ እንደመጣች ነገርኩት፡፡ የዛሬ ወር ዱባይ ነበርኩ ብሎ የያዛትን ዲጂታል ካሜራ ከነካካ በኋላ ፊልሙን ዝግጁ አድርጎ እንዳየው አቀበለኝ፡፡ አፍ እና ጭን ተጋጥመው /.../ በስሜት ጥድፊያ ይዋከባሉ፡፡ ፊልሙን ለማየት እንዳቀረቀርኩ ደረኩ፡፡ አንገቴን ቀና እንዳላደርግ ሀፍረት በግሩፕ ሰፍሮብኝ ሸብቦ ያዘኝ፡፡

ካሜራውን ስመልስለት መቅረጽህን ታውቃለች? ለነገሩ ይህቺ ልጅ ሀበሻ አይደለችም አልኩት፡፡ ለማምለጫ እንጂ ልጅቷን ኢትዮ ስፖት ዌብ ሳይት ላይ ተደጋጋሚ እርቃን ገላ በሚያጋልጥ ሁኔታ ፎቶ ተነስታ ስትለቅ ነው የማውቃት፡፡ በደንብ እንደምታውቅ እና ክፍያውን ጨምሮ እንዳደረገው ነገረኝ፡፡ የፈለገውን ያህል ቢከፍላት ከ1000 ዶላር በላይ አይከፍላትም፡፡ እሱ ግን የሚያፍሰውን ያፍሳል፡፡ እህቶቻችን ባለማወቅ ከወሲብ ውጭ ሌላም ንግድ መጠቀሚያ እየሆኑ ነው፡፡ እዚህ የመን ውስጥ አሁን ሳዑዲ ያሉ ሁለት እህትማማቾች አውቅ ነበር፡፡ ትልቅየዋ ጀርመናው ጓደኛ አላት፡፡ ከእሱ ጋር የምታደርገውን ነገር በህገ-ወጥ ሁኔታ ስትፈጽም ታናሽዬው ቪዲዮ ካሜራ ይዛ መቅረጽዋን ከራሷ አንደበት ሰምቻለሁ፡፡ እንደጀብዱ በተሰበሰብንበት ያወሩልን 500 ዶላር ሰጥቷቸው ነበር፡፡ እነዚህ አይነት ነገሮች በመጀመሪያ የራስን ሰብዓዊ ክብር፣ ሞራል ከማዝቀጥ አንጻር ቀጥሎ የወገንን ብሎም የሀገርን ስም....እያልን እንድናስብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንዳሰው ችግራችንን እንነጋገር ነው አላማዬ፡፡ ባለማወቅም የሚሰራ ነገር መኖሩንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው በሞባይል ስልኬ ከደረሰኝ መልዕክት ውስጥ ስሟን ካስተዋወቀችኝ በኋላ ‹‹....እግዚአብሄር ይመስገን አለኝ፡፡ /አይ እታለም ቢኖርሽ ለምን ተሰደድሽ?/ ለራሴ እና ለቤተሰቦቼ እንጂ ጎረምሳ ልቀልብ አልወጣሁም፡፡/ቱ..ቱ..ቱ.. ያሳድግሽ፡፡ እኔም እኮ እያልኩ ያለሁት ለራሳችን ምን ያህል አውቀናል? ቤተሰብ በችግር ሲማቅቅ እኛ ለምን ስራ ጠልቶ እንደ ውሻ እጅ እጅ የሚያይ ሰው እንቀልባለን ነው፡፡/ እና አረብ ሀገር ያሉ በተለይ ዱባይ አያልክ ሰውን ባታጎሳቁል ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎችን ወክዬ መናገሬ ግን አይደለም፡፡ ያለከውን የሚሰሩ አሉ፡፡ የሉም አልልም፡፡ እናንተ ጋርም እንዳሉ እህቶቼ ይነግሩኛል፡፡ እዚህ ዱባይ የብዙ ሴቶችን ትዳር እና ጓደኝነት እንደምትበጠብጥ ልብ ያልክ አልመሰለኝም፡፡..›› ይላል፡፡ ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው በተለይ ዱባይ ያልኩበት ቦታ የት ነው? እኔ ያልኩት ‹‹..ጥቂቶች ደግሞ በሉብናን /ቤይሩት/፣ ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን.. ኩዌት ያሉ ሴቶቻችን የሱዳን ወንዶች ሲሻሙ እና የለፉበትን አባክነው ቤት ተከራይተውላቸው ማስቀመጣቸው…›› ነው፡፡ ያውም ጥቂቶች እንጂ ሁሉም አላልኩም፡፡ እህቴ ቅድሚያ አስተውሎ ማንበብ ቢቀድምስ?

‹‹ዱባይ የማውቃቸው በርካታዎች ሞልተዋል፡፡ እህቴም /የአጎቴ ልጅ/ ጭምር አለች፡፡ በጅምላ የሰውን ሰብዓዊ ክብር የሚደፈጥጥ ነገር አልሰራም፤ አልናገርምም፡፡ ሞያዬም አይፈቅድም፡፡ የማንንም ህይወት መንካትም ሆነ ማጨለም ህልሜ አይደለም፡፡ የእኔ አላማ በአቅም ማጣት ካልተገደበ በስተቀር ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡ ችግሩን መነጋገር እና መፍትሄ ለሚያስፈልገው ከእነ መፍትሄው ብንነጋገር የሚደርሰው ጉዳት የሚቀንስበት፣ ብሎም የሚቆምበትን መንገድ ለመፈለግ ነው ዋናው አላማዬ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ፍልሰት በምን ዘዴ ይቁም ሳይሆን ይቀንስ? የሚለውን መነጋገር ስላለብን ነው የምጽፈው፡፡ በተጨማሪም ለብዙ ነገር አጋልጦ የሰጠን መጥፎ ተግባራችን ቢቻል ቢቀር ካልሆነም ቢቀንስ ያለው መሰደብ፣ መንቋሸሽ፣ መናቁ ይቀንሳል፡፡ መሰደዳችን በድህነት መሰደባችን አንሶ በመጥፎ ነገር ሀገርም ማሰደባችን ቢቀርስ ከሚል ነው፡፡ በአረቡ አለም ላይ ለሀበሻ ያላቸው አመለካከት ጥሩ አለመሆኑን ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ሆኖ ሳለ በመጥፎ ስራችን አጠቃላይ ያ-ሀበሺያ፣ ሀበሻ ጋህባ../ሀበሾች ሸርሙጦች፣ ሀበሻ ሸርሙጣ/ የሚል የጅምላ ስድብ አትርፈናል፡፡ ይህን ስም መፋቅ ቢከብድ ቢያንስ እንዲቀንስ ማድረግ ብንችል ከሚል ሀሳብ ተነስቼ ነው ያሰብኩት፡፡

አይነቱ ይለያይ እንጂ ያሰደደን ችግራችን ነው፡፡ተሰደን በሰራንበት ቤተሰብ ለውጠናል ወይ? ለራሳችንስ ሆነናል? አዎ አብዛኞች የሰሩትን ሰርተው ለቤተሰባቸው እና ለራሳቸው የጠቀሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቤተሰብ የሚበላው አጥቶ ሲራብ አሸሸ ገዳሜን በረጅሙ ሲቀውጡት ከርመው ያለምንም ሳንቲም ታመው በአዋጡልኝ ሀገር የሚገቡ አሉ፡፡ ያልረዱት፣ የረሱት ቤተሰብ ላይ ሄደው ሸክም የሚሆኑ፡፡ ይሄ ምኑ ነው ውሸት?

በዋነኛነት ግን ከላይ የጠቃቀስኳቸው እንዳሉ ሆነው በመታሰር፣ በመደብደብ፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው በየቦታው አካላቸው እየጎደለ እና እየተገደሉ ስላሉ ወገኖቻችን ድምጽ እናሰማ፡፡ ለመፍትሄ የሚሆን ሀሳብ እንወያይ....ችግራችን ነው እንነጋገርበት ያልኩት፡፡ አስተውሎ መራመድ ብልህነት ነው፡፡ የወገን ሰቆቃ መቆሚያ ጊዜው እስኪደርስ የሚቀንስበትን መንገድ እንፈልግ፡፡

ዋናውን ታሪክ አልጀመርኩም በዋናው ታሪክ እንገናኛለን
ቸር እንሰንብት

No comments:

Post a Comment