Wednesday, August 1, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል  ሶስት
ለካ ራስ ማጥፋትምከባድ ነው?..አቃተኝ!!
      በግሩም ተ/ሀይማኖት

  ሁለት አንባቢዎቼ የሚናገሩትን አያውቁትም እና ይቅር በላቸው የሚያስብል አስተያየት አስፍረው አይቻለሁ፡፡ የወገን ስቃዩ አይነገር..የሚሰሩት ሀገርን የሚያሰድብ ጸያፍ ስራ አይነሳ የሚሉ ገጥመውኛል፡፡ ቅር አይለኝም ማንም እንዳቅሙ ማሰብ እንደሚችለው ነው የሚያስበው፡፡ ከአቅምህ በላይ አስብ፣ አገናዝብና ተረዳኝ ተብሎ አይወቀስም፡፡ የሌለውን አምጣ፣ ያልተሰጠውን ፀጋ ተላበስ አይባልም፡፡ ‹‹..ሁሉም በተሰጠው ጸጋ ያገልግል…›› አይደል የሚለው ቅዱሱ መጽሀፍ? ታዲያ ያለ ተፈጥሮው ጭካኔህን ትተህ ሰብዓዊ ሁን፣ የሰው ስራ ማራከስህን ትተህ ራስህ ሰርተህ አሳይ አይባልም፡፡ ያልተሰጠውን ከየት ሊያመጣ? ተፈጥሮው ማጥላላት እና ሰውን ማንጓጠጥ፣ ከማገናዘብ ይልቅ በጭፍን መጓዝ ከሆነ ከዚህ ጨለማ ያውጣህ ብሎ ወንድማዊ ጸሎት ከማድረግ ውጭ ቱ!..ቱ!..ያሳድግህ ብልግናህ ካንተ ይዝለቅ አይባልም፡፡ ምንም ቢሆን ወንድም ነው ክፉ ያስብ እንጂ ክፉ ማሰብ ከእኛ አይጠበቅም፡፡ መጥፎ ሀሳብ ከእኛ ዘንድ ይራቅ..

   የመን በባህር ስገባ ያየሁትን ስቃይ እና በባህር የሚገቡ ሁሉ የሚያዩትን መከራ በመጽሀፍ ለማዘጋጀት ከሶማሊያ ጀምሮ መረጃዎቼን እያሰባሰብኩ ቆየሁ፡፡ ቀድመውኝ ወደ የመን ለገቡትም ሆነ ከኋላዬ ለተከተሉኝ በዛ ያሉ ስደተኞች መጠይቅ ፎርም በትኜ መረጃ ጠይቄያለሁ፡፡ 27ሰው ቃለ-ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 12 የሚሆኑን በኮንትራት ለቤት ሰራተኛነት መጥተው ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ሁለቱ ለ20 አመት የመን የኖሩ የቀድሞ ባህር ሀይል ባልደረባዎች ናቸው፡፡ ከዱባይ ከመጡት ውስጥ 7 ያህሉን አናግሬያለሁ፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለቱን በሞባይል ስልኬ በድብቅ ነው የቀረጽኳቸው፡፡ ምክንያቱም ለቃለ-ምልልስ ከማሳመኔ በፊት ነገሩ በድንገት በመነሳቱ ነው፡፡ ከቀዳኋቸው በኋላ ግን አለሳልሼ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ አሁን ታሪኳን ያቀረብኩት ልጅ መግቢያው ላይ እንደ ተናገርኩት ለምን እንዲህ አይነት ዝርጥጥ ቃላት ተጠቀምሽ ከባህል ስርዓታችን አንጻር ስላልኳት ነው መረር ያለ ነገር በእልህ ተናግራ ልታወራኝ የተነሳችው፡፡      

    ይህን ያስተዋለ፣ እውነቱን የሚያውቅ አንድ ሳሙኤል ተስፋዬ የተባለ አንባቢ ‹‹..በጣም የሚገርም ነው። አንዳንዶቹ የሚናገሩትን አይቁም። እንዴት ሰው ባልኖረበት ነገር አሳፋሪ መልስ ይሰጣል? እሱ ከሌላው ጋጠወጥ አድራጎት ካለው በምኑ ነው የሚለየው? /ወዳጄ አትሳሳት በምንም አይለይም፡፡ ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም በማለት አንድ እህቴ መልሳለታለች፡፡ ተደናቁረው ሊያደናቁሩነ የሞከሩት ሴቶች እህቶቻችንን ለአረብ በማቃጠር የሚሸጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ በአረብ ሀገር ነዋሪ ከመሆናቸው አልፎ ኢትዮሰፖት የሚባል ዌብሳይት ላይ ለገቢያ የሚያመቻች እርቃን ፎቶ የሚለጥፉ ናቸው፡፡ ለአብነት ይህን ክሊክ አድርገው ተመለከቱ…
http://www.ethiospot.com/photo/hubby-is-this-mar-like-tej-konjo-like-flower./ ለማንኛውም ልቦና ይስጠው ከማለት ውጪ ምን ይባላል? ግሩም ሃሳቦችህ እስካሁን አንዳንድ የተለያዩ ሚዲያዎች ነካኳቸው እንጂ እንዳንተ በግልጽ አላቀረቧቸውም ነበር፡፡ ዛሬም እድሜ ላንተ ጫፉ ላይ ቆመሃል። ነገ ድግሞ እኛም እያገዝንህ ወደ ውስጥ ትገባለህ ከዛም እኛ በአረብ አገር ያለን ሰዎች ምን ያክል ባህላችንን እያጎደፍን እንዳለን ሁሉም ያውቃል ማለት ነው፡፡ ከዛም በምክር ያለ ሆነው ለውጥ በእፍረት ይመጣል ማለት ነው። አንተም አሁን በበርሜል ያለውን ግድፈታችንን በማንኪያ ጨለፍከው እንጂ ገና ምንም አልነካኽውም። እናም ካንተ ብዙ እንጠብቃለን። አቀራረብህ በጣም ግልጽና የተብራራ ነው። ቀጥል።…››ሲል አደራውን የበለጠ አጥብቆብኛል፡፡ ምስጋናዬ የላቀ ነው እንዲህ ከጎን የሚሰለፍ ችግሩን የሚያውቅ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ታዲያ ቃለ ይከበር እኛም እያገዝንህ ብለሀል፡፡

       ሌላው አንባቢዬ ደግሞ ‹‹..ያልከው ነገር እውነት ነው ምንም ስህተት የለውም የሚገርመው እንኳን ይህ ነገር ስህተት እንደሆነ ስትነግራቸው የሚመልሱልህ መልስ በጣም የሚያሳፍር ነው። ከሱዳን ወይም ከሌላ አገር ዜጋ ጋር መጋባታቸውና አብረው መኖራችው አይደለም ችግሩ፡፡ በአንድ ወንድ ሁለት ሶስቱ ሲጣሉ የሚታየው ነገር ነው ይበልጥ አንተነትህን እንድትጠላ የሚያደርግህ። እነሱም ቢሆኑ አብረው መዝለቅ እንደማይችሉ ነገር ግን ላላቸው በጣም አጭር ጊዜ ያውም የሕይወት አጋር ላለሆነ ሰው መደባደብ ብሎም እስከ መጋደል የሚያደርሱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባር ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጥሎ ነው የተመጣው። ለማንኛውም ማወቅ ያለብን መልካም አስተሳሰብ እና መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው ሴቶች የሉም ማለት አይቻልም አሉ። /አዎ እኔም አምናለሁ አሉ፡፡ ያውም አንገት ደፍተው የሚሰሩ…ከኢትዮጵያ ሲወጡ ለፍቅር አለያም ለትዳር ጓደኛቸው የሰጡትን ቃል የሚጠብቁ….በጣም ብዙዎች መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው አጋጣሚም የረዳቸው….ሞልተዋል፡፡ ሁሌም ስናነብ እነዚህን ከግምት እናስገባ፡፡/  ነገር ግን መጥፎ ስነ-ምግባር ባላቸው ጥቂት ሰዎች ተሸፍነዋል።

     ተውጠዋል፡፡

     አበበች በስደት አገር ብታጠፋ አንድ ሃበሻ አጠፋች እንጂ አበበች አጠፋች የሚል የለም። ስለዚህ የብዙሃኑ በሆነ ስም ላይ ግለሰብ ወሳኝ መሆን አይችልም ሃሳብ ማቅረብ እንጂ። ለለውጥ ከሆነ ግን ግለሰብ የሚኖረው ሚና ትልቅ ሊሆን ይችላል። አሁንም አንተን የምልህ እንዲህ አይነት ነገሮችን በተከታታይ ፖስት ብታደርግ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ባሁኑ ወቅት በአረብ አገር ካሉት ስዎች ውስጥ 75% በላይ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ብሎጎችን ማየታቸውና ማንበባቸው አይቀርም። ቢያንስ ቢያንስ አጠቃላይ ለውጥ ባይመጣ እንኳን መጠነኛ የሆነ ነገር ማየት እንችላለን ብዬ አምናለሁ።ይበል ያሰኛል።….›› ይህን የመሳሰሉ በርካታ አስተያየቶች ደርሰውኛል፡፡ ለአስተያየቶቻችሁ ምስጋናዬ የከበረ ነው፡፡

     የበለጠ ደግሞ አባቴ ወታደር እያለ የሰራትን ቤት ካርታ አሲዘው ስለሆነ የላኩኝ ቤታቸውንም እንደሚያጡ ሳስበው ሰቀጠጠኝ፡፡ ሞቴ ብዙ ነገራቸውን እንደሚያጨልመው በተቃራኒው ተስፋቸው፣ በልቶ ማደራቸው፣ መጠለያ ይዞ መቆየታቸው ሁሉ በእኔ ላይ የተጣለ ሀላፊነት እንደሆነ ሳውቅ ራሴን ጠላሁት፡፡.. ብዬ ነው በቀጠሮ ያቆየኋችሁ፡፡ ቀጠልኩ…ተከተሉኝ..

     ገመድ ብፈልግ ከየት ላግኝ? መርዝ ነገርም ፈለኩ፡፡ ግን ምንም አላገኘሁም፡፡ ወይ አለመታደል ለካ ራስን ማጥፋም ከባድ ነው አቃተኝ፡፡ እንደምንም እግሬን አንፈርክኬ ለመቆም ሞከርኩ፡፡ አቃተኝ እና ወደኩኝ፡፡ ስወድቅ ጓ!...የሚለውን ድምጽ ሰምተው ልጆቹ መጡ፡፡ ሲመታኝ አለመጎዳቴን አይተው የሚበላ ነገር አምጥተው እንደ ውሻ በሰሀን ወረወሩልኝ፡፡ እህሉን ሳየው ጠንከር ያለ ርሃብ ተሰማኝ፡፡ ሽንቴን ሸንቼ የተጨማለቀ ሰውነቴን ታጥቤ ለመብላት ግርግዳ ተደግፌ እየተራመድኩ መጸዳጃ ቤት ገባሁ፡፡ ሽንቴ የምጥ ያህል ሲያስቃትተኝ ቆይቶ ያደናገጠኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ስሸና ማቃጠሉ እና በደም መታጀቡ ብቻ ሳይሆን ከሰገራዬ ጋር ተቀላቅሎ መሆኑ ይበልጥ አደናገጠኝ፡፡ አሁን ራሴን የማጥፋቱ ፍላጎት ዳግም ውስጤ አቆጠቆጠ፡፡ ቁስለቱም ከውስጤ ይቆጠቁጠኝ ጅመሯል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ እንደማያኖሩኝ ታሰበኝ፡፡ ይጠርዙኛል /ወደ ኢትዮጵያ ይመልሱኛል/ ችግራቸውን አብዝቼ እንዲህ ሆኜ አይተው ሰቀቀን ከምሆንባቸው ራሴን ማጥፋቱን መረጥኩ፡፡

    በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መኖር አልፈቅድም፡፡ የፍራሹን ጨርቅ ባለ በሌለ ሀይሌ ቀድጄ ሸምቀቆ አድርጌ አሰርኩና የደረጃው መደገፊያ ብረት ላይ አሰርኩት፡፡ እንደ ምንም ራሴን ከተትኩት፡፡ ግን እንዴት ያስፈራል? ጣር ይዞኝ የማወጣውን ድምጽ ሰምተው ተሯሩጠው ገመዱን በጠሱት፡፡ ተዝለፍልፌ ወሜት ስወድቅ አንደኛው በእርግጫ ጠለዘኝ፡፡ ለሁለት አንጠልጥለው መኪና የኋላኛው እቃ መጫኛ ውስጥ ከተቱኝ፡፡  አንደኛው ምን ሊያመጣ እንደሆነ እንጃ ሮጦ ወደ ውስጥ ሲገባ በኮቴው ድምጽ ታወቀኝ፡፡ ከፈት አደረገና የሆነ ፌስታል አምጥቶ ላዬ ላይ ጣለው፡፡ ወዴት እንደወሰዱኝ ከተማውን ስለማላውቅ አላውቀውም፡፡ ከተማውን ባውቀውም ስለማይታየኝ አላውቀውም፡፡ የሆነ ዘዋራ ስፍራ ከመኪና አውርደው ሲጥሉኝ ፌስታሉንም አጠገቤ አስቀመጡልኝ፡፡ መኪናቸውን አስነስተው ሲሄዱ ያለሁበትን አካባቢ ዞር ዞር ብዬ ቃኘሁት፡፡ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ነው፡፡ አንዲት ከርታታ እንጀራ ፍለጋ ከሀገሯ የተሰደደች ምስኪን ቆሻሻ ተብላ ቆሻሻ ቦታ ብትጣል ለእነሱ ምን ይደንቃል? ለእኔ ግን አስለቀሰኝ፡፡ በድህነቴ፣ በእድሌ አለቀስኩ፡፡ በፈጣሪዬ አዘንኩበትና አለቀስኩ፡፡ ለምን እንዲህ ሲያደርጉኝ ዝም አለ? ለምን ፈጠረኝ አልኩ፡፡ እኛ ለአረብ መጫወቻ ነው የተፈጠርነው ስል አለቀስኩ፡፡ አልቅሼ…አልቅሼ… አልወጣልሽ አለኝ፡፡

     እዛ ቦታ ምን ያህል ሰዓት እንደቆየሁ አላውቅም፡፡ በህመሙ፣ በለቅሶው ድካምና ህመም ስለነበረብኝ አሸለበኝ፡፡ አጠገቤ አንድ ሰው ቆሞ ያናግረኛል፡፡ የነቃሁት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ የምችለውን ያህል ነገርኩት፡፡ በታክሲ ወስዶ ከሀበሻዎች ጋር አገናኘኝ፡፡ /ከተኙት ሁለት ሴቶች አንዷን አሳየችኝ፡፡ አፏን ገርበብ አድርጋው ያለ ሀሳብ ተኝታለች/ መጀመሪያ ካገናኘኝ ሁለት ልጆች አንዷ ናት፡፡ አዘኑልኝ አጥበውኝ የሚበላ ነገር አበሉኝ፡፡ ሳይጠየፉ ገላዬን አጠቡኝ፡፡ አይኗ ዳግም እንባ የማመንጨት ተግባሩን ቀጠለ፡፡ ሳግ ይተናነቃት ጀመር፡፡ ከተኛችበት ተነስታ ጫፉ ላይ ተቀምጣ ከነበረው አልጋ ላይም ሸርተት ብላ መሬት ሽርቁጥ ብላ ተቀመጠች፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ አለመጠየፋቸው እንደሆነ ያስለቀሳት ገመትኩ፡፡ ሁኔታዋ ውስጤን ነካው እኔም የመን ውስጥ በእስር ሳሳልፍ አስታማሚ በሌለበት ታምሜ ለሽንት የሚያነሳኝ አጥቼ የተከሰተውን አስታውሼ እሷን በማባባል ፋንታ አጋዥ ሆንኩና ተገኘሁ፡፡ ሁለታችንም ባሳለፍነው መከራ ትዝታ ተሰንገን እንባዋን በእንባዬ አጀብኩት፡፡ አላቀስኳት ወይም አስለቀሰችኝ፡፡

    ‹‹..ገብቶሀል ግን ለምን እንደማለቅስ? ማንም ሰው ብሎ አያየኝም፡፡ ከእንግዲህ ተስፋ የለኝም ያልኩትን ሴት፣ ግማቱ ለራሴ ያስጠላኝን ሴት ሳይጠየፉ አጠቡኝ፡፡ እላዬ ላይ የደረቀ ቆሻሻዬን ላስቲክ ጓንት አድረገው አስለቀቁልኝ፡፡ የወቀስኩት ፈጣሪዬ ለካ አልረሳኝም፡፡ ለካ ወገንም ለወገኑ አይጨክንም አልኩ፡፡ አጣጥበውኝ ልብስ ሊለውጡልኝ ፈልገው ከእኔ ጋር አብረው የጣሉትን ፌስታል ሲከፍቱት ውስጡ ፓስፖርቴን አገኙት፡፡ ከገባሁበት ቪዛ ውጪ መኖሪያን አላሰሩልኝም፡፡ ልጆቹ ግን ያን ያደረጉት ይዛ ጠፋች እንዲባል መሆኑን አስጠጊዎቼ ነግሩኝ፡፡ ለምን ቆሻሻ መጣያው ጋር እንደጣሉኝ እና ምን እንዲህ እንዳደረገኝ ጠየቁኝ፡፡

    የደረሰብኝን ሁሉ እውነቱን ስነግራቸው አዝነው አይዞሽ እኛ አለን አሉኝ፡፡ በእርግጥም ብዙ ነገር ረዱኝ፡፡ ለሽንት መጸዳጃ በገባሁ ቁጥር አንደኛውን ለይቼ ማስተናገድ አቃተኝ፡፡ ሁሌ ተቅማጥ እንደ ያዘው ለአንደኛው ስቀመጥ ተቀላቅሎ ይወጣል፡፡ ህጋዊ ስላልሆንኩ በግልጽ ሆስፒታል ሄጄ መታከም ስለማልችል አንደኛዋ ልጅ የምታውቀው ዶ/ር ስለነበር ህክምና በድብቅ እንዲሰጠኝ አናገሩት፡፡ ትንሽ ካገገምኩ ከሳምንት በኋላ መረመረኝ፡፡ የፌስቱላ ችግር ስለተከሰተብኝ ህክምናው በቀላሉ ሊሰጥ እንደማይችል ነገራቸው፡፡ ለሰው ልጅ የተፈጠረውን መከራ ሁሉ ለብቻዬ ያሸከመኝ መሰለኝ፡፡ ከማልወጣው አረንቋ ውስጥ መዘፈቄን አስቤ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ መፍትሄው በድብቅ የግል ክሊኒክ ውስጥ ለጊዜው የሚሆን ከፍተኛ ህክምና መውሰድ እንዳለብኝ ተናገረ፡፡ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ደግሞ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ 4ወር ከ17 ቀን ብሰራም የሰጡኝ ገንዘብ ስለሌለ ምን ማድረግ ይቻላል? አልከስ ተጎጂዋ እኔ ነኝ፡፡ ባለቅስ አልወጣልሽ አለኝ፡፡

     የሚችሉትን ያህል እንደሚሞክሩ ካልሆነ ወደ ሀገር የምመለስበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ነገሩኝ፡፡ ከዛ በፊት ግን ለመታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ለሰው ሁሉ እየነገሩ ቤተ ክርስቲያንም..በቻሉት ቦታ ሁሉ ለመኑልኝ፡፡ ዶ/ሩ ግን ገንዘቡን ብቻ በድብቅ ህክምናዬን ለሚከታተልበትም ሆነ በድብቁ ክሊኒክ ለሚደረገው ህክምና እንዲረዳኝ ብቅ ባለ ቁጥር ውለታ እንድውልለት ይጠይቀኝ ጀመር፡፡ ለስሜት ውጥረቱ..ሆጵ ላለ ገላው ማስከኛ አፌን ላበድረው ይፈልጋል፡፡ ያለኝ አማራጭ ፍቃደኛ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ አንድ ሊያሲዘኝ ይችላል፡፡ ሁለት ታክሜ ድኜ ለመስራት እፈልጋለሁ፡፡ ትለውጠናለች ብለው ያሲያዙትን የቤት ካርታም ለማስለቀቅ መዳን አለብኝ፡፡ ስለዚህ ይሄ ዶክተር ብቻ በመሆኑ ያለኝ አማራጭ እንቢ እንዳልለው ራሴ ለራሴ መከርኩት፡፡ ቀን እስኪያልፍ…ብዬ ጀመርኩት፡

      ከዚያ በኋላ ህክምናውንም እየተከታተልኩ ለእነሱ ሸክም መሆን ከበደኝ፡፡ ሁለት ወር ሙሉ ተሸከሙኝ፡፡ ከዛ በኋላ እነሱ ገላቸውን ሸጠው ቁጭ ብዬ መብላቱ ተናነቀኝ፡፡ ሰው ቤት ተቀጥሬ እየሰራሁ በየጊዜው ህክምናውን ማግኘት ከባድ መሆኑን ስረዳ እንም እነሱ የሰሩትን ለመስራት ሞከርኩ፡፡ ፈራ ተባ እያልኩ አንድ ቀን ከአንዱ ጋር ሄድኩ፡፡ ያልጠበኩት እና አሳፋሪ ድርጊት ፈጸምኩ፡፡ ወሲብ ሲፈጽም ሽንትና እንትኔ ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ ፈሰሰ፡፡ አልጋውን አበላሸሁበት፡፡ ጠፍጥፎ አንሶላውን አሳጥቦ እንኳን ሊመልሰኝ ከጊቢው ብቻ አስወጥቶ ጣለኝ፡፡ ለጓደኞቼ ደወልኩላቸው፡፡ በታክሲ መጥተው ወሰዱኝ፡፡ አይዞሽ እያሉ አጽናኑኝ፡፡ ሌላ ጊዜ በአፍ ብቻ መፈጸም ለሚፈልግ አንድ ሰው መስራት ጀመርኩ፡፡ አንዴ ከገባህበት ደግሞ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ነው፡፡ሳንቲም ተርፎኝ ለቤተሰብ መላክ ጀመርኩ፡፡…..ደንበኞቼ በረከቱ፡፡ አፌ ተግባሩ በዛ መብያና መናገሪያ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ስራ ተመደበለት፡፡ እንደማንኛውም ሰው ለሄዋን በተፈቀደው ቦታ ወሲብ መፈጸም አልችልም፡፡ ያን ካደረኩ ሽንትና ሰገራዬ ተቀላቅሎ…ይፈሳል፡፡  ይህ ሁኔታ በክሊኒክ ውስጥም በድብቅ ህክምና ቢደረግልኝም ሙሉ ለሙሉ አልቆመም፡፡ ድንገት አሁን ሀገሬ ስገባ የተሻለ ህክምና አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡     

    ታዲያ እንዲህ አይነት አስጠሊታ ህይወት እየኖርኩ አንተ አስጠሊታ ያልከውን ቃል ባወጣ ባላወጣ ምን ለውጥ አለው? እርግጥ ይህን በማድረጌ ታዝንብኛለህ? ይህን ባላደርግ የቤተሰቦቼን ካርታ አስለቅቅ ነበር፡፡ በልተው እንዲያድሩ አደርግ ነበር? እኔስ በምን አይነት…. አሁንም እንባ አቋረጣት፡፡ በመሀል በመሀል እንባዋን ባፈሰሰች ቁጥር እኔም አጃቢነቴን ሳላጓድል እዚህ ድረስ አወጋን፡፡
   ወደኋላ ተመልሼ ካለችኝ ላስታውስ ‹‹…ይሄ ባህላችን፣ ስርዓታችን.. ቅብርጥሴ ለምትሉት ነገር አስበህ ከሆነ ተወው፡፡ ባህል ስርዓት ቅብርጥሴ እያለ የሚጀነነው ማህበረሰብ አንገዋሎ ከተፋቸው ምስኪኖች ተወልጄ ነው ለዚህ ሁሉ መከራ የተዳረኩት፡፡ ታዲያ ወግ ስርዓት ለእኔ ምኔ ነው? ቁርስ አልሆነኝ ምሳ….›› ብላኝ ነበር፡፡ ይህ አባባሏ ለእኔ የተንጠፈጠፈ እውነት ነው፡፡ ልክ እንደ ኑግ ዘይት የጠራ…ምክንያቱም በርሃብ፣ በችግር ለተተበተበ ሰው ምኑ ነው? የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ አለን እያልን ሶስት ሺህ ዘመን ስናወራ ሳንሰራ ቀርተን ድህነት እጣፋንታችን ይመስል ተጎብሮብን እንደ ሸማ ለብሰነው፣ እንደኩታ አጣፍተነው አብሮን ከርሟል፡፡ ይህን ስል ታሪካችን ባህላችን አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፡፡ ማዕረጋችንም ጌጣችንም ነው፡፡ ግን ማዕረግም ጌጥም የሚደምቀው ተርበው ተቸግረው አይደለም፡፡ ሲኖረን..ሰርተን ስንለወጥ ነው እንጂ በችግር ሰዓት ታሪክ፣ ባህል ወግ ስርዓት ችግር የሚቀርፍ ባውንድ አይደለም፡፡ አይሆንምም፡፡ የቸገረው፣ የራበው ሰው ያን መጠበቂያ ትዕግስትም አቅምም አይኖረውም፡፡ የዚህች ልጅን ትንፋሽም የተረዳሁት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ??? መስራቷ ልክ ናት? ወይስ መስራት አልነበረባትም? ምን ማድረግ ነበረባት?? 
             እንወያይበትና ወደ ቀጣይ እንሄዳልን
                 

No comments:

Post a Comment