Wednesday, August 1, 2012

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር
ክፍል ሁለት
የፌስቱላ ችግር የተከሰተብኝ በግፍ በተሰራብኝ…ነው
በግሩም ተ/ሀይማኖት

ወደንም ሳንወድም የምንሰራው ስራ ለሀገር ሊያኮራም ሊያሳፍርም ይችላል፡፡ ሊያኮራ የሚችለው የግድ ባንዲራ አውለብልበን አለያም በምርምር ግኝት አስመዝግበን ብቻ አይደለም፡፡ ስደት የወጡበትን አላማ አሳክቶ መመለስም ለቤተሰብ ማጉረስም አኩሪ ነው፡፡ ከሀገር፣ ከቤተሰብ፣ ከቀያችን አርቆ ያስወጣን አላማ ነውና ያኮራል፡፡ የሚያሳፍረው ደግሞ መጥፎ ቦታ ተሰልፈን ስንገኝ ነው፡፡ በአረብ ሀገር ያሉ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚሰሩበት ነገር ከዚህ የተለየ አይሆን፡፡ ያኮራል አለያም ያሳፍራል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ጥቂቶች ከደረሰባቸው መከራ ለመውጣት ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ይሆንና እንደዋዛ መጥፎውን ድርጊት ይገቡበታል፡፡ ከ70% እና ከ80% በላይ የሚሆኑት ወደው እንዳልሆነ ለሽርሙጥናም ሆነ ለሌላ አስከፊ ስራ የሚዳረጉት ካነጋገርኳቸው ሰዎች ለማወቅ ችያለሁ፡፡ መጥፎ የሚባለው ህይወት ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን ማሰብ ግድ ይላል፡፡ ምላሹም ለስራ ሲሄዱ የሚፈጸምባቸው ግፍ እንዲቆም ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡

ህይወት ጉዞዋ እኛ በፈቀድነው ብቻ ሳይሆን ባልፈቀድነውም ይሆንና ያላሰብነው አረንቋ ውስጥ ትዶለናለች፡፡ በአንድ ወቅት ዱባይ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውን ማፈስ ተጀመረ፡፡ ይህ ችግር ሲከሰት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ መኖሪያ ፍቃድ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም በኮንትራት ስራ እየሄዱ በሚደርስባቸው ግፍ ተማረው ሲጠፉ ፓስፖርታቸው ቀጣሪዎቻቸው እጅ ስለሚቀር ነው፡፡ ታዲያ አፈሳው መኖሪያ ወረቀት ለሌለው ሱሪ በአንገት የማስወለቅ ያህል ምጥ አስምጧል፡፡ ከተያዙ የአይን አሻራ ይነሳሉ ወደ ሀገራቸው ይጠረዛሉ /ይላካሉ/፡፡ አይን አሻራ የመነሳቱ ነገር ደግሞ ዳግም ከስድስት አመት በፊት ወደ ዱባይ እንዳይገቡ ያስከለክላል፡፡ ስለዚህ ስደተኛው ያለው አማራጭ ሳይያዝ ሀገር ገብቶ በቪዛ ዳግም ወደ ዱባይ መግባት ነው፡፡ ሳይያዙ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በየመን በኩል እንደጉድ ይጎርፉ ጀመሩ፡፡

ይሄ ደግሞ በህገ-ወጥ አጓጓዦች ነው የሚከወነው፡፡ ምክንያቱም ዱባይ ከየመን ጋር ድንበርተኛ ስላልሆነች ገና የኦማንን ድንበር ተጥሶ በጨለማ በጫካ ስለሆነ የሚጓዙት ነው፡፡ ላለመያዝ የነገ ህይወትን ችግር ውስጥ ላለመክተት ዛሬ መቸገር ግድ ሆነ፡፡ በዚህን ወቅት በየመንገዱ የተደፈሩ፣ የታሰሩ፣ የተዘረፉ እና የተለያየ አይነት ፈርጀ ብዙ ችግር ያስተናገዱ ሞልተዋል፡፡ በለስ ቀንቷቸው ምንም ሳይገጥማቸው የገቡም ብዙ ናቸው፡፡ በአፈሳው የተያዘ ሰው ከዱባይ ጋር ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ..ያባብለዋል፡፡ የአይን አሻራ ከተነሳ ዳግም ወደ ዱባይ መመለስ አይቻልምና፡፡ ከችግር እና ስራ አጥነት ጋር ሀገር ገብቶ ቤተሰብ ላይ መቀመጥም የማይታሰብ ነው..ስለዚህ የደረሰውን ግፍ ተቀብሎ የመን መግባት አማራጭ እና አማራጭ ብቻ ነው፡፡

በዛን ወቅት ወደ የመን የመጣችሁ ከህገ-ወጥ አጓጓዦቹ ጀምሮ በየመንገዱ እያንዳንዳችሁ የደረሰባችሁን መከራ ዛሬ ዱባይ ያላችሁ፣ ወደ ሌላ ሀገር የተዘዋወራችሁም ሆነ ኢትዮጵያ የገባችሁ ታስታውሱታላችሁ፡፡ በፖሊስ ተይዘው ሲደበደቡ የከረሙ ገንዘባቸውን የተነጠቁ ጥቂቶች የተደፈሩ ነበሩ፡፡ ጥቂቶቻችሁን ዛሬ ዳግም ፌስቡክ ስላገናኘን ምስክርነታችሁን ብታሰፍሩት ሌላው ቢማርበት ጥሩ ነበር፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ጉዳያችሁን አስፈጽማለሁ ብለው አሳር መከራችሁን ያሳዩዋችሁ ብዙ አሉ፡፡ እዛ የምትሰሪውን እዚህ ስሪ ብለው አሳልፈው ለአረብ የሸጧችሁንም ታስታውሳላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

አንድ ከእኔ ጋር የተያያዘ ክፍል ቤት የተከራየ ጥቂቶቻችሁን የማገት ያህል ለፖሊስ አሲዛችኋለሁ ብሎ እያስፈራራ ገንዘባቸሁን ነጥቆ፣ ሴትነታችሁን ጠልቆ የተጫወተበት አውቃለሁ፡፡ ወገኖቹን ያሰቃይ የነበረ በፊት የመን የኖረ ከዱባይ ከመጣ አረመኔ ጋር ተጠማምጄ ነበር፡፡ ጉዳይ አስፈጽማለሁ ብለው የወገናቸውን ደም ከሚመጡት አንዱ ይህ ሰው ሲሆን ጎረቤቴ በመሆኑ ሁሉን ለማየት ታድያለሁ፡፡ በአንዴ አርባ እና ሀምሳ ሰው እያመጣ የሁላችንም ቤት አቅሙ እስከፈቀደ አስተናግዷችኋል፡፡ በዛውም መረጃዬን ስብስቤያለሁ፡፡ ከስባት ልጆች ጋርም ቃለ-ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡ ለዛሬ የአንዷን ላቅርብላችሁ፡፡

ደስ የሚል ቁመና ያላት ‹‹..ቁመትሽ ሎጋ ነው የእኔ አለም..›› የምታሰኝ ጠይም ናት፡፡ የደስ ደስ ያላት፡፡ ከጊዜያዊ ምቾት ውጭ ድህነት ሽንቁጥ አድርጎ እንዳሳደጋት ያስታውቃል፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ 95 ከመቶ የቀመሰው ጽዋ ነው፡፡ ከዱባይ በኦማን አድርጎ ያመጣቸው ሰው 16.000 ድርሀም ዘርፏታል፡፡ ሁሉም ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ በኢትዮጵያ ወደ 35000 አካባቢ መሰለኝ በዛን ወቅት ምንዛሪ፡፡ እሷ ግን ምንም ሳይመስላት ‹‹ተዉት ተመልሼ ስሄድ በአንድ ሳምንት ጠባ..ጠባ ባደርግ የማገኘው ነው…›› አለች፡፡ ጠላታችሁ ድንግጥ ይበል አመዴ ቦነነ፡፡ ከየትኛው ዩነቨርስቲ የብልግና /መረንነት/ ዲግሪዋን እንደወሰደች እያሰላሰልኩ ብቻዋን የማናግርበትን ሁኔታ አቀድኩ፡፡

በዛ ያሉት ሺሻ ላይ አፋችሁን ለጉሙ የተባሉ ይመስል ተያይዘውታል፡፡ እርግጠኛ ነኝ የእናታቸውን ጡት እንኳን እንዲህ አልመጠጡም፡፡ ከጡጦ ቀጥሎ ሺሻ የጀመሩ ያስመስልባቸዋል፡፡ ዱባይ እንደ የመን ጫት ስለማይገኝ እንደ ጫት ሻይ ቅጠሉን ከካሮት ወይም ከመቅዶኒስ ቅጠል ጋር ጉንጫቸው ውስጥ ወጥቀው ተክዚና መያዝ ለምደዋል፡፡ የመን ጫቱ ስላለ ወጥቀውታል፡፡ ሁለቱ ልጆች ግን የለመዱትን ስላረጉ ነው እዛ የሚጠቀሙትን ያወኩት፡፡ ምስጢር ካወጣሁ ይቅርታ!!

ወደ ግማሽ የሚሆኑት ከምኑም ያልሆኑ የእህል እና ውሀ ሱስ ብቻ ያለባቸው አሉ፡፡ አጨዋወታቸው ደርዝ ያለው በእርጋታ የተሞሉም ናቸው፡፡ ከላይ የጠቀስኳት ልጅ ስልኳ እረፍት የለውም፡፡ እሷም ትደውላለች፡፡ ጎበዝ ደዋይ ነች፡፡ ያጠናሁት ነገሯ አንዱ ጋር ትደውልና ‹‹ያ-ባባ መንገድ ላይ እኮ ተዘረፍኩ፡፡ አንተ ነሀ እዛ ከደረስኩ በኋላ ላክልኝ ስልህ…›› ይሄ እኮ ያ ባለ ሆቴሉ ነው ትላቸዋለች አብረዋት ላሉት፡፡ ትንሽ ቆይታ ትቀጥላለች ‹‹..ወላ! ወላ! አሁን ካርድ መግዣ የሚሆን ሳንቲም እንኳን የለኝም፡፡ ዛሬውኑ ላክልኝ…›› ስልኩ ይዘጋል፡፡ ልጁ ገንዘብ እንደተላከላት ካወቀ እንደሚነጥቃት በእኔ መታወቂያ ላወጣላት በስሜ ከሁለት ሰው ተልኮላታል፡፡ የሚገርመው ግን አንዴ ካወጣሁት ላይ ሁለት ሺህ ድርሃሙን የሱዳኒ ባልዋን ስም ነግራኝ ላክለት ብላኛለች፡፡ ልኬያለሁም፡፡

አጋጣሚዎች ተገጣጠሙ እና ያስመጣቸው ጨካኝ ሰክሮ ከሚስቱ ሲጣላ ሸሽተው ሶስት ሆነው እኔ ቤት አደሩ፡፡ መኝታዬን ለቅቄላቸው አረቢያን መጅሊስ ላይ ጋደም ብዬ ከሁሉም ለየት ብላ ካየኋት ልጅ ጋር ያሰብኩትን ማውራት ቀጠልን፡፡ ሁለቱ ሸለብ አድርጓቸዋል፡፡ ሞባይል ስልኬ ሪከርድ የሚለው ላይ ሆኖ ተቀመጠ፡፡ ለምንድን ያንን መረን ቃል እንደተጠቀመች፣ ድርጊቱን ብታደርገው እንኳን እንደ ጀብድ በዛ ሁሉ ሰው መሀል ማውራቷ አግባብ እንዳልሆነ ነገርኳት፡፡ ሌሎቹንም ወደዛ ተግባር መምራት ነው፡፡ ፊቷ ልውጥውጥ አለ፡፡ አፈጠጠችብኝ፡፡ ሶስት አራት የተሻሻሉ የብልግና ስድቦችን ልትለጥፍልኝ ነው ስል አሰብኩ፡፡ ‹‹እኔነኝ ወደ ብልግና የምመራቸው? ራሱ መከራው ስቃዩ መሮጫ ማምለጫ ማጣቱ ነገሮች ሳይወዱ ወደዛ ይመሩዋቸዋል፡፡ ማንም መሸርሞጥ ፈልጎ አይሸረሙጥም…›› እንባዋ ተንደርድሮ የትራስ ልብሴን አጠመቀው፡፡ ላባብላት አልሞከርኩም፡፡ ስደት ላይ እያሉ እንባ ማፍሰስ እጣቢ ውሀ የመድፋት ያህል ቀላል መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እስኪበቃኝ ቀምሼዋለሁም፡፡

ጋደም ካለችበት ቀና ብላ በአትኩሮት ስታየኝ ቁስል ኖሯት እንደነካኋት ታወቀኝ እና ተጸጸትኩ፡፡ ቢሆንም ቁስሏንም፣ ያቆሰላትን ታሪክም ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ በአንዴ ቅላትን ባሰተናገደ ድፍርስ አይኗ ገልመጥ አድርጋኝ ‹‹ምን ማወቅ ፈለግህ? ለምንስ?..›› አስተያየቷ ያስፈራል፡፡ ቢሆንም ከጀመርኩ ወደኋላ የለም እና ወደፊት በሉለት ይለይለት የሚለውን እያቀነቀንኩ ቀጠልኩ፡፡ አስረዳኋት፡፡ ከነገርኩህ ትጠየፈኛለህ፤ እንደ ሰው አታየኝም….በፍፁም ወደሽ የምታመጪው ነገር እንደሌለ አውቃለሁ አልኳት፡፡ በእርግጥም አንባቢዎቼ የፈለገ ጸያፍ ድርጊት ላይ ተሰልፈው ስታገኟቸው ወደው እንዳላደረጉት አስቡ፡፡ አይኖቿ እንባ ጨርሰው እስኪደርቁ እያለቀሰች አወጋችኝ፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን አገዝኳት፡፡ የእኔም እንባ እጢዎች ስራ አልፈቱም፡፡ እንዲያውም ኦቨርታይም ሁሉ ሳይሰሩ አልቀሩም፡፡ እዚህ ጋር አንዳንድ ጸያፍ ቃላትን በራሴ ያጻጻፍ ስለቀየርኳቸው……

‹‹ጠባ..ጠባ..› ስላልኩ ነው የገረመህ? ረጀም ታሪክ አለው፡፡ ግን ድርጊቱን እየፈጸምኩ ጠራሁት አልጠራሁት ምን ለውጥ አለው? ይሄ ባህላችን፣ ስርዓታችን.. ቅብርጥሴ ለምትሉት ነገር አስበህ ከሆነ ተወው፡፡ ባህል ስርዓት ቅብርጥሴ እያለ የሚጀነነው ማህበረሰብ አንገዋሎ ከተፋቸው ምስኪኖች ተወልጄ ነው ለዚህ ሁሉ መከራ የተዳረኩት፡፡ ታዲያ ወግ ስርዓት ለእኔ ምኔ ነው? ቁርስ አልሆነኝ ምሳ…የተንጠፈጠፈ እውነት ነው፡፡ ልክ እንደ ኑግ ዘይት የጠራ…ምክንያቱም በርሃብ፣ በችግር ለተተበተበ ሰው ምኑ ነው? የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ አለን እያልን ሶስት ሺህ ዘመን ስናወራ ሳንሰራ ቀርተን ድህነት እጣፋንታችን ይመስል ተጎብሮብን እንደ ሸማ ለብሰነው፣ እንደኩታ አጣፍተነው አብሮን ከርሟል፡፡ ይህን ስል ታሪካችን ባህላችን አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፡፡ ማዕረጋችንም ጌጣችንም ነው፡፡ ግን ማዕረግም ጌጥም የሚሆነው ሲኖረን..ሰርተን ስንለወጥ ነው እንጂ በችግር ሰዓት ችግር የሚቀርፍ ባውንድ አይደለም፡፡ አይሆንምም፡፡ የቸገረው፣ የራበው ሰው ያን መጠበቂያ ትዕግስትም አቅምም አይኖረውም፡፡ የዚህች ልጅን ትንፋሽም የተረዳሁት ከዚህ አንጻር ነው፡፡

ቀጠለች እኔም የእሷን ታሪክ ቀጠልኩ…..ለኮንትራት የቤት ሰራተኝነት ነው ዱባይ የሄድኩት፡፡ ሴትዮዋ በስራ የምትሳቃየኝ አንሶ ለወሲባዊ ስሜቷ አሳሬን ታሳየኛለች፡፡ ስራዬን አስትታ ሻዎር እንግባ ትለኛለች፤ መኝታ ቤት አስገብታኝ በር ትዘጋለች፡፡ ምን ልታደርጉ የሚል እንዳይኖር መቼም ለጸሎት እንደማይሆን ይገባችኋል፡፡ ሰውየው በሌላ በኩል ፍዳዬን አበላው፡፡ ሌሊት ይመጣና ሴንጢ ደቅኖብኝ ‹‹..አርጄ ቆሻሻ ውስጥ እጥልሻለሁ..›› ብሎ ብልቱን አፌ ላይ ይደቅናል፡፡ ያለቻቸውን አንድ ጥሪት የቤት ካርታ አሲዘው ብር ተበድረው ሲልኩኝ ታሳልፍልኛለች ብለው ነው፡፡ የላኩኝ ቤተሰቦቼ ነገር ትዝ ይለኛል ብድራቸውን እንኳን ሳይከፍሉ ባለ እዳ አድረጌያቸው ቤታቸውን አስወርሼ ጎዳና ተዳዳሪ አድርጌያቸው ልሞት? እልና የፈቀደውን ያደርጋል፡፡ ማዳሟ በልምምጥም ገንዘብ በመስጠትም የተጣባትን መጥፎ አባዜ ትወጣለች፡፡ በአንድ ወቅት ለሳምንት ወደ አቡዳቢ ሊዝናኑ ሲሄዱ እሱም ለራሱ ሲል እሷም ለራሷ ስትል አብሬያቸው እንድሄድ ፈለጉ፡፡ ልጆቹ ደግሞ ለእኛ ማን አለን ሲሉ ቅሪ ተባልኩ፡፡ እግራቸው ወጣ እንዳለ እሱም በበኩሉ ያስቸግረኝ የነበረው ትልቁ ልጅ ሰባት ጓደኞቹን ለእራት ስለጠራ ምግብ እንዳዘጋጅ ነገረኝ፡፡ የቻልኩትን ሰራሁ፡፡

ልጆቹ ማታ ላይ ተሰባበሰቡ፡፡ በሉ ጠጡ ሙዚቃ ከፍተው ይጨፍሩ ጀመር፡፡ አንዴ እንዲህ አድርጊ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲህ አድርጊ ሲሉኝ ስደክም አመሸሁ፡፡ እስካሁንም ያልገባኝ ነገር ያጨሳሉ፡፡ ሀሺሽ አልመሰለኝም፡፡ በኋላ ሲጠሩኝ ስሄድ መሀል አስገብተው ይጎነታትሉኝ ጀመር፡፡ እንደ ሻንጉሊት አረደጉኝ፡፡ አንደኛው ከኪሱ የሆነ ብልቃጥ አውጥቶ መሀረብ ላይ ሲያፈስ አየሁት፡፡ ሁለቱ እጄን ግጥም አድርገው ሲይዙኝ አፌ እና አፍንጫዬ ላይ አድርጎ አፈነኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም፡፡ ከስንት ቀን በኋላ እንደነቃሁ እግዚአብሄር ይወቅ፡፡ ስነቃ የተኛሁበት ቦታ በደም፣ በሽንት እና የቀጠነ ሰገራ ተጨማልቋል፡፡ ሽቴንም ምኔንም እዛው እየለቀኩ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰውነቴ ላይ ሁሉ ደርቋል፡፡ ሽታው ለራሴ አስጠላኝ፡፡ ለመነሳት አልቻልኩም፡፡ ጭኔ መሀል ያለው ቁስለት በዋዛ የሚያንቀሳቅሰኝ አልመሰለኝም፡፡ ያለሁበትን ቦታ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በጣም የቆሸሸ፣ አቧራ የጠገበ እና በአሮጌ እቃዎች የተሞላ ነው፡፡ ግራውንድ መሰለኝ፡፡ አደጋው እስከ ተፈጸመብኝ ሰዓት ድረስ አራት ወር ከአስራ ሰባት ቀኔ ነው፡፡ ቤቱ ግራውንድ እንዳለው አላውቅም፡፡

ሁለቱም እግሬ ስላልታዘዘልኝ እየተንፏቀኩ ደረጃውን እንደምንም ወጣሁት፡፡ ሁለቱ የሴትዮዋ ልጆች ሲያዩኝ እንደመዝናኛ ፊልም በእንፉቅቄ ይስቁብኝ ጀመር፡፡ አለቀስኩ በጣሙን አምርሬ አለቀስኩ፡፡ አይዞሽ ባይ በሌለበት ለእነሱ ለቅሶዬ ደስታ ፈጥሮባቸው ሲንከተከቱ እኔን ግን እንባዬ አጠበኝ፡፡ ሽንት ቤት መግባት ፈለኩ እና እንደምንም ገባሁ፡፡ ሽንቴ እና እንትኔ እኩል ተቀላቅሎ ወረደ፡፡ ቸግር እንደተፈጠረብኝ ተረዳሁ፡፡ ራሴን ማጥፋት ፈለኩ፡፡ ተመልሼም ወደ ነበርኩበት ግራውንድ ወረድኩ፡፡ መታነቅ ነው ፍላጎቴ….በሀሳቤ እናቴ ታየችኝ፡፡ አባቴ በዘበኝነት የሚያገኛትን ገቢ የሚጠብቁ ታናናሾቼ ታዩኝ፡፡ የበለጠ ደግሞ ወታደር እያለ የሰራትን ቤት ካርታ አሲዘው ስለሆነ የላኩኝ ቤታቸውንም እንደሚያጡ ሳስበው ሰቀጠጠኝ፡፡ ሞቴ ብዙ ነገራቸውን እንደሚያጨልመው በተቃራኒው ተስፋቸው፣ በልቶ ማደራቸው፣ መጠለያ ይዞ መቆየታቸው ሁሉ በእኔ ላይ የተጣለ ሀላፊነት እንደሆነ ሳውቅ ራሴን ጠላሁት፡፡

ቀጣዩን ይዤ ብቅ ልል ቃል እገባለሁ፡፡ በጣም ስለረዘመብኝ መቁረጥ ግድ ብሎኝ ነው እና በስሱ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡


No comments:

Post a Comment